በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን አውጡ

ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን አውጡ

“ልጆችን ለብቻ ማሳደግ ቀላል አይደለም፤ በተለይ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በሚሆኑበትና ሌሎች ወጣቶች ሲያደርጉ እንደሚያዩት እነሱም በወላጆቻቸው ላይ ማመፅ በሚጀምሩበት ወቅት ይህ ይበልጥ ከባድ ይሆናል።”—ደልሲ፣ ደቡብ አፍሪካ

ተፈታታኝ ሁኔታ፦

መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” አብዛኞቹ ልጆች “ለወላጆች የማይታዘዙ” እንደሚሆኑ ተንብዮአል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2

የመፍትሔ ሐሳቦች፦

“ልጆች ጥሩ አስተዳደግ እንዲኖራቸው መመሪያ ሊወጣላቸውና ከእነሱ ምን እንደሚጠበቅ ሊያውቁ” እንደሚገባ አስታውሱ። (ዘ ሲንግል ፓረንት ሪሶርስ፣ በብሩክ ኖኤል) የልጆችና የቤተሰብ ሥነ ልቦና ምሁር የሆኑት ባሪ ጊንዝበርግ እንደተናገሩት “በግልጽ የተቀመጡ መመሪያዎች ካሉ በቤተሰብ አባላት መካከል ያለው ግንኙነት የተሻለና ውጥረት የሌለበት ይሆናል።” አክለውም “የምናወጣቸው መመሪያዎች ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ከተቀመጡ ቤተሰቡ ይበልጥ ደስተኛ ይሆናል” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ የምታወጧቸው መመሪያዎች ግልጽ እንዲሆኑ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

ጥብቅ ሁኑ፤ እንዲሁም ቃላችሁን ጠብቁ። (ማቴዎስ 5:37) በአውስትራሊያ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ልጆች ብዙውን ጊዜ የሚቀብጡት ወላጆች አንዳንድ ነገሮችን መከልከል የሚያቅታቸውና ልጆቻቸው የፈለጉትን እንዲያደርጉ የሚፈቅዱላቸው ከሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “መረን የተለቀቀ ልጅ . . . እናቱን ያሳፍራል።”—ምሳሌ 29:15

ልጆቻችሁ በነጠላ ወላጅ በማደጋቸው የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷችሁ ልታቀብጧቸው አይገባም። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ያስሚን “ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን የማሳድጋቸው ያለ አባት በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ያሳዝኑኛል” በማለት ትናገራለች። እንዲህ የሚሰማት መሆኑ ስህተት ባይሆንም ይህ ስሜት የማመዛዘን ችሎታዋን እንዲጋርድባት አልፈቀደችም።

የማይለዋወጥ አቋም ይኑራችሁ። አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ኦርቶሳይኪያትሪ እንደሚለው ‘ልጆች፣ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መፈጸም ምንጊዜም ተግሣጽ እንደሚያስከትል አስቀድመው ማወቃቸው አስቸጋሪ ባሕርይ እንዳያዳብሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።’ ያስሚን እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “ከልጆቼ ጋር ቁጭ ብለን ስለሚሰጣቸው ተግሣጽ ተወያይተናል። ጥፋት ሲሠሩ በተነጋገርነው መሠረት ሁልጊዜ ተግሣጽ ለመስጠት ጥረት አደርጋለሁ። ያም ቢሆን መጀመሪያ እነሱ የሚሉትን አዳምጣለሁ፤ ከዚያም የፈጸሙት ድርጊት ቤተሰቡን እንዴት እንደጎዳው በእርጋታ አስረዳቸዋለሁ። ቀደም ብሎ የተወሰነውን ቅጣት የምሰጣቸው ይህን ካደረግሁ በኋላ ነው።”

ምክንያታዊ ሁኑ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ተግሣጽ አትስጡ። ትክክለኛ የሆነው ነገር እንዲፈጸም ለማድረግ ጥብቅ መሆን ቢያስፈልግም እንደየሁኔታው ማስተካከያ ማድረግ ሊኖርባችሁ ይችላል። ያዕቆብ 3:17 “ከላይ [ከአምላክ] የሆነው ጥበብ . . . ምክንያታዊ” እንደሆነ ይናገራል። ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች በችኮላ ወይም በንዴት ገንፍለው እያለ እርምጃ አይወስዱም። ወይም ደግሞ ‘ቃል ቃል ነው’ በሚል ብቻ ሳያመዛዝኑ አንድ ነገር አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ መጀመሪያ ስለ ጉዳዩ ያስቡበታል ምናልባትም ይጸልዩበታል፤ ከዚያም ይበልጥ ተረጋግተው ተገቢ የሆነውን እርምጃ ይወስዳሉ።

የማይለዋወጥ አቋም መያዝ እንዲሁም ጥብቅና ምክንያታዊ መሆን ከእናንተ ጥሩ ምሳሌነት ጋር ተዳምረው ግልጽ መመሪያዎችን እንድታወጡ ያስችሏችኋል፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ደግሞ ልጆቻችሁ በቤት ውስጥ የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።