በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምኩራቦችኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የሰበኩባቸው ቦታዎች

ምኩራቦችኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የሰበኩባቸው ቦታዎች

 ምኩራቦች​—ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የሰበኩባቸው ቦታዎች

“ከዚያም በምኩራቦቻቸው እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ . . . በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።”—ማቴዎስ 4:23

ኢየሱስ ወደ ምኩራቦች ይሄድ እንደነበር የሚናገሩ ታሪኮችን በወንጌሎች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ እናገኛለን። ኢየሱስ ባደገባት በናዝሬትም ይሁን ማረፊያው በነበረችው በቅፍርናሆም ከተማ በሚሆንበት ወቅት አሊያም በአገልግሎት ባሳለፈው የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በሄደበት በማንኛውም ከተማና መንደር ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክና ለማስተማር ብዙውን ጊዜ የሚመርጠው ስፍራ ምኩራብ ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ በአገልግሎት ስላሳለፈው ጊዜ ሲናገር “አይሁዳውያን ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በቤተ መቅደሱ ሁልጊዜ አስተምር ነበር” ብሏል።—ዮሐንስ 18:20

በተመሳሳይም የኢየሱስ ሐዋርያትና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ በአይሁዳውያን ምኩራቦች ውስጥ ያስተምሩ ነበር። ይሁንና አይሁዳውያን በምኩራቦች ውስጥ ማምለክ የጀመሩት እንዴት ነው? እነዚህ የአምልኮ ስፍራዎች በኢየሱስ ዘመን ምን ይመስሉ ነበር? እስቲ ስለ እነዚህ ቦታዎች በዝርዝር እንመልከት።

በአይሁዳውያን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበራቸው። አይሁዳውያን ወንዶች በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚከበሩት በዓላት ላይ ለመገኘት በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። በሌሎች ጊዜያት ግን በፓለስቲና የሚኖሩትም ሆነ ከዚያ ውጪ ባሉ አገሮች የሚገኙት በርካታ የአይሁዳውያን ማኅበረሰቦች ለአምልኮ የሚጠቀሙት በአካባቢያቸው የሚገኙትን ምኩራቦች ነበር።

ምኩራቦችን መጠቀም የተጀመረው መቼ  ነው? ይህ የሆነው አይሁዳውያን በግዞት ወደ ባቢሎን በተወሰዱበት (607-537 ዓ.ዓ.) ወቅት እንደሆነ አንዳንዶች ያምናሉ፤ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቤተ መቀደስ ወድሞ ነበር። ምኩራቦችን መጠቀም የተጀመረው አይሁዳውያን ከምርኮ በተመለሱበት ጊዜ አካባቢም ሊሆን ይችላል፤ በዚያ ወቅት ካህኑ ዕዝራ ሕዝቡ የአምላክን ሕግ ይበልጥ ለማወቅና ለመረዳት ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸው ነበር።—ዕዝራ 7:10፤ 8:1-8፤ 10:3

“ምኩራብ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል መጀመሪያ ላይ “ስብሰባ” ወይም “ጉባኤ” የሚል ትርጉም ነበረው። ይህ ቃል ሰብዓ ሊቃናት በተባለው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ግሪክኛ ትርጉም ውስጥ የተሠራበት በዚህ መንገድ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ቃሉ ሰዎች ለአምልኮ የሚሰባሰቡበትን ሕንፃ ለማመልከት ይሠራበት ጀመር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ የሄደባቸው ሁሉም ከተሞች ማለት ይቻላል የራሳቸው ምኩራብ ነበራቸው፤ አንዳንድ ከተሞች ከአንድ በላይ ምኩራቦች የነበሯቸው ሲሆን በኢየሩሳሌም ደግሞ ብዙ ምኩራቦች ነበሩ። እነዚህ ሕንፃዎች ምን ይመስሉ ነበር?

ለአምልኮ የሚያገለግሉ መጠነኛ የሆኑ ቤቶች። አይሁዳውያን በአብዛኛው ምኩራቦችን ለመገንባት የሚመርጡት ከፍ ባሉ ስፍራዎች ላይ ሲሆን የምኩራቦቹ መግቢያ (1) ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ እንዲሆን ያደርጉ ነበር። ሆኖም ሁልጊዜ በዚህ መንገድ ምኩራቦችን መገንባት ስለማይቻል እነዚህ መሥፈርቶች የማይሟሉባቸው ጊዜያት የነበሩ ይመስላል።

በዚህ መንገድ የተሠሩት ምኩራቦች አብዛኛውን ጊዜ ቅልብጭ ያሉ ሲሆኑ በውስጣቸው ብዙ ቁሳቁሶች አይኖሩም። በምኩራቦች ውስጥ ጎላ ብለው ከሚታዩት ቁሳቁሶች አንዱ የማኅበረሰቡ ውድ ንብረት እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩት የቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅልሎች የሚቀመጡበት ሳንዱቅ (2) ወይም ሣጥን ነው። ስብሰባ በሚካሄድበት ጊዜ ይህ ሣጥን በተወሰነለት ቦታ ላይ የሚቀመጥ ሲሆን ስብሰባው ሲያበቃ ቀድሞ ወደነበረበት አስተማማኝ የሆነ ክፍል ይመለሳል (3)።

በዚህ ሣጥን አጠገብ ከተሰብሳቢው ትይዩ (4) ወንበሮች የሚገኙ ሲሆን ፊት ለፊት ባሉት በእነዚህ ወንበሮች ላይ የምኩራብ አለቆችና የክብር እንግዶች ይቀመጡ ነበር። (ማቴዎስ 23:5, 6) በአዳራሹ መሃል አካባቢ ከፍ ያለ መድረክ የሚገኝ ሲሆን መድረኩ ላይ ተናጋሪው የሚጠቀምበት አትራኖስና ወንበር ይቀመጣል (5)። ከመድረኩ ፊት ለፊት እንዲሁም በስተግራና በስተቀኝ ተሰብሳቢዎች የሚቀመጡባቸው አግዳሚ ወንበሮች ይደረደራሉ (6)።

ብዙውን ጊዜ ከምኩራቦቹ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን የሚሸፍነው በአካባቢው ያለው ጉባኤ ነበር። ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉም የጉባኤው አባላት በፈቃደኝነት የሚያደርጉት መዋጮ ሕንፃውን ለመንከባከብና ለማደስ ይውል ነበር። ይሁንና በምኩራቦች ውስጥ ስብሰባዎች የሚካሄዱት እንዴት ነበር?

በምኩራብ የሚካሄድ አምልኮ። በምኩራብ የሚካሄደው የአምልኮ ፕሮግራም የውዳሴ መዝሙርን፣ ጸሎትንና ከቅዱሳን መጻሕፍት ማንበብን የሚያካትት ከመሆኑም ሌላ በፕሮግራሙ ላይ ትምህርትና ስብከት ይሰጥ ነበር። ስብሰባው የሚጀመረው ሺማ የሚባለውን የአይሁዶችን የእምነት መግለጫ በመድገም ነው። ቃሉ የተወሰደው በስብሰባው ላይ ከሚደገሙት ጥቅሶች መካከል ከመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ነው፤ ጥቅሱ “እስራኤል ሆይ ስማ [ሺማ]፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” ይላል።—ዘዳግም 6:4

ቀጥሎም ከቶራህ ማለትም ሙሴ ከጻፋቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ የተወሰነ ክፍል ይነበብና ይብራራል። (የሐዋርያት ሥራ 15:21) ከዚያም ከነቢያት መጻሕፍት ላይ የተወሰኑ ክፍሎች (ሃፍቶራህ) ከተነበቡ በኋላ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል እንዲሁም ትምህርቱን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ይገለጻል። አንዳንድ ጊዜ ይህንን ክፍል የሚያቀርቡት እንግዳ የሆኑ ተናጋሪዎች ነበሩ፤ በሉቃስ 4:16-21 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው  ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት እንዳነበበ የሚገልጸው ታሪክ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል።

እርግጥ በዚያ ወቅት ለኢየሱስ የተሰጠው ጥቅልል በዘመናችን እንዳሉት መጽሐፍ ቅዱሶች በምዕራፍና በቁጥር የተከፋፈለ አልነበረም። በመሆኑም ኢየሱስ በግራ እጁ ጥቅልሉን እየተረተረ በቀኝ እጁ ደግሞ እየጠቀለለ የሚፈልገውን ጥቅስ ለማግኘት ሲሞክር በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን። ጥቅሱ ከተነበበ በኋላ ጥቅልሉ እንደነበረው ተመልሶ ይጠቀለላል።

ብዙውን ጊዜ ጥቅሶቹ የሚነበቡት መጀመሪያ በተጻፉበት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን ከዚያም ወደ አረማይክ ቋንቋ ይተረጎሙ ነበር። ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ጉባኤዎች በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ይጠቀሙ ነበር።

በዕለታዊ ሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ሚና ነበራቸው። ምኩራቦች ከአይሁዳውያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር በጣም የተቆራኙ በመሆናቸው ምኩራቦቹም ሆኑ ከእነሱ ጋር ተያይዘው የተሠሩ ወይም አጠገባቸው ያሉ ሌሎች ሕንፃዎች ለተለያዩ ዓላማዎች ያገለግሉ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ሕንፃዎች እንደ ፍርድ ቤት ያገለግላሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ለስብሰባ ይጠቀምባቸዋል፤ አልፎ ተርፎም በሕንፃው ውስጥ በሚገኙ የመመገቢያ ክፍሎች ውስጥ ትላልቅ ስብሰባዎች ይካሄዱ እንዲሁም ምግብ ይቀርብ ነበር። ከምኩራቡ አጠገብ በተሠሩ ሕንፃዎች ውስጥ ለመንገደኞች ማረፊያ ክፍል የሚዘጋጅላቸው ጊዜም ነበር።

በሁሉም ከተሞች ውስጥ ያሉት ምኩራቦች ትምህርት ቤት ነበራቸው ማለት ይቻላል፤ በአብዛኛው እነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት ምኩራቦቹ ባሉበት ሕንፃ ውስጥ ነው። ትናንሽ ልጆች በአንድ ክፍል ውስጥ ታጭቀው አንድ አስተማሪ ሰም በተቀባ ጽላት ላይ የተጻፉ ትላልቅ ፊደላትን በመጠቀም ማንበብ ሲያስተምራቸው በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የጥንቱ የአይሁድ ማኅበረሰብ ማንበብና መጻፍ እንዲችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ተራው ሕዝብም እንኳ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያውቅ ነበር።

ይሁንና ምኩራቦች በዋነኝነት የሚያገለግሉት አምልኮን ቋሚ በሆነ መንገድ ለማካሄድ ነበር። በመሆኑም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የሚያካሂዷቸው ስብሰባዎች በአይሁድ ምኩራቦች ውስጥ ከሚካሄዱት ስብሰባዎች ጋር የሚመሳሰሉ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም። የክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ዓላማም በጸሎትና በውዳሴ መዝሙሮች አማካኝነት እንዲሁም የአምላክን ቃል በማንበብና በማብራራት ለይሖዋ አምልኮ ማቅረብ ነበር። በምኩራቦች ውስጥ የሚካሄዱትና ክርስቲያኖች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች የሚመሳሰሉት በዚህ ብቻ አይደለም። በሁለቱም የአምልኮ ቦታዎች የተለያዩ ወጪዎች የሚሸፈኑት በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነበር፤ የአምላክን ቃል የማንበብና የማብራራት መብት ለቀሳውስት ብቻ የተተወ አልነበረም፤ እንዲሁም ስብሰባዎቹን የሚያደራጁትና የሚመሩት ኃላፊነት ያላቸው የጎለመሱ ወንዶች ነበሩ።

በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ተከታዮቹ የተዉትን ምሳሌ በጥብቅ ለመከተል ይጥራሉ። በመሆኑም በመንግሥት አዳራሾቻቸው ውስጥ የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች በጥንት ዘመን በምኩራቦች ውስጥ ይደረጉ ከነበሩት ስብሰባዎች ጋር የሚያመሳስሏቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። ከሁሉ በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰበሰቡበት ዓላማ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ያሉ እውነትን የሚወዱ ሰዎች ምንጊዜም ከነበራቸው ዓላማ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይህም ‘ወደ አምላክ መቅረብ’ ነው።—ያዕቆብ 4:8

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የጋምላ ምኩራብ ፕላን ላይ ተመሥርቶ በድጋሚ የተገነባ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምኩራብ ውስጥ በነበሩት ትምህርት ቤቶች ከ6 እስከ 13 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወንዶች ልጆች ይማሩ ነበር