በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሉን​—አስገራሚ ድምፅ ያለው ወፍ

ሉን​—አስገራሚ ድምፅ ያለው ወፍ

ጆሮ ጭው የሚያደርገው የሉን ጩኸት በቀላሉ ከአእምሮ አይጠፋም። * ይህ ወፍ የሚገኘው በካናዳ፣ በአውሮፓና በሰሜናዊ ዩናይትድ ስቴትስ ርቀው ባሉ ሐይቆችና ወንዞች አቅራቢያ ሲሆን ኮሽታ በማይሰማባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ድምፁ ከርቀት ያስተጋባል።

በውኃ አካላት አካባቢ የሚኖረው ይህ ውብ የወፍ ዝርያ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኒሶታ ግዛት መለያ ምልክት ነው፤ ሉኒ በተባለው የካናዳ ባለ አንድ ዶላር ሳንቲም ላይም ሥዕሉ ይገኛል። ይህ ወፍ ከቦታ ቦታ የሚፈልስ ሲሆን የቅዝቃዜውን ወቅት የሚያሳልፈው በስተ ደቡብ ባሉ አገሮች ነው። ታዲያ ሉን የተባለው ወፍ የሚያሰማውን ድምፅ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የተለያዩ አስገራሚ ድምፆች

ሉኖች በጣም አስደናቂ የሆኑ የተለያዩ ድምፆችን ማውጣት ይችላሉ። ምሽት አካባቢ ወይም ማታ ላይ የሚያሰሙት የማላዘን ዓይነት ድምፅ ከርቀት ይሰማል። ወንድና ሴት ሉኖች እርስ በርስ ለመግባባት አሊያም ከጫጩቶቻቸው ወይም ከሌሎች ሉኖች ጋር ለመነጋገር እንደ ጉጉት ዓይነት ድምፅ ያወጣሉ። አደገኛ ሁኔታ ሲኖር የሚያሰሙት የማስጠንቀቂያ ድምፅም አለ፤ እንደ ማስካካት ያለው ይህ ድምፅ “የእብደት ሳቅ” ተብሎም ተገልጿል። ሉኖች በሚበርሩበት ጊዜ የሚያሰሙት ድምፅ ይህ ብቻ ነው።

ሉኖች ቀጭንና ወፍራም ድምፆችን እያከታተሉ በማውጣት የሚያሰሙት ድምፅም አለ። እንዲህ ያለውን ድምፅ የሚያወጡት ተባዕቶቹ ብቻ ሲሆኑ በርድዎች ካናዳ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ይህን የሚያደርጉት “የመኖሪያ ክልላቸውን ለማስከበር ይመስላል።” መጽሔቱ አክሎም “እያንዳንዱ ተባዕት የራሱ የሆነ የተለየ ድምፅ ያወጣል። . . . የወፉ ክብደት በጨመረ መጠን ድምፁም ጎርናና ይሆናል” ብሏል። ከዚህም በላይ ተባዕቱ “የመኖሪያ አካባቢውን በሚለውጥበት ጊዜ ድምፁን ይቀይራል።” እንዲሁም መጽሔቱ እንደተናገረው ወፉ “በተቻለ መጠን ከቀድሞው የአካባቢው ነዋሪ የተለየ ድምፅ ለማውጣት ይጥራል።”

ውብና ቀልጣፋ ሆኖም ከርፋፋ

ሉን የሚያብረቀርቅና ወደ ጥቁር የሚወስድ አረንጓዴ ጭንቅላት፣ ቀይ ዓይኖች እንዲሁም ረጅምና ሹል መንቆር ያለው ወፍ ነው። የላባው ቀለም እንደየወቅቱ ይቀያየራል።

ሉኖች የተዋጣላቸው አዳኞች ከመሆናቸውም ሌላ ትላልቅ የሆኑ እንደ ዳክዬ ዓይነት እግሮች ስላሏቸው ጎበዝ ዋናተኞችና ጠላቂዎች ናቸው። እስከ 60 ሜትር ድረስ ጠልቀው ሊገቡና አንዳንዴም ከውኃ ውስጥ ሳይወጡ ለበርካታ ደቂቃዎች ሊቆዩ ይችላሉ።

ይሁን እንጂ ይህ ወፍ ለመብረር ሲነሳና በርሮ ሲያርፍ ያን ያህል ቀልጣፋ አይደለም። ሉን ክብደት ስላለው ሰፋ ያለ “ማኮብኮቢያ” ቦታ ያስፈልገዋል፤ አየር ላይ መንሳፈፍ ከመጀመሩ በፊት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሜትሮች ክንፉን እያርገበገበ ውኃ ላይ መንደርደር አለበት። በዚህም የተነሳ ሉኖች ስፋት ያለው ሐይቅ ወይም ወንዝ ይመርጣሉ። ውኃ ላይ በሚያርፉበት ጊዜ ደግሞ ጎማዎቹን መዘርጋት እንዳቃተው አውሮፕላን እግሮቻቸውን ወደኋላ አጥፈው በከፍተኛ ፍጥነት ይወርዳሉ። ከዚያም በሆዳቸው ውኃው ላይ እምቦጭ ብለው ያርፉና ለተወሰነ ርቀት እየተንሸራተቱ ይሄዳሉ።

የሉን ትላልቅ እግሮች ለዋና እጅግ ተስማሚ ይሁኑ እንጂ የሚገኙት ሰውነቱ መሃል ላይ ሳይሆን ወደ ኋላ አካባቢ በመሆኑ ወፎቹ ሲራመዱም ሆነ ሲቆሙ ያን ያህል አይማርኩም። በዚህም ምክንያት ሉኖች ጎጆዎቻቸውን የሚሠሩት ውኃ አቅራቢያ ሲሆን ይህም በቀላሉ ወደ ውኃው ለመግባት ያመቻቸዋል።

ሁለቱም ወላጆች እንቁላሎቻቸውን (አብዛኛውን ጊዜ የሚጥሉት ሁለት ነው) የሚታቀፉት በየተራ እየተፈራረቁ ነው፤ እንቁላሎቹ ዳለቻ ቀለም ያላቸው ሲሆን በላያቸው ያሉት ጥቁር ነጠብጣቦች ከአካባቢያቸው ጋር እንዲመሳሰሉ ያደርጓቸዋል። ጫጩቶቹ በአማካይ በ29 ቀን ውስጥ ይፈለፈላሉ። ጫጩቶቹ በተፈለፈሉ በሁለት ቀናት ውስጥ መዋኘት እንዲሁም ከአጭር ርቀት መጥለቅ ይችላሉ። በሚደክማቸው ጊዜ ደግሞ በወላጃቸው ጀርባ ላይ ተፈናጥጠው ዘና ይላሉ። ከሁለት ወይም ከሦስት ወር በኋላ መብረር ሲችሉ ወላጆቻቸውን ትተው የራሳቸውን ኑሮ ይጀምራሉ።

ሉን ካሉት ጠላቶች መካከል ንስሮች፣ ገል የሚባሉት ወፎችና ራኩን የሚባሉት እንስሳት ይገኙበታል፤ ከሁሉ የሚከፋው ጠላቱ ግን የሰው ልጅ ነው። ከእርሳስ (ሌድ) የተሠሩ የማጥመጃ መረብ ማስመጫዎች እና የነዳጅ ዘይት ፍሳሽ ወፎቹን ይመርዟቸዋል። ከዚህም ሌላ በአሲድ ዝናብ ምክንያት የሚመጣ የኬሚካል ብክለት ሉኖች የሚመገቡት ዓሣ እንዲቀንስ ያደርጋል። ጀልባዎች በውኃ ላይ ሲሄዱ የሚፈጥሩት ሞገድ ጎጇቸውን ያፈርስባቸዋል። በተጨማሪም በሐይቆች ዳርቻ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ገለልተኛ አካባቢ የሚፈልጉትን እነዚህን ወፎች ከተፈጥሮ መኖሪያቸው እንዲሸሹ ያደርጓቸዋል።

ያም ቢሆን አሁንም ብዛት ያላቸው ሉኖች አሉ። በመሆኑም ይህ እጅግ የሚያምር ወፍ ልዩ በሆነው ድምፁና በአስደናቂ እንቅስቃሴው አእዋፍ አፍቃሪዎችን ሲያስደንቅ ይኖራል።

^ አን.2 ይህ ወፍ ታላቁ የሰሜን ጠላቂ እና ታላቁ የሰሜን ሉን ተብሎም ይጠራል።

Page 16, loon landing: Spectrumphotofile; page 17, loon chick: © All Canada Photos/SuperStock; loon vocalizing: © Roberta Olenick/age fotostock