በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን አስቀድሙ

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን አስቀድሙ

“ሰውነቴ ሁልጊዜ በድካም ይዝል ነበር፤ ሥራን፣ ልጅ ማሳደግን፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን እንዲሁም የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወንና ለእረፍት የሚሆን ጊዜ ማግኘት ያስቸግረኝ ነበር።”—ዮኮ፣ ጃፓን

ተፈታታኝ ሁኔታ፦

የሁለት ወንዶች ልጆች እናት የሆነችው ሚራንዳ እንዲህ ብላለች፦ “የሚያግዘኝ የትዳር ጓደኛ ሳይኖር ሁሉንም ነገር ማሟላት የሚጠበቅብኝ መሆኑ ከምንም በላይ ተፈታታኝ ነው፤ ሰብዓዊ ሥራ እየሠሩ የቤተሰቡን ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላትና አስፈላጊውን ሥልጠና መስጠት ይከብዳል።”

የመፍትሔ ሐሳቦች፦

ለእናንተም ሆነ ለልጆቻችሁ ይበልጥ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለይታችሁ እወቁ፤ ከዚያም ለእነዚህ ነገሮች ቅድሚያ ስጧቸው።

ሌሎች ነገሮች፣ ቅድሚያ ልትሰጧቸው የሚገቡ ነገሮችን ቦታ እንዲይዙባችሁ አትፍቀዱ፤ እንዲሁም ጊዜያችሁንና ገንዘባችሁን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ማብቃቃትን ተማሩ። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ የልጆቻችሁ ጤንነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው፤ በመሆኑም ለፍታችሁ ያገኛችሁትን ገንዘብ ሰውነትን የሚገነባ ምግብ ለመግዛት አውሉት። እንዲህ ማድረግ ለሕክምና ሲባል አላስፈላጊ ወጪዎች ከማውጣት ይጠብቃችኋል። ገበያ ከመሄዳችሁ በፊት የምትገዟቸውን ነገሮች በዝርዝር መዝግቡ። ይህም አንድን ነገር ስለወደዳችሁት ብቻ ሳታስቡበት በመግዛት ገንዘብ ከማባከን ይጠብቃችኋል። ከአራት ልጆቹ ጋር በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ሮቤርቶ “ምግብ ማዘጋጀት እወዳለሁ” ይላል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ለምንፈልጋቸው ነገሮች ሳይሆን በእርግጥ ለሚያስፈልጉን ነገሮች ትኩረት መስጠትን ተምሬያለሁ፤ ከሚያስፈልጉን ነገሮችም እንኳ ለእያንዳንዱ ቀን ይበልጥ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እለያለሁ።”

ለፍታችሁ ያገኛችሁትን ገንዘብ ሰውነትን የሚገነባ ምግብ ለመግዛት አውሉት። እንዲህ ማድረግ ለሕክምና ሲባል አላስፈላጊ ወጪዎች ከማውጣት ይጠብቃችኋል

የማትጠቀሙባቸውን መጻሕፍት፣ ልብሶችና ዕቃዎች አስወግዱ። አንዲት ነጠላ እናት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ኮተት ማብዛት ውጥረት ማብዛት ነው። ብዙ ዕቃ ካላችሁ ይህንን ማጽዳት፣ መጠገንና መንከባከብ ሥራ ይጨምርባችኋል። ኑሯችሁን ለማቅለል መፍትሔው ያሏችሁን ዕቃዎች መቀነስ ነው።”

ልጆቻችሁ ሁልጊዜ ማታ ማታ ዕቃዎቻቸውን በቦታቸው እንዲያስቀምጡ አሠልጥኗቸው። ቤታችሁ እንዳይዝረከረክ ጥረት አድርጉ። እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ልጆቻችሁ ክፍላቸውን አልፎ ተርፎም አጠቃላይ ቤቱን የማስተካከል ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። እናንተ ጥሩ ምሳሌ መሆናችሁ ልጆቻችሁ በዚህ ረገድ ታዛዦች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።

ሥራ በጣም ቢበዛባችሁም ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ ማሳለፍ አለባችሁ፤ ጥቂት ቢሆንም ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እስከተቻለ ድረስ ይህ በቂ ነው የሚለው አመለካከት ትክክል አይደለም። ከልጆቻችሁ ጋር የቻላችሁትን ያህል ሰፊ ጊዜ ማሳለፍ አለባችሁ። ልጆቻችሁ የእናንተን ጊዜና ትኩረት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።—ዘዳግም 6:7

ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ አብራችሁ ተመገቡ፤ እንዲሁም ይህን ጊዜ አስደሳች አድርጉት። የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ኮሌት እንዲህ ትላለች፦ “ማታ ላይ ሁላችንም ተሰባስበን አንድ ላይ ለመመገብ የወሰንን ሲሆን በዚህ ወቅት ስሜታችንን አውጥተን እንነጋገራለን፤ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንወያያለን። ይህ የምግብ ሰዓት በቤተሰባችን ውስጥ እስከዛሬም ድረስ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል።”