በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስ ነበረው?

ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስ ነበረው?

ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስ ነበረው?

የለም፣ ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረውም። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ በኖረበት ዘመን እኛ ዛሬ ያለን ዓይነት ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረም። ይሁን እንጂ፣ ምኩራቦች የተለያዩ የቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅልሎች የነበሯቸው ሲሆን እንደምናውቀው እነዚህ ጽሑፎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነዋል። ኢየሱስ ናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ከኢሳይያስ ጥቅልል ላይ አንብቦ ነበር። (ሉቃስ 4:16, 17) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጲስድያ ውስጥ በነበረችው በአንጾኪያ ‘የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ሲነበቡ’ ሰምቷል። (የሐዋርያት ሥራ 13:14, 15) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብም የሙሴ ሕግ ‘በየሰንበቱ በምኵራብ ይነበብ’ እንደነበር ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 15:21

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ላይ የነበሩ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅልሎች ነበሯቸው? የንግሥት ህንደኬ ባለሟል የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ላይ ከደቀ መዝሙሩ ከፊልጶስ ጋር በተገናኘበት ወቅት “በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ” ስለነበር የራሱ ቅጂ ሊኖረው እንደሚችል ግልጽ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 8:26-30) ሐዋርያው ጳውሎስ “ጥቅልል መጻሕፍቱን በተለይም የብራና መጻሕፍቱን” እንዲያመጣለት ጢሞቴዎስን ጠይቆት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:13) ምንም እንኳ ጳውሎስ የትኞቹን ጥቅልሎች እንደፈለገ ባይጠቅስም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ሊሆኑ ይችላሉ።

የሴማዊ ቋንቋዎች ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት አለን ሚለርድ እንደተናገሩት ምናልባት ከጥንት አይሁዳውያን መካከል የቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅልሎች በግል ሊኖራቸው የሚችለው “በፓለስቲና ምድር የሚኖሩ ታዋቂ ሰዎች፣ ተምረዋል ተብለው የሚታሰቡ ሁሉ፣ አንዳንድ ፈሪሳውያንና እንደ ኒቆዲሞስ ያሉ መምህራን” ናቸው። ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ዋጋው ውድ መሆኑ ነበር። ሚለርድ “አንድ የኢሳይያስ መጽሐፍ ቅጂ ዋጋው ከስድስት እስከ አሥር ዲናር” ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል። ሙሉው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “ከ15 እስከ 20 ጥቅልሎችን ይይዝ ነበር” ብለዋል። በሌላ አባባል የእነዚህ ጥቅልሎች ዋጋ የአንድን ሰው የዓመት ገቢ ግማሹን ያክላል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎች የግል ቅጂ እንደነበሯቸው አይናገርም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጥቅሶችን አስታውሶ ይናገር ስለነበር የጠለቀ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንደነበረው ምንም ጥያቄ የለውም። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10፤ 19:4, 5) በአጠቃላይ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደልብ ሊገኝ ይችላል፤ ታዲያ ይህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ እንድናውቅ ሊያነሳሳን አይገባም?