በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቀድሞ ዘመን የኖረ አንድ አታሚ መጽሐፍ ቅዱስን አስፋፋ

በቀድሞ ዘመን የኖረ አንድ አታሚ መጽሐፍ ቅዱስን አስፋፋ

 በቀድሞ ዘመን የኖረ አንድ አታሚ መጽሐፍ ቅዱስን አስፋፋ

መጻሕፍትንና ጥቅልሎችን በእጅ እየጻፉ ማዘጋጀት የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ አለው። መጻሕፍትን በማተሚያ መሣሪያ ማተም ግን ያን ያህል ረጅም ዕድሜ አላስቆጠረም። እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ መጻሕፍትን በማተሚያ መሣሪያ ማዘጋጀት የተጀመረው በ868 ዓ.ም. በቻይና ሲሆን በወቅቱ ሕትመት የሚካሄደው በእንጨት ላይ የተቀረጹ ፊደላትንና ምስሎችን በመጠቀም ነበር። በ1455 አካባቢ ጀርመናዊው ዮሐንስ ጉተንበርግ፣ በተፈለገው መልክ በተርታ ሊደረደሩ የሚችሉ ከብረት የተቀረጹ የተለያዩ ፊደላትን በመጠቀም ማተም የሚቻልበትን ዘዴ ፈለሰፈ፤ ከዚያም በላቲን ቋንቋ የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ አትሞ አወጣ።

 መጽሐፍ ቅዱሶችና ሌሎች መጻሕፍት በስፋት መሠራጨት የጀመሩት ግን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይኸውም መጻሕፍትን ማተም የታወቀ ኢንዱስትሪ ከሆነ በኋላ ነበር። ኑረምበርግ በጀርመን ውስጥ ላለው የሕትመት ኢንዱስትሪ ማዕከል የነበረች ሲሆን የዚያች ከተማ ተወላጅ የነበረው አንቶን ኮበርገር ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን በስፋት በማዘጋጀትና በማተም ረገድ የመጀመሪያው ሰው ሳይሆን አይቀርም።

ኮበርገርን ጨምሮ የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ አታሚዎች በየትኛውም አገር ለሚኖሩ ሰዎች ባለውለታ ናቸው። እስቲ ስለ ኮበርገርና ስላከናወነው ሥራ እንመልከት።

‘ለመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ቦታ ይሰጥ ነበር’

ኮበርገር በ1470 በኑረምበርግ ከተማ የመጀመሪያውን ማተሚያ ቤት ከፈተ። የድርጅቱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት በባዝል፣ በስትራስቡርግ፣ በሊዮንና በሌሎችም የአውሮፓ ከተሞች በአንድ ጊዜ በ24 ማተሚያ ማሽኖች ይሠራ ነበር፤ ማተሚያ መሣሪያዎቹን የሚያንቀሳቅሱ ሰዎችን እንዲሁም የእጅ ባለሙያዎችንና ሌሎችን ጨምሮ 100 የሚሆኑ ሠራተኞች በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥረው ነበር። ኮበርገር የመካከለኛው ዘመን የላቲን ጽሑፎችንና በዘመኑ የነበረውን አብዛኛውን ሳይንሳዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ አትሟል። በሥራ ላይ በነበረባቸው ጊዜያት 236 የተለያዩ ጽሑፎችን አትሞ ነበር። አንዳንዶቹ ጽሑፎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ገጾች ያሏቸው ሲሆኑ እያንዳንዱ ገጽ በእጅ በሚንቀሳቀሱ ማተሚያዎች አማካኝነት በየተራ ይታተም ነበር።

ኮበርገር ለማተም የሚጠቀምባቸው ፊደላት ቅርጽ ከፍተኛ ጥራት እንዲኖረው ያደርግ ስለነበር እሱ የሚያትማቸው መጻሕፍት በውበታቸውና በተነባቢነታቸው ዝና አትርፈው ነበር። “ኮበርገር ፊደላቱ ወዲያው ወዲያው ቀለም እንዲቀቡና ቅርጻቸው ልቅም ያለ እንዲሆን ይፈልግ ነበር” በማለት አልፍሬድ ቦርኬል የተባሉት የታሪክ ምሑር ጽፈዋል። “ያረጁ ፊደላት ለማተሚያነት እንዲያገለግሉ አይፈቀድም ነበር።” በተጨማሪም ኮበርገር ካተማቸው መጻሕፍትና መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል ብዙዎቹ በጥሩ ሁኔታ የተሠሩ ሥዕላዊ መግለጫዎች ነበሯቸው፤ እነዚህ ሥዕሎች የሚታተሙት በእንጨት ላይ የተቀረጹ ምስሎችን በመጠቀም ነበር።

ኮበርገር ሥራውን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ “ለአንድ መጽሐፍ፣ ይኸውም ለመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ቦታ እንደሚሰጥ በግልጽ ይታይ ነበር” በማለት የኮበርገርን የሕይወት ታሪክ ያዘጋጁት ኦስካር ሄዝ ጽፈዋል። ኮበርገርና የሥራ ባልደረቦቹ በተቻለ መጠን ትክክለኛ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ለማግኘት በጣም ለፍተዋል። ይህ ሥራ በጭራሽ ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም በእጅ የተገለበጡት አብዛኞቹ የብራና ጽሑፎች የሚገኙት በገዳማት ውስጥ ሲሆን እንደ ውድ ንብረት ተደርገው ስለሚታዩ ለመገልበጥ የሚፈልግ ሰው እንኳ መዋስ የሚችለው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር፤ ለዛውም ፈቃድ ከተገኘ ነው።

የላቲንና የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱሶች

ኮበርገር በላቲን ቋንቋ ያዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ (ቢብሊያ ላቲና) 15 ጊዜ ያተመው ሲሆን የመጀመሪያው እትም የወጣው በ1475 ነበር። አንዳንዶቹ እትሞች የኖኅን መርከብ፣ አሥርቱን ትእዛዛትና የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ የሚያሳዩ ሥዕላዊ መግለጫዎችን የያዙ ነበሩ። በ1483 ኮበርገር በጀርመንኛ ያዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ (ቢብሊያ ጀርማኒካ) በ1,500 ቅጂዎች ያተመ ሲሆን ይህም በወቅቱ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ነበረ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የአንባቢዎቹን ስሜት ለመቀስቀስና ጥቅሶቹን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እንዲሁም ማንበብ የማይችሉ ሰዎች፣ የሚያውቋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ትዝ እንዲሏቸው ለመርዳት ሲባል ከ100 በላይ ሥዕላዊ መግለጫዎችን ይዞ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የነበሩት ሥዕሎች ከጊዜ በኋላ በተሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥዕላዊ መግለጫዎች በተለይም በጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ኮበርገር በ1483 ያዘጋጀው የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳጅነት እያገኘ መጥቶ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ሌላ የጀርመንኛ እትም ማዘጋጀት ሳይችል ቀርቷል። ኮበርገር ይህን እትም ለማዘጋጀት መሠረት አድርጎ የተጠቀመው በ14ኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀውንና ቤተ ክርስቲያኗ ያገደችውን የዎልደንሳውያን ትርጉም ነበር፤ በእርግጥ ኮበርገር የጀርመንኛውን እትም ሲያዘጋጅ የረዱት ሰዎች ይህን ትርጉም ቤተ ክርስቲያኗ ከምትቀበለው የላቲን ቩልጌት ጋር ለማስማማት በጥንቃቄ አስተካክለውት ነበር። * በቀጣዩ ዓመት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት ስምንተኛ የዎልደንሳውያንን ማኅበረሰብ ለመደምሰስ ተንቀሳቀሱ። ከዚያ በኋላም መጽሐፍ ቅዱስ ተራው ሕዝብ በሚጠቀምበት ቋንቋ እንዳይተረጎም ቤተ ክርስቲያን ያስነሳችው ተቃውሞ ይበልጥ እየተባባሰ ሄደ። መጋቢት 22, 1485 በጀርመን የሜይንዝ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ቤርቶልድ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ መተርጎሙን የሚያወግዝ መግለጫ አወጡ። በቀጣዩ ዓመት ጥር 4 ላይ ሊቃነ ጳጳሳት ቤርቶልድ ይህን መግለጫ በድጋሚ አወጡ። ተቃውሞው እየከረረ በመሄዱ ኮበርገር መጽሐፍ ቅዱስን በጀርመንኛ እንደገና ለማተም አልደፈረም።

የሆነ ሆኖ አንቶን ኮበርገር ድካሙ በከንቱ አልቀረም። አዲስ የተፈለሰፈውን የሕትመት ጥበብ በመጠቀም ብዙ ዓይነት መጻሕፍትን እያዘጋጀ በአውሮፓ ውስጥ ረከስ ባለ ዋጋ እንደ ልብ እንዲገኙ በማድረግ ረገድ የመሪነቱን ቦታ ይዞ ነበር። ኮበርገር በዚህ ረገድ ያከናወነው ሥራ መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሰው እጅ እንዲገባ ረድቷል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 “ዎልደንሳውያን—ከመናፍቅነት ወደ ፕሮቴስታንትነት” የሚለውን በመጋቢት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ሲጣል፤ በወርቅ ቅብ ያጌጠ ፊደል፤ ልቅም ያለ ቅርጽ ባላቸው የማተሚያ ፊደላት የተዘጋጀ ጽሑፍ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮበርገር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሥዕል ያጌጡና ስለ ዘፍጥረት 1:1 የተሰጡ ማብራሪያዎችን የያዙ የኮበርገር የላቲንና የጀርመን መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የመጽሐፍ ቅዱሶቹ ፎቶዎች፦ Courtesy American Bible Society Library፤ ኮበርገር፦ Mit freundlicher Genehmigung der Linotype GmbH