በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሊሳካላችሁ ይችላል!

ሊሳካላችሁ ይችላል!

“ሁለቱ ሴቶች ልጆቼ ሳላስበው እቅፍ አድርገው ‘እማዬ፣ እንወድሻለን!’ ሲሉኝ በጣም እደሰታለሁ።”—አና፣ በፖላንድ የምትኖር ነጠላ እናት

“ልጆቼ ለማደርግላቸው ነገር ብዙውን ጊዜ አድናቆታቸውን ስለሚገልጹ ደስ ይለኛል። አንዳንድ ጊዜ ትናንሽ ስጦታዎችን ለምሳሌ ሥዕል ስለው ይሰጡኛል። ይህን ስመለከት ልፋቴ በእጥፍ እንደተካሰ ይሰማኛል።”—ማሲሞ፣ በጣሊያን የሚኖር ነጠላ አባት

“ትካዜ ሲገባኝ ከልጆቼ አንዱ አቅፎ ይስመኝና በጣም እንደሚወደኝ ይነግረኛል።”—ያስሚን፣ በደቡብ አፍሪካ የምትኖር አንዲት ነጠላ እናት

እነዚህ አስተያየቶች ንቁ! መጽሔት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ነጠላ ወላጆች መጠይቅ በመላክ ካገኛቸው ምላሾች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ብዙዎቹ ነጠላ ወላጆች (አብዛኞቹ እናቶች ናቸው)፣ የሚያግዛቸው አፍቃሪ የትዳር ጓደኛ ቢኖራቸው ደስ ይላቸው እንደነበረ ገልጸዋል። * ይሁን እንጂ በግልጽ ከተናገሩት ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ካሉበት ሁኔታ ጋር ራሳቸውን አስማምተው መኖር ችለዋል።

እነዚህ ነጠላ ወላጆች ራሳቸውን ከዚህ ከባድ ኃላፊነት ጋር አስማምተው መኖርና ኃላፊነታቸውን በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው? እነዚህ ወላጆች ጠቃሚ ነጥቦችን የጠቀሱ ከመሆኑም ሌላ ስሜታቸውን ሳይሸሽጉ በግልጽ ተናግረዋል፤ ከዚህም ሌላ ኃላፊነታቸውን በተሳካ መንገድ ለመወጣት የረዷቸውን አንዳንድ ቁልፍ መመሪያዎች ገልጸዋል፤ በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ እነዚህን ሐሳቦች እንመለከታለን። አንቺም ነጠላ ወላጅ ከሆንሽ፣ እነዚህ ርዕሶች የተጣለብሽን ከባድ ኃላፊነት በመወጣት ረገድ እንዲሳካልሽ ብቻ ሳይሆን ደስተኛ ሆነሽ ይህን ማድረግ እንድትችይ እንደሚረዱሽ ተስፋ እናደርጋለን። እርግጥ ነው፣ በፍጥነት በሚለዋወጠውና አስተማማኝ ባልሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ኃላፊነትሽን በተሳካ መንገድ መወጣት ከባድ ትግል ይጠይቅብሻል። *

ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ርዕሶች ከታች በቀረቡት ስድስት ነጥቦች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ነጠላ ወላጆች በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ያብራራሉ፦

  1. የሌሎችን ድጋፍ ማግኘት

  2. ከልጆች ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ

  3. ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስቀደም

  4. ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን ማውጣት

  5. ጥሩ የሥነ ምግባር ደንቦችን ለልጆች ማስተማር

  6. በቤተሰብ ውስጥ ለአምላክ ቦታ መስጠት

^ አን.5 በመላው ዓለም አብዛኞቹ ነጠላ ወላጆች ሴቶች ናቸው። በመሆኑም በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ስለ ነጠላ ወላጆች ስንናገር የተጠቀምነው በአንስታይ ፆታ ነው። ይሁንና በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለነጠላ አባቶችም ይሠራሉ።

^ አን.6 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት አብዛኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሁለቱም ወላጆች ላሉባቸው ቤተሰቦችም ሊጠቅሙ ይችላሉ።