በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

ኢየሱስ ታዛዥነትን ተምሯል

ኢየሱስ ታዛዥነትን ተምሯል

አንዳንድ ጊዜ መታዘዝ ይከብድሃል?— * ከሆነ ይህ የሚያስገርም አይደለም። ሁሉም ሰው መታዘዝ የሚከብደው ጊዜ አለ። ኢየሱስም እንኳ መታዘዝን መማር አስፈልጎት እንደነበር ታውቃለህ?—

ሁሉም ልጆች መታዘዝ ያለባቸው ማንን እንደሆነ ታውቃለህ?— አባትና እናታቸውን ካልክ ትክክል ነህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ይላል። (ኤፌሶን 6:1) የኢየሱስ አባት ማን ነው?— ይሖዋ አምላክ ነው፤ ይሖዋ የእኛም አባት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) የኢየሱስ አባት ዮሴፍ እናቱ ደግሞ ማርያም ናት ብለህ ከመለስክም ትክክል ነህ። ዮሴፍና ማርያም የኢየሱስ ወላጆች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?—

መልአኩ ገብርኤል፣ ማርያም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽማ ባታውቅም ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። ይሖዋ ማርያም እንድትፀንስ ለማድረግ ታላቅ ተአምር ፈጽሟል። ገብርኤል ሁኔታውን ለማርያም ሲያብራራ “የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስ፣ የአምላክ ልጅ ይባላል” ብሏታል።—ሉቃስ 1:30-35

አምላክ በሰማይ የነበረውን የልጁን ሕይወት በማርያም ማህፀን ውስጥ አስቀመጠው። ከዚያም የአምላክ ልጅ ልክ እንደማንኛውም ሕፃን በማርያም ማህፀን ውስጥ አደገ። ከዘጠኝ ወር ገደማ በኋላ ኢየሱስ ተወለደ። በዚህ መሃል ዮሴፍ ማርያምን ስላገባት ብዙ ሰዎች የኢየሱስ እውነተኛ አባት ዮሴፍ ይመስላቸው ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ዮሴፍ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ሁለት አባቶች አሉት ሊባል ይችላል!

ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ይሖዋን በጣም እንደሚወደው የሚያሳይ አንድ ነገር አደረገ። በዚያ ወቅት የኢየሱስ ቤተሰቦች እንደ ልማዳቸው የፋሲካን በዓል ለማክበር ረጅም ጉዞ በማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ነበር። ከበዓሉ በኋላ በናዝሬት ወደሚገኘው ቤታቸው ሲመለሱ ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ አብሯቸው አለመኖሩን አላስተዋሉም ነበር። ሊረሱት የቻሉት ለምን ይመስልሃል?—

በዚያ ወቅት ዮሴፍና ማርያም ሌሎች ልጆች ወልደው ነበር። (ማቴዎስ 13:55, 56) ከዚህም በተጨማሪ ዘመዶቻቸው ለምሳሌ ያዕቆብና ዮሐንስ ከአባታቸው ከዘብዴዎስና ከእናታቸው ከሰሎሜ ጋር ሆነው አብረዋቸው ሳይጓዙ አልቀሩም፤ ሰሎሜ የማርያም እህት እንደሆነች ይታሰባል። ማርያም፣ ኢየሱስ አብረዋቸው ከሚጓዙት ዘመዶቻቸው ጋር እንደሆነ አስባ ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 27:56፤ ማርቆስ 15:40፤ ዮሐንስ 19:25

ዮሴፍና ማርያም፣ ኢየሱስ አብሯቸው እንዳልሆነ ሲያውቁ ግን በፍጥነት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በዚያም በጭንቀት ተውጠው ልጃቸውን ይፈልጉት ጀመር። በመጨረሻም በሦስተኛው ቀን ቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኙት። ማርያም “ልጄ፣ ምነው እንዲህ አደረግከን? እኔና አባትህ እኮ በጣም ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው። ኢየሱስ ግን “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” በማለት መለሰላቸው።—ሉቃስ 2:45-50

ዮሴፍና ማርያም መጀመሪያ ኢየሱስን ሊፈልጉት የሚገባው በቤተ መቅደሱ ነበር ሊባል የሚችለው ለምን ይመስልሃል?

ኢየሱስ ለእናቱ እንዲህ ዓይነት መልስ መስጠቱ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማሃል?— በአምላክ ቤት ውስጥ ሆኖ ይሖዋን ማምለክ እንደሚወድ ወላጆቹ ያውቁ ነበር። (መዝሙር 122:1) በመሆኑም ኢየሱስ፣ ወላጆቹ መጀመሪያ ሊፈልጉት የሚገባው በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደሆነ ማሰቡ ትክክል አይመስልህም?— ከዚያ በኋላ ማርያም ኢየሱስ ስለተናገረው ነገር ታስብ ነበር።

ኢየሱስ ለዮሴፍና ለማርያም ምን አመለካከት ነበረው?— መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስ አብሯቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ እንደ ወትሮውም ይታዘዛቸው ነበር” ይላል። (ሉቃስ 2:51, 52) ከኢየሱስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?— ትክክል ነህ፣ እኛም ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል።

ይሁንና መታዘዝ ለኢየሱስ ሁልጊዜ በጣም ቀላል ነበር ማለት አይደለም፤ በሰማይ የሚኖረው አባቱ የሰጠውን ትእዛዝ መፈጸም እንኳ ያስጨነቀው ጊዜ ነበር።

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ አምላክ እንዲያደርግ ያዘዘውን ነገር ማስቀረት ይቻል እንደሆነ ይሖዋን ጠይቆ ነበር። (ሉቃስ 22:42) ሆኖም ኢየሱስ ቀላል ባይሆንለትም አምላክን ታዝዟል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ” ይላል። (ዕብራውያን 5:8) እኛም እንደ ኢየሱስ መታዘዝን መማር የምንችል ይመስልሃል?—

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።