በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን አደንንና ዓሣ ማጥመድን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል?

መጽሐፍ ቅዱስ አደንንም ሆነ ዓሣ ማጥመድን አያወግዝም። (ዘዳግም 14:4, 5, 9, 20፤ ማቴዎስ 17:27፤ ዮሐንስ 21:6) ያም ሆኖ እንስሳትን የሚያድኑ ወይም ዓሣ የሚያጠምዱ ክርስቲያኖች በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል።

አምላክ ለኖኅና ለዘሮቹ እንስሳትን አርደው እንዲበሉ ፈቅዶላቸዋል፤ እርግጥ ነው፣ እንስሳውን ከመብላታቸው በፊት ደሙን ማፍሰስ ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 9:3, 4) ይህ መመሪያ የእንስሳት ሕይወት ምንጭ አምላክ በመሆኑ ለእንስሳቱ ሕይወት አክብሮት ሊኖረን እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ያሳያል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ችሎታቸውን ለማሳየት ወይም ለመዝናኛ ብለው ለሕይወት አክብሮት እንደሌላቸው በሚያሳይ መንገድ እንስሳትን በጭካኔ አይገድሉም።—ምሳሌ 12:10

ከዚህም በተጨማሪ ስለ ጉዳዩ ያለንን ዝንባሌ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። ዓሣ አጥማጆች የነበሩት ሐዋርያት ብዙ ዓሣ መያዛቸው ሳያስደስታቸው አልቀረም። ያም ሆኖ ዓሣ በማጥመድም ሆነ በአደን ረገድ ስለነበራቸው ችሎታ በጉራ ይናገሩ ወይም ከሌሎች ጋር ለመወዳደርና ወንድነታቸውን ለማሳየት ብለው በእነዚህ ተግባራት ይካፈሉ እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም፤ አሊያም ደግሞ እንስሳትን ማሳደዱ፣ መታገሉ ወይም መግደሉ ስለሚያስደስታቸው ዓሣ ያጠምዱ ወይም እንስሳትን ያድኑ እንደነበር አልተገለጸም።—መዝሙር 11:5፤ ገላትያ 5:26 NW

በመሆኑም ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል:- ‘ይሖዋ ለሕይወት ያለውን አመለካከት በማክበር ረገድ ምሳሌ እሆናለሁ? አስተሳሰቤም ሆነ ንግግሬ በአደን ወይም ዓሣ በማጥመድ ላይ ያተኮረ ነው? አኗኗሬ እንስሳትን ማደንና መግደል ወይም ዓሣ ማጥመድ እንደሚያስደስተኝ የሚያሳይ ነው ወይስ የአምላክ አገልጋይ መሆኔን ይጠቁማል? አደን ወይም ዓሣ ማጥመድ ከማያምኑ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንድመሠርት ወይም ቤተሰቤን ችላ እንድል ያደርገኛል?’—ሉቃስ 6:45

የዕለት ምግባቸውን ለማግኘት ሲሉ እንስሳትን የሚያድኑ ወይም ዓሣ የሚያጠምዱ ክርስቲያኖች፣ እነዚህን ተግባራት በሚያከናውኑበት ወቅት መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ ለማለት በቂ ምክንያት እንዳላቸው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ማንኛውንም ነገር ከአምላክ መንግሥት ጋር ከተያያዙ እንቅስቃሴዎች ባለማስቀደም በአምላክ ላይ እምነት እንዳለንና በእሱ እንደምንታመን እናሳያለን። (ማቴዎስ 6:33) ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች አደንና ዓሣ ማጥመድን በተመለከተ የወጡ “የቄሣር” ሕጎችን በሙሉ ባለ ሥልጣናት ቢያስገድዷቸውም ባያስገድዷቸውም ይታዘዛሉ።—ማቴዎስ 22:21፤ ሮሜ 13:1

አንዳንዶች ከአደንና ዓሣ ከማጥመድ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር አስተሳሰባቸውን ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ማስማማት ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ኤፌሶን 4:22-24) በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች በሕሊናቸው ላይ ተመሥርተው የሚያደርጉትን ውሳኔ ልናከብርላቸው ይገባል። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ተገቢ ምክር ሰጥቷል:- “እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቍርጥ ሐሳብ አድርግ።” (ሮሜ 14:13) እንዲህ ያለ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርና አክብሮት ማሳየት በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ከማድረጉም በላይ የሕይወት ሁሉ ምንጭ የሆነውን ፈጣሪያችንን ያስደስተዋል።—1 ቆሮንቶስ 8:13 a

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጠበቂያ ግንብ 10-111 (ግንቦት 15, 1990 እንግሊዝኛ) “የአንባቢያን ጥያቄዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።