በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ውጥረትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ውጥረትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ውጥረት አለብህ?

  • በውጥረት ልፈነዳ ነው

  • ከዚህ በላይ መሸከም አልችልም

  • ያን ያህል አልተወጠርኩም

  • ውጥረት የሚባል ነገር አያውቀኝም

ውጥረትን መቋቋም ከባድ ጭነት ከማጓጓዝ ጋር ይመሳሰላል። አንድ ትልቅ የጭነት መኪና እንዲህ ያለውን ጭነት ለረጅም ርቀት በቀላሉ ሊያጓጉዘው ይችላል። ለአንዲት ትንሽ መኪና ግን እንዲህ ያለውን ጭነት ለአጭር ርቀት እንኳ መጎተት ሞተሯን ይጎዳዋል። አንተም ውጥረት የሚበዛብህ ከሆነ “ሞተርህ” ማለትም ሰውነትህ ተመሳሳይ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል።

ይህ ሲባል ታዲያ ያለህበትን ሁኔታ ለማስተካከል ምንም ማድረግ አይቻልም ማለት ነው? በጭራሽ! ውጥረት ከአቅምህ በላይ ሆኖ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስብህ፣ ወይ ያለብህን ጭነት መቀነስ አሊያም የበለጠ ኃይል ያለው “ሞተር” ማግኘት ያስፈልግሃል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱንም እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሸክምህን አቅልል

ተፈታታኝ ሁኔታ፦ የተጣበበ ፕሮግራም

“የግድ መሥራት ያለብኝ ነገር እያለ አንድ ሰው እንዳግዘው ወይም በአንድ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንድካፈል ይጠይቀኛል። እኔ ደግሞ ማንንም እምቢ ብዬ ማስቀየም አልፈልግም።”—ካሪና *

መፍትሔ፦ ‘አልችልም’ ማለትን ተማር።

መጽሐፍ ቅዱስ “በትሑት ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። (ምሳሌ 11:2) ትሑት መሆን ወይም አቅምህን ማወቅ፣ ያለብህ ጭነት ከምትችለው በላይ እንደሚሆንብህ ሲሰማህ ‘አልችልም’ ማለት እንድትችል ኃይል ይሰጥሃል።

እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረግ የምትችለው ሁልጊዜ አይደለም፤ ለምሳሌ ወላጆችህ የቤት ውስጥ ሥራዎችህን እንድታጠናቅቅ በሚያዙህ ጊዜ ‘አልችልም’ ማለት ተገቢ አይሆንም። ይሁን እንጂ ሁሉንም ሰው ‘እሺ’ በማለት በራስህ ላይ ጭነት የምታበዛ ከሆነ ውሎ አድሮ ነገሮች ከአቅምህ በላይ ይሆናሉ። ትላልቅ የጭነት መኪኖችም እንኳ የጭነት ገደብ አላቸው።

ጠቃሚ ምክር፦ አንድን ሰው በቀጥታ ‘አልችልም’ ማለት የሚከብድህ ከሆነ ‘አስቤበት ልንገርህ’ ማለት ትችላለህ። ከዚያም ቁርጥ ያለ ምላሽ ከመስጠትህ በፊት ‘በእርግጥ ለዚህ ሥራ የሚሆን ጊዜና ጉልበት አለኝ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ተፈታታኝ ሁኔታ፦ ዛሬ ነገ ማለት

“አንድ ሥራ ከባድ መስሎ ከታየኝ ለሌላ ጊዜ አቆየዋለሁ። ከዚያ ግን ይህን ሥራ መሥራት እንዳለብኝ እያሰብኩ መጨነቄ አይቀርም። በመጨረሻ ሥራውን ስጀምረው የሚኖረኝ ጊዜ አጭር ስለሚሆን በጥድፊያ መሥራት ይኖርብኛል፤ ይህ ደግሞ ውጥረት ይፈጥርብኛል።”—ዜሪና

መፍትሔ፦ ሥራውን በአንዴ ልትጨርሰው ባትችልም እንኳ ጀምረው።

መጽሐፍ ቅዱስ “በሥራችሁ አትለግሙ” በማለት ይመክራል። (ሮም 12:11) አንድን ከባድ ሥራ ማከናወን በራሱ ጫና ይፈጥራል፤ ታዲያ ዛሬ ነገ በማለት ለምን በራስህ ላይ የበለጠ ሸክም ትጨምራለህ? ሥራውን ማከናወንህ ላይቀርልህ ዛሬ ነገ ማለትህ ጊዜ ከማራዘም ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም!

አንድ ሥራ ለማከናወን እንድትነሳሳ የምትሠራቸውን ነገሮች በዝርዝር ጻፍ። ከበድ ያሉ ሥራዎችን ከፋፍላቸው። ካሮል የምትባል አንዲት ወጣት “ዝርዝር ማውጣት እወዳለሁ” በማለት ትናገራለች። “አብዛኛውን ጊዜ መጀመሪያ ላይ የምጽፈው በጣም የምጠላቸውን ሥራዎች ነው፤ እነዚህን አከናውኜ ስጨርስ የቀረው ሥራ ቀላል ይሆንልኛል። እንዲህ ስታደርጉ የማትወዱት ሥራ ሳይታወቃችሁ ስለሚያልቅ ይበልጥ የምትወዷቸውን ነገሮች ለማከናወን ጊዜ ታገኛላችሁ!”

ጠቃሚ ምክር፦ አንድን ሥራ ለመጀመር የሚያታግልህ ከሆነ ሰዓትህን ለ10 ወይም ለ15 ደቂቃ ሙላና ወዲያውኑ ሥራውን ጀምረው። ሰዓትህ፣ የሞላኸው ደቂቃ ማብቃቱን ሲጠቁምህ 10 ወይም 15 ደቂቃ የሚፈጅ ሥራ አከናውነሃል ማለት ነው። ሥራውን አንዴ ከጀመርከው በኋላ ደግሞ መቀጠሉ ያን ያህል ከባድ ላይሆንብህ ይችላል።

ዕቃዎችህን በሥርዓት አስቀምጥ። ይህ ካልሆነ ከተዝረከረኩ ዕቃዎች መሃል ንጹሕ ልብሶችን ወይም ደብተርህን ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ውጥረት ይጨምርብሃል። ጠዋት ላይ ሊያጋጥም የሚችለውን ወከባና ጥድፊያ ለመቀነስ ከመተኛትህ በፊት ዕቃዎችህን ለመሰታተር አምስት ደቂቃ መድብ

የበለጠ ኃይል ያለው “ሞተር” ይኑርህ

ሰውነትህን ተንከባከብ።

ጤናማ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ ብዙ ማከናወን እንድትችል ኃይል እንደሚሰጡህ ባለሙያዎች ይስማማሉ። * ሰውነትህን መንከባከብ ደግሞ ያን ያህል ከባድ አይደለም። ቀላል የሆኑ አንዳንድ እርምጃዎችን በመወሰድ መጀመር ትችላለህ። እንቅልፍን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እስቲ ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

  1. በቂ እንቅልፍ ተኛ። ቢያንስ በትምህርትና በሥራ ቀናት፣ ቋሚ በሆነ ሰዓት ለመተኛትና ለመነሳት ሞክር።

  2. ከመተኛትህ በፊት በሰውነትህ ላይ ጫና የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን ቀንስ። ወደ መኝታ ከመሄድህ በፊት ባሉት ሦስት ሰዓቶች ውስጥ አካላዊ እንቅስቃሴ አታድርግ፤ እንዲሁም የምትተኛበት ጊዜ እየቀረበ ሲሄድ ከበድ ያሉ ምግቦችንና ካፌይን ያለባቸው መጠጦችን ከመወሰድ ተቆጠብ።

  3. ልትተኛ ስትል የመኝታ ክፍልህ ጨለምለም እንዲል እንዲሁም ጸጥ ያለና ምቹ እንዲሆን አድርግ።

የሌሎችን ድጋፍ ጠይቅ።

የወላጆችህንና የጓደኞችህን እርዳታ ለመጠየቅ አታመንታ። እንዲህ ማድረግህ ጠቃሚ ነው? አዎን፣ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የሌሎችን ድጋፍ ማግኘት ከውጥረት መጨመር ጋር በተያያዘ በልብህ፣ በደም ሥሮችህና በሽታን በመከላከል አቅምህ ላይ የሚመጡ ጉዳቶችን ይቀንሳል።

እነዚህ ጥናቶች “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። (ምሳሌ 12:25) ልብህ በጭንቀት ሲወጠር እውነተኛ ወዳጆች “መልካም ቃል” በመናገር ሊያበረታቱህ ይችላሉ፤ በዚያ ወቅት የሚያስፈልግህም እንዲህ ያለ ድጋፍ ነው።

ውጥረትን ለመቋቋም ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልግሃል? ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች ከተሰኘው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ጥራዝ 1 (እንግሊዝኛ) እና 2 ላይ የሚከተሉትን ምዕራፎች ተመልከት።

ጥራዝ 1

ጥራዝ 2

 

^ አን.12 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.24 አመጋገብንና አካላዊ እንቅስቃሴን በሚመለከት ጠቃሚ ምክር ለማግኘት የሰኔ 2010 ንቁ! ከገጽ 12-14 እንዲሁም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተመልከት።

^ አን.33 እነዚህን ርዕሶች በመስከረም 2008 ንቁ! ከገጽ 26-28 እና በሰኔ 2009 ንቁ! ከገጽ 19-21 ላይም ማግኘት ይቻላል።

ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?

በሕይወታችሁ ውስጥ ምን ዓይነት ውጥረት ያጋጥማችኋል? ውጥረትን ለመቋቋም በጣም ውጤታማ ሆነው ያገኛችኋቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው?