በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን እርዳታ ጠይቁ

የአምላክን እርዳታ ጠይቁ

“ባለቤቴ እኔንና ልጆቼን ጥሎን በሄደበት ወቅት አምላክ እንዲረዳን ተማጸንኩት። እሱም ጸሎቴን መልሶልኛል። ከሚያስፈልገን ነገር አንዳች አጥተን አናውቅም። የእሱ እርዳታና መመሪያ ተለይቶን አያውቅም።”—ማኪ፣ ጃፓን

ሰዎች ለቁሳዊ ነገሮች የሚሰጡት ትኩረት እየጨመረ በሄደበት በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙዎች ለአምላክ ቦታ አይሰጡም። ያም ቢሆን ፈጣሪያችን ስለ እኛ የሚያስብ ሲሆን በሕይወታችን ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። በኢሳይያስ 41:10 ላይ አምላክ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ . . . እረዳሃለሁ” በማለት ለእኛ ያለውን ስሜት ጥሩ አድርጎ ገልጿል።

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ጠቃሚ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አማካኝነት እንዴት እንደሚረዳን ተመልክተናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ብቻ የያዘ መጽሐፍ አይደለም። የአምላክን ግሩም ባሕርያትና ለእኛ ያለውን ፍቅር ይገልጽልናል። በመሆኑም ነጠላም ሆኑ ባለትዳር የሆኑ ብዙ ክርስቲያን ወላጆች እንደተገነዘቡት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ተግባራዊ ስናደርግ የአምላክን ጥሩነት በሕይወታችን መመልከት እንችላለን።

ሮቤርት፣ ኦስትሪያ፦ “ይሖዋ አምላክ ከማናችንም የተሻለ አባት ወይም እናት ነው። ልጆቻችን ምን እንደሚያስፈልጋቸው ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚጠብቃቸውም ያውቃል። ስለዚህ ከሴት ልጄ ጋር ብዙ ጊዜ ወደ እሱ እጸልያለሁ።”

አዩሳ፣ ጃፓን፦ “ልጄ ይሖዋ በሚሰጠን ድጋፍ በመተማመን ‘ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለሆነ ሁሉም ነገር ደህና ይሆናል’ ብሎ ሲናገር ልቤ በሐሴት ይሞላል።”

ክርስቲና፣ ጣሊያን፦ “ልፈታው የማልችል ችግር ሲያጋጥመኝ ወደ ይሖዋ እጸልይና ጉዳዩን ለእሱ እተወዋለሁ። ይህን ካደረግሁ በኋላ ችግሩ ከሁሉ በተሻለ መንገድ መፍትሔ እንደሚያገኝ ስለማውቅ ወዲያው ውስጣዊ ሰላም ይሰማኛል።”

ሎራንቲን፣ ፈረንሳይ፦ “ነጠላ ወላጅ ብሆንም ይሖዋ እንደባረከኝ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይሖዋ ለተቸገሩትና አባት ወይም እናት ለሌላቸው እንደሚደርስላቸው ማረጋገጥ ችያለሁ።”

ኬኮ፣ ጃፓን፦ “አምላክ አያዳላም። ሁለቱም ወላጆች ላሉባቸውም ሆነ በአንድ ወላጅ ለሚተዳደሩ ቤተሰቦች ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያል።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34

አምላክ ለእኛ ያለውን ርኅራኄና አሳቢነት የሚያንጸባርቀው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። . . . እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” (ማቴዎስ 11:28-30) ኢየሱስና በሰማይ ያለው አባቱ ይሖዋ አምላክ፣ በእነሱ እንክብካቤ ሥር ስንሆን ደኅንነት እንዲሰማን እንደሚፈልጉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መዝሙር 34:8 “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” ይላል። በእርግጥም አምላክ፣ እሱ የሚሰጣችሁ ምክር ጠቃሚ እንደሆነና ለእናንተ የሚበጀውን እንደሚያስብላችሁ በራሳችሁ ሕይወት እንድትመለከቱ ይፈልጋል። ታዲያ እንደ አባት ሆኖ ያቀረበላችሁን ግብዣ ትቀበላላችሁ?