በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ንብረት መሆን ጸጋ ነው

የይሖዋ ንብረት መሆን ጸጋ ነው

የይሖዋ ንብረት መሆን ጸጋ ነው

“የይሖዋ ነን።”—ሮም 14:8

1, 2. (ሀ) ምን መብት አግኝተናል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር “ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ዘፀ. 19:5) እስራኤላውያን የእሱ ንብረት መሆናቸው እንዴት ያለ ውድ መብት ነበር! በዛሬው ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም የይሖዋ ንብረት የመሆን ክቡር መብት አላቸው። (1 ጴጥ. 2:9፤ ራእይ 7:9, 14, 15) ይህ በእርግጥ ዘላለማዊ ጥቅም የሚያስገኝልን መብት ነው።

2 የይሖዋ ንብረት መሆን መብት ከመሆኑም ባሻገር ኃላፊነትም ያስከትላል። አንዳንዶች እንደሚከተለው በማለት ይጠይቁ ይሆናል፦ ‘ይሖዋ የሚጠብቅብኝን መፈጸም እችል ይሆን? ኃጢአት ብሠራ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አጣ ይሆን? የይሖዋ ንብረት መሆን ነፃነት ቢያሳጣኝስ?’ ለእነዚህ አሳሳቢ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን የተገባ ነው። በመጀመሪያ ግን ‘የይሖዋ ንብረት መሆናችን ምን ጥቅሞችን ያስገኝልናል?’ የሚለውን ጥያቄ እንመርምር።

የይሖዋ ንብረት መሆን ደስታ ያስገኛል

3. ረዓብ አምላክን ለማገልገል ያደረገችው ምርጫ ጥቅም ያስገኘላት እንዴት ነው?

3 የይሖዋ ንብረት የሆኑ ሰዎች ይህ መብታቸው ጥቅም ያስገኝላቸዋል? እስቲ በጥንቷ ኢያሪኮ ትኖር የነበረችውን ጋለሞታይቱን ረዓብን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ረዓብ ርኩስ የነበሩትን የከነዓናውያንን አማልክት ከልጅነቷ ጀምሮ ታመልክ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ስላቀዳጃቸው ድሎች ስትሰማ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ተገነዘበች። ስለሆነም አምላክ የመረጠውን ሕዝብ ለማዳን ስትል ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል እርምጃ ወሰደች፤ እንዲህ በማድረግም የወደፊት ሕልውናዋን ለእነሱ አደራ ሰጠች። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጋለሞታይቱ ረዓብ መልእክተኞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ ካስተናገደቻቸውና በሌላ መንገድ እንዲሄዱ ካደረገች በኋላ በሥራ ጻድቅ ተብላ አልተጠራችም?” (ያዕ. 2:25) ከአምላክ ሕግ ፍቅርንና ፍትሕን ከተማረው ንጹሕ ሕዝብ ጋር መቆጠር መቻሏ ያስገኘላትን ጥቅሞች አስብ። የቀድሞ አኗኗራን እርግፍ አድርጋ መተው በመቻሏ ምን ያህል ተደስታ ይሆን! ከዚያ በኋላ አንድ እስራኤላዊ ያገባች ሲሆን ቦዔዝ የተባለ ወንድ ልጅ ወልዳለች፤ ይህንን ልጅ ግሩም ባሕርያት ያሉት የአምላክ ሰው እንዲሆን አድርጋ አሳድጋዋለች።—ኢያሱ 6:25፤ ሩት 2:4-12፤ ማቴ. 1:5, 6

4. ሩት ይሖዋን ለማገልገል በመምረጧ የተጠቀመችው እንዴት ነው?

4 ሞዓባዊቷ ሩትም ይሖዋን ለማገልገል መርጣለች። ሩት በልጅነቷ ካሞሽንና ሌሎች የሞዓብ አማልክትን ሳታመልክ አትቀርም፤ ከጊዜ በኋላ ግን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ያወቀች ከመሆኑም ሌላ ወደ አገሯ ተሰዶ የመጣ አንድ እስራኤላዊ አገባች። (ሩት 1:1-6ን አንብብ።) ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሩትና የባሏ ወንድም ሚስት የሆነችው ዖርፋ ከአማታቸው ከኑኃሚን ጋር ወደ ቤተልሔም ጉዞ ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ ኑኃሚን፣ ሁለቱን ወጣት ሴቶች ወደ ወላጆቻቸው ቤት እንዲመለሱ ነገረቻቸው። ምክንያቱም ለሩትና ለዖርፋ በእስራኤል መኖር ከባድ ይሆንባቸው ነበር። ዖርፋ “ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ [ተመለሰች]”፤ ሩት ግን እንዲህ አላደረገችም። ሩት እምነቷን በሥራ ያሳየች ከመሆኑም በላይ የማን ንብረት መሆን እንዳለባት አውቃለች። በመሆኑም ኑኃሚንን እንዲህ ብላታለች፦ “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል።” (ሩት 1:15, 16) ሩት ይሖዋን ለማገልገል በመምረጧ አምላክ በሰጠው ሕግ መሠረት መበለቶች፣ ድሆችና መሬት የሌላቸው ሰዎች የነበራቸውን ልዩ መብት በማግኘት ተጠቅማለች። በይሖዋ ክንፍ ሥር በመጠለሏ ደስታ፣ ጥበቃና ደኅንነት ማግኘት ችላለች።

5. ይሖዋን በታማኝነት ከሚያገለግሉ ሰዎች የተረዳኸው ነገር ምንድን ነው?

5 ራሳቸውን ለይሖዋ ከወሰኑ በኋላ እሱን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ አንዳንድ ግለሰቦችን ታውቅ ይሆናል። እነዚህ ወንድሞች ይሖዋን በማገልገላቸው ምን ጥቅም እንዳገኙ ጠይቃቸው። ከችግር ነፃ የሆነ ሰው ባይኖርም ማስረጃዎቹ በአብዛኛው ‘ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው’ በማለት መዝሙራዊው የተናገራቸውን ቃላት የሚደግፉ ናቸው።—መዝ. 144:15 NW

ይሖዋ የሚጠብቅብን ነገር ምክንያታዊ ነው

6. ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር ማድረግ አንችልም ብለን መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው?

6 ‘ይሖዋ ከእኔ የሚጠብቀውን ነገር ማድረግ እችል ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። የአምላክ አገልጋይ ስለ መሆን፣ ሕጉን ጠብቆ ስለ መኖርና ስሙን ለሌሎች ሰዎች ስለ መናገር ስታስብ እነዚህን ነገሮች ማድረግ በጣም ከባድ እንደሚሆንብህ ይሰማህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ እስራኤላውያንንና የግብፁን ንጉሥ እንዲያነጋግር በተላከ ጊዜ ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ፣ ከሙሴ የጠበቀው ምክንያታዊነት የጎደለው ነገር አልነበረም። ይሖዋ ‘ምን ማድረግ እንዳለበት አስተምሮት’ ነበር። (ዘፀአት 3:11፤ 4:1, 10, 13-15ን አንብብ።) ሙሴ የተደረገለትን እርዳታ በመቀበሉ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም የሚገኘውን ደስታ አጣጥሟል። ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ረገድም ምክንያታዊ ነው። ፍጹም እንዳልሆንን ስለሚያውቅ ሊረዳን ይፈልጋል። (መዝ. 103:14) የኢየሱስ ተከታይ በመሆን አምላክን ማገልገል ከባድ ነገር ሳይሆን እረፍት የሚሰጥ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ የሕይወት ጎዳና ሌሎችን የሚጠቅም ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል። ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ” ብሏል።—ማቴ. 11:28, 29

7. ይሖዋ ከአንተ የሚጠብቀውን ነገር ለመፈጸም ስትጥር የእሱ እርዳታ እንደማይለይህ መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ ብርታት ለማግኘት በእሱ እስከተማመንን ድረስ የሚያስፈልገንን ማበረታቻ ምንጊዜም ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤርምያስ በተፈጥሮው ደፋር አልነበረም። ይሖዋ ነቢይ አድርጎ ሲሾመው ኤርምያስ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” ብሏል። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ “ከእንግዲህ የእርሱን ስም አላነሣም” በማለት ተናግሯል። (ኤር. 1:6፤ 20:9) ይሁንና ኤርምያስ ይሖዋ በሰጠው ማበረታቻ ታግዞ ብዙዎች ሊሰሙት የማይፈልጉትን መልእክት ለ40 ዓመታት መስበክ ችሏል። ይሖዋ “ልታደግህና፣ ላድንህም፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ አበረታቶታል።—ኤር. 1:8, 19፤ 15:20

8. በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ ሙሴንና ኤርምያስን እንዳበረታታቸው ሁሉ እኛም በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት ክርስቲያኖች የሚጠበቀውን ነገር ለማድረግ ስንጥር ይረዳናል። ዋናው ነገር በአምላክ መታመን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው በቃሉና በጉባኤ አማካኝነት የሚሰጠንን እርዳታ በመቀበል ነው። ይሖዋ አካሄዳችንን እንዲመራልን የምንፈቅድ ከሆነ ለእሱ ታማኝ ከመሆን የሚያግደን ምንም ነገር አይኖርም።

ይሖዋ ለሕዝቦቹ በግለሰብ ደረጃ ያስባል

9, 10. በመዝሙር 91 ላይ ቃል የተገባልን ምን ዓይነት ጥበቃ እንደምናገኝ ነው?

9 አንዳንዶች ራሳቸውን ለይሖዋ ስለ መወሰን ሲያስቡ ‘ኃጢአት ሠርቼ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ባጣስ?’ የሚለው ሐሳብ ያስጨንቃቸዋል። ደስ የሚለው ነገር ይሖዋ ከእሱ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ጠብቀን ማቆየት እንድንችል የሚያስፈልገንን ጥበቃ ሁሉ ያደርግልናል። ይህ ሁኔታ በ91ኛው መዝሙር ላይ እንዴት እንደተገለጸ እንመልከት።

10 መዝሙር 91 እንዲህ በማለት ይጀምራል፦ “በልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ የሚኖር ሰው ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ጥላ ሥር ለራሱ ማረፊያ ያገኛል። ይሖዋን ‘አንተ መጠጊያዬና ምሽጌ፣ የምታመንብህም አምላኬ ነህ’ እለዋለሁ። እሱ ራሱ ከወፍ አዳኙ ወጥመድ . . . ያድንሃል።” (መዝ. 91:1-3 NW) አምላክ የሚወዱትንና በእሱ የሚታመኑትን ለመጠበቅ ቃል እንደገባ ልብ በል። (መዝሙር 91:9, 14ን አንብብ።) ታዲያ ይሖዋ የሚያደርገው ጥበቃ ምን ዓይነት ነው? ይሖዋ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ለሚመጣበት የዘር ሐረግ ጥበቃ ለማድረግ ሲል አንዳንድ ጊዜ ለጥንት አገልጋዮቹ አካላዊ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። ይሁን እንጂ ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት ለማጉደል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት በዲያብሎስ ግፊት የታሰሩ፣ ሥቃይ የደረሰባቸው እንዲሁም የተገደሉ በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች አሉ። (ዕብ. 11:34-39) እነዚህ ሰዎች ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ድፍረት ያገኙት ይሖዋ ንጹሕ አቋማቸውን እንዲያጎድፉ ሊያደርጋቸው ከሚችል መንፈሳዊ አደጋ ስለጠበቃቸው ነው። በመሆኑም መዝሙር 91⁠ን መንፈሳዊ ጥበቃ እንደምናገኝ የተገባልን ቃል እንደሆነ አድርገን መረዳት እንችላለን።

11. ‘የልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ’ ምንድን ነው? በዚያ ቦታ አምላክ ጥበቃ የሚያደርገው ለእነማን ነው?

11 በዚህ መዝሙር ላይ የተጠቀሰው ‘የልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ’ መንፈሳዊ ጥበቃ የምናገኝበት ምሳሌያዊ ቦታ ነው። የአምላክ እንግዶች በመሆን ከእሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በዚህ ቦታ እስካሉ ድረስ ጥበቃ ስለሚደረግላቸው ምንም ነገር ወይም ማንኛውም አካል ለአምላክ ባላቸው እምነትና ፍቅር ላይ አደጋ አያደርስባቸውም። (መዝ. 15:1, 2፤ 121:5) ይህ ቦታ ሚስጥራዊ የተባለው የማያምኑ ሰዎች ሊረዱት ስለማይችሉ ነው። ‘አንተ የምተማመንብህ አምላኬ ነህ’ ለሚሉ ሁሉ ይሖዋ በዚህ ቦታ ላይ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ጥበቃ ከምናገኝበት ከዚህ ቦታ ሳንወጣ እስከኖርን ድረስ ‘ወፍ አዳኝ’ በሆነው በሰይጣን ወጥመድ ተይዘን የይሖዋን ሞገስ እናጣለን ብለን ከልክ በላይ መጨነቅ አይኖርብንም።

12. ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

12 ከአምላክ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? መዝሙራዊ የተለያዩ አደገኛ ሁኔታዎችን የጠቀሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ‘በጨለማ የሚያደባ ቸነፈርና የቀትር ረፍራፊ’ ይገኙበታል። (መዝ. 91:5, 6) “ወፍ አዳኙ” በርካታ ሰዎችን በራስ ሐሳብ በመመራት ምኞት አጥምዷቸዋል። (2 ቆሮ. 11:3) ሌሎችን በስግብግብነት፣ በኩራትና በፍቅረ ንዋይ አጥምዷቸዋል። አንዳንዶችን ደግሞ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ዝግመተ ለውጥና የሐሰት ሃይማኖት በመሳሰሉት ፍልስፍናዎች ያታልላቸዋል። (ቆላ. 2:8) እንዲሁም በርካታ ሰዎች ልቅ የሆነ የፆታ ግንኙነት ወጥመድ ሆኖባቸዋል። እንዲህ ያሉት አጥፊ መንፈሳዊ ቸነፈሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዲያጡ ምክንያት ሆነዋል።—መዝሙር 91:7-10ን አንብብ፤ ማቴ. 24:12

ለአምላክ ያለህን ፍቅር መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

13. ይሖዋ መንፈሳዊ ደኅንነታችንን አደጋ ላይ ከሚጥል ነገር የሚጠብቀን እንዴት ነው?

13 ይሖዋ ሕዝቡን ከእነዚህ መንፈሳዊ አደጋዎች የሚጠብቀው እንዴት ነው? መዝሙር 91 በመቀጠል “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል” ይላል። (መዝ. 91:11) በሰማይ የሚኖሩ መላእክት ምሥራቹን መስበክ እንድንችል ይመሩናል፤ እንዲሁም ይጠብቁናል። (ራእይ 14:6) ከዚህ በተጨማሪም የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት በሚሰጡበት ወቅት ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥብቅ በመከተል በሐሰት ትምህርቶች እንዳንታለል ጥበቃ ያደርጉልናል። እነዚህ ሽማግሌዎች የዓለም ዝንባሌዎችን ለመቋቋም ትግል በማድረግ ላይ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ እርዳታ ያደርጉላቸዋል። (ቲቶ 1:9፤ 1 ጴጥ. 5:2) በተጨማሪም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ፣ የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም እንዲሁም ሀብትንና ዝናን እንድናሳድድ ከሚቀርቡ ማባበያዎች አልፎ ተርፎም ከሌሎች በርካታ ጎጂ ምኞቶችና ግፊቶች እኛን ለመጠበቅ መንፈሳዊ ምግብ ያዘጋጅልናል። (ማቴ. 24:45) አንተስ እንዲህ ያሉ አደገኛ ሁኔታዎችን እንድትቋቋም የረዳህ ምንድን ነው?

14. አምላክ እኛን ለመጠበቅ ባደረጋቸው ዝግጅቶች መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

14 ይሁንና ጥበቃ ከምናገኝበት ከአምላክ “ሚስጥራዊ ቦታ” ሳንወጣ ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል? ራሳችንን ከአደጋ፣ ከወንጀል፣ ከበሽታና ከመሳሰሉት ነገሮች ለመጠበቅ ምንጊዜም ጥረት እንደምናደርገው ሁሉ ራሳችንን ከመንፈሳዊ አደጋዎች ለመጠበቅም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በመሆኑም ይሖዋ በጽሑፎቻችን እንዲሁም በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት በሚሰጠን መመሪያ ዘወትር መጠቀም ይኖርብናል። እንዲሁም ከሽማግሌዎች ምክር ማግኘት ያስፈልገናል። ከዚህም በተጨማሪ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያላቸው የተለያየ ባሕርይ ጥቅም አስገኝቶልናል። በእርግጥም ከጉባኤው ጋር መቀራረባችን ጥበበኞች እንድንሆን ይረዳናል።—ምሳሌ 13:20፤ 1 ጴጥሮስ 4:10ን አንብብ።

15. ይሖዋ የእሱን ሞገስ ከሚያሳጣህ ከማንኛውም ነገር እንደሚጠብቅህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ የእሱን ሞገስ እንድናጣ ከሚያደርገን ከማንኛውም ነገር ጥበቃ የሚያደርግልን መሆኑን የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም። (ሮም 8:38, 39) ይሖዋ ጉባኤውን ኃያል የሆኑ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጠላቶች ሊያደርሱበት ከሚችሉት ጥቃት ጥበቃ አድርጎለታል፤ ብዙውን ጊዜ የእነዚህ ጠላቶች ዋነኛ ግብ እኛን መግደል ሳይሆን ቅዱስ ከሆነው አምላካችን ማቆራረጥ ነው። ይሖዋ “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል” በማለት የገባው ቃል እውነት መሆኑ ታይቷል።—ኢሳ. 54:17

ነፃነት የሚሰጠን ማን ነው?

16. ዓለም ነፃነት ሊሰጠን አይችልም የምንለው ለምንድን ነው?

16 የይሖዋ ንብረት መሆን ነፃነት ያሳጣን ይሆን? በፍጹም፤ እንዲያውም ነፃነት የሚያሳጣን የዓለም ክፍል መሆናችን ነው። ይህ ዓለም ከይሖዋ የራቀ ሲሆን ገዥው ሰዎችን በባርነት ቀንበር የያዘውና ጨካኝ አምላክ የሆነው ሰይጣን ነው። (ዮሐ. 14:30) ለምሳሌ ያህል፣ የሰይጣን ዓለም ሰዎችን ነፃነት ለማሳጣት ኢኮኖሚው የሚያሳድረውን ጫና ይጠቀማል። (ከራእይ 13:16, 17 ጋር አወዳድር።) ኃጢአትም ቢሆን ሰዎችን ባሪያ ለማድረግ የሚያስችል የማታለል ኃይል አለው። (ዮሐ. 8:34፤ ዕብ. 3:13) አማኝ ያልሆኑ ሰዎች፣ ከይሖዋ ትምህርቶች ጋር የሚቃረን የአኗኗር ዘይቤዎችን መከተል ነፃነት እንደሚያስገኝ ይናገሩ ይሆናል፤ ይሁንና እነሱን የሚሰማ ግለሰብ ብዙም ሳይቆይ ኃጢአት የሞላበትና ወራዳ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ባሪያ ሲሆን ይታያል።—ሮም 1:24-32

17. ይሖዋ ምን ዓይነት ነፃነት ይሰጠናል?

17 በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ራሳችንን ለእሱ አሳልፈን ከሰጠን ጉዳት ሊያስከትልብን ከሚችል ከማንኛውም ነገር ነፃ ያወጣናል። በአንዳንድ መንገዶች ያለንበት ሁኔታ ከአደገኛ በሽታ ለመገላገል ሲል ሕይወቱን ልምድ ላለው የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ከሰጠ ታካሚ ጋር ይመሳሰላል። ሁላችንም በወረስነው ኃጢአት ምክንያት ሕይወታችን አደጋ ተጋርጦበታል። ከኃጢአት ውጤት በመገላገል የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሊኖረን የሚችለው በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ራሳችንን ለይሖዋ ከሰጠን ብቻ ነው። (ዮሐ. 3:36) የሕክምና ባለሙያውን ዝና ስንሰማ በእሱ ላይ ያለን እምነት እንደሚጨምር ሁሉ ስለ ይሖዋ እያወቅን በሄድን መጠን በእሱ ይበልጥ እንታመናለን። በመሆኑም የይሖዋ ንብረት ለመሆን ስናስብ የሚሰማንን ማንኛውንም ፍርሃት ለማሸነፍ የሚረዳንን ፍቅር ማዳበር እንድንችል የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናታችንን እንቀጥል!—1 ዮሐ. 4:18

18. የይሖዋ ንብረት መሆን ምን ያስገኛል?

18 ይሖዋ ለሁሉም ሰው የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል። የአምላክ ቃል “አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ [ነው]” ይላል። (ዘዳ. 30:19, 20) ይሖዋ በራሳችን ተነሳስተን እሱን ለማገልገል በመምረጥ ለእሱ ያለንን ፍቅር እንድናሳይ ይፈልጋል። የምንወደው አምላካችን ንብረት መሆናችን ምንጊዜም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል እንጂ ነፃነት አያሳጣንም።

19. የይሖዋ ንብረት መሆን የጸጋ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

19 ኃጢአተኞች እንደመሆናችን መጠን ፍጹም የሆነው አምላክ ንብረት መሆን አይገባንም ነበር። የአምላክ ንብረት ልንሆን የቻልነው በጸጋው ነው። (2 ጢሞ. 1:9) በመሆኑም ጳውሎስ “ብንኖር የምንኖረው ለይሖዋ ነው፤ ብንሞትም የምንሞተው ለይሖዋ ነው። ስለዚህ ብንኖርም ሆነ ብንሞት የይሖዋ ነን” በማለት ጽፏል። (ሮም 14:8) የይሖዋ ንብረት ለመሆን በመምረጣችን በፍጹም አንጸጸትም።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የይሖዋ ንብረት መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

• ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር ማድረግ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ንብረት በመሆናቸው ምን ጥቅም እንዳገኙ ሌሎችን ጠይቅ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ጥበቃ የሚያደርገው በየትኞቹ መንገዶች ነው?