በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

እኔ ማን ነኝ?

እኔ ማን ነኝ?

ማይክል፣ ብራድ ወደ እሱ ሲመጣ ሲያይ ምን ሊለው እንደሆነ ስለገባው ፍርሃት አደረበት። ብራድም “ሃይ ሚኪ፣ እስቲ ይቺን ሞክራት!” አለው። ማይክል እንደጠረጠረው ብራድ የተጠቀለለ ማሪዋና ይዞ ነበር። ማይክል ሊቀበል ባይፈልግም እንደ ፈሪ መታየት ደግሞ አልፈለገም። ፈራ ተባ እያለ “እእእ . . . አይ ለዛሬ ይለፈኝ” አለው።

ጄሲካ፣ ብራድ ወደ እሷ ሲመጣ ስታይ ሐሳቡ ስለገባት ምን እንደምትለው ተዘጋጀች። ብራድም “ሃይ ጄሲ፣ እስቲ ይቺን ሞክሪያት!” አላት። ጄሲካ እንደጠረጠረችው ብራድ የተጠቀለለ ማሪዋና ይዞ ነበር። ጄሲካ በልበ ሙሉነት “አይ፣ አልፈልግም” አለችው። አክላም “ሳንባዬን እፈልገዋለሁ። . . . አንተ ራስህ ማጨስህ ገርሞኛል! ብልጥ ትመስለኝ ነበር!” በማለት መለሰችለት።

ከላይ በተገለጹት ሁኔታዎች ላይ ጄሲካ ተጽዕኖውን በተሻለ መንገድ መቋቋም የቻለችው ለምንድን ነው? ከማይክል በተለየ መልኩ ጄሲካ ማንነቷን ታውቃለች። ማንነትን ማወቅ ሲባል ማን መሆንህንና ምን ዓይነት አቋም እንዳለህ መገንዘብ ማለት ነው። ማንነትህን ማወቅህ፣ የሚያጋጥምህን ፈተና ለመቋቋም ይኸውም ሕይወትህን ሌሎች እንዲመሩት ከመፍቀድ ይልቅ አንተ በምታምንበት መንገድ ለመምራት ኃይል ይሰጥሃል። ታዲያ እንዲህ ያለውን በራስ የመተማመን መንፈስ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? እስቲ ከዚህ በታች ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክር።

1 ምን ጠንካራ ጎኖች አሉኝ?

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ችሎታዎችህንና መልካም ባሕርያትህን ማወቅህ የበለጠ በራስህ እንድትተማመን ያደርግሃል።

ይህን አስብ፦ እያንዳንዱ ሰው የተለያዩ ስጦታዎች አሉት። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች በኪነ ጥበብ ወይም በሙዚቃ ረገድ ተፈጥሮ ያደላቸው ችሎታ ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ወደ ስፖርት ያዘነብላሉ። ራኬል መኪና መጠገን ትወዳለች። * “አሥራ አምስት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ መካኒክ ለመሆን ወሰንኩ” ብላለች።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ሐዋርያው ጳውሎስ “የተዋጣልኝ ተናጋሪ ባልሆን እንኳ እውቀት የሚጎድለኝ ግን አይደለሁም” በማለት ጽፎ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:6) ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥልቅ እውቀት ስለነበረው ሌሎች ቢፈታተኑትም ከአቋሙ ንቅንቅ አላለም። የእነዚህ ሰዎች አሉታዊ አስተሳሰብ በራስ የመተማመን ስሜቱን እንዲያናጋበት አልፈቀደም።​—2 ቆሮንቶስ 10:10፤ 11:5

ራስህን ገምግም። ያለህን አንድ ተሰጥኦ ወይም ችሎታ ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

አሁን ደግሞ ያሉህን ጥሩ ባሕርያት ግለጽ። (ለምሳሌ ያህል፣ አሳቢ ነህ? ለጋስ ነህ? እምነት የሚጣልብህ ነህ? ሰዓት አክባሪ ነህ?)

․․․․․

“ሰዎች ሲፈልጉኝ ልደርስላቸው እሞክራለሁ። ሥራ ይዤ ሳለ አንድ ሰው ሊያናግረኝ ቢፈልግ፣ ሥራውን ትቼ አዳምጠዋለሁ።”​—ብሪአን

ያሉህን መልካም ባሕርያት ለይተህ ለማወቅ ከተቸገርህ እያደግህ ስትሄድ ያሻሻልከውን አንድ ባሕርይ ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ከዚህ በታች ጻፈው።​— “እኩዮችህ ምን ይላሉ?” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡትን ምሳሌዎች ተመልከት።

․․․․․

2 ምን ድክመቶች አሉኝ?

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ሰንሰለት የቱንም ያህል ጠንካራ ቢሆን የላላ ቦታ ካለው በቀላሉ ሊበጠስ እንደሚችል ሁሉ አንተም ድክመቶችህ እንዲቆጣጠሩህ ከፈቀድህ ማንነትህ ሳታስበው ሊቀየርና መጥፎ ስብዕና ልታዳብር ትችላለህ።

ይህን አስብ፦ ፍጹም የሆነ ማንም ሰው የለም። (ሮም 3:23) ሁሉም ሰው ሊያስተካክላቸው የሚፈልጋቸው አንዳንድ ባሕርያት አሉት። ሴጃ የምትባል አንዲት ወጣት “ጥቃቅን በሆኑ ነገሮች የምበሳጨው ለምንድን ነው?” ካለች በኋላ “በማይረባ ነገር የምናደድ ሲሆን ስሜቴን መቆጣጠር ያቅተኛል!” በማለት ተናግራለች።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ጳውሎስ ድክመቶቹን ያውቅ ነበር። እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋና በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።”—ሮም 7:22, 23

ራስህን ገምግም። የትኞቹን ድክመቶች ማሻሻል ያስፈልግሃል?

․․․․․

“የፍቅር ፊልሞችን ከተመለከትኩ በኋላ የምተክዝ ሲሆን ‘እኔም ፍቅረኛ በኖረኝ’ ብዬ እመኛለሁ። በመሆኑም ከእንዲህ ዓይነቱ መዝናኛ መራቅ እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ።”​—ብሪጀት

3 ምን ግቦች አሉኝ?

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ግቦች ሲኖሩህ ሕይወትህ አቅጣጫና ዓላማ ይኖረዋል። በተጨማሪም ያሰብከውን ነገር እንዳታከናውን እንቅፋት ሊሆኑብህ ከሚችሉ ሰዎችና ሁኔታዎች ለመራቅ ይበልጥ ትነሳሳለህ።

ይህን አስብ፦ ኮንትራት ታክሲ ይዘሃል እንበል፤ ሹፌሩ የመኪናው ነዳጅ እስኪያልቅ ድረስ ዝም ብሎ እንዲነዳ ትነግረዋለህ? ይህ ሞኝነት ከመሆኑም ሌላ አክሳሪ ነው! ግቦች ማውጣትህ አቅጣጫ የሌለው ሕይወት ከመምራት ይልቅ በሕይወትህ ውስጥ አንድ ነገር ለማከናወን ይረዳሃል። ግብ ካለህ ልትደርስበት ያሰብከው ቦታ አለ፤ እዚያ እንዴት እንደምትደርስም እቅድ አውጥተሃል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ጳውሎስ “እኔ መድረሻውን እንደማያውቅ ሰው አልሮጥም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:26) ጳውሎስ ምንም ዓላማ ሳይኖረው ሕይወቱን እንዲያው በዘፈቀደ ከመምራት ይልቅ ግቦች ያወጣ ሲሆን ግቦቹን ዳር ለማድረስ በሚያስችለው መንገድ ኖሯል።—ፊልጵስዩስ 3:12-14

ራስህን ገምግም። በአንድ ዓመት ውስጥ ልትደርስባቸው የምትፈልጋቸውን ሦስት ግቦች ከዚህ በታች ጻፍ።

  1. ․․․․․

  2. ․․․․․

  3. ․․․․․

አሁን ደግሞ ከላይ ከገለጽካቸው መካከል ትልቅ ቦታ የምትሰጠውን ግብ ምረጥና እዚያ ላይ ለመድረስ ከአሁን ጀምሮ ማድረግ የምትችለውን ነገር ጻፍ።

․․․․․

“በሥራ ካልተጠመድኩ ጊዜዬን ዝም ብዬ አባክናለሁ። ግቦች አውጥቶ እነሱን ለማሳካት ጥረት ማድረጉ የተሻለ ነው።”​—ሆሴ

4 የማምንባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የምታምንበት ነገር ከሌለህ የራስህ አቋም የሌለህ ወላዋይ ሰው ትሆናለህ። አካባቢዋን ለመምሰል ቀለሟን እንደምትቀያይረው እንደ እስስት ሁሉ አንተም ከእኩዮችህ ጋር ለመመሳሰል ትጥራለህ፤ ይህ ደግሞ የራስህ ማንነት እንደሌለህ የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ነው።

ይህን አስብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖችን ‘ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምረው እንዲያረጋግጡ’ ያበረታታቸዋል። (ሮም 12:2) በምታምንባቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተህ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ሌሎች ምንም ቢያደርጉ አንተ በአቋምህ ትጸናለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ነቢዩ ዳንኤል ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ከቤተሰቦቹና ከእምነት አጋሮቹ ርቆ ለመኖር ቢገደድም የአምላክን ሕግ ለመጠበቅ ‘ወስኖ’ ነበር። (ዳንኤል 1:8) እንዲህ በማድረጉም በአቋሙ ጸንቶ ለመኖር ችሏል። በእርግጥም ዳንኤል ከሚያምንባቸው ነገሮች ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል።

ራስህን ገምግም። የምታምንባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ለምሳሌ ያህል፦

  • አምላክ እንዳለ ታምናለህ? ከሆነ ለምን? አንተ በግልህ አምላክ መኖሩን እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

  • አምላክ ያወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንደሚጠቅሙህ ታምናለህ? ከሆነ እንዲህ እንድትል ያደረገህ ምንድን ነው? ለምሳሌ ያህል፣ እንደ እኩዮችህ “በነፃነት” ከመኖር ይልቅ አምላክ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር የሰጣቸውን ሕጎች መታዘዝ ደስተኛ እንደሚያደርግህ የምታምነው ለምንድን ነው?

እነዚህ በችኮላ መልስ ሰጥተህ የምታልፋቸው ጥያቄዎች አይደሉም። ለእምነትህ መሠረት የሆኑትን ነገሮች ጊዜ ወስደህ አስብባቸው። እንዲህ ማድረግህ የምታምንባቸውን ነገሮች ለማስረዳት ይበልጥ ዝግጁ እንድትሆን ይረዳሃል።​—ምሳሌ 14:15፤ 1 ጴጥሮስ 3:15

“በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች በራስህ እንደማትተማመን ካዩ ያሾፉብሃል፤ እኔ ደግሞ በእምነቴ እንደማልተማመን እንዲሰማቸው አልፈልግም። ስለዚህ ስለማምንባቸው ነገሮች ግልጽና ጠንካራ ማስረጃ ለማቅረብ ተዘጋጀሁ። ‘አይ፣ እኔ ሃይማኖቴ ስለማይፈቅድ ይህን ማድረግ አልችልም’ ከማለት ይልቅ ‘እንደዚህ ማድረግ ትክክል አይመስለኝም’ ማለቱ የተሻለ ነው። ይሄ እኔ የማምንበት ነገር ነው።”​—ዳንዬል

ነገሩን ለማጠቃለል ያህል አንተስ፣ ቀለል ያለ ነፋስ ወዲያና ወዲህ እንደሚያንገዋልለው ቅጠል መሆን ይሻልሃል? ወይስ ኃይለኛ አውሎ ነፋስንም እንኳ መቋቋም እንደሚችል ዛፍ መሆንን ትመርጣለህ? ማንነትህን በተመለከተ በራስህ የምትተማመን ከሆነ እንደ ዛፉ ትሆናለህ። ይህ ደግሞ ‘እኔ ማን ነኝ?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ያስችልሃል።

ማንነትህን በተመለከተ በራስህ የምትተማመን ከሆነ አፈሩን በሥሮቹ ቆንጥጦ እንደያዘና ኃይለኛ አውሎ ነፋስን መቋቋም እንደሚችል ዛፍ ትሆናለህ

 

^ አን.8 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።