በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች አንድ እየሆኑ ነው—እንዴት?

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች አንድ እየሆኑ ነው—እንዴት?

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች አንድ እየሆኑ ነው—እንዴት?

“አንድነት” ሲባል ምን ማለት ነው? አንዳንዶች ግጭት ወይም ጠብ አለመኖሩ አንድነት እንዳለ የሚጠቁም እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ብሔራት የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙና ለሰላም በቀረቡት ሐሳቦች ከተስማሙ አንድነት አላቸው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ሐቁ ይህ ነው? እንደዚያ ማለት አይቻልም።

ለአብነት ያህል፣ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ብሔራት በሺዎች የሚቆጠሩ የሰላም ስምምነቶችን ቢፈራረሙም እነዚህ ውሎች ፈርሰዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ የዓለም መሪዎች ከሰላም ወይም ከአንድነት ይልቅ የሚያሳስባቸው የበላይነታቸውን ማስጠበቅ ስለሆነ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ብሔራት ወታደራዊ ኃይላቸው ከሌሎች ቢያንስ ምን ሊከተል እንደሚችል በማሰብ ይፈራሉ።

ስለዚህ ሁለት ብሔራት እርስ በርስ አለመዋጋታቸው ብቻ በመካከላቸው ሰላምና አንድነት እንዳለ አያመለክትም። አንዱ በሌላው ላይ ሽጉጥ ደግነው የቆሙ ሁለት ሰዎች፣ የያዙትን መሣሪያ ቃታ ስላልሳቡት ብቻ በመካከላቸው ሰላም አለ ማለት ይቻላል? እንዲህ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው! በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ብሔራት የሚገኙበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እየተባባሰ መሄዱ መንግሥታት አንድ ቀን የጦር መሣሪያቸውን ይጠቀሙበት ይሆናል የሚል ሥጋት እንዲፈጠር አድርጓል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ጥፋት እንዳይደርስ ለመከላከል ምን እየተደረገ ነው?

የኑክሌር የጦር መሣሪያ ሥጋት—የአንድነት ጠር

ብዙዎች የኑክሌር መሣሪያን ዝውውር የሚያግደው ስምምነት (ኑክሌር ነን ፕሮሊፈሬሽን ትሪቲ) ይህን ችግር እንደሚያስወግደው ተስፋ ያደርጋሉ። በ1968 የፀደቀውና በሥራ ላይ የዋለው ይህ ስምምነት የኑክሌር መሣሪያ የሌላቸው አገራት ይህን መሣሪያ እንዳይሠሩ እንዲሁም መሣሪያው ያላቸው አገራት ደግሞ እንዳያዘዋውሩ የሚያግድ ነው። ይህ ስምምነት በአሁኑ ጊዜ ከ180 በሚበልጡ መንግሥታት ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ዓላማውም ብሔራት ያላቸውን የጦር መሣሪያዎች በተቻለ መጠን ለማጥፋት ነው።

እነዚህ ብሔራት የወሰዱት እርምጃ በጣም ጥሩ ቢመስልም አንዳንድ ተቺዎች ይህ ስምምነት የኑክሌር የጦር መሣሪያ የሌላቸው አገራት ይህን መሣሪያ እንዳይሠሩ ለማገድ የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ይሰማቸዋል። በመሆኑም ስምምነቱን ከፈረሙት አገራት አንዳንዶች ሐሳባቸውን ይቀይሩ ይሆናል የሚል ፍራቻ አለ። በእርግጥም፣ አንዳንድ ብሔራት ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል እንደሚያስችላቸው የሚያስቡትን የጦር መሣሪያ እንዳይሠሩ መከልከላቸው ፍትሕ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።

ነገሩን የሚያወሳስበውና ምናልባትም አደጋ የመፈጠሩን አጋጣሚ ይበልጥ የሚያባብሰው ደግሞ የትኛውም መንግሥት የኑክሌር ኃይል እንዳያመነጭ አለመከልከሉ ነው። ይህም የኑክሌር ኃይልን ለልማት እንደሚጠቀሙ የሚናገሩ ብሔራት በድብቅ የኑክሌር የጦር መሣሪያ እያመረቱ ይሆናል የሚል ሥጋት እንዲፈጠር አድርጓል።

በአሁኑ ጊዜ የኑክሌር የጦር መሣሪያ ያላቸው አገራትም እንኳ ስምምነቱን አያከብሩ ይሆናል። አንዳንድ ተቺዎች ‘የኑክሌር የጦር መሣሪያ ከፍተኛ ክምችት ያላቸው አገራት መሣሪያቸውን ያስወግዳሉ አሊያም ይቀንሳሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው’ በማለት ይናገራሉ። አንድ ምንጭ እንደገለጸው ብሔራት የጦር መሣሪያ ክምችታቸውን እንዲያስወግዱ ወይም እንዲቀንሱ ለማድረግ “በአሁኑ ጊዜ እርስ በርስ በሚጋጩ አገራት መካከል ጠንካራ ወዳጅነትና መተማመን ስለሚያስፈልግ ይህ ይሆናል ብሎ [ማመን ያስቸግራል]።”

የሰው ልጆች አንድነት እንዲኖር ለማድረግ ምንም ያህል በቅንነት ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም። ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን አያስደንቃቸውም፤ ምክንያቱም የአምላክ ቃል “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” ይላል። (ኤርምያስ 10:23) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 16:25) ሰብዓዊ መንግሥታት አንድነት ለማስገኘት የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም ውጤት አያመጣም። ያም ሆኖ ተስፋ የለንም ማለት አይደለም።

የእውነተኛ አንድነት ምንጭ

ዓለማችን አንድ እንደምትሆን አምላክ ተስፋ እንደሰጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፤ ሆኖም ይህ አንድነት በሰው ልጆች ጥረት የሚገኝ አይደለም። በዓለም ዙሪያ የሰው ልጆች በሰላም እንዲኖሩ ዓላማ ያለው ፈጣሪ የሰው ልጅ ሊያከናውነው ያልቻለውን ነገር እሱ ይፈጽመዋል። አንዳንዶች ይህ እንደሚፈጸም ማመን ይከብዳቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ የሰው ልጆች በሰላምና በስምምነት እንዲኖሩ ነበር። a አምላክ የሰው ዘሮች በአንድነት እንዲኖሩ ያለው ዓላማ አሁንም እንዳልተለወጠ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ጥቅሶች ያረጋግጣሉ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት:-

“የእግዚአብሔርን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቈርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።”መዝሙር 46:8, 9 የ1954 ትርጉም

“በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”ኢሳይያስ 11:9

“ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ውርደት ከምድር ሁሉ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።”ኢሳይያስ 25:8

“ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።”2 ጴጥሮስ 3:13

• “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”ራእይ 21:4

እነዚህ ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ለሰው ዘሮች አንድነት ለማምጣት ኃይልም ሆነ ችሎታ ስላለው ነው። (ሉቃስ 18:27) ይህንን ለማድረግ ፍላጎትም አለው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ “በጎ [ሐሳብ] . . . በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው” ይላል።—ኤፌሶን 1:8-10

አምላክ ‘ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ምድር’ እንደሚያመጣ የሰጠው ተስፋ እንዲያው የሕልም እንጀራ አይደለም። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይሖዋ አምላክ ቃል የገባውን ነገር በተመለከተ “በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል” ብሏል።—ኢሳይያስ 55:11

በአምላክ ቃል አንድ መሆን

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ብዙውን ጊዜ ሃይማኖት የሰው ዘሮች አንድነት እንዲኖራቸው ሳይሆን እንዲከፋፈሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ደግሞ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፤ ፈጣሪ እንዳለ የምናምን ከሆነ አምላኪዎቹ እርስ በርስ ሰላምና አንድነት ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ አይሆንም? አዎን፣ እንዲህ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው!

ሃይማኖት በሰው ልጆች መካከል የሚፈጥረው መከፋፈል፣ የይሖዋ አምላክንም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን አመለካከት አያንጸባርቅም። እንዲያውም ሃይማኖቶች አንድነትን ለማምጣት የአምላክን ዓላማ ከማራመድ ይልቅ የሰውን እቅድ ማስፋፋታቸው የሚያስወግዛቸው ነው። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “ግብዞች” ብሎ የጠራቸው ከመሆኑም በላይ እንዲህ ብሏቸዋል:- “ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ በትንቢት የተናገረው ትክክል ነው፤ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልኩኛል፣ ትምህርታቸውም የሰው ሥርዓት ነው።’”—ማቴዎስ 15:7-9

ከዚህ በተቃራኒ እውነተኛው አምልኮ በሰዎች መካከል አንድነት እንዲኖር ያደርጋል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር:- “በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ። እርሱ በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል። እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:2, 4

በዛሬው ጊዜ ከ230 በሚበልጡ አገራት የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋ አምላክ አንድነትን በተመለከተ የሰጣቸውን መመሪያ ይከተላሉ። የአንድነታቸው መሠረት ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት” በማለት ጽፏል። (ቈላስይስ 3:14) ጳውሎስ የተጠቀመበት “የሚያስተሳስረውን” የሚለው የግሪክኛው ቃል የሰውነታችንን ጅማት ሊያመለክት ይችላል። በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙት ጅማቶች እንደ ገመድ ጠንካራ ሲሆኑ ሁለት አስፈላጊ ሥራዎችን ያከናውናሉ። የሰውነታችን ክፍሎች ቦታቸውን ይዘው እንዲቀመጡ የሚረዱ ከመሆኑም በላይ አጥንቶቻችንን አንድ ላይ አጣብቀው ይይዛሉ።

ከፍቅር ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህ ባሕርይ ሰዎች እርስ በርስ እንዳይገዳደሉ በማድረግ ብቻ አይወሰንም። የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ሰዎች የተለያየ አስተዳደግ ቢኖራቸውም በሰላም አብረው መኖር እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ለአብነት ያህል፣ በተለምዶ ወርቃማው ሕግ ተብሎ የሚጠራውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። በማቴዎስ 7:12 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” ብሏል። በርካታ ሰዎች ይህን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋቸው ጭፍን ጥላቻን እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል።

‘እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’

የይሖዋ ምሥክሮች፣ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” የሚለውን የኢየሱስ መመሪያ በመታዘዝ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። (ዮሐንስ 13:35) የዘር መከፋፈልና የፖለቲካ አለመረጋጋት በነበረባቸው ጊዜያት እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር አስደናቂ በሆነ መንገድ ታይቷል። ለአብነት ያህል፣ በ1994 በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር አሳይተዋል። የሁቱ ጎሣ አባላት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው ቱትሲ የሆኑ ወንድሞቻቸውን ከጥቃት ጠብቀዋል!

እርግጥ ነው፣ የዓለም መንግሥታት እንዲህ ዓይነት ፍቅር በማዳበር ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንዲኖር ማድረግ ይችላሉ ብሎ ማሰቡ የማይመስል ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በወሰነው ጊዜ ይህን እንደሚያደርግ ይናገራል። ይሁን እንጂ ሰዎች በዛሬው ጊዜም እንኳ ፍቅርን በመልበስ አንድነት ሊኖራቸው ይችላል።

ባለፈው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ቃሉ በዘመናችን ስላለው ጠቀሜታ ለሰዎች በመናገር ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዓታት አሳልፈዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት ማግኘታቸው አንድነት ያስገኘላቸው ሲሆን ከእነዚህም አንዳንዶቹ ቀደም ሲል በመካከላቸው ጥላቻ ነበር። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል አረቦችና አይሁዳውያን፣ አርመኖችና ቱርኮች እንዲሁም ጀርመኖችና ሩስያውያን ይገኙበታል።

ታዲያ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስገኘው አንድነት ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በአቅራቢያህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር አሊያም በገጽ 2 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች ወደ አንዱ መጻፍ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብሔራት በሺዎች የሚቆጠሩ የሰላም ስምምነቶችን ቢፈራረሙም እነዚህ ውሎች ፈርሰዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ሰብዓዊ መንግሥታት መፈጸም ያልቻሉትን ማከናወን ተችሏል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ቃል የእውነተኛ አንድነት ምንጭ ማን እንደሆነ ይጠቁመናል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሁቱና የቱትሲ ጎሣ አባላት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ ሆነው ለአምልኮ የሚጠቀሙበትን ቤት ሲሠሩ