በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልባችሁን በመጠበቅ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆናችሁ ኑሩ

ልባችሁን በመጠበቅ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆናችሁ ኑሩ

ልባችሁን በመጠበቅ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆናችሁ ኑሩ

“አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።”—ምሳሌ 4:23

1-3. (ሀ) ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን አቅልለው እንደሚመለከቱ የሚያሳዩት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) የሥነ ምግባር ንጽሕና ምን ያህል ዋጋ እንዳለው መመርመር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

 ዕሉ ሲታይ የድሮ ይመስላል። ምናልባትም በቤቱ ውስጥ ካሉት ሌሎች ማስጌጫዎች ጋር የማይሄድ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ባለቤቱ ሥዕሉን ብዙም ስላልፈለገው አሮጌ ቁሳቁሶችን ለሚሸጥ አንድ የእርዳታ ድርጅት ሰጠው። መጀመሪያ ላይ 250 ብር ገደማ እንዲሸጥ ተተምኖ የነበረው ይህ ሥዕል ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጣ ታወቀ! በእርግጥም ይህ ሥዕል ድንቅ የፈጠራ ውጤት ነበር። ይህን ውድ ቅርስ ንቆት የነበረው የመጀመሪያው ባለቤት ይህን ሲያውቅ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ገምት!

2 ብዙውን ጊዜ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናንም በተመለከተ ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን አቅልለው ይመለከቱታል። እንዲያውም አንዳንዶች ጊዜ ያለፈበትና ከዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የማይሄድ ነው የሚል አመለካከት አላቸው። በመሆኑም ለማይረባ ነገር ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። አንዳንዶች ለቅጽበት የጾታ ስሜታቸውን ለማርካት ሲሉ ንጽሕናቸውን ያጎድፋሉ። ሌሎች ደግሞ በእኩዮቻቸው ወይም በተቃራኒ ጾታ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን የሚያጎድፍ ድርጊት ይፈጽማሉ።—ምሳሌ 13:20

3 ብዙዎች የሥነ ምግባር ንጽሕና ምን ያህል ውድ ሀብት እንደሆነ የሚገነዘቡት ስህተት ከፈጸሙ በኋላ ነው። ብዙውን ጊዜ ደግሞ የሚፈጽሙት ስህተት ከባድ መዘዝ የሚያስከትል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው የጾታ ብልግና መፈጸም የሚያስከትለው መዘዝ “እንደ እሬት የመረረ ነው።” (ምሳሌ 5:3, 4) በሥነ ምግባር በተበላሸው በዚህ ዓለም ውስጥ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናህን በክብር መያዝና መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ለዚህ ሊረዱን የሚችሉ ሦስት ነጥቦችን እንመለከታለን።

ልብህን ጠብቅ

4. ምሳሌያዊው ልብ ምንድን ነው? ልንጠብቀው የሚገባንስ ለምንድን ነው?

4 በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ ለመኖር ልብን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” ሲል ይገልጻል። (ምሳሌ 4:23) እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ልብህን” የሚለው አነጋገር ምን ያመለክታል? ይህ አነጋገር ቃል በቃል አካላዊውን ልብ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። ሐሳብህን፣ ስሜትህንና ዝንባሌህን ጨምሮ ውስጣዊ ማንነትህን በጠቅላላ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” ይላል። (ዘዳግም 6:5) ኢየሱስ ይህ ትእዛዝ ከሁሉም ትእዛዛት የላቀ እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:29, 30) በእርግጥም ልባችን ከፍተኛ ዋጋ ያለው በመሆኑ ልንጠብቀው ይገባናል።

5. ልብ ጠቃሚ የመሆኑን ያህል አደገኛም ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

5 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው” ሲል ይገልጻል። (ኤርምያስ 17:9) ልብ ተንኰለኛ ወይም አደገኛ ሊሆንብን የሚችለው በምን መንገድ ነው? ለምሳሌ ያህል መኪና ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ በአደጋ ጊዜ ሕይወት ለማትረፍ ሊረዳ ይችላል። ይሁን እንጂ አሽከርካሪው መሪውን በሚገባ በመጠቀም መኪናውን መቆጣጠር ካልቻለ መኪናው በሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። በተመሳሳይም ልብህን መጠበቅ ካልቻልክ ውስጣዊ ስሜትህና ፍላጎትህ ሕይወትህን ሊቆጣጠረውና ለአደጋ ሊዳርግህ ይችላል። የአምላክ ቃል “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 28:26) ረጅም ጉዞ ከመጀመርህ በፊት ካርታ ለመመልከት እንደምትሞክር ወይም ሰው እንደምትጠይቅ ሁሉ የአምላክን ቃል መመሪያህ አድርገህ የምትጠቀምበት ከሆነ በጥበብ ጎዳና ልትሄድና ከአደጋ ልትጠበቅ ትችላለህ።—መዝሙር 119:105

6, 7. (ሀ) ቅድስና ምንድን ነው? የይሖዋ አገልጋዮችስ ይህን ባሕርይ ማሳየታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች የይሖዋን ቅድስና ማንጸባረቅ እንደሚችሉ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

6 እኛ በትክክለኛው አቅጣጫ ካልመራነው በቀር ልባችን በራሱ የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ አያነሳሳንም። ይህን ማድረግ ከፈለግን የሥነ ምግባር ንጽሕናን መጠበቅ ባለው ከፍተኛ ዋጋ ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ይህ ባሕርይ ንጽሕናንና ከኃጢአት ድርጊቶች መራቅን ከሚያመለክተው የቅድስና ባሕርይ ጋር የተሳሰረ ነው። ቅድስና የይሖዋ አምላክ መለያ የሆነ ውድ ባሕርይ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቅሶች ይህን ባሕርይ ከይሖዋ ጋር አያይዘው ይገልጹታል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ቅድስና ለእግዚአብሔር” በማለት ይናገራል። (ዘጸአት 28:36) ይሁንና ይህ የላቀ ባሕርይ ፍጽምና ከጎደለን የሰው ልጆች ጋር ምን ግንኙነት አለው?

7 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” ብሎናል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) አዎን፣ የይሖዋን የቅድስና ባሕርይ በመኮረጅ በእሱ ፊት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን። በመሆኑም ንጹሕ ካልሆኑና ከሚያረክሱ ድርጊቶች የምንርቅ ከሆነ ባገኘነው ውድ አጋጣሚ በመጠቀም የሉዓላዊውን አምላክ ግሩም ባሕርይ ለማንጸባረቅ እየጣርን ነው ሊባል ይችላል። (ኤፌሶን 5:1) ይሖዋ ጥበበኛና ምክንያታዊ አምላክ በመሆኑ የማንችለውን ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። ስለሆነም ቅድስናን ማንጸባረቅ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። (መዝሙር 103:13, 14፤ ያዕቆብ 3:17) መንፈሳዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅ ጥረት እንደሚጠይቅ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በክርስቶስ ፊት ቅንና ንጹሕ መሆን እንደሚገባ’ ጠቁሟል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ክርስቶስና አባቱ የዋሉልን ውለታ የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እንድናደርግ ግድ አይለንም? እንደ እውነቱ ከሆነ ላሳዩን ፍቅር ውለታቸውን ልንመልስ አንችልም። (ዮሐንስ 3:16፤ 15:13) ሆኖም በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነን በመኖር ለዋሉልን ውለታ አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ለይሖዋ ያለንን አመስጋኝነት የምንገልጽበት አንዱ መንገድ እንደሆነ ከተገነዘብን እንደ ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከተው ከመሆኑም በላይ ልባችንን ለመጠበቅ ጥረት እናደርጋለን።

8. (ሀ) ምሳሌያዊ ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ጭውውታችን ስለ እኛ ምን ሊጠቁም ይችላል?

8 ልባችንን በመጠበቅ ረገድ መንፈሳዊ አመጋገባችንም ወሳኝነት አለው። አእምሯችንና ልባችን ዘወትር ጥሩ መንፈሳዊ ምግብ እንዲመገብ ጥረት ማድረግ ያለብን ከመሆኑም በላይ ሐሳባችን በሙሉ በአምላክ መንግሥት ምሥራች ላይ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል። (ቆላስይስ 3:2) ጭውውታችን እንኳ ሳይቀር ይህንን የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት። ሰብዓዊ ነገሮችንና የብልግና ወሬዎችን እያነሳን ማውራት የሚቀናን ከሆነ ይህ ሁኔታ ልባችንን የሞላው ምን እንደሆነ ሊጠቁም ይችላል። (ሉቃስ 6:45) ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ የሆኑና የሚያንጹ ነገሮችን የማውራት ልማድ ሊኖረን ይገባል። (ኤፌሶን 5:3) ልባችንን መጠበቅ እንችል ዘንድ ጥንቃቄ ልናደርግባቸው የሚገቡ አንዳንድ አደጋዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል እስቲ ሁለቱን እንመልከት።

ከዝሙት ሽሽ

9-11. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 6:18 ላይ የሚገኘውን ምክር ችላ የሚሉ ሰዎች የጾታ ብልግና ለመፈጸም በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ከዝሙት የምንሸሽ ከሆነ ከየትኞቹ ነገሮች እንርቃለን? (ሐ) ታማኙ ሰው ኢዮብ ምን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል?

9 ይሖዋ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካኝነት ያስጻፈው ምክር ብዙዎች ልባቸውን እንዲጠብቁና በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነው እንዲኖሩ ረድቷቸዋል። ጳውሎስ “ከዝሙት ሽሹ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) “ከዝሙት ታቀቡ” እንዳላለ ልብ በል። ክርስቲያኖች ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሕይወትን ሊያሳጣ ከሚችል ከማንኛውም አደገኛ ሁኔታ ሮጠው ለማምለጥ እንደሚጥሩ ሁሉ እንዲህ ካሉ የብልግና ድርጊቶችም መሸሽ ይኖርባቸዋል። ይህን ምክር ችላ ካልን ከባድ የጾታ ብልግና ልንፈጽምና የአምላክን ሞገስ ልናጣ እንችላለን።

10 ለምሳሌ ያህል አንዲት እናት ትንሽ ልጅዋን አጥባና አለባብሳ ወደ አንድ ቦታ ይዛው ለመሄድ ተዘጋጀች እንበል። ልጁ የሚሄዱበት ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ውጭ ወጥቶ ለመጫወት እናቱን ፈቃድ ጠየቀ። እናቱ እንዲጫወት ብትፈቅድለትም “ቆሻሻ ውኃ ወዳቆረው ጉድጓድ አካባቢ እንዳትደርስ። እዚያ ሄደህ ልብስህ ቢቆሽሽ ትገረፋለህ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠችው። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግን ጭቃ እንዳይነካው እየተጠነቀቀ ቀስ ብሎ በውኃው ዳር ዳር ሲሄድ ተመለከተችው። ለጊዜው ጭቃ ያልነካው ቢሆንም እንኳ እናቱ ውኃው አጠገብ እንዳይደርስ የሰጠችውን ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ባለመስማቱ ራሱን ለችግር አጋልጧል። (ምሳሌ 22:15) ብዙ ወጣቶችና የተሻለ ማስተዋል አላቸው የሚባሉ አዋቂዎች ጭምር እንዲህ ዓይነት ስሕተት ሲሰሩ ይታያሉ። እንዴት?

11 ብዙዎች “ለሚያስነውር ምኞት” በተሸነፉበት በዚህ ዘመን ልቅ የሆነ የጾታ ብልግናን የሚያስፋፋ አዲስ ኢንዱስትሪ ብቅ ብሏል። (ሮሜ 1:26, 27) የወሲብ ድርጊቶችን የሚያሳዩ መጽሔቶች፣ መጻሕፍት፣ ቪዲዮዎችና የኢንተርኔት ፕሮግራሞች እንደ አሸን ፈልተዋል። ራሳቸውን ለእነዚህ ነገሮች ያጋለጡ ሰዎች ከዝሙት እየሸሹ ናቸው ሊባል አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ቸል በማለት እነዚህን ነገሮች አቅልለው የሚመለከቱ ሰዎች ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል። ልባቸውን ከመጠበቅ ይልቅ በቀላሉ ከአእምሮ በማይጠፉ ምናባዊ ምሥሎች እየመረዙት ነው። (ምሳሌ 6:27) ስሕተት እንዲሠራ ሊፈትኑት የሚችሉ ነገሮችን እንዳያይ ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን ከገባው ከታማኙ ኢዮብ ጥሩ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ኢዮብ 31:1) በእርግጥም ኢዮብ ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

12. ክርስቲያን ተጋቢዎች በሚጠናኑበት ጊዜ ‘ከዝሙት ሊሸሹ’ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 በተለይ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በምንጠናናበት ጊዜ ‘ከዝሙት መሸሻችን’ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ይህ ጊዜ በተስፋና በጉጉት የተሞላ አስደሳች ጊዜ መሆን ያለበት ቢሆንም በመጠናናት ላይ ያሉ አንዳንድ ወጣቶች የጾታ ብልግና በመፈጸም ገና ከጅምሩ ያበላሹታል። በዚህም ሳቢያ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር፣ ራስን በመግዛትና ይሖዋ አምላክን በመታዘዝ ላይ የተመሰረተ ጥሩ ትዳር መገንባት የሚችሉበትን አጋጣሚ ያጣሉ። ክርስቲያን የሆኑ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በመጠናናት ላይ በነበሩበት ወቅት የጾታ ብልግና ፈጸሙ። ከተጋቡ በኋላ ሚስትየዋ ኅሊናዋ በጣም እንዳሰቃያትና በሠርጋቸው ቀን እንኳ ሳይቀር ደስታዋን እንዳሳጣት ሳትሸሽግ ተናግራለች። “ይሖዋ ይቅር እንዲለኝ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጠይቄዋለሁ፤ ይህ ሁኔታ ከተፈጸመ ሰባት ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ኅሊናዬ አሁንም ድረስ ይወቅሰኛል” በማለት ገልጻለች። እንዲህ ያለ ኃጢአት የፈጸሙ ክርስቲያኖች የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲረዷቸው መጠየቅ ይኖርባቸዋል። (ያዕቆብ 5:14, 15) ይሁን እንጂ ብዙ ክርስቲያን ተጋቢዎች በሚጠናኑበት ጊዜ ጥንቃቄ በማድረግ ከእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ራሳቸውን ይጠብቃሉ። (ምሳሌ 22:3) አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን በሚገልጹበት ጊዜ ገደብ አልፈው ላለመሄድ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በሚጠናኑበት ጊዜ ሌላ ሰው አብሯቸው እንዲገኝ የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ ሰው በሌለባቸው ቦታዎች ብቻቸውን ከመሆን ይቆጠባሉ።

13. ክርስቲያኖች ይሖዋን ከማያመልክ ሰው ጋር መጠናናት የሌለባቸው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር መጠናናት የሚጀምሩ ክርስቲያኖች ከባድ ችግሮች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ የታወቀ ነው። አንድ ክርስቲያን ይሖዋ አምላክን ከማይወድ ሰው ጋር በጋብቻ ለመተሳሰር እንዴት ያስባል? ክርስቲያኖች መጋባት ያለባቸው ይሖዋን ከሚወዱና የሥነ ምግባር ንጽሕናን በተመለከተ ያወጣቸውን መስፈርቶች ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር ብቻ ነው። የአምላክ ቃል የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?”—2 ቆሮንቶስ 6:14

14, 15. (ሀ) አንዳንዶች “ዝሙት” የሚለውን ቃል በተመለከተ ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው? (ለ) “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? ክርስቲያኖች ‘ከዝሙት መሸሽ’ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

14 በተጨማሪም እውቀት ወሳኝ ነው። ዝሙት ምን እንደሆነ በትክክል ካላወቅን ሙሉ በሙሉ ከዝሙት መሸሽ አንችልም። በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎች “ዝሙት” የሚለውን ቃል በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው። በቀጥታ የጾታ ግንኙነት እስካልፈጸሙ ድረስ ከጋብቻ ውጪ የጾታ ስሜታቸውን ማርካት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ላልተፈለገ እርግዝና እንዳይጋለጡ ምክር የሚሰጡ አንዳንድ የታወቁ የጤና ተቋማት እንኳ ሳይቀሩ ወጣቶች እርግዝና የማያስከትሉ ጸያፍ የሆኑ የጾታ ብልግናዎችን እንዲፈጽሙ ያበረታታሉ። እንዲህ ያለው ምክር በጣም የተሳሳተ ነው። የሥነ ምግባር ንጽሕናን መጠበቅ ሲባል ከጋብቻ ውጭ ከሚመጣ ያልተፈለገ እርግዝና መሸሽ ማለት ብቻ አይደለም። በተጨማሪም “ዝሙት” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም።

15 “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ፖርኒያ የተባለው የግሪክኛ ቃል ሰፊ ትርጉም አለው። ይህ ቃል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የጾታ ግንኙነትና የጾታ ብልቶችን ጸያፍ በሆነ መንገድ መጠቀምን ያመለክታል። በአፍና በፊንጢጣ የሚፈጸም ወሲብ እንዲሁም የሌላውን የጾታ ብልት ማሻሸት የመሳሰሉ በዝሙት አዳሪ ቤቶች የሚፈጸሙ የተለያዩ የጾታ ብልግናዎችም በፖርኒያ ሥር የሚጠቃለሉ ድርጊቶች ናቸው። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች “ዝሙት” አይደሉም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ራሳቸውን እያታለሉ ከመሆናቸውም በላይ የሰይጣን ወጥመድ ሰለባ ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:26) በተጨማሪም የሥነ ምግባር ንጽሕናን መጠበቅ እንደ ዝሙት ከሚቆጠሩ ድርጊቶች መራቅ ማለት ብቻ አይደለም። ‘ከዝሙት ለመሸሽ’ ከባድ ኃጢአት የሆነውን ፖርኒያን እንድንፈጽም ሊያደርግ ከሚችል ማንኛውም ዓይነት የጾታ ርኩሰትና ብልግና መራቅ አለብን። (ኤፌሶን 4:19) እንዲህ ካደረግን ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ እንችላለን።

ማሽኮርመም ከሚያስከትለው አደጋ ተጠበቁ

16. ፍቅራዊ ስሜትን መግለጽ ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው? ይህንንስ የሚደግፍ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ አለ?

16 በተጨማሪም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ ከፈለግን ከማሽኮርመም መቆጠብ አለብን። አንዳንዶች ማሽኮርመም እንዲሁ ለቀልድ ያህል የሚደረግ ምንም ጉዳት የማያስከትል ነገር ነው ብለው ይከራከራሉ። እርግጥ ነው፣ ፍቅራዊ ስሜት የሚገለጽበት ተገቢ ጊዜና ቦታ አለው። ይስሐቅ ከርብቃ ጋር “ሲዳራ” የታየ ሲሆን ይህን የተመለከቱ ሰዎች ወንድምና እኅት አለመሆናቸውን ሊገነዘቡ ችለዋል። (ዘፍጥረት 26:7-9) ይስሐቅና ርብቃ ባልና ሚስት ስለነበሩ ይህን ማድረጋቸው ስሕተት አልነበረም። ማሽኮርመም ግን ከዚህ የተለየ ነገር ነው።

17. ማሽኮርመም የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችለውስ ምንድን ነው?

17 ማሽኮርመም የሚለው ቃል አንድ ሰው የማግባት እቅድ ሳይኖረው የሚያሳየውን ፍቅራዊ ስሜት ያመለክታል። የሰዎች አፈጣጠርና ባሕርይ የተለያየ እንደመሆኑ መጠን የሚያሽኮረምሙባቸው መንገዶችም የዚያኑ ያህል የተለያዩ ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በግልጽ የማይታዩ ሊሆኑ ይችላሉ። (ምሳሌ 30:18, 19) በመሆኑም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ድርቅ ያለ ሕግ ማውጣት መፍትሔ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ራስን በሐቀኝነት መመርመርና ምንጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ለማድረግ መጣር የተሻለ ነው።

18. አንዳንዶች ለማሽኮርመም የሚገፋፋቸው ምንድን ነው? ማሽኮርመም ጎጂ የሆነውስ ለምንድን ነው?

18 ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንደተወደዱ ወይም እንደተፈቀሩ ሲያውቁ በጣም ደስ እንደሚላቸውና ኩራት እንደሚሰማቸው የታወቀ ነው። ይህ ያለ ነገር ነው። በራሳችንም ሆነ በሌላው ሰው ላይ እንዲህ ያለ ስሜት ለመፍጠር ስንል እናሽኮረምማለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የሌላውን ሰው ስሜት ምን ያህል እየጎዳን እንዳለን ተገንዝበናል? ምሳሌ 13:12 “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” በማለት ይገልጻል። አንድን ሰው ሆን ብለን የምናሽኮረምም ከሆነ ያ ሰው ምን እየተሰማው እንዳለ ላናውቅ እንችላለን። ግለሰቡ መጠናናት እንደምትጀምሩ ብሎም እንደምትጋቡ አድርጎ ሊያስብ ይችላል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ስሜቱ ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል። (ምሳሌ 18:14) ሆን ብሎ በሌሎች ሰዎች ስሜት መጫወት ጭካኔ ነው።

19. ማሽኮርመም በክርስቲያኖች ትዳር ላይ ምን አደጋ ሊያስከትል ይችላል?

19 በተለይ ደግሞ ባለትዳር የሆኑ ሰዎችን ከማሽኮርመም መቆጠብ በጣም አስፈላጊ ነው። ባለትዳር ለሆነ ሰው ፍቅራዊ ስሜት ማሳየት ተገቢ አይደለም። በተመሳሳይም ባለትዳር የሆኑ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸው ላልሆነ ሰው እንዲህ ያለ ፍቅራዊ ስሜት ማሳየት የለባቸውም። የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህ ምንም ስሕተት እንደሌለበት ይሰማቸዋል። አንዳንዶች የግል ምስጢራቸውን ከትዳር ጓደኛቸው በመደበቅ እንዲህ ላለ “ጓደኛቸው” እስከመንገር ይደርሳሉ። በዚህም ሳቢያ የሚፈጠረው ቅርርብ ስሜታቸውንና ችግራቸውን የሚረዳላቸው ይህ ሰው ብቻ እንደሆነ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ይህ ደግሞ ትዳርን ሊያናጋና አልፎ ተርፎም ሊያፈርስ ይችላል። ትዳር ያላቸው ክርስቲያኖች ኢየሱስ አንድ ሰው መጀመሪያ የሚያመነዝረው በልቡ እንደሆነ በመግለጽ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 5:28) እንግዲያው ልባችንን በመጠበቅ እንዲህ ያለ ውድቀት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ሁኔታዎች እንራቅ።

20. ንጹሕ ሥነ ምግባራችንን እንዴት አድርገን ልንመለከተው ይገባል?

20 በብልግና በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅ ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መልሶ ለማግኘት ከመጣር ይልቅ መጀመሪያውኑ እንዳይጎድፍ መጠንቀቅ እንደሚቀል አስታውስ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ‘ይቅርታው ብዙ’ ስለሆነ ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ከኃጢአታቸው ማንጻት ይችላል። (ኢሳይያስ 55:7) ሆኖም ይሖዋ የጾታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎችን ድርጊታቸው ከሚያስከትልባቸው መዘዝ አይጠብቃቸውም። መዘዙ ለበርካታ ዓመታት አልፎ ተርፎም ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል። (2 ሳሙኤል 12:9-12) ልብህን በመጠበቅ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነህ ለመኖር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። በይሖዋ ፊት ያለህን ንጹሕ የሥነ ምግባር አቋም እንደ ውድ ሀብት አድርገህ ተመልከተው። ይህን አቋምህን ምንም ነገር እንዲያበላሽብህ አትፍቀድ!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ምንድን ነው? በጣም አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

• ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• ከዝሙት መሸሽ ሲባል ምን ነገሮችን ይጨምራል?

• ከማሽኮርመም መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድን መኪና ባግባቡ ማሽከርከር ካልተቻለ በሕይወት ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማስጠንቀቂያዎችን ቸል ማለታችን ምን ሊያስከትልብን ይችላል?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምንጠናናበት ጊዜ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን መጠበቃችን ደስታ ያስገኝልናል፣ አምላክንም ያስከብራል