በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች ምን ይላሉ?

ወላጆች ምን ይላሉ?

ወላጆች ምን ይላሉ?

ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ መታዘዝ ያለውን ጥቅም ልታስተምሯቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ትልልቅ ሰዎች ለመሆን በሚያደርጉት እድገት ጠቃሚ የሆኑ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ልትረዷቸው የምትችሉትስ እንዴት ነው? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አንዳንድ ወላጆች የሰጡትን አስተያየት እስቲ እንመልከት።

ማኅበራዊ ሕይወትና የቤት ውስጥ ሥራዎች

“አንድ ላይ ምግብ እየተመገብን ስለ ውሏችን በምንወያይበት ጊዜ ልጆቻችን እንዴት ማዳመጥ እንዳለባቸው ይማራሉ። ልጆቻችን እናትና አባታቸው በትዕግሥት ሲያዳምጡ ሲመለከቱ ለራሳቸውም ይሁን አንዳቸው ለሌላው ያላቸው አክብሮት እየጨመረ ይሄዳል።”​—ሪቻርድ፣ ብሪታንያ

“ልጆቻችን እርስ በርሳቸው ሲከባበሩና በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ያለ እኛ ጣልቃ ገብነት ሲፈቱት መመልከት እጅግ ያስደስታል። እንዲሁም ከአዋቂዎች ጋር በልበ ሙሉነት ያወራሉ።”​—ጆን፣ ደቡብ አፍሪካ

“ፍጹም ስላልሆንኩ አንዳንዴ ሳላስበው የልጆቼን ስሜት እጎዳለሁ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ለሠራሁት ስህተት ይቅርታ መጠየቄ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል።”​—ጃኔል፣ አውስትራሊያ

“ልጆቻችንን አስፈላጊ የሆኑ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ እናሠለጥናቸዋለን። ልጆች ሌሎችን የሚጠቅም ተግባር እንዲያከናውኑ ማስተማራችን ቤተሰባችን የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ልጆቻችን የእርካታ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።”​—ክላይቭ፣ አውስትራሊያ

“ልጆቻችንን አንዳቸው የሌላውን ችግር የሚረዱ፣ የሚከባበሩ እንዲሁም ይቅር ባይ እንዲሆኑ ማስተማር ቀላል ባይሆንም እንኳ ወሳኝ ነገር ነው።”​—ዩኮ፣ ጃፓን

ንጽሕናና ጤና አጠባበቅ

“ልጆቻችን ሕጻናት ሳሉ ገላቸውን መታጠብ እናስተምራቸው የነበረ ሲሆን ደስ ብሏቸው ገላቸውን እንዲታጠቡ ለማድረግ ስንል በሰው ቅርጽ የተሠሩ ሳሙናዎች፣ የካርቱን ፊልም ገጸ ባሕርያትን የሚመስሉ ሻምፖዎች እንዲሁም የእንስሳት ቅርጽ ያላቸው ትንንሽ ስፖንጆች እንጠቀም ነበር።”​—ኤድጋር፣ ሜክሲኮ

“የቧንቧ ውኃ በሌለበት ቦታ በምንኖርበት ጊዜ ከውጭ ስንመጣ እጃችንን መታጠብ እንድንችል ምንጊዜም ሳሙናና የተቀዳ ውኃ አመቺ በሆነ ቦታ አስቀምጥ ነበር።”​—ኢንዱራንስ፣ ናይጄሪያ

“ለልጆቻችን በየቀኑ ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ የምንሰጣቸው ሲሆን የተመጣጠነ ምግብ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት እንነግራቸዋለን። ልጆቹ ምግብ ውስጥ ስለሚጨማመሩት የተለያዩ ነገሮች ለማወቅ ስለሚጓጉ ምግብ ሳዘጋጅ እንዲረዱኝ አደርጋለሁ። አብረን ምግብ በመሥራት የምናሳልፈው ጊዜ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ያስችለናል።”​—ሳንድራ፣ ብሪታንያ

“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቃሚ ነው፤ ስለሆነም ወላጆች እንደመሆናችን መጠን ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እንጥራለን። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን መሮጥ፣ መዋኘት፣ ቴኒስ ወይም ቅርጫት ኳስ መጫወት አሊያም ብስክሌት መንዳት ልጆቻችንን ያስደስታቸዋል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አስደሳችም እንደሆነ ይማራሉ።”​—ከረን፣ አውስትራሊያ

“ልጆች ከምንም በላይ የሚያስፈልጋቸው ከወላጆቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ነው። ይህንን ሊተካ የሚችል ሌላ ምንም ነገር የለም፤ ገንዘብ፣ ስጦታ ወይም ሽርሽር መሄድ ይህን ሊያካክሱት አይችሉም። ሥራ የምገባው ጠዋት ላይ ማለትም ልጆቼ ትምህርት ቤት በሚሆኑበት ሰዓት ብቻ ነው። በመሆኑም ከሰዓት በኋላ ያለውን ጊዜ ከእነሱ ጋር ማሳለፍ እችላለሁ።”—ሮሚና፣ ጣሊያን

ተግሣጽ

“ከሁሉ የተሻለ ነው የሚባል አንድ የተግሣጽ ዓይነት እንደሌለ ተገንዝበናል፤ ከዚህ ይልቅ የተግሣጹ ዓይነት እንደ ሁኔታው ይለያያል። አንዳንድ ጊዜ ከልጁ ጋር በቁም ነገር ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግ በቂ ሊሆን ሲችል በሌላ ወቅት ደግሞ ልጁ የሚወዳቸውን ነገሮች መከልከል ሊያስፈልግ ይችላል።”​—ኦግቢቲ፣ ናይጄሪያ

“ልጆቻችን የሰጠናቸውን መመሪያዎች ተረድተዋቸው እንደሆነ ለማረጋገጥ ደግመው እንዲነግሩን እናደርጋለን። ከዚያም መመሪያዎቹን ተግባራዊ ማድረጋቸውን እንከታተላለን። ልጆቻችን የተነገራቸውን ነገር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከፈለግን፣ ሳይታዘዙ በሚቀሩበት ጊዜ ተገቢውን ቅጣት በመስጠት እኛም የድርሻችንን መወጣት አለብን።”​—ክላይቭ፣ አውስትራሊያ

“ለልጆቼ ተግሣጽ በምሠጥበት ጊዜ ፊት ለፊት ሊያዩኝ እንዲችሉ በርከክ ማለት ውጤታማ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይህም ሙሉ ትኩረታቸውን ለማግኘት ይረዳኛል። በተጨማሪም ከምናገራቸው ቃላት ያልተናነሰ መልእክት የሚያስተላልፈውን በፊቴ ላይ የሚነበበውን ስሜት እንዲያዩ ያስችላቸዋል።”​—ጄነፈር፣ አውስትራሊያ

“ልጆቻችን የነገርናቸውን ነገር ተግባራዊ እንዳላደረጉ በግልጽ በሚታይበት ጊዜም እንኳ ‘አንተ እኮ ፈጽሞ አትሰማም’ ላለማለት እንጠነቀቃለን። በተጨማሪም አንዱን ልጅ በሌላው ፊት አንገሥጽም። የሚያስቆጣንን ነገር በሌሎች ፊት ሲያደርጉ ድምፃችንን ቀስ አድርገን እንነግራቸዋለን፤ አሊያም ደግሞ ለብቻቸው ወስደን እናነጋግራቸዋለን።”​—ሩዲ፣ ሞዛምቢክ

“ልጆች በቀላሉ ሊቀረጹ የሚችሉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሌሎችን መኮረጅ ይወዳሉ። ከዚህም የተነሳ አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች፣ የመገናኛ ብዙኃንና የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያደርሱባቸውን መጥፎ ተጽዕኖዎች መቋቋም እንዲችሉና ትክክለኛ በሆኑ መመሪያዎች ላይ የተመሠረተ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲያዳብሩ መርዳት ያስፈልገናል። በጥሩ ሥነ ምግባር መታነጻቸው ጎጂ የሆነ ማንኛውም ጥያቄ ሲቀርብላቸው እምቢ እንዲሉ ይረዳቸዋል።”​—ግሬግዋር፣ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ

“የምንሰጠው ተግሣጽ ጥብቅ፣ ሚዛናዊና በተናገርነው መሠረት የሚፈጸም መሆን ያስፈልገዋል። ልጆች ጥፋት መሥራታቸው የሚያስከትልባቸውን መዘዝ ሊያውቁና የተናገራችሁትን እንደምትፈጽሙ ሊገነዘቡ ይገባል።”​—ኦወን፣ እንግሊዝ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።”​—ቆላስይስ 3:21

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አጭር የቤተሰብ ታሪክ

ነጠላ ወላጅ ሆኖ ውጤታማ መሆን

ከሉሲንዳ ፎርስተር ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

ነጠላ ወላጅ በመሆንሽ ከምንም በላይ ተፈታታኝ የሆነብሽ ነገር ምንድን ነው?

ወላጅ መሆን በራሱ ከባድ ነው፤ ነጠላ ወላጅ እንደመሆኔ ይበልጥ ተፈታታኝ የሆነብኝ ነገር ጊዜዬንና ጉልበቴን በተገቢው መንገድ መጠቀም ነው። በልጆቼ አእምሮ ውስጥ ጠቃሚ መመሪያዎችንና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን ለመቅረጽ እንዲሁም አብሬያቸው ለመዝናናትና ለመደሰት ጊዜ ያስፈልገኛል። ብዙውን ጊዜ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት ስል ዘና የምልበትን ጊዜ መሥዋዕት ማድረግ ይኖርብኛል።

ከልጆችሽ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ እንድትችዪ ምን ታደርጊያለሽ?

ልጆች፣ ወላጆቻቸው ከተፋቱ በኋላ ያለመረጋጋት ስሜት ሊያድርባቸውና ሊናደዱ ይችላሉ። ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ ዓይን ዓይናቸውን እያየሁ ረጋ ባለ መንገድ ማነጋገር አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ይህንንም ለማድረግ እስክንረጋጋ ድረስ ከጠበቅሁ በኋላ ያሳሰበኝን ነገር ሳላጋንን ለመግለጽ ጥረት አደርጋለሁ። ልጆቼ ሐሳባቸውን እንዲገልጹልኝ ከጠየቅኋቸው በኋላ መልስ ሲሰጡኝ በጥሞና አዳምጣቸዋለሁ፤ እንዲሁም ስሜታቸውን በጣም እንደማከብር አሳያለሁ። ለትምህርታቸው ትኩረት እሰጣለሁ፤ እንዲሁም ለሚያከናውኑት ነገር አመሰግናቸዋለሁ። ምንጊዜም እርጋታ በሰፈነበትና ዘና ባለ ሁኔታ አብረን እንመገባለን። በተጨማሪም በጣም እንደምወዳቸው አዘውትሬ እነግራቸዋለሁ።

ተግሣጽ የምትሰጫቸው እንዴት ነው?

ልጆች በግልጽ የተቀመጠ መመሪያ ሊሰጣቸው የሚገባ ሲሆን ወላጆችም ቃላቸውን መለዋወጥ የለባቸውም። ደግ ሆኖም ጥብቅ ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ። አንድ ተግባር ስህተት የሆነው ለምን እንደሆነ ለልጆቼ ማብራራትና ማሳመን ይኖርብኛል። በተጨማሪም ተግሣጽ ከመስጠቴ በፊት አንድን ነገር ያደረጉት ለምን እንደሆነ ለመረዳት እንድችል በርካታ ጥያቄዎችን በመጠየቅ አመለካከታቸውንና ስሜታቸውን ለማወቅ ጥረት አደርጋለሁ። ተሳስቼ ከሆነ ለምሳሌ ያህል፣ አንድን ሁኔታ የተረዳሁት በተሳሳተ መንገድ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ልጆችሽ ሰው አክባሪ እንዲሆኑ የምታሠለጥኛቸው እንዴት ነው?

ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ይኸውም ሌሎችን መያዝ ያለብን እነሱ እኛን እንዲይዙን በምንፈልግበት መንገድ እንደሆነ አስታውሳቸዋለሁ። (ሉቃስ 6:31) ልጆቼ በመካከላቸው የተፈጠረውን ችግር በተቻለ መጠን ራሳቸው እንዲፈቱ አበረታታቸዋለሁ፤ እንዲሁም የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥማቸው ጉዳዩን ረጋ ብለው በደግነት መያዝ ያለውን ጠቀሜታ አስተምራቸዋለሁ።

ዘና ለማለት ምን ታደርጋላችሁ?

ለእረፍት ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ አቅማችን የሚፈቅደው ሁልጊዜ ስላልሆነ ብዙ ወጪ የማያስወጡ መዝናኛዎችን ለማግኘት ጋዜጦችን እንመለከታለን። ከቤታችን ወጣ ብለን እንንሸራሸራለን ወይም ዕፅዋት ወደሚለሙበት አካባቢ በመሄድ ዞር ዞር እያልን አትክልቶችን እናያለን። በአትክልት ቦታችን ለቅመምነት የሚያገለግሉ ዕፅዋትን የምንተክል ሲሆን ምግብ ስናዘጋጅ በጓሯችን ከተከልናቸው ዕፅዋት መምረጥ መቻላችን ያስደስተናል። ለመዝናናት የምንሄደው በአካባቢያችን ወደሚገኝ መናፈሻ ቢሆንም እንኳ መዝናኛ አስፈላጊ ነገር ነው።

ቤተሰባችሁ ምን በረከቶችንና አስደሳች ነገሮችን አግኝቷል?

በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ቢሆንብንም እርስ በርስ አቀራርቦናል፤ እንዲሁም ያሉንን በረከቶች ማድነቅን ተምረናል። ልጆቼ የየራሳቸውን ስብዕና ሲያዳብሩ ማየት ያስደስተኛል። አሁን ባሉበት ዕድሜ ላይ ልጆቼ ከእኔ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚፈልጉ ሲሆን እኔም አብሬያቸው መሆን ያስደስተኛል። ሳዝን ወይም ስደሰት ስለሚገባቸው አንዳንድ ጊዜ እቅፍ አድርገው ያጽናኑኛል። ፍቅራቸውን የሚገልጹበት መንገድ በጣም ያስደስተኛል። ከሁሉ በላይ ግን ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የረዳንን አሳቢ የሆነውን ፈጣሪያችንን ፍቅር ቀምሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ወላጅ ለመሆን በማደርገው ጥረት እንድገፋበት የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል።—ኢሳይያስ 41:13

[ሥዕል]

ሉሲንዳ ከልጆቿ ከብሪ እና ሼ ጋር