በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አስተምር

ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አስተምር

ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አስተምር

‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ አስተምሯቸው።’—ማቴዎስ 28:19, 20

1. የመጽሐፍ ቅዱስን ስርጭት በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል?

 የይሖዋ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩትና በስፋት ከተሰራጩት መጻሕፍት አንዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ2,300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በመሆኑም ከ90 በመቶ የሚበልጠው የምድር ነዋሪ መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ ቋንቋ ማግኘት ይችላል።

2, 3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት በተመለከተ ግራ መጋባት የተፈጠረው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰነ ክፍል ያነብባሉ። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ደጋግመው አንብበውታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ትምህርቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ይናገራሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት በተመለከተ በመካከላቸው ስምምነት የለም። ሁኔታውን ይበልጥ ግራ የሚያጋባ የሚያደርገው ደግሞ የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባላት በሆኑ ግለሰቦች መካከል ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነት መኖሩ ነው። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን፣ ምንጩንና ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ጥርጣሬ አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎች፣ የመሐላ ሥነ ሥርዓት ሲፈጽሙ ወይም በፍርድ ቤት እውነቱን ለመናገር ቃል ሲገቡ የሚጠቀሙበት ቅዱስ መጽሐፍ ብቻ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ።

3 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ለሰው ልጆች ያስተላለፈውን መልእክት ወይም ኃይል ያለውን ቃሉን የያዘ መጽሐፍ ነው። (ዕብራውያን 4:12) የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲያውቁ እንፈልጋለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና እንዲያስተምሩ’ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን ተልዕኮ መፈጸም ያስደስተናል (ማቴዎስ 28:19, 20) ለሰዎች በምንመሠክርበት ወቅት፣ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ በሚገኘው ግራ የሚያጋባ ሃይማኖታዊ ሁኔታ የተጨነቁ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እናገኛለን። እነዚህ ሰዎች ስለ ፈጣሪያችን ማንነት እውነቱን ማወቅ የሚፈልጉ ከመሆኑም በላይ የሕይወትን ትርጉም በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ይሻሉ። ብዙ ሰዎችን የሚያሳስቧቸውን ሦስት ጥያቄዎች እስቲ እንመልከት። እያንዳንዱን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ የሃይማኖት መሪዎች ምን የተሳሳተ ትምህርት እንደሚያስተምሩና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ግን ምን እንደሚል እንመረምራለን። ጥያቄዎቹ (1) አምላክ ስለ እኛ ያስባል? (2) የተፈጠርነው ለምንድን ነው? እና (3) ስንሞት ምን እንሆናለን? የሚሉት ናቸው።

አምላክ ስለ እኛ ያስባል?

4, 5. ሰዎች፣ አምላክ አያስብልንም ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

4 በቅድሚያ የመጀመሪያውን ጥያቄ እንመልከት፤ አምላክ ስለ እኛ ያስባል? ብዙ ሰዎች የዚህ ጥያቄ መልስ አያስብም የሚል እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ መሆናቸው ያሳዝናል። እንዲህ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት የሚኖሩበት ዓለም በጥላቻ፣ በጦርነትና በመከራ የተሞላ መሆኑ ነው። ‘አምላክ በእርግጥ የሚያስብ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ነገሮች ሲደርሱ ዝም ብሎ አይመለከትም ነበር’ ይላሉ።

5 ሰዎች አምላክ አያስብልንም የሚል አመለካከት እንዲያድርባቸው ያደረገው ሌላው ምክንያት ደግሞ የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ እንዲሰማቸው ስላደረጓቸው ነው። ብዙውን ጊዜ ቀሳውስት አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲከሰቱ የሚሰጡት አስተያየት ምንድን ነው? አንዲት ሴት ሁለት ትንንሽ ልጆቿን በመኪና አደጋ ባጣችበት ጊዜ አንድ ቄስ “ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው፤ አምላክ ልጆቹን የወሰዳቸው ሁለት ተጨማሪ መላእክት ስላስፈለጉት ነው” ብለዋታል። ቀሳውስት እንዲህ ያሉ አስተያየቶች ሲሰጡ እየደረሱ ላሉት መጥፎ ነገሮች አምላክን ተጠያቂ ማድረጋቸው ነው። ይሁን እንጂ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማንም ሲፈተን፣ ‘እግዚአብሔር ፈተነኝ’ አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ይሖዋ አምላክ ክፉ የሆነ ነገር እንዲደርስ ፈጽሞ አያደርግም። እንዲያውም ‘ክፋትን ማድረግ ከአምላክ ዘንድ የራቀ’ ነው።—ኢዮብ 34:10

6. በዓለማችን ከሚታየው ክፋትና መከራ በስተጀርባ ያለው ማን ነው?

6 ታዲያ ክፋትና መከራ እንዲህ የበዛው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት፣ የሰው ዘር በጥቅሉ የአምላክን የጽድቅ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማክበር ፈቃደኛ ባለመሆን የእርሱን የበላይ ገዥነት ለመቀበል አሻፈረኝ ማለቱ ነው። ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር ስለሆነ’ የሰው ልጆች ባይታወቃቸውም እንኳ የአምላክ ጠላት ለሆነው ለሰይጣን እየተገዙ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህን ሐቅ መገንዘባችን መጥፎ ሁኔታዎች ሊኖሩ የቻሉበትን ምክንያት ለመረዳት ቀላል ያደርግልናል። ሰይጣን ክፉና በጥላቻ የተሞላ ከመሆኑም በላይ አታላይና ጨካኝ ነው። ስለዚህ ይህ ዓለም የገዥውን ባሕርይ ማንጸባረቁ እንደማይቀር መጠበቅ ይገባናል። ክፋት እንዲህ መብዛቱ ምንም አያስገርምም!

7. ለሚያጋጥሙን መከራዎች ምክንያት የሚሆኑት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

7 ለሚደርስብን መከራ ምክንያት የሆነው ሌላው ነገር የሰው ልጅ ፍጽምና የጎደለው መሆኑ ነው። ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የበላይ ለመሆን ይታገላሉ፤ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ጦርነት፣ ጭቆናና መከራ ያስከትላል። መክብብ 8:9 [NW] “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” በማለት ሁኔታውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። መከራ ሊኖር የቻለበት ሌላው ምክንያት ደግሞ “ጊዜና አጋጣሚ” ነው። (መክብብ 9:11 NW) ብዙውን ጊዜ ሰዎች አደጋ ላይ እንዲወድቁ የሚያደርጋቸው በአጉል ሰዓት አጉል ቦታ ላይ መገኘታቸው ነው።

8, 9. አምላክ በእርግጥ እንደሚያስብልን እንዴት እናውቃለን?

8 በሰዎች ላይ እየደረሰ ላለው መከራ መንስኤው አምላክ አለመሆኑን ማወቅ የሚያጽናና ነው። ያም ሆኖ አምላክ የእኛ ሁኔታ በእርግጥ ያሳስበዋል? መልሱ አዎን የሚል መሆኑ በጣም ያስደስታል! ሰዎች መጥፎ ጎዳና እንዲከተሉ አምላክ ለምን እንደፈቀደላቸው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚነግረን ይሖዋ ለሰው ልጆች እንደሚያስብ እናውቃለን። አምላክ ይህን ያደረገው ከእርሱ ሉዓላዊነትና ከሰው ልጆች ታማኝነት ጋር ተያይዘው በተነሱት ሁለት አከራካሪ ጉዳዮች ምክንያት ነው። ይሖዋ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ለእኛ የመግለጽ ግዴታ የለበትም። ይሁንና ለእኛ ስለሚያስብ ምክንያቱን እንድናውቅ አድርጓል።

9 አምላክ እንደሚያስብልን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ እንመልከት። በኖኅ ዘመን ምድር በክፋት ስትሞላ ‘ልቡ እጅግ አዝኖ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:5, 6) ዛሬስ ከዚያ የተለየ ስሜት ሊሰማው ይችላል? በፍጹም፣ ምክንያቱም አምላክ መቼም አይለወጥም። (ሚልክያስ 3:6) አምላክ ግፍን የሚጠላ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ሲሠቃዩ ማየት አይፈልግም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የሰው ልጆች አገዛዝና የዲያብሎስ ተጽዕኖ ያስከተለውን ጉዳት በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወግድ ያስተምራል። ይህ አምላክ እንደሚያስብልን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ አይደለም?

10. ይሖዋ ስለ ሰው ልጆች ሥቃይ ምን ይሰማዋል?

10 የሃይማኖት መሪዎች በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን አሳዛኝ ሁኔታዎች የአምላክ ፈቃድ እንደሆኑ አድርገው መናገራቸው ፈጽሞ ስህተት ነው። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ሥቃይ ለማስወገድ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። አንደኛ ጴጥሮስ 5:7 ‘እርሱ ስለ እናንተ ያስባል’ ይላል። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይህ ነው!

የተፈጠርነው ለምንድን ነው?

11. አብዛኛውን ጊዜ በዓለም ያሉ ሃይማኖቶች ሰው የተፈጠረበትን ምክንያት በተመለከተ ምን ይላሉ?

11 ብዙ ሰዎች የሚያሳስባቸውን ሁለተኛ ጥያቄ ደግሞ እንመልከት፤ የተፈጠርነው ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ በዓለም ያሉ ሃይማኖቶች ሰው ምድር ላይ የሚኖረው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የሚል መልስ ይሰጣሉ። ምድር በሌላ ቦታ ለሚኖር ሕይወት መሸጋገሪያ ብቻ እንደሆነች አድርገው ያስባሉ። አንዳንድ ቀሳውስት አምላክ አንድ ቀን ይህችን ፕላኔት ያጠፋታል ብለው በሐሰት ያስተምራሉ። እንዲህ ባሉት ትምህርቶች የተነሳ ብዙ ሰዎች የሚጠብቃቸው ነገር ሞት ብቻ እንደሆነ በማሰብ የተቻላቸውን ያህል ሕይወትን ማጣጣም እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። በምድር ላይ የተፈጠርንበትን ምክንያት በተመለከተ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?

12-14. አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

12 አምላክ ለምድርም ሆነ ለሰው ልጆች አስደናቂ ዓላማ አለው። ‘ምድርን የፈጠረው የሰው መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ባዶ እንድትሆን’ አይደለም። (ኢሳይያስ 45:18) ከዚህም በላይ ይሖዋ ‘ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጽንቷታል።’ (መዝሙር 104:5) አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ማወቃችን የተፈጠርንበትን ምክንያት እንድንገነዘብ ይረዳናል።

13 ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2 ይሖዋ ምድርን የሰው መኖሪያ እንድትሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዳዘጋጃት ይገልጹልናል። በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ተፈጥረው ሲያበቁ ሁሉም ነገር “እጅግ መልካም” ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ውብ የአትክልት ሥፍራ በሆነችው በኤደን ያስቀመጣቸው ከመሆኑም በላይ የተትረፈረፈ ምግብ ሰጥቷቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ‘እንዲባዙ፣ ምድርን እንዲሞሏትና እንዲገዟት’ ተነግሯቸዋል። እንደ እነርሱ ፍጹማን የሆኑ ልጆች መውለድና መኖሪያቸው የሆነውን የአትክልት ሥፍራ በምድር ዙሪያ ማስፋፋት ይጠበቅባቸው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ እንስሳትን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መግዛት ነበረባቸው።—ዘፍጥረት 1:26-28

14 የይሖዋ ዓላማ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ቤተሰብ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም እንዲኖር ነው። የአምላክ ቃል “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። (መዝሙር 37:29) አዎን፣ ሰዎች የተፈጠሩት ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። ይህ የአምላክ ዓላማ ነው፤ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትም ይኸው ነው!

ስንሞት ምን እንሆናለን?

15. በዓለም ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ስንሞት ምን እንሆናለን ብለው ያስተምራሉ?

15 አሁን ደግሞ ብዙ ሰዎችን የሚያሳስበውን ሦስተኛ ጥያቄ እንመልከት፤ ስንሞት ምን እንሆናለን? በዓለም ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሃይማኖቶች በሰው አካል ውስጥ ያለች አንዲት ነገር ሥጋው ከሞተም በኋላ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች ብለው ያስተምራሉ። አንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች አሁንም ድረስ አምላክ ክፉዎችን እሳታማ ሲኦል ውስጥ ከቶ ለዘላለም በማሠቃየት ይቀጣቸዋል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነው? ሞትን በተመለከተ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?

16, 17. መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ምን ይላል?

16 የአምላክ ቃል “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና . . . ምንም ዋጋ የላቸውም” ይላል። ሙታን ‘ምንም የማያውቁ’ እንደመሆናቸው መጠን መስማት፣ ማየት፣ መናገርና ማሰብ የማይችሉ ከመሆኑም በላይ ምንም ዓይነት ስሜት አይሰማቸውም። ሙታን ምንም ዓይነት ዋጋ ወይም ደሞዝ አይቀበሉም። ምንም መሥራት የማይችሉ በመሆናቸው እንዴት ዋጋ ሊቀበሉ ይችላሉ? ከዚህም በላይ “ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል።” ስለዚህ ምንም ዓይነት ስሜት የላቸውም።—መክብብ 9:5, 6, 10

17 መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ሐሳብ ግልጽና የማያሻማ ነው፤ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በሌላ ቦታ መኖሩን አይቀጥልም። ከሞትን በኋላ በሕይወት የሚቀጥል የአካል ክፍል የሌለን በመሆኑ በሪኢንካርኔሽን የሚያምኑ ሰዎች እንደሚያስቡት ዳግመኛ ሌላ አካል ለብሰን ልንወለድ አንችልም። ይህን ነጥብ በሚከተለው ምሳሌ ማስረዳት ይቻላል:- ሕይወታችን እንደ ሻማ ብርሃን ነው። የሻማው ብርሃን ሲጠፋ እንዳልነበረ ይሆናል እንጂ የትም አይሄድም።

18. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሙታን ምንም እንደማያውቁ ሲማር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ይችላል?

18 ይህ ለመረዳት ቀላል የሆነ ግን ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እውነት ያለውን አንድምታ እስቲ አስብ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሙታን ምንም እንደማያውቁ ሲገነዘብ፣ በሞት ያንቀላፉት የቀድሞ አባቶቹ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ምንም ያህል ቁጡዎች ቢሆኑ ሊጎዱት እንደማይችሉ በቀላሉ መረዳት መቻል ይኖርበታል። በተጨማሪም በሞት የተለዩት ወዳጅ ዘመዶቹ መስማት፣ ማየት፣ መናገርም ሆነ ማሰብ እንደማይችሉ እንዲሁም ምንም ዓይነት ስሜት እንደማይሰማቸው ወዲያውኑ ሊገነዘብ ይገባዋል። በመሆኑም መንጽሔ ውስጥ ገብተው ሊቋቋሙት በማይችሉት የብቸኝነት ስሜት ሊማቅቁ ወይም እሳታማ ሥፍራ ውስጥ ገብተው ሊሠቃዩ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላክ የሚያስባቸው ሙታን ወደፊት ትንሣኤ እንደሚያገኙ ያስተምራል። ይህ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው!—ዮሐንስ 5:28, 29

በአገልግሎታችን እንድንጠቀምበት የተዘጋጀ አዲስ መጽሐፍ

19, 20. ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምን ኃላፊነት አለብን? በአገልግሎታችን ልንጠቀምበት የምንችል መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚረዳ ምን ጽሑፍ ተዘጋጅቶልናል?

19 ብዙ ሰዎች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል እስካሁን የተመለከትነው ሦስቱን ብቻ ነው። እያንዳንዱን ጥያቄ ስንመረምር መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት ግልጽና የማያሻማ እንደሆነ ተመልክተናል። እንዲህ ያሉትን እውነቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ማካፈል ምንኛ የሚያስደስት ነው! ሆኖም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አጥጋቢ መልስ የሚሹላቸው አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሰዎች እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ የመርዳት ኃላፊነት አለብን።

20 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ግልጽ በሆነና የተማሪውን ልብ በሚማርክ መንገድ ማስተማር ፈታኝ ነው። ይህን ፈታኝ ሁኔታ እንድንወጣ ለመርዳት “ታማኝና ልባም ባሪያ” አንድ መጽሐፍ አዘጋጅቶልናል። መጽሐፉ የተዘጋጀው በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን እንድንጠቀምበት ለመርዳት ታስቦ ነው። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ይህ ባለ 224 ገጽ መጽሐፍ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የሚል ርዕስ አለው።

21, 22. ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ካሉት ጠቃሚ ገጽታዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

21 “አምላካዊ ታዛዥነት” በተባለው በ2005 የተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ የወጣው ይህ መጽሐፍ የተለያዩ ጠቃሚ ገጽታዎች አሉት። ለምሳሌ ያህል፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አምስት ገጽ የሚሸፍን መቅድም አለው። በመቅድሙ ውስጥ በሚገኙት ሥዕሎችና ጥቅሶች ተጠቅማችሁ ሰዎችን ማወያየት ቀላል እንደሚሆንላችሁ ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም በመቅድሙ ውስጥ የሚገኘውን ሣጥን በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ ጥቅስ እንዴት ማውጣት እንደሚችሉ ልታሳዩአቸው ትችላላችሁ።

22 ይህ መጽሐፍ ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ የተጻፈ ነው። በተቻለ መጠን ትምህርቱን ከተማሪው ጋር አያይዞ በማቅረብ ልቡን ለመንካት ጥረት ተደርጓል። በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ የመግቢያ ጥያቄዎች የሚገኙ ሲሆን መጨረሻ ላይ ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል። ይህ ሣጥን በምዕራፉ መጀመሪያ ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን ይዟል። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት ግሩም ሥዕሎች፣ እነርሱን የሚያብራሩ ሐሳቦችና ምሳሌያዊ አገላለጾች ተማሪው አዳዲስ ነጥቦችን እንዲያስተውል ይረዱታል። ዋናው የመጽሐፉ ክፍል ቀላል በሆነ መንገድ የተዘጋጀ ቢሆንም ተማሪው ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት የሚፈልግ ከሆነ በጥልቀት ውይይት ልታደርጉባቸው የምትችሉባቸውን በጣም አስፈላጊ የሆኑ 14 ርዕሰ ጉዳዮች የያዘ ተጨማሪ ክፍል አለ።

23. ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ አጠቃቀም በተመለከተ ምን ምን ሐሳቦች ቀርበዋል?

23 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉና የተለያዩ ሃይማኖቶችን ይከተሉ የነበሩ ሰዎችን ማስተማር እንድንችል እኛን ለመርዳት የተዘጋጀ ነው። ተማሪው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እውቀት የሌለው ከሆነ አንድ ምዕራፍ ለመጨረስ ከአንድ የጥናት ክፍለ ጊዜ በላይ ሊወስድበት ይችላል። ምዕራፉን ለመጨረስ ከመጣደፍ ይልቅ የተማሪውን ልብ ለመንካት ጣር። ተማሪው በመጽሐፉ ላይ የተገለጸውን ምሳሌ መረዳት ከከበደው አብራራለት፤ አሊያም ሌላ ተመሳሳይ ምሳሌ ንገረው። በሚገባ ተዘጋጅ፣ መጽሐፉን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ እንዲሁም ‘የእውነትን ቃል በትክክል ለማስረዳት’ እንድትችል አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ።—2 ጢሞቴዎስ 2:15

ላገኛችሁት ውድ መብት አድናቆት ይኑራችሁ

24, 25. ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጣቸው ውድ መብቶች ምንድን ናቸው?

24 ይሖዋ ለሕዝቡ ውድ መብቶችን ሰጥቷቸዋል። ስለ እርሱ ማንነት እውነቱን እንድናውቅ አስችሎናል። ይህን መብት አቅልለን ልንመለከተው አይገባም! ደግሞም ይሖዋ ዓላማዎቹን የገለጸው ለትዕቢተኞች ሳይሆን ለትሑታን ነው። ኢየሱስ ይህንን አስመልክቶ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 11:25) የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነውን ይሖዋን ከሚያገለግሉት ትሑታን መካከል መቆጠር ውድ መብት ነው።

25 በተጨማሪም ይሖዋ ሌሎችን ስለ እርሱ የማስተማር መብት ሰጥቶናል። ስለ አምላክ የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ ሰዎች ሌሎች ለእርሱ የተዛባ አመለካከት እንዲያድርባቸው እንዳደረጉ አስታውስ። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይሖዋ ለሰዎች ምንም የማያስብ ደንታ ቢስ አምላክ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት አድሮባቸዋል። ይህን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት የበኩልህን አስተዋጽኦ ለማበርከት ትጓጓለህ? በየትኛውም ሥፍራ የሚኖሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ስለ አምላክ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲያገኙ ትፈልጋለህ? እንግዲያው በቅንዓት በመስበክና ቅዱሳን መጻሕፍት ወሳኝ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያስተምሩትን ትምህርት ለሌሎች በማስተማር ይሖዋን በፍቅር ተገፋፍተህ እንደምትታዘዘው በተግባር አሳይ። እውነትን የሚሹ ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መማር ያስፈልጋቸዋል።

መልስህ ምንድን ነው?

• አምላክ እንደሚያስብልን እንዴት እናውቃለን?

• የተፈጠርነው ለምንድን ነው?

• ስንሞት ምን እንሆናለን?

• የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ካሉት ገጽታዎች ይበልጥ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘኸው የትኛውን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ መከራና ሥቃይ እንደሚወገድ ያስተምራል

[ምንጭ]

ከላይ በስተቀኝ ያለችው ልጅ:- © Bruno Morandi/age fotostock; በስተግራ ያለችው ሴት:- AP Photo/Gemunu Amarasinghe; ከታች በስተቀኝ ያሉት ስደተኞች:- © Sven Torfinn/Panos Pictures

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጻድቃን በገነት ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ