በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል

ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል

ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ልክ ሲተያዩ የተሰማውን መጥፎ ስሜት መቼም ቢሆን አይረሳውም። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ እንዳዘነበት ወይም ቅር እንደተሰኘበት የሚጠቁም ነገር በፊቱ ላይ ተመልክቶ ይሆን? ይህንን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ “ጌታም ዞር ብሎ ጴጥሮስን አየው” ከማለት ውጪ ምንም አይናገርም። (ሉቃስ 22:61) ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የሠራው ስህተት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በዚያች ቅጽበት መገንዘብ ችሎ ነበር። የተፈጸመው ነገር ልክ ጌታው አስቀድሞ እንደተናገረው ነበር፤ የሚወደውን ጌታውን ፈጽሞ እንደማይክደው በተደጋጋሚ ተናግሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ጌታውን ክዷል። በመሆኑም ይህ ወቅት ጴጥሮስ በሕይወቱ ውስጥ በጣም ያዘነበት ቀን ሳይሆን አይቀርም።

ሆኖም ጴጥሮስ ከዚህ በኋላ ምንም ተስፋ የለውም ማለት አይደለም። ጴጥሮስ ታላቅ እምነት ያለው ሰው በመሆኑ ስህተቱን አስተካክሎ ወደ ቀድሞው አቋሙ የመመለስ እንዲሁም ኢየሱስ ካስተማራቸው ታላላቅ ትምህርቶች አንዱ የሆነውን ይቅር ባይነትን የመማር አጋጣሚ ነበረው። ሁላችንም ይህን ትምህርት መማር ያስፈልገናል፤ እንግዲያው ጴጥሮስ ይህን ትምህርት ሲማር ያደረገውን አስቸጋሪ ጉዞ እስቲ እንመልከት።

ብዙ መማር ነበረበት

ከላይ ያለው ሁኔታ ከመፈጸሙ ከስድስት ወራት ገደማ በፊት ጴጥሮስ ይኖርባት በነበረችው በቅፍርናሆም ከተማ ሳሉ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” በማለት ጠይቆት ነበር። ጴጥሮስ ይህን ሐሳብ ሲያቀርብ በጣም ይቅር ባይ እንደሆነ አድርጎ አስቦ ሊሆን ይችላል። በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት አስተማሪዎች አንድ ሰው ይቅርታ ማድረግ ያለበት ሦስት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር! ኢየሱስ ግን “እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” በማለት መለሰለት።—ማቴዎስ 18:21, 22

ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ የደረሰበትን እያንዳንዱን በደል እየቆጠረ መመዝገብ እንዳለበት መናገሩ ነበር? በፍጹም፤ ጴጥሮስ 7 ጊዜ ይቅር ለማለት ሲጠይቅ ኢየሱስ 77 ጊዜ ይቅር ሊል እንደሚገባ መናገሩ የበደለን ሰው ይህን ያህል ጊዜ ይቅር ማለት ይገባል ብሎ ቁጥር መወሰን እንደማይቻል የሚያሳይ ነበር። ኢየሱስ በወቅቱ ሰፍኖ የነበረው ርኅራኄና ይቅር ባይነት የጎደለው መንፈስ በጴጥሮስም ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ጠቁሟል፤ በመዝገቡ ላይ ያሰፈረውን ሒሳብ እንደሚያወራርድ የሒሳብ ሠራተኛ በደልን የመቁጠር አዝማሚያ በብዙዎች ዘንድ ይታይ ነበር። ከአምላክ መሥፈርት አንጻር የምናሳየው ይቅር ባይነት ግን በጣም ሰፊ ነው።

ጴጥሮስ ኢየሱስ የሰጠውን ሐሳብ አልተቃወመም። ይሁንና የተሰጠውን ትምህርት ከልቡ ተቀብሎት ይሆን? አንዳንድ ጊዜ ስለ ይቅር ባይነት ይበልጥ የምንማረው እኛ ራሳችን ይቅር መባል የሚያስፈልገን ሁኔታ ሲያጋጥመን ነው። እስቲ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የተከናወኑትን ሁኔታዎች መለስ ብለን እንመልከት። በዚያ አስጨናቂ ወቅት ጴጥሮስ በርካታ ስህተቶችን በመፈጸሙ የጌታውን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገው ነበር።

ጴጥሮስ የፈጸማቸው ስህተቶች

ይህ ዕለት በጣም ወሳኝ ነበር፤ ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት የሚጠናቀቅበት ጊዜ ስለደረሰ ይህ ለእሱ የመጨረሻ ምሽት ነው። ለሐዋርያቱ ሊያስተምራቸው የሚፈልገው ብዙ ነገሮች የነበሩት ሲሆን ከእነዚህ አንዱ ትሕትና ነው። ኢየሱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ በትሕትና ረገድ ምሳሌ ትቶላቸዋል፤ ብዙውን ጊዜ ይህ ሥራ የሚሰጠው ዝቅተኛ ለሆነ አገልጋይ ነው። ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ልታጥብ ነው?” የሚል ጥያቄ አነሳ፤ ይህም የኢየሱስ ድርጊት ትክክል መሆኑን እንደተጠራጠረ የሚያሳይ ነበር። ከዚያም እግሩን ሊያጥበው ሲል ለመከላከል ሞከረ። እንደገና ደግሞ ሐሳቡን ቀይሮ እግሩን ብቻ ሳይሆን እጁንና ራሱንም ጭምር እንዲያጥበው ኢየሱስን ጠየቀው! ሁኔታው ትዕግሥት የሚፈታተን ቢሆንም ኢየሱስ እግራቸውን ማጠቡ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያትና ምን ትርጉም እንዳለው ረጋ ባለ መንፈስ ገለጸ።—ዮሐንስ 13:1-17

ከዚህ ብዙም ሳይቆይ ግን ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ታላቅ ማን እንደሆነ መከራከር ጀመሩ። ኩራት በተንጸባረቀበት በዚህ አሳፋሪ ድርጊት የጴጥሮስም እጅ እንደነበረበት ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን ኢየሱስ በደግነት እርማት የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ መልካም ጎናቸውን በማንሳት ይኸውም በታማኝነት ከጌታቸው ጎን መቆማቸውን በመጥቀስ አድናቆቱን ገለጸላቸው። አክሎም ሁሉም ጥለውት እንደሚሸሹ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ሞትም እንኳ ቢመጣ ከኢየሱስ እንደማይለይ ገለጸ። ኢየሱስ ግን በዚያ ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ተናገረ። ጴጥሮስ ይህን እንደማያደርግ በመግለጽ ብቻ ሳይወሰን “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” በማለት በጉራ ተናገረ!—ማቴዎስ 26:31-35፤ ማርቆስ 14:27-31፤ ሉቃስ 22:24-28

ኢየሱስ በጴጥሮስ ሁኔታ ትዕግሥቱ ተሟጥጦ ይሆን? በፍጹም፤ እንዲያውም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሁሉ ኢየሱስ ፍጽምና የጎደላቸው ሐዋርያቱ ባላቸው በጎ ጎን ላይ ትኩረት አድርጓል። ጴጥሮስ እንደሚክደው ቢያውቅም እንዲህ ብሎታል፦ “እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ፤ አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።” (ሉቃስ 22:32) በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ከስህተቱ እንደሚማርና እንደ ቀድሞው በታማኝነት በአገልግሎቱ እንደሚቀጥል ያለውን እምነት ገልጿል። እንዴት ያለ የደግነትና የይቅር ባይነት መንፈስ ነው!

ከዚያም በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ በነበሩበት ወቅት ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ጊዜ እርማት የሚያሻው ድርጊት ፈጽሟል። ኢየሱስ በሚጸልይበት ወቅት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ነቅተው እንዲጠብቁ ነግሯቸው ነበር። ኢየሱስ እጅግ ተጨንቆ ስለነበር ድጋፍ የሚያስፈልገው ቢሆንም ወደነሱ ሲመለስ ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት ከአንዴም ሁለቴ እንቅልፍ ጥሏቸው አገኛቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ሁኔታቸውን እንደተረዳላቸውና ይቅር እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ “መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” አላቸው።—ማርቆስ 14:32-38

ብዙም ሳይቆይ ችቦና ቆመጥ የያዙ እንዲሁም ሰይፍ የታጠቁ ብዙ ሰዎች መጡ። ይህ ጥንቃቄና ብልሃት የሚያስፈልግበት ወቅት ነበር። ጴጥሮስ ግን በችኮላ እርምጃ ወሰደ፤ ሰይፉን መዞ ማልኮስ የተባለውን የሊቀ ካህናቱን ባሪያ በመምታት አንዱን ጆሮውን ቆረጠው። ኢየሱስ በእርጋታ ጴጥሮስን ካረመውና የባሪያውን ጆሮ ከፈወሰ በኋላ ከዓመፅ መራቅ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ተከታዮቹ እስከ ዛሬ ድረስ የሚመሩበትን መሠረታዊ ሥርዓት ተናገረ። (ማቴዎስ 26:47-55፤ ሉቃስ 22:47-51፤ ዮሐንስ 18:10, 11) ጴጥሮስ እስካሁን ድረስ በርካታ ስህተቶችን በመፈጸሙ የጌታውን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገው ነበር። የእሱ ሁኔታ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ [እንደምንሰናከል]” ያስታውሰን ይሆናል። (ያዕቆብ 3:2) ከእኛስ መካከል በእያንዳንዷ ዕለት የአምላክ ይቅርታ የማያስፈልገው ማን አለ? ጴጥሮስ በዚህ ምሽት የፈጸመው ስህተት ይህ ብቻ አልነበረም። ከዚህ የከፋ ነገር አጋጥሞታል።

ከሁሉ የከፋው የጴጥሮስ ስህተት

ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን ሰዎች የሚፈልጉት እሱን ከሆነ ሐዋርያቱን እንዲተዉአቸው ጠየቃቸው። ሰዎቹ ኢየሱስን ሲያስሩት ጴጥሮስ ቆሞ ከመመልከት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም። ከዚያም እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ እሱም ጥሎት ሸሸ።

ኢየሱስ በመጀመሪያ የተወሰደው ቀድሞ ሊቀ ካህናት ወደነበረው ወደ ሐና ቤት ሲሆን ጴጥሮስና ዮሐንስም መሸሻቸውን ትተው ወደዚህ መጥተዋል። ሰዎቹ ኢየሱስን ከዚያ አውጥተው ወደ ሌላ ቦታ ሲወስዱት ጴጥሮስና ዮሐንስ ይከተሉት ጀመር፤ ሆኖም ይህን የሚያደርጉት “በርቀት” ሆነው ነበር። (ማቴዎስ 26:58፤ ዮሐንስ 18:12, 13) ጴጥሮስ ፈሪ ሰው አልነበረም። በርቀትም እንኳ ኢየሱስን መከተል በተወሰነ መጠንም ቢሆን ድፍረት እንደሚጠይቅ ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ኢየሱስን የያዙት ሰዎች መሣሪያ የታጠቁ ናቸው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ጴጥሮስ ከእነሱ በአንዱ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር። ያም ቢሆን ግን ጴጥሮስ ካስፈለገ ከጌታው ጋር ለመሞት እንኳ ፈቃደኛ እንደሆነ የተናገረውን ያህል ፍቅርና ታማኝነት ሳያሳይ ቀርቷል።—ማርቆስ 14:31

በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ልክ እንደ ጴጥሮስ “በርቀት” ማለትም ማንም ሳያውቅባቸው ክርስቶስን መከተል ይፈልጋሉ። ይሁንና ጴጥሮስ ራሱ በኋላ ላይ እንደጻፈው በትክክል ክርስቶስን መከተል የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ይህን ማድረጋችን ምንም ዓይነት ችግር ቢያስከትልብን በሁሉም ነገር የክርስቶስን አርዓያ በመከተል በተቻለን መጠን ወደ እሱ መቅረብ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21

ጴጥሮስ እንዳይታይ በመጠንቀቅ ኢየሱስን የያዙትን ሰዎች ሲከተል ቆይቶ በመጨረሻ በኢየሩሳሌም ውስጥ ካሉት ትላልቅ ቤቶች ወደ አንዱ ደረሰ። ቤቱ ባለጸጋ የሆነውና ተደማጭነት ያለው የሊቀ ካህናቱ የቀያፋ ነበር። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ቤቶች በዙሪያቸው አጥር ይኖራቸዋል። ጴጥሮስ መግቢያው ጋ ሲደርስ እንዳይገባ ተከለከለ። ከጴጥሮስ ቀድሞ ወደ ግቢው ገብቶ የነበረው ዮሐንስ ወጥቶ በር ጠባቂዋን በማነጋገር ጴጥሮስን አስገባው። ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር አብሮ የቆየ አይመስልም፤ አሊያም ደግሞ ከጌታው ጎን ለመቆም ሲል ወደ ቤት ውስጥ አልገባም። በኢየሱስ ላይ የሚመሠክሩት ሐሰተኛ ምሥክሮች ችሎቱ ወደሚካሄድበት ቤት ሲገቡና ሲወጡ ከሚመለከቱትና የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም እሳት ከሚሞቁት አንዳንድ ባሪያዎችና የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ጋር በግቢው ውስጥ ቆሞ ነበር።—ማርቆስ 14:54-57፤ ዮሐንስ 18:15, 16, 18

በር ጠባቂ የነበረችውና ጴጥሮስን ያስገባችው አገልጋይ ጴጥሮስ ወደ እሳቱ ብርሃን ሲጠጋ በደንብ አየችው። በዚህ ጊዜ ስላወቀችው ወደ እሱ እየጠቆመች “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው። ጴጥሮስ ያልጠበቀው ነገር ስለሆነበት ኢየሱስን እንደማያውቀው በመናገር ካደ፤ እንዲያውም ሴትየዋ ስለ ምን እያወራች እንደሆነ እንዳልገባው ተናገረ። ሰው እንዳያየው ሲል ወደ ግቢው መግቢያ አካባቢ ቢሄድም አንዲት ሌላ ሴት ስታየው አወቀችው፤ እሷም “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” በማለት ተናገረች። ጴጥሮስም “ሰውየውን አላውቀውም!” በማለት ይምል ጀመር። (ማቴዎስ 26:69-72) ጴጥሮስ በዚህ መንገድ ኢየሱስን ለሁለተኛ ጊዜ ካደው፤ ዶሮ ሲጮኽ የሰማው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና በጣም ተረብሾ ስለነበር ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ለማስታወስ አልቻለም።

ይህ ከሆነ የተወሰነ ጊዜ ቢያልፍም ጴጥሮስ አሁንም ከሰው እይታ ለመሰወር እየሞከረ ነበር። ሆኖም በግቢው ውስጥ ሰብሰብ ብለው የቆሙ ሰዎች ወደ እሱ ቀረቡ። ከሰዎቹ መካከል ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው ማልኮስ የተባለ ባሪያ ዘመድ ይገኝበት ነበር። እሱም ጴጥሮስን “በአትክልቱ ስፍራ ከእሱ ጋር አይቼህ የለም እንዴ?” አለው። ጴጥሮስም ሰዎቹ እንደተሳሳቱ ለማሳመን ይጥር ጀመር። ምናልባትም ‘የተናገርኩት ውሸት ከሆነ እርግማን ይድረስብኝ’ እያለ ሳይምል አልቀረም። ጴጥሮስ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ ለሁለተኛ ጊዜ ዶሮ ሲጮኽ ሰማ።—ዮሐንስ 18:26, 27፤ ማርቆስ 14:71, 72

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ችሎቱ ከሚካሄድበት ክፍል ወጣ፤ በረንዳው ላይ ሆኖ በግቢው ውስጥ የሚከናወነውን ነገር መመልከት ይችል ነበር። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ከጴጥሮስ ጋር ዓይን ለዓይን የተጋጩት በዚህ ጊዜ ነበር። በዚያች ቅጽበት ጴጥሮስ ጌታውን በጣም እንዳሳዘነው ተሰማው። ጴጥሮስ በጥፋተኝነት ስሜት ተውጦ ግቢውን ለቅቆ ወጣ። ከዚያም በማዘቅዘቅ ላይ ያለችው ጨረቃ በምትሰጠው ብርሃን እየተመራ ወደ ከተማዋ አውራ ጎዳናዎች አቀና። የሚያየው ሁሉ ጭልም አለበት። እንባ ይተናነቀው ጀመር። ከዚያም ስሜቱ ፈንቅሎት ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።—ማርቆስ 14:72፤ ሉቃስ 22:61, 62

ብዙ ጊዜ አንድ ሰው እንዲህ ያለ ከባድ ስህተት እንደፈጸመ ሲገነዘብ ኃጢአቱ ይቅር ሊባልለት እንደማይችል ይሰማው ይሆናል። ጴጥሮስ እንዲህ ሳይሰማው አልቀረም። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የሠራው ስህተት ይቅር የማይባል ነበር?

ጴጥሮስ የሠራው ኃጢአት ይቅር የማይባል ነበር?

ጴጥሮስ ጎህ ከቀደደ በኋላ በቀኑ ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች ሲመለከት ሐዘኑ ምን ያህል ጥልቅ ሊሆን እንደሚችል መገመት ያስቸግራል። ኢየሱስ ለሰዓታት ሲሠቃይ ከቆየ በኋላ በመጨረሻም ሲሞት ጴጥሮስ በጸጸት ስሜት ተውጦ መሆን አለበት። ጴጥሮስ፣ ጌታው ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ዕለት በሥቃዩ ላይ ሥቃይ እንደጨመረበት ባሰበ ቁጥር ሕሊናው እረፍት ሳይነሳው አይቀርም። ጴጥሮስ በከፍተኛ ሐዘን ቢዋጥም የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም። ይህን የምንለው ብዙም ሳይቆይ ከወንድሞቹ ጋር መገናኘቱን እንደቀጠለ ዘገባው ስለሚናገር ነው። (ሉቃስ 24:33) ሁሉ ነገር የጨለመ በሚመስልበት በዚያ ሌሊት ባደረጉት ነገር ሐዋርያቱ በሙሉ ተቆጭተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ አንድ ላይ መሆናቸው በተወሰነ መጠንም ቢሆን እርስ በርሳቸው እንዲጽናኑ ረድቷቸው መሆን አለበት።

ጴጥሮስ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ካደረገባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ይህ ነው ማለት ይቻላል። አንድ የአምላክ አገልጋይ በኃጢአት ሲወድቅ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ነገር ስህተቱ ምን ያህል ከባድ ነው የሚለው ሳይሆን ከወደቀበት በመነሳት ሁኔታዎችን ለማስተካከል ምን ያህል ጥንካሬ አለው የሚለው ነው። (ምሳሌ 24:16) ጴጥሮስ መንፈሱ ቢደቆስም ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር አብሮ በመሆን ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። አንድ ሰው በሐዘን ወይም በጸጸት ስሜት ሲደቆስ ቶሎ የሚቀናው ራሱን ማግለል ነው፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ አደጋ አለው። (ምሳሌ 18:1) ከዚህ ይልቅ ከእምነት ባልጀሮቻችን ጋር ተቀራርበን በመኖር መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን መልሰን ለማግኘት መጣር የጥበብ አካሄድ ነው።—ዕብራውያን 10:24, 25

ጴጥሮስ የኢየሱስ አስከሬን በመቃብሩ ውስጥ እንዳልተገኘ የሚገልጸውን አስደንጋጭ ዜና መስማት የቻለው ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር ስለነበር ነው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ይህን ሲሰሙ ኢየሱስ ወደ ተቀበረበት ስፍራ እየሮጡ ሄዱ። ከሁለቱ በዕድሜ የሚያንሰው ዮሐንስ ሳይሆን አይቀርም፤ መቃብሩ ቦታ ቀድሞ የደረሰው እሱ ነበር። ሆኖም ታሽጎ የነበረው የመቃብሩ በር ተከፍቶ ሲያገኘው ለመግባት አመነታ። ጴጥሮስ ግን ከመሮጡ ብዛት ትንፋሽ ቢያጥረውም እየተንደረደረ ወደ ውስጥ ገባ። በእርግጥም መቃብሩ ባዶ ነበር!—ዮሐንስ 20:3-9

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ አምኖ ነበር? መጀመሪያ ላይ አላመነም ነበር፤ ታማኝ የሆኑ ሴቶች መላእክት እንደተገለጡላቸውና ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን እንደገለጹላቸው ቢናገሩም እንኳ የተናገሩትን ለመቀበል ከብዶት ነበር። (ሉቃስ 23:55 እስከ 24:11) ቀኑ እየተገባደደ ሲሄድ ግን በጴጥሮስ ልብ ውስጥ የነበረው ሐዘንና ጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ ተወገደ። ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ ተነስቷል! ለሁሉም ሐዋርያቱ ተገልጦላቸዋል። ይሁንና ከዚያ በፊት ለአንድ ሐዋርያ ለብቻው ተገልጦለት ነበር። ሐዋርያት በዚያኑ ቀን “ጌታ በእርግጥ ተነስቷል፤ ለስምዖንም ተገልጦለታል!” ብለው ነበር። (ሉቃስ 24:34) በተመሳሳይም ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚያ ልዩ ቀን ሲጽፍ ኢየሱስ “ለኬፋም ታየ፤ ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ ታየ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:5) ኬፋ እና ስምዖን የሚሉት ስሞች የጴጥሮስ ሌላ መጠሪያዎች ናቸው። ኢየሱስ በዚያኑ ቀን ጴጥሮስ ብቻውን ሳለ ሳይገለጥለት አልቀረም።

ኢየሱስና ጴጥሮስ በድጋሚ ሲገናኙ የሆነውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ጴጥሮስ የሚወደውን ጌታውን እንደገና በሕይወት በማየቱ እንዲሁም ባደረገው ነገር ማዘኑንና መጸጸቱን ለመግለጽ አጋጣሚ በማግኘቱ ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን። ጴጥሮስ በዚህ ወቅት ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው የኢየሱስን ይቅርታ ማግኘት ነበር። ኢየሱስ ምሕረት እንዳደረገለት ማን ሊጠራጠር ይችላል? ሙሉ በሙሉ ይቅርታ አድርጎለታል! በዛሬው ጊዜ ኃጢአት የሠሩ ክርስቲያኖች የጴጥሮስን ሁኔታ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። አምላክ ይቅር ሊለን እንደማይችል ፈጽሞ ሊሰማን አይገባም። ኢየሱስ “ይቅርታው ብዙ” የሆነውን አምላክ ባሕርይ ሙሉ በሙሉ አንጸባርቋል።—ኢሳይያስ 55:7

ይቅር እንዳለው የሚያሳዩ ተጨማሪ ማረጋገጫዎች

ኢየሱስ ሐዋርያቱን በድጋሚ ሊያገኛቸው ስለፈለገ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ነግሯቸው ነበር። እዚያ ሲደርሱ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ለማጥመድ ፈለገ። አንዳንዶቹም አብረውት ማጥመድ ጀመሩ። ጴጥሮስ አብዛኛውን ሕይወቱን ባሳለፈበት ሐይቅ ላይ እንደገና መሥራት ጀመረ። ጀልባው የሚያሰማውን ሲጢጥ የሚል ድምፅ እንዲሁም ማዕበሉ ከጀልባው ጋር ሲላተም የሚፈጠረውን ድምፅ ሲሰማና ሻካራ የሆኑትን መረቦች በእጁ ሲዳስስ የቀድሞ ትዝታው ሳይቀሰቀስበት አልቀረም። የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት በማብቃቱ ከዚህ በኋላ በሕይወቱ ምን እንደሚያደርግ እያውጠነጠነ ይሆን? ብዙም ውጥረት ወደማያስከትለው የዓሣ አስጋሪነት ሙያ መመለስ አምሮት ይሆን? ያም ሆነ ይህ ሐዋርያቱ ሌሊቱን ሙሉ ሲያሰግሩ ቢያድሩም ምንም ዓሣ አልያዙም ነበር።—ማቴዎስ 26:32፤ ዮሐንስ 21:1-3

ይሁን እንጂ ሊነጋጋ ሲል ከባሕሩ ዳርቻ አካባቢ አንድ ድምፅ ተጣርቶ መረባቸውን በሌላኛው አቅጣጫ እንዲጥሉ ነገራቸው። በተባሉት መሠረት መረባቸውን ሲጥሉ 153 ዓሦች ያዙ! በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ፣ ሲያናግራቸው የነበረው ማን እንደሆነ ተገነዘበ። ከጀልባዋ ዘሎ ባሕሩ ውስጥ በመግባት እየዋኘ ወደ ዳርቻው ሄደ። በባሕሩ ዳርቻ ላይ ኢየሱስ ዓሣውን በከሰል ጠብሶ ሰጣቸው። የኢየሱስ ትኩረት ያረፈው ጴጥሮስ ላይ ነበር።

ኢየሱስ ወደተከመሩት ዓሦች እያመለከተ ሳይሆን አይቀርም “ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” በማለት ጠየቀው። ጴጥሮስ ዓሣ የማስገሩ ሥራ ለኢየሱስ ካለው ፍቅር ይበልጥበት ይሆን? ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ እንደካደው ሁሉ ኢየሱስም ለእሱ ያለውን ፍቅር በጓደኞቹ ፊት ለማረጋገጥ የሚያስችሉት ሦስት አጋጣሚዎች ሰጠው። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደሚወደው ሲገልጽ ኢየሱስም ፍቅሩን እንዴት ማሳየት እንደሚችል ነገረው፤ ይህን የሚያደርገው ከምንም ነገር በላይ ቅዱሱን አገልግሎት በማስቀደም እንዲሁም ታማኝ ተከታዮቹን ያቀፈውን የክርስቶስን መንጋ በመመገብና በመንከባከብ ነው።—ዮሐንስ 21:4-17

ኢየሱስ ይህን በማድረጉ ጴጥሮስ አሁንም ቢሆን በኢየሱስም ሆነ በአባቱ ዘንድ ተፈላጊ እንደሆነ አረጋግጧል። ጴጥሮስ በክርስቶስ አመራር ሥር በመሆን በጉባኤው ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህ ኢየሱስ ጴጥሮስን ሙሉ በሙሉ ይቅር እንዳለው የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው! ጴጥሮስ ኢየሱስ ባሳየው ምሕረት ልቡ እንደተነካ ምንም ጥርጥር የለውም።

ጴጥሮስ የተሰጠውን ኃላፊነት ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት አከናውኗል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ወንድሞቹን አበረታቷል። ጴጥሮስ የክርስቶስን ተከታዮች በደግነትና በትዕግሥት ተንከባክቧል እንዲሁም መግቧል። ስምዖን ይባል የነበረው ይህ ሰው ኢየሱስ ከሰጠው ጴጥሮስ ወይም ዐለት ከሚለው ስም ጋር በሚስማማ መንገድ በምንም ነገር የማይናወጥ፣ ጠንካራና አስተማማኝ በመሆን በጉባኤው ላይ መልካም ተጽዕኖ አሳድሯል። ጴጥሮስ ራሱ የጻፋቸው ፍቅር የተንጸባረቀባቸው ሁለት ደብዳቤዎች ለዚህ ግሩም ምሥክር የሚሆኑ ሲሆን እነዚህ ደብዳቤዎች ጠቃሚ ትምህርት የሚገኝባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ደብዳቤዎች ጴጥሮስ ይቅር ባይነትን በተመለከተ ከኢየሱስ ያገኘውን ትምህርት ፈጽሞ እንዳልረሳው ያሳያሉ።—1 ጴጥሮስ 3:8, 9፤ 4:8

እኛም ከዚህ ትምህርት መውሰድ እንችላለን። አምላክ ለምንሠራቸው በርካታ ስህተቶች ይቅር እንዲለን በየዕለቱ እንጠይቀዋለን? ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዳለን በመተማመን ራሳችንን ከመኮነን እንቆጠባለን? እንዲሁም ሌሎችን ይቅር እንላለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጴጥሮስን በእምነቱ ጌታውን ደግሞ በምሕረቱ መምሰል እንችላለን።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጴጥሮስ በርካታ ስህተቶችን በመፈጸሙ የጌታውን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገው ነበር፤ ከእኛስ መካከል በእያንዳንዷ ዕለት የአምላክ ይቅርታ የማያስፈልገው ማን አለ?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጌታም ዞር ብሎ ጴጥሮስን አየው”

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ጌታ ለስምዖን ተገልጦለታል!’