በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታመመ ወዳጃችሁን መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

የታመመ ወዳጃችሁን መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

 የታመመ ወዳጃችሁን መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

በጠና የታመመ ጓደኛህን ለመጠየቅ ሄደህ የምትናገረው ቃል ጠፍቶህ ያውቃል? እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ መወጣት እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። እንዴት? ሁኔታው ከባሕል ወደ ባሕል ሊለያይ ስለሚችል በዚህ ረገድ የተወሰነ ደንብ ማውጣት አይቻልም። የሰዎች ባሕርይም በእጅጉ ይለያያል። ስለዚህ አንድን የታመመ ሰው የሚያጽናና ነገር ሌላውን ላይረዳ ይችላል። እንዲሁም የሕመምተኛው ሁኔታና ስሜት ከቀን ወደ ቀን ሊለያይ ይችላል።

አስፈላጊው ነገር በታመመው ግለሰብ ቦታ ራስህን በማስቀመጥ እሱ ወይም እሷ ከአንተ ምን እንደሚፈልጉ ለመረዳት መሞከር ነው። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ላይ የተመሠረቱ ጥቂት ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

ጥሩ አዳማጭ ሁን

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች፦

“ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት።”ያዕቆብ 1:19

“ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።”መክብብ 3:7

▪ አንድ የታመመ ጓደኛህን ስትጠይቀው በትኩረትና በርኅራኄ አዳምጥ። ምክር ለመስጠት አትቸኩል ወይም ምንጊዜም የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ እንዳለብህ አይሰማህ። በችኮላ ስትናገር ሳታስበው የሚጎዳ ነገር ልትናገር ትችላለህ። የታመመ ጓደኛህ የሚያዋራህ ሐሳብ እንድትሰጠው ሳይሆን ልቡንና አእምሮውን ከፍቶ የሚያዳምጠው ሰው ስለሚፈልግ ነው።

ስለዚህ ጓደኛህ ሐሳቡን በነፃነት እንዲገልጽ ፍቀድለት። ሲናገር አታቋርጠው ወይም የተለመዱ አባባሎችን እየተናገርክ ያለበትን ችግር አታጣጥል። ኤሚሊዮ * እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በማጅራት ገትር ምክንያት የማየት ችሎታዬን አጥቻለሁ። አንዳንድ ጊዜ በጣም ስለምተክዝ ጓደኞቼ ‘ችግር ያለብህ አንተ ብቻ አይደለህም። ከአንተ የባሰ ችግር ያላቸው ስንት ሰዎች አሉ!’ በማለት ሊያጽናኑኝ  ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ያለሁበትን ሁኔታ አቅልለው መመልከታቸው እንደማያጽናናኝ አይገነዘቡም። እንዲያውም እንዲህ ብለው መናገራቸው የበለጠ እንዳዝን ያደርገኛል።”

ጓደኛህ ነቀፌታ ይደርስብኛል ብሎ ሳይፈራ የልቡን አውጥቶ እንዲናገር አድርግ። እንደፈራ ቢነግርህ ‘አትፍራ’ ብለህ ከመናገር ይልቅ ስሜቱን ተረዳለት። “ሁኔታዬ አሳስቦኝ ማልቀሴ በአምላክ እንደማልተማመን የሚያሳይ አይደለም” ስትል የካንሰር በሽታ ያለባት ኤሊያና ተናግራለች። ጓደኛህን አንተ እንደምትፈልገው ሆኖ እንዲገኝ ሳትጠብቅ በማንነቱ ለመቀበል ጥረት አድርግ። አሁን ከወትሮው ባሕርይው በተለየ በቀላሉ ሊከፋውና ሊነጫነጭ እንደሚችል ከግምት አስገባ። ስለዚህ ታጋሽ ሁን። ተመሳሳይ ነገር እየደጋገመ የሚናገር ቢሆንም እንኳ አዳምጠው። (1 ነገሥት 19:9, 10, 13, 14) ስሜቱን ለአንተ ማካፈል እንዳለበት ይሰማው ይሆናል።

የሌሎችን ችግር እንደ ራስህ አድርገህ የምትመለከትና አሳቢ ሁን

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች፦

“ደስ ከተሰኙ ሰዎች ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር አልቅሱ።”ሮም 12:15

“ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።”ማቴዎስ 7:12

▪ ራስህን በጓደኛህ ቦታ አድርገህ አስብ። ጓደኛህ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ እየተዘጋጀ፣ ሕክምና እየወሰደ ወይም የምርመራ ውጤት እየጠበቀ ከሆነ ውጥረት ውስጥ ስለሚገባ በቀላሉ ሊከፋው ይችላል። ችግሩን ለመረዳትና ባሕርይውን ለመቻል ጥረት አድርግ። በዚህ ጊዜ በተለይም ከግል ጉዳይ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎችን መጠየቅ ላያስፈልግ ይችላል።

“ሕመምተኞች ስለ ሕመማቸው በፈለጉት ጊዜ የፈለጉትን ያህል ሲናገሩ ስሟቸው” በማለት የሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት አና ካታሊፎዝ ተናግረዋል። “ለመጫወት ፈቃደኛ በሚሆኑበት ጊዜ በፈለጉት ርዕሰ ጉዳይ ላይ አዋሯቸው። ለማውራት በማይፈልጉበት ጊዜ ግን በፍቅር እጃቸውን ያዝ አድርጋችሁ ዝም ብላችሁ መቀመጣችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ የሚያስፈልጋቸው አብሯቸው የሚያለቅስ ሰው እንደሆነ ትገነዘቡ ይሆናል።”

የጓደኛህን ሚስጥር ጠብቅ። ሁለት ጊዜ ካንሰር ይዟቸው የዳኑት ሮሳን ኬሊክ የሚባሉ ደራሲ እንዲህ ብለዋል፦ “የታመመ ጓደኛህ የሚነግርህን ነገር ሚስጥር እንደሆነ አድርገህ አስብ። ቤተሰቡን ወክለህ እንድትናገር እስካልተጠየቅክ ድረስ ማንኛውንም መረጃ ለሌላ ሰው አትናገር። ለሌላ ሰው ምን ነገር ብትናገር እንደማይከፋው ሕመምተኛውን ጠይቀው።” በአንድ ወቅት ካንሰር የነበረበት ኤድሰን እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ጓደኛዬ፣ ካንሰር እንደያዘኝና በሕይወት ብዙም እንደማልቆይ የሚገልጽ ወሬ አዛመተ። እስቲ አስቡት ገና ቀዶ ሕክምና ማድረጌ ነበር። ካንሰር እንዳለብኝ ባውቅም ከሰውነቴ በተወሰደው ናሙና ላይ የሚደረገው የምርመራ ውጤት ገና እየተጠባበቅሁ ነበር። ውጤቱ ካንሰሩ በሰውነቴ ውስጥ እንዳልተሰራጨ የሚያሳይ ነበር። ወሬው መሰራጨቱ ግን የሚጎዳ ነው። ባለቤቴ ሌሎች በሚሰነዝሩት አሳቢነት በጎደላቸው አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተጎድታለች።”

ጓደኛህ የትኛውን የሕክምና ዓይነት እንደሚወስድ እያሰበ ከሆነ አንተ በእሱ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን እንደምታደርግ ለመናገር አትቸኩል። የካንሰር በሽተኛ የነበሩት ሎሪ ሆፕ የተባሉ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል፦ “ካንሰር ላለበት ወይም ከካንሰር ሕመም ለዳነ ሰው ማንኛውንም ዓይነት ጽሑፍ ወይም ዜና ከመላካችሁ በፊት እንዲህ ዓይነቱን ነገር ይፈልግ እንደሆነ መጠየቃችሁ የተሻለ ነው። አለበለዚያ በአሳቢነት ተነሳስታችሁ ያደረጋችሁት ነገር እናንተ ባታውቁትም እንኳ ጓደኛችሁን ሊጎዳው ይችላል።” አንዳንድ ሰዎች ስለተለያዩ የሕክምና ዓይነቶች ብዙ መረጃ ማግኘት ላይፈልጉ ይችላሉ።

ለታመመው ሰው የቅርብ ጓደኛ ብትሆንም እንኳ ልትጠይቀው ስትሄድ ብዙ ሰዓት አትቆይ። ልትጠይቀው መሄድህ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም ጓደኛህ ግን ብቻውን የሚሆንበት ጊዜ ሊፈልግ ይችላል። ደክሞት ሊሆን ስለሚችል ለማውራት ሌላው ቀርቶ ለረጅም ሰዓት አንተን ለማዳመጥ ኃይል ላይኖረው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ቶሎ ለመሄድ የቸኮልክ የሚያስመስል ነገር አታድርግ። ጓደኛህ ምን ያህል እንደምታስብለት ማየት ይፈልጋል።

አሳቢነት ማሳየት ሚዛናዊና አስተዋይ መሆንን ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል፣ ለታመመው ጓደኛህ ምግብ ከማዘጋጀትህ በፊት ምን ዓይነት ምግብ እንደሚፈልግ  ብትጠይቀው የተሻለ ነው። ታመህ ምናልባትም ጉንፋን ይዞህ ከሆነ እስኪሻልህ ድረስ ሄደህ አለመጠየቅህ ፍቅር የተሞላበት እርምጃ ነው።

የምታበረታታ ሁን

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች፦

“የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።”ምሳሌ 12:18

“ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለውና በጨው የተቀመመ ይሁን።”ቆላስይስ 4:6

▪ ስለታመመው ጓደኛህ አዎንታዊ አመለካከት ካለህ በምትናገራቸው ቃላትና በድርጊትህ መገለጹ አይቀርም። ጓደኛህን መጀመሪያ ላይ እንድትቀርበው ያደረጉህ እነዚያው ባሕርያት አሁንም እንዳሉት ተገንዝበህ እንደ ድሮው ተመልከተው። ሕመሙ ከጓደኛህ ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አትፍቀድ። ጓደኛህን ተስፋ እንደሌለው ሰው አድርገህ የምታናግረው ከሆነ እሱም ራሱን በዚያው መንገድ ማየት ሊጀምር ይችላል። በዘር ሊተላለፍ የሚችል የአጥንት በሽታ ያለባት ሮቤርታ የምትባል አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “እንደ ማንኛውም ሰው ተመልከቱኝ። የአካል ጉዳተኛ ብሆንም የራሴ አመለካከትና ፍላጎት ያለኝ ሰው ነኝ። እንደ አሳዛኝ ፍጡር አድርጋችሁ አትመልከቱኝ። የማልረባ ሰው አድርጋችሁ አታናግሩኝ።”

የምትናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን የምትናገርበት መንገድም ልዩነት እንደሚያመጣ አስታውስ። የድምፅ ቃናህ እንኳ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ኤርኔስቶ ካንሰር እንዳለበት ከተነገረው ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ጓደኛው ከውጭ አገር ደውሎ “አንተን ካንሰር ይይዝሃል ብዬ ማመን ያዳግተኛል!” አለው። ኤርኔስቶ ሁኔታውን አስታውሶ ሲናገር “ጓደኛዬ ‘አንተ’ እና ‘ካንሰር’ የሚሉትን ቃላት የተናገረበት የድምፅ ቃና ፍርሃት ለቀቀብኝ” ብሏል።

ሎሪ ሆፕ የተባሉት ደራሲ ሌላ ምሳሌ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል፦ “‘እንዴት ነህ?’ የሚለው ጥያቄ ብዙ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ይህን ጥያቄ ያነሳው ሰው የድምፅ ቃና፣ ፊቱ ላይ የሚነበበው ስሜት፣ ከሕመምተኛው ጋር ያለው ወዳጅነትና ቅርበት ብሎም ጊዜው ሕመምተኛውን ሊያጽናናው፣ ሥቃይ ሊጨምርበት ወይም ፍርሃት ሊቀሰቅስበት ይችላል።”

የታመመው ጓደኛህ የሚያስብለት፣ ስሜቱን የሚረዳለትና የሚያከብረው ሰው እንዳለ ሆኖ እንዲሰማው መፈለጉ ያለ ነገር ነው። ስለዚህ ግለሰቡን ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተውና ከአጠገቡ ሆነህ እንደምትረዳው አረጋግጥለት። የጭንቅላት ዕጢ የነበረባት ሮሲማሪ የተባለች አንዲት ሴት “በጣም ያበረታታኝ ነገር ጓደኞቼ እንደሚወዱኝ ሲናገሩ መስማቴና ምንም ነገር ቢያጋጥመኝ ከጎኔ እንደማይለዩ ማወቄ ነበር” ብላለች።—ምሳሌ 15:23፤ 25:11

ከመርዳት ወደኋላ አትበል

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።”1 ዮሐንስ 3:18

▪ ጓደኛህ ሕመሙ ከታወቀለት ጊዜ አንስቶ በሕክምና ላይ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ የሚያስፈልገው ነገር ሊለዋወጥ ይችላል። በዚህ ጊዜ ሁሉ እርዳታ ሊያስፈልገው ይችላል። በደፈናው “የምትፈልገው ነገር ካለ ንገረኝ” ከማለት ይልቅ ልትረዳው የምትችለውን ነገር ለይተህ ጥቀስ። ለጓደኛህ እንደምታስብለት በተግባር ማሳየት ከምትችልባቸው መንገዶች መካከል ምግብ ማዘጋጀት፣ ማጽዳት፣ ልብስ ማጠብ፣ መተኮስ፣ መላላክ፣ ገበያ መሄድና ጓደኛህን ወደ ሕክምና ቦታ በመኪና ማመላለስ የመሳሰሉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል። እምነት የሚጣልብህና ሰዓት አክባሪ ሁን። በተጨማሪም ቃልህን ጠብቅ።—ማቴዎስ 5:37

ሮሳን ኬሊክ የተባሉ ደራሲ “ልናደርግለት የምንችለው ነገር ትልቅም ይሁን ትንሽ ሕመምተኛው እስኪሻለው ድረስ ሊጠቅመው ይችላል” በማለት ተናግረዋል። ሁለት ጊዜ ካንሰር ይዟት የዳነች ሲልቪያ የተባለች ሴትም በዚህ አባባል ትስማማለች። “ጓደኞቼ ለጨረር ሕክምና በየቀኑ ወደ ሌላ ከተማ በመኪና ያመላልሱኝ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ መንፈስን የሚያድስና የሚያጽናና ነበር! በመንገድ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን እያወራን እንሄዳለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከሕክምናው በኋላ አንድ ቦታ ገብተን ቡና እንጠጣ ነበር። ይህ ደግሞ ደህና እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር።”

ይሁን እንጂ ጓደኛህ የሚያስፈልገውን ነገር በትክክል እንደምታውቅ አድርገህ አታስብ። “ደጋግማችሁ ጠይቁ” በማለት ኬሊክ ሐሳብ ይሰጣሉ። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ለመርዳት ባላችሁ ፍላጎት የተነሳ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር አትሞክሩ። እንዲህ ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኛውን ከመርዳት ይልቅ ጭራሽ ተስፋ እንዲቆርጥ  ሊያደርገው ይችላል። ምንም ነገር እንዳደርግ ካልፈቀዳችሁልኝ ምንም ነገር ማድረግ አትችይም የሚል መልእክት እያስተላለፋችሁልኝ ነው። አሁንም ነገሮችን ማከናወን እንደምችል እንዲሰማኝ እፈልጋለሁ። ሰዎች እንደ ምስኪን እንዲያዩኝ አልፈልግም። ማድረግ የምችለውን ነገር እንዳደርግ እርዱኝ።”

ጓደኛህ አሁንም ነገሮችን የማከናወን ችሎታ እንዳለው እንዲሰማው የሚፈልግ እንደሆነ ግልጽ ነው። የኤድስ ሕመምተኛ የሆነው አዲልሰን እንዲህ ብሏል፦ “ስትታመሙ ሰዎች ምንም እንደማትጠቅሙ ወይም ምንም ነገር ማከናወን እንደማትችሉ አድርገው እንዲመለከቷችሁ አትፈልጉም። ጥቃቅን ነገሮችን መሥራት ቢሆንም እንኳ የሆነ እርዳታ ማበርከት ትፈልጋላችሁ። አንድ ነገር መሥራት እንደምትችሉ ማወቃችሁ በራሱ ጥሩ ስሜት ይፈጥርላችኋል! በሕይወት የመቀጠል ፍላጎታችሁን ይጨምርላችኋል። ሰዎች ውሳኔ እንዳደርግ ሲፈቅዱልኝና ውሳኔዬን ሲያከብሩልኝ ደስ ይለኛል። አንድ ሰው ታመመ ሲባል የአባትነት፣ የእናትነት ወይም ማንኛውም ዓይነት ኃላፊነቱን መወጣት አይችልም ማለት አይደለም።”

ግንኙነታችሁን አታቋርጡ

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፣ ደግሞም ለመከራ ቀን እንደተወለደ ወንድም ነው።”ምሳሌ 17:17 NW

▪ በቦታ ርቀት ወይም በሌላ ምክንያት ጓደኛህን ሄደህ መጠየቅ የማትችል ከሆነ ስልክ መደወል፣ ማስታወሻ ወይም ኢሜይል መጻፍ ትችላለህ። ስለምን ጉዳይ ልትጽፍለት ትችላለህ? አለን ዉልፌልት የተባሉ የሥነ ልቦና ባለሙያ እንዲህ በማለት ምክር ይሰጣሉ፦ “አብራችሁ ስላሳለፋችሁት አስደሳች ጊዜ ጻፉለት። በቅርቡ በድጋሚ እንደምትጽፉለት ቃል ግቡለት . . . እንዲሁም ቃላችሁን ጠብቁ።”

ያልሆነ ነገር እናገራለሁ ወይም ስህተት እሠራለሁ ብለህ በመፍራት የታመመ ጓደኛህን ከማበረታታት ወደኋላ አትበል። አብዛኛውን ጊዜ አጠገቡ መገኘትህ ብቻ እንኳ ልትረዳው እንደምትፈልግ ያሳያል። ሎሪ ሆፕ በመጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ሁላችንም የተሳሳተ መልእክት የሚያስተላልፍ ነገር ልንናገር ወይም ልናደርግ እንችላለን፤ አሊያም ደግሞ ሳይታወቀን በሆነ መንገድ ሰው እንጎዳለን። ችግሩ ይህ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እሳሳታለሁ ብለህ በመፍራት የአንተ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መራቅህ ነው።”

በጠና የታመመው ጓደኛህ የአንተ እርዳታ የሚያስፈልገው ከምንጊዜውም በበለጠ በዚህ ጊዜ ነው። “እውነተኛ ወዳጅ” መሆንህን አሳይ። እሱን ለመርዳት የምታደርገው ጥረት ሥቃዩን ባያስቀርለትም እንኳ የምትወደው ሰው የገጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲቋቋም ልትረዳው ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።