በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በስም ልታውቀው ትችላለህ?

አምላክን በስም ልታውቀው ትችላለህ?

አንድን የታወቀ ሰው ሰላም ማለትና በስሙ እየጠሩ ማነጋገር ትልቅ መብት ነው። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚጠሩት “ክቡር ፕሬዚዳንት፣” “ግርማዊነትዎ” ወይም “ክቡርነትዎ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ነው። በመሆኑም አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን “እባክህ፣ በስሜ ብቻ ጥራኝ” ቢልህ እንደ ትልቅ ክብር እንደምትቆጥረው ምንም ጥርጥር የለውም።

እውነተኛው አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “እኔ [ይሖዋ] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው” ብሏል። (ኢሳይያስ 42:8) * ይሖዋ “ፈጣሪ፣” “ሁሉን ቻይ” እና “ሉዓላዊ ጌታ” እንደሚሉት ያሉ በርካታ የማዕረግ ስሞች ቢኖሩትም ታማኝ አገልጋዮቹ ሁልጊዜ በተጸውኦ ስሙ እንዲጠሩት በመፍቀድ አክብሯቸዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ሙሴ በአንድ ወቅት አምላክን “ይሖዋ፣ ይቅርታ አድርግልኝ” በማለት ተማጽኗል። (ዘፀአት 4:10 NW) ንጉሥ ሰለሞንም በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ በተወሰነበት ጊዜ ጸሎቱን የከፈተው “[ይሖዋ] ሆይ” በማለት ነበር። (1 ነገሥት 8:22, 23) ነቢዩ ኢሳይያስ የእስራኤልን ሕዝብ ወክሎ አምላክን ባነጋገረበት ጊዜ “[ይሖዋ] ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ” ብሏል። (ኢሳይያስ 63:16) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የሰማዩ አባታችን በስሙ እንድንጠራው ይፈልጋል።

ይሖዋን በስም መጥራት አስፈላጊ ቢሆንም እሱን በስም ማወቅ ግን ከዚያ የበለጠ ነገር ይጠይቃል። ይሖዋ እሱን ለሚወድና በእሱ ለሚታመን ሰው “ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ” በማለት ቃል ገብቶለታል። (መዝሙር 91:14) የአምላክን ስም ማወቅ የአምላክን ጥበቃ በማግኘት ረገድ ቁልፍ የሆነ ነገር በመሆኑ ስሙን ማወቅ ብዙ ነገሮችን ያጠቃለለ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ታዲያ ይሖዋን በስም ለማወቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በዚህና ቀጥሎ በተጠቀሱት አንዳንድ ጥቅሶች ላይ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር” የሚለውን ስም ይጠቀማል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ አምላክ የተጠራው ይሖዋ በሚለው የግል ስሙ ነው።