በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን ማሳደግ—ከሕፃንነት እስከ ጉርምስና

ልጆችን ማሳደግ—ከሕፃንነት እስከ ጉርምስና

ልጆችን ማሳደግ—ከሕፃንነት እስከ ጉርምስና

“ልጆቻችሁ አምስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በቤተሰባቸው አባላት ተከብበው ስለሚቆዩ ጥሩ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ኮትኩቶ ማሳደግ ቀላል ነው። ትምህርት ቤት መሄድ ከጀመሩ በኋላ ግን ከእነሱ የተለየ ጠባይና አነጋገር ካላቸው ልጆች ጋር ይገናኛሉ።”​—ቫልቴር፣ ጣሊያን

ልጆች እያደጉ ሲሄዱ በዙሪያቸው ስላለው ዓለም ያላቸው እውቀት ይሰፋል። ከተለያዩ ሰዎች ጋር ይኸውም አብረዋቸው ከሚጫወቱና ከሚማሩ ልጆች እንዲሁም ከዘመድ አዝማድ ጋር ሐሳብ ይለዋወጣሉ። ከላይ የተጠቀሰው ቫልቴር እንደገለጸው ልጃችሁ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ፣ ሕፃን ሳለ ታደርጉት እንደነበረው በሕይወቱ ላይ ተጽዕኖ የምታሳድሩት እናንተ ብቻ መሆናችሁ ይቀራል። ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት ባሉት ዓመታት ለልጃችሁ የታዛዥነትንና የጥሩ ምግባርን አስፈላጊነት ማስተማራችሁ ጠቃሚ የሆነው ለዚህ ነው። ከዚህም ሌላ ትክክል ወይም ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ መመሪያ መስጠታችሁ አስፈላጊ ነው።

እነዚህን ነገሮች እንዲያዳብሩ ልጆችን መርዳት ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ነው። “በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ገሥጽ፣ ውቀስ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ማስፈለጉ የማይቀር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) እስራኤላውያን ወላጆች የአምላክን ሕግ በተመለከተ “ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) ይህ ጥቅስ እንደሚያመለክተው ለልጆቻችሁ ቀጣይ የሆነ ትምህርት መስጠታችሁ አስፈላጊ ነው።

ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ያስከትላል። ከእነዚህ መካከል እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።

ለማዳመጥ ጊዜ አለው

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመናገር ጊዜ እንዳለው’ ሁሉ ለማዳመጥም ጊዜ እንዳለው ይናገራል። (መክብብ 3:7) ታዲያ ልጃችሁ፣ እናንተን ጨምሮ ሌሎች በሚናገሩበት ጊዜ በትኩረት እንዲያዳምጥ ልታሠለጥኑት የምትችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ምሳሌ መሆን ነው። ልጆቻችሁን ጨምሮ ሌሎች ሲናገሩ እናንተ ራሳችሁ በትኩረት ታዳምጣላችሁ?

ልጆች ትኩረታቸው በቀላሉ ስለሚሰረቅ ከእነሱ ጋር ለመነጋገር በምትሞክሩበት ጊዜ ትዕግሥታችሁ ሊፈተን እንደሚችል ጥያቄ የለውም። እያንዳንዱ ልጅ ከሌሎች የተለየ ነው፤ ስለዚህ አስተዋዮች በመሆን ልጃችሁ የምትነግሩት ነገር እንዲገባው በምን መንገድ ሐሳባችሁን ብትገልጹለት የተሻለ እንደሆነ ለይታችሁ እወቁ። ለምሳሌ ያህል፣ በብሪታንያ የሚኖር ዴቪድ የሚባል አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ የነገርኳትን ነገር በራሷ አባባል እንድትደግምልኝ አደርጋለሁ። በመሆኑም እያደገች ስትሄድ የምንነግራትን ነገር ይበልጥ ማዳመጥ ጀምራለች።”

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በሚያስተምርበት ጊዜ “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 8:18) አዋቂዎች እንዴት እንደሚያዳምጡ ማሰብ ካስፈለጋቸው ልጆችማ እንዲህ ማድረግ ይበልጥ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም!

“እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ”

መጽሐፍ ቅዱስ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” በማለት ይናገራል። (ቆላስይስ 3:13) ልጆች ይቅር ባይ እንዲሆኑ ሥልጠና ሊሰጣቸው ይችላል። እንዴት?

በጥሞና ማዳመጥን አስመልክቶ ቀደም ሲል እንደተወያየነው ሁሉ በነፃ ይቅር በመባባል ረገድም ምሳሌ መሆን ያስፈልጋችኋል። ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ይቅር ባይ እንደሆናችሁ ልጆቻችሁ እንዲያዩ አድርጉ። መሪና የምትባል በሩሲያ የምትኖር አንዲት እናት ይህን ለማድረግ ትጥራለች። “ሌሎችን ይቅር በማለት፣ ለሰላም ስንል ነገሮችን በመተው እንዲሁም ሌሎችን ባለመቀየም ለልጆቻችን ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እንጥራለን” ብላለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ስህተት ስሠራ ልጆቼን ይቅርታ እጠይቃለሁ። እነሱም ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት እንዲሁ ማድረግን እንዲማሩ እፈልጋለሁ።”

አለመግባባቶችን መፍታት መቻልና ይቅር ባይ መሆን ልጆች ትልቅ ሰው ሲሆኑ የግድ የሚያስፈልጋቸው ባሕርይ ነው። ስለዚህ ልጆቻችሁ ለሌሎች አሳቢ እንዲሆኑና ለጥፋታቸው ኃላፊነት መውሰድን እንዲለምዱ ከአሁኑ አሠልጥኗቸው። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ በጣም የሚጠቅማቸው ውድ ስጦታ ትሰጧቸዋላችሁ።

“አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ”

“ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ” በተባለው በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ልጆቻችሁ አመስጋኝ እንዲሆኑ ማሠልጠን የምትችሉት ገና ትንንሾች እያሉ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” በማለት ጽፏል።—ቆላስይስ 3:15

ልጆች ገና ትንንሾች እያሉም እንኳ ጥሩ ምግባር ማሳየትንና ለሌሎች አሳቢ መሆንን ሊማሩ ይችላሉ። እንዴት? ዶክተር ካይል ፕሩዬት “የአመስጋኝነትን መንፈስ በልጆቻችሁ ውስጥ መቅረጽ የምትችሉበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ በቤት ውስጥ ሁልጊዜ አመስጋኝ መሆን ነው” በማለት ወላጆች በተሰኘ መጽሔት ላይ ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ይህም ሲባል ሌሎች ለሚያደርጉላችሁ እገዛ ወይም ለሚያሳዩአችሁ አሳቢነት ምን ያህል አመስጋኞች እንደሆናችሁ አዘውትራችሁ ትገልጻላችሁ ማለት ነው። . . . ይህ እንዲሁ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ነገር አይደለም።”

በብሪታንያ የሚኖረው ሪቻርድ ይህን ለማድረግ ይጣጣራል፤ “እኔና ባለቤቴ ደግነት ያሳዩንን ሰዎች፣ ለምሳሌ አስተማሪዎችን ወይም ወላጆቻችንን እንዴት ማመስገን እንደሚቻል በተግባር እናሳያለን” ብሏል። “አንድ ቦታ ተጋብዘን ስንሄድ ለቤተሰቡ ምስጋናችንን ለመግለጽ ካርድ ካዘጋጀን በኋላ ልጆቹ በሙሉ እንዲፈርሙበት ወይም ሥዕል እንዲሥሉበት እናደርጋለን።” ልጆቻችሁ መልካም ምግባር ማሳየትንና አመስጋኝ መሆንን መማራቸው የኋላ ኋላ ከሌሎች ጋር ዘላቂና የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

“ልጅን ከመቅጣት ወደ ኋላ” አትበሉ

ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ ማንኛውም ድርጊት የሚያስከትለው ውጤት እንዳለ ማወቃቸው አስፈላጊ ነው። ልጆች ገና በትንሽነታቸውም እንኳ ለሚፈጽሙት ድርጊት ተጠያቂ ናቸው፤ ለወላጆቻቸው ሥልጣን ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤትና በማኅበረሰቡ ውስጥ ላለው ሥልጣን መገዛት ይኖርባቸዋል። ልጆቻችሁ የዘሩትን እንደሚያጭዱ ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ። (ገላትያ 6:7) እንዴት?

መጽሐፍ ቅዱስ “ልጅን ከመቅጣት ወደ ኋላ አትበል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 23:13) ልጃችሁ አንድ ጥፋት ካጠፋ እንደሚቀጣ በግልጽ ነግራችሁት ከሆነ ልጁን ከመቅጣት ወደኋላ አትበሉ። “የተናገሩትን ቃል መጠበቅ አስፈላጊ ነው” በማለት ኖርማ የምትባል በአርጀንቲና የምትኖር አንዲት እናት ትናገራለች። “የተናገሩትን አለመፈጸም አንድ ልጅ የፈለገውን ለማግኘት የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች እንዲፈላልግ ያበረታታዋል።”

ወላጆች፣ አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን መዘዞች ልጆቻቸው በቅድሚያ እንዲያውቁ በማድረግ ልጆቹ ጥፋት ከፈጸሙ በኋላ የሚፈጠረውን አተካራ ማስወገድ ይችላሉ። ልጆችም መመሪያዎችንና እነዚህን መመሪያዎች መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ ካወቁ፣ እንዲሁም ቅጣቱ በመለማመጥ የማይቀር መሆኑን ከተገነዘቡ ብዙውን ጊዜ የታዘዙትን ነገር ያለማንገራገር ይፈጽማሉ።

እርግጥ ነው፣ ተግሣጽ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በቁጣ መሰጠት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ” በማለት ይናገራል። (ኤፌሶን 4:31) ተግሣጽ መቼም ቢሆን በጭካኔ የሚሰጥ ቅጣት ሊሆን አይገባም፤ እንዲሁም አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት የሚያስከትል መሆን የለበትም።

ይሁን እንጂ ልጃችሁ ትዕግሥታችሁን የሚፈታተን ነገር በሚያደርግበት ጊዜ ቁጣችሁን መቆጣጠር የምትችሉት እንዴት ነው? በኒው ዚላንድ የሚኖር ፒተር የሚባል አንድ አባት “ይህ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም” በማለት በግልጽ ተናግሯል፤ “ይሁን እንጂ ልጆች፣ የተቀጡት ወላጃቸው ራሱን መቆጣጠር ስለተሳነው ሳይሆን በሠሩት ጥፋት የተነሳ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።”

ፒተርና ባለቤቱ፣ ተግሣጽ የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም እንዲያስተውሉ ልጆቻቸውን ይረዷቸዋል። ፒተር “ልጆቹ መጥፎ ነገር ፈጽመው እንኳ ቢሆን እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ከማሳየት ይልቅ ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንደሚገባቸው እንነጋገራለን” ብሏል።

“ምክንያታዊነታችሁ . . . የታወቀ ይሁን”

አምላክ ለሕዝቡ የሚሰጠውን እርማት በተመለከተ “ተገቢውን ቅጣት እሰጥሃለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 46:28) እናንተም ተገቢና ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት የምትሰጡ ከሆነ ጥሩ ውጤት ታገኛላችሁ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች “ምክንያታዊነታችሁ . . . የታወቀ ይሁን” በማለት ጽፎላቸዋል።—ፊልጵስዩስ 4:5

ምክንያታዊ መሆን የልጆቻችሁን ክብር በማይነካ መልኩ እርማት መስጠትን ይጨምራል። በጣሊያን የሚኖር ሳንቲ የሚባል አንድ አባት እንዲህ ይላል፦ “ወንዱንም ሆነ ሴቷን ልጄን ፈጽሞ አላንቋሽሻቸውም። ከዚህ ይልቅ የችግሩን መንስኤ ለይቼ ለማወቅና ይህን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት እጥራለሁ። በተቻለ መጠን ልጆቼን በሌሎች ፊት ሌላው ቀርቶ አንዳቸውን በሌላው ፊት አልቀጣም። እንዲሁም በሰው ፊትም ሆነ ለብቻችን ስንሆን ድክመቶቻቸውን እያነሳሁ አላሾፍባቸውም።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሪቻርድም ቢሆን ምክንያታዊ መሆን ያለውን ጥቅም ተገንዝቧል። “ልጆች ባጠፉ ቁጥር የቅጣቱን መጠን እየጨመሩ መሄድ አይገባም” ይላል። “ልጁን አንድ ጊዜ ከቀጣችሁት በኋላ ጥፋቱን ደጋግማችሁ እያነሳችሁ መውቀስ ተገቢ አይደለም።”

ልጆችን ማሳደግ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ቢሆንም ትልቅ ወሮታ ያስገኛል። ዬሌና የምትባል በሩሲያ የምትኖር አንዲት እናት ይህን ተገንዝባለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “ከልጄ ጋር ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ ስል በሳምንት ውስጥ የተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ለመሥራት መርጫለሁ። ይህን ማድረግ ጥረት የሚጠይቅ ከመሆኑም ሌላ ገቢያችን እንዲቀንስ ያደርጋል፤ ይሁንና እንዲህ ማድረጌ ልጄን ምን ያህል እንደሚያስደስተውና በጣም እንዳቀራረበን ስመለከት በከፈልኩት መሥዋዕት አልቆጭም።”

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች ለሌሎች አሳቢነት እንዲያሳዩ ሊሠለጥኑ ይችላሉ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለልጆቻችሁ እርማት የምትሰጡት ክብራቸውን በማይነካ መልኩ መሆን ይኖርበታል