በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከ10 እስከ 13 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ብራዚላውያን ተማሪዎች መካከል 17 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በጉልበተኞች ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል፤ አሊያም እነሱ ራሳቸው በሌሎች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ።​—ኦ ኤስታዶ ደ ሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል

በአሁኑ ጊዜ ከ12 ዓመት በታች በሆኑ ልጆች ላይ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የኮሌስትሮል መጠን መጨመር፣ የኩላሊት ጠጠርና የጉበት በሽታ እየታየ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? ሳይንቀሳቀሱ ረጅም ጊዜ ማሳለፍ፣ ገንቢ ያልሆኑ ምግቦችን መመገብና ከልክ ያለፈ ውፍረት ናቸው።​—ኤቢሲ፣ ስፔን

በዩናይትድ ስቴትስ መካከለኛ ገቢ ባለው አንድ ቤተሰብ ውስጥ በ2008 የተወለደን ልጅ እስከ 18 ዓመት ለማሳደግ የሚወጣው ወጪ 221,190 የአሜሪካ ዶላር (የዋጋ ግሽበትን ግምት ውስጥ ካስገባን 291,570 የአሜሪካ ዶላር) እንደሚደርስ መንግሥት ያወጣው አንድ ግምታዊ አኃዝ ያሳያል።​የዩናይትድ ስቴትስ ግብርና ሚኒስቴር፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ማጫወት ተረሳ

በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት በብሪታንያ ከሚኖሩ ወላጆች መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆኑት “ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚያጫውቱ” እንደረሱ ተናግረዋል። አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ልጆቻቸውን ማጫወት አሰልቺ እንደሚሆንባቸው የገለጹ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ይህን ለማድረግ ጊዜ እንደሌላቸው ወይም ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚያጫውቱ ግራ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። በሥነ ልቦና መስክ ፕሮፌሰር የሆኑት ታንያ ባይረን ከላይ ያለውን ጥናት አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “ወላጆች ልጆቻቸውን ጥሩ አድርገው ማጫወት እንዲችሉ አራት ነገሮች ያስፈልጋሉ፤ እነሱም ትምህርት፣ ተነሳሽነት፣ የአስተሳሰብ ጥምረትና የሐሳብ ልውውጥ ናቸው።” ከሦስት ወላጆች መካከል አንዱ ከልጁ ጋር የኮምፒውተር ጨዋታ ለመጫወት ቢመርጥም አብዛኞቹ ልጆች ይህን ጨዋታ መጫወት የሚፈልጉት ብቻቸውን ነው። ከ5 እስከ 15 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ለመጫወት ከሚመርጧቸው ጨዋታዎች መካከል እንደ ዳማና ቼዝ የመሳሰሉ ጨዋታዎች እንዲሁም ከቤት ውጭ የሚካሄዱ ጨዋታዎች ይገኙበታል።

ለልጆች የሚነበቡ ታሪኮች

ለልጆቻቸው ማታ ላይ ታሪክ ለማንበብ ጊዜ ያጡ አባቶችን ለመርዳት የሚያስችል የኢንተርኔት አገልግሎት ተዘጋጅቷል። የሲድኒው ዴይሊ ቴሌግራፍ እንደዘገበው “አባትየው የልጆች ታሪክ ሲያነብ በአንድ የተራቀቀ ሶፍትዌር አማካኝነት ከተቀዳ በኋላ ታሪኩ ከሙዚቃና ከሌሎች ድምፆች ጋር ተቀናብሮ ለልጁ በኢሜይል ይላክለታል።” ስለ ሰብዓዊ ግንኙነት የሚያጠኑ ባለሙያዎች ግን ይህ ቴክኖሎጂ ጠቃሚ ስለመሆኑ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል። በአውስትራሊያ በሚገኘው የኒውካስል ዩኒቨርሲቲ የቤተሰብ ምርምር ፕሮግራም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሪቻርድ ፍሌቸር ‘ለአንድ ልጅ ማንበብ ከልጁ ጋር መቀራረብን ይጨምራል’ ብለዋል። አባቶች ለልጆቻቸው በሚያነቡበት ጊዜ ከእነሱ ጋር ያወራሉ፣ ያቅፏቸዋል እንዲሁም ይሳሳቃሉ። ዶክተር ፍሌቸር እንደተናገሩት አጠገባቸው ሆኖ ለልጆች ማንበብ የሚያስገኘውን ጥቅም ሊተካ የሚችል ኢሜይል የለም።