የመካከለኛው ዘመን የሜካኒክስ ሊቃውንት
በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚከናወኑ ተደጋጋሚ ሥራዎችን የሚሠሩት ያለ ሰው እገዛ የሚንቀሳቀሱ ማሽኖች ናቸው። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ዓይነት ማሽኖች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠሩት መቼ ነው? የአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮት በጀመረበት ወቅት ይኸውም ከጥቂት መቶ ዓመታት በፊት ነው? አውቶማቲክ ማሽኖች የተፈለሰፉት ይህ ከመሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት መሆኑን ስታውቅ ትገረም ይሆናል።
የእስላማዊ ሳይንስ ወርቃማ ዘመን በሚባለው ከ8ኛው እስከ 13ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ገደማ ባለው ጊዜ መባቻ አካባቢ የመካከለኛው ምሥራቅ ምሁራን፣ የሳይንስና የፍልስፍና ጽሑፎችን ወደ አረብኛ ተርጉመዋል፤ በዚህ መንገድ እንደ አርክሚዲስ፣ አርስቶትል፣ ቴሲቢየስ፣ የእስክንድርያው ሄሮ እና የባይዛንትየሙ ፊሎ የመሳሰሉት እውቅ ግሪካውያን ሥራዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ አድርገዋል። * ከስፔን አንስቶ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ አቋርጦ እስከ አፍጋኒስታን የሚደርሰው እስላማዊ ግዛት ምሁራን፣ እነዚህንና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን በማግኘታቸው አውቶማቲክ ማሽኖችን ለመሥራት የሚያስችል እውቀት ሊኖራቸው ችሏል።
የቴክኖሎጂ ታሪክ ምሁር የሆኑት ዶናልድ ሂል እንደተናገሩት እነዚህ ማሽኖች “ለበርካታ ሰዓታት፣ ቀናትና ከዚያም ለሚበልጥ ጊዜ የሰው እገዛ ሳያስፈልጋቸው መሥራት ይችሉ ነበር።” ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? መሐንዲሶቹ፣ ማሽኖቹ ያለሰው እገዛ ራሳቸውን ለማንቀሳቀስ የሚያስችሏቸው የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች ፈልስፈው ነበር። ማሽኖቹ ከፍ ተደርገው በተሠሩ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ያለ ውኃን በመጠቀም የማያቋርጥ የኃይል ምንጭ ያገኙ ነበር። እንዲሁም ማሽኖቹ እየተከፈተና እየተዘጋ ውኃ እንዲገባ ወይም እንዲቆም አሊያም የፍሰቱን አቅጣጫ እንዲቀይር የሚያደርግ አውቶማቲክ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ ከመሆኑም ሌላ የተቀመጠላቸውን ልክ እንዳያልፉ የሚያደርግ ሥርዓት ነበራቸው። ከዚህም ሌላ ማሽኖቹ የሆነ እክል ቢያጋጥማቸው የከፋ ብልሽት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል የሚያስችል ዘዴ ነበራቸው፤ ይህ ዘዴ በዛሬው ጊዜ ላሉት ተመሳሳይ መሣሪያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ዶናልድ ሂል ተናግረዋል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት፦
ጥበበኞቹ የሙሳ ልጆች
ሦስቱ የሙሳ ልጆች (በአረብኛ ባኑ ሙሳ) በዘጠነኛው መቶ ዘመን በባግዳድ ይኖሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች፣ ከእነሱ ቀድመው የነበሩትን ፊሎና ሄሮ የተባሉ ግሪካውያን ሥራዎች እንዲሁም የሕንድ፣ የቻይናና የፋርስ መሐንዲሶችን ሥራዎች በማጥናት ከ100 የሚበልጡ መሣሪያዎችን ፈልስፈዋል። አክሳን ማስኡድ የተባሉት የሳይንስ ጸሐፊ እንደሚሉት የሙሳ ልጆች ከሠሯቸው ንድፎች መካከል የሚፈሱበትን መንገድ በየተወሰነ ጊዜ የሚቀያይሩ ፏፏቴዎች (ፋውንቴን) እንዲሁም አስገራሚ የሆኑ ሰዓቶች ይገኙበታል። ከዚህም ሌላ የሚጠጣ ውኃ የሚቀዱና ራሳቸውን በራሳቸው የሚሞሉ አውቶማቲክ ዕቃዎች ንድፍ ሠርተዋል፤ እነዚህ ዕቃዎች ይህን የሚያደርጉት ወደ ውስጥ የሚገባውን ፈሳሽ መጠን የሚቆጣጠሩ ተንሳፋፊዎችና ቫልቮች እንዲሁም በስበትና በግፊት አማካኝነት ፈሳሽ ነገሮች ወደ ላይ እንዲወጡ የሚያደርግ ቱቦ (ሳይፈን) አጣምረው በመጠቀም ነበር። ጂም አል ካሊሊ የተባሉት የታሪክ ምሁር እንደተናገሩት የሙሳ ልጆች ሻይ የምትቀዳ ሰው የምታክል አሻንጉሊት እንዲሁም የዋሽንት ተጫዋች ሞዴል ሠርተዋል፤ ይህ የዋሽንት ተጫዋች ሞዴል “በተቀመጠለት ፕሮግራም መሠረት የሚሠራ የመጀመሪያው ማሽን ሳይሆን አይቀርም።”
እነዚህ አውቶማቲክ መሣሪያዎች ከዘመናዊዎቹ ማሽኖች ጋር የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር አለ። ይሁን እንጂ አክሳን ማስኡድ የተባሉት የሳይንስ ጸሐፊ እንደገለጹት የጥንቶቹ መሣሪያዎች “የሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይሆን የውኃ ግፊት ነበር፤ የአሠራራቸው ሥርዓት ግን በአብዛኛው [ከዘመናዊዎቹ ማሽኖች ጋር] ተመሳሳይ ነው።”
አል ጀዛሪ—“የሮቦት ቴክኖሎጂ አባት”
ኢብን አል ራዛዝ አል ጀዛሪ፣ በሜካኒካል ጥበብ ንድፈ ሐሳብና አጠቃቀም ዙሪያ ያዘጋጀውን ጽሑፍ (አንዳንድ ጊዜ ኮምፔንዲየም ኦን ዘ ቲዎሪ ኤንድ ፕራክቲስ ኦቭ ዘ ሜካኒካል አርትስ ተብሎ ይተረጎማል) በ1206 አጠናቀቀ። ይህ ጽሑፍ “የማሽኖች ንድፍ ጥናት” ተብሎ ተጠርቷል። ከአል ጀዛሪ ቴክኖሎጂዎች አንዳንዶቹ የሙሳ ልጆች ካዘጋጇቸው ንድፎች ይበልጥ የተራቀቁ ከመሆናቸውም በላይ መግለጫዎቹና ሥዕሎቹ ዝርዝር ሐሳብ የያዙ በመሆናቸው ዘመናዊ መሐንዲሶች እነዚህን መሠረት በማድረግ መሣሪያዎቹን ዳግመኛ ሊሠሯቸው ይችላሉ።
የአል ጀዛሪ መጽሐፍ፣ ውኃ ወደ ላይ እንዲወጣ የሚያደርጉ መሣሪያዎችን፣ የውኃ ሰዓቶችን፣ የሻማ ሰዓቶችን፣ ውኃ የሚቀዱ መሣሪያዎችንና ሙዚቃ የሚጫወቱ አውቶማቲክ መሣሪያዎችን ሥዕል የያዘ ነው። ከዚህም ሌላ በውኃ ኃይል የሚሠሩ ሽክርክሪቶች በክብ ቅርጽ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ወደ ፊትና ወደ ኋላ የሚሄድን ነገር (ፒስተን) እንዲያንቀሳቅስ የሚያደርግ ፓምፕ ንድፍ በመጽሐፉ ላይ ይገኛል፤ ይህ ፓምፕ ውኃው በከፍተኛ ግፊት እንዲወነጨፍ ለማድረግ ያስችላል። በፈሳሽ አማካኝነት የሚሠሩ (ሃይድሮሊክ) ፓምፖች መሠረታዊ ንድፍ በምዕራቡ ዓለም ከመታየቱ ከሦስት መቶ ዓመት በፊት አል ጀዛሪ የዚህ ዓይነት ንድፍ እንደሠራ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።
በተጨማሪም አል ጀዛሪ አስገራሚ ሆኖም ጠቃሚ የሆኑ ሰዓቶች ሠርቷል። ከላይ የሚታየው የዝሆን ሰዓት በዱባይ በሚገኝ አንድ የገበያ ማዕከል እንደ አዲስ ተሠርቷል። በዝሆኑ ሆድ ውስጥ በሚገኝ ውኃ ማጠራቀሚያ ውስጥ የተቀመጠው ጎድጓዳ ሳህን ሰዓት ለመቁጠር ያስችላል። ሳህኑ ቀዳዳ ያለው ሲሆን በ30 ደቂቃ ውስጥ በውኃ ይሞላና ወደ ታች ይሰምጣል፤ በዚህ ጊዜ ገመዶቹንና ኳሶቹን ጨምሮ በዝሆኑ ጀርባ ላይ ያሉት የተለያዩ ነገሮች እንቅስቃሴ ይጀምራሉ። በዚህ ሂደት አማካኝነት ሳህኑ በገመድ ተስቦ በመውጣት ውኃው ላይ ስለሚንሳፈፍ ሂደቱ እንደ አዲስ ይጀምራል። ይህ መሣሪያና አል ጀዛሪ እንደሠራቸው የሚነገሩ ሌሎች አውቶማቲክ ማሽኖች ይህ ምሁር “የሮቦት ቴክኖሎጂ አባት” የሚል ስያሜ እንዲሰጠው አድርገዋል።
በእርግጥም የሰው ልጅ ስላለው የፈጠራ ችሎታ የሚያወሳው ታሪክ በጣም የሚያስደንቅ ነው! ይሁን እንጂ ይህን ታሪክ ማወቃችን የሚያስተምረን ነገርም አለ። በተለየ መንገድ እንድናስብ ይረዳናል። ብዙዎች በዘመናችን ባለው የቴክኖሎጂ እድገት በሚኩራሩበት በዚህ ወቅት ይህን ታሪክ ማወቃችን ቀደም ባሉት ዘመናት የኖሩት ብሩህ አእምሮ ያላቸው ምሁራን ምን ያህል ባለውለታዎቻችን እንደሆኑ እንድናስታውስ ያደርገናል።
^ አን.3 የአረብ ምሁራን ስላካሄዱት የትርጉም ሥራ ለማወቅ በየካቲት 2012 ንቁ! ላይ የወጣውን “አረብኛ የምሁራን ቋንቋ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
Pump: © Gianni Dagli Orti/The Art Archive at Art Resource, NY; clock: © The Metropolitan Museum of Art/Art Resource, NY