በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የዝንቦች ሃልቲር

የዝንቦች ሃልቲር

ዝንቦች በአየር ላይ እንደ ልባቸው ለመገለባበጥና አቅጣጫቸውን ለመቀየር የሚያስችላቸው ምንድን ነው? ኃይለኛ ነፋስ ቢነፍስባቸውም አቅጣጫቸውን ሳይለቁ ጉዟቸውን መቀጠል እንዲችሉ የሚረዳቸው ምንድን ነው? ለዚህ በተወሰነ መጠን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ከሁለቱም ክንፎቻቸው ጀርባ የሚገኙት ሃልቲር የሚባሉ ትናንሽ የአካላቸው ክፍሎች ናቸው። *

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ሃልቲር እንደ ክብሪት እንጨት ከታቹ ቀጭን ሆኖ ጫፉ አካባቢ ወፈር ይላል። ዝንቦች በሚበርሩበት ጊዜ ሃልቲሮቻቸው ከክንፎቻቸው ጋር እኩል በሆነ ፍጥነት ሆኖም በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ላይና ወደ ታች ይርገበገባሉ። የሳይንስ ሊቃውንት፣ ዝንቦች በሚበርሩበት ጊዜ ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ የሚረዷቸው ሃልቲሮቻቸው እንደሆኑ ማወቅ ችለዋል።

ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ አዳፕቴሽንስ ኢን ዘ ናቹራል ወርልድ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ወፈር ያለው የሃልቲሮች ጫፍ “እንደ ሰዓት ፔንዱለም በአንድ የተወሰነ አቅጣጫ ብቻ ይንቀሳቀሳል።” ኢንሳይክሎፒዲያው እንደገለጸው አንድ ዝንብ በሚበርበት ጊዜ ፈልጎም ይሁን ነፋስ ሲነፍስበት ድንገት ቢገለበጥ “ሃልቲሩም ተጠምዝዞ አቅጣጫውን ይቀይራል። በሃልቲሩ ላይ የሚገኙት በርካታ ነርቮች የሃልቲሩን እንቅስቃሴ ወደ አንጎል ያስተላልፋሉ፤ በዚህ ወቅት ዝንቡ . . . አቅጣጫውን እንዳይስት የሚያስችለውን እርምጃ ይወስዳል።” በዚህ ምክንያት ዝንቦች በሚበሩበት ጊዜ እንደ ልባቸው መገለባበጥ የሚችሉ ከመሆኑም ሌላ በቀላሉ አይያዙም።

መሐንዲሶች ከሮቦቶችና ከመንኮራኩሮች እንዲሁም የነፍሳትን የበረራ ዘዴ በመኮረጅ ከሚሠሩ ሮቦቶች ጋር በተያያዘ የሃልቲርን አሠራር በብዙ መንገዶች ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ይሰማቸዋል። የበረራ ቴክኖሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ራፋል ዝቢኮቭስኪ “እንደ ዝንብ ካለች ትንሽና ብዙም የማትስብ ፍጥረት ይህ ሁሉ ትምህርት ይገኛል ብሎ ማን ያስባል?” ሲሉ ጽፈዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የዝንብ ሃልቲር በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

^ አን.3 ሃልቲር እንደ ዝንብና ቢንቢ ባሉት ባለ ሁለት ክንፍ ነፍሳት ክንፍ ላይ ተቀጥሎ የሚገኝ ነገር ነው።