በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ወላጆቼ ስሜቴን የማይረዱኝ ለምንድን ነው?

ወላጆቼ ስሜቴን የማይረዱኝ ለምንድን ነው?

ከዚህ በታች የቀረበውን ውይይት እንደምትመለከት አድርገህ አስብ።

ዓርብ ምሽት 12 ሰዓት ገደማ ነው፤ የ17 ዓመቱ ዳንኤል ከቤት ለመውጣት ይዘገጃጃል፤ ወላጆቹ የሚመለስበትን ሰዓት እንዳይጠይቁት ስለፈራ ፈጠን ፈጠን ብሎ ወደ በሩ በማምራት “ቻው!” አላቸው።

ጥያቄው ግን አልቀረለትም።

እናቱ “ዳኒ፣ ስንት ሰዓት ትመለሳለህ?” አለችው።

ዳኒ ወደኋላ መለስ ብሎ “እምም . . . እእእ . . . ትንሽ ቆያለሁ፤ ግን አትጠብቁኝ” አለ። ከዚያም በፍጥነት በሩን ከፍቶ ሊወጣ ሲል አባቱ “ቆይ እንጂ ዳንኤል፣ ምንድን ነው ጥድፊያው?” አለው።

ዳኒ አሁንም እንደገና መለስ አለ፤ አባቱም ኮስተር ብሎ “ከአራት ሰዓት በኋላ ማምሸት እንደማይቻል ታውቃለህ አይደል? አንዲት ደቂቃ እንዳታሳልፍ!” አለው።

ዳኒም “እንዴ አባዬ” ካለ በኋላ እንደመነጫነጭ እያለ “ጓደኞቼ በዚህ ሰዓት መግባት እንዳለብኝ ቢሰሙ ምን ያህል እንደሚያሾፉብኝ ታውቃለህ?” አለ።

አባቱ ግን ከአቋሙ ፍንክች አላለም። “ነግሬሃለሁ እንግዲህ፣ አንዲት ደቂቃ እንዳታሳልፍ!” አለው።

አንተም እንደዚህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቅ ይሆናል። ቤት ከምትገባበት ሰዓት ብቻ ሳይሆን ከሙዚቃ ምርጫህ፣ ከጓደኞችህ ወይም ደግሞ ከአለባበስህ ጋር በተያያዘ ወላጆችህ ያወጡት ሕግ ጥብቅ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

“እናቴ ካገባች በኋላ የእንጀራ አባቴ በማዳምጣቸው ሙዚቃዎች ሁሉ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ጀመረ። ሲዲዎቼን በሙሉ መጣል ነበረብኝ!”​ብራንደን *

“እናቴ ‘ጓደኞች የሌሉሽ ለምንድን ነው?’ እያለች ሁልጊዜ ትጨቀጭቀኛለች። ሆኖም ከአንዳንድ ልጆች ጋር ለመዝናናት እንድትፈቅድልኝ ስጠይቃት ልጆቹን ስለማታውቃቸው አብሬያቸው እንዳልሆን ትከለክለኛለች። ይህ ደግሞ በጣም ያበሳጫል!”​ካሮል

“አባቴና የእንጀራ እናቴ እንድለብስ የሚፈልጉት ሰፊ የሆኑ ቲሸርቶችን ነው። በዚያ ላይ ደግሞ አባቴ ቁምጣዎቼ ከጉልበት በላይ ከሆኑ ‘በጣም አጥረዋል’ ብሎ ድርቅ ይላል!”​ሴሬና

አንተና ወላጆችህ መስማማት ካቃታችሁ ምን ማድረግ ትችላለህ? ጉዳዩን ልትነጋገሩበት ትችሉ ይሆን? “ወላጆቼ ብዙ ጊዜ ማዳመጥ አይፈልጉም” በማለት የ17 ዓመቷ ጆአን ትናገራለች። የ15 ዓመቷ ኤሚ ደግሞ “ወላጆቼ ስሜቴን እንደማይረዱልኝ ከተሰማኝ ዝም ማለት እመርጣለሁ” ትላለች።

ሆኖም ቶሎ ተስፋ አትቁረጥ! ወላጆችህ አንተ ከምታስበው በላይ ለማዳመጥ ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አምላክም እንኳ ሰዎች ጉዳያቸውን ሲያቀርቡለት ያዳምጣቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ ስለ ዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ያቀረበውን ልመና ይሖዋ ሰምቶታል።​—ዘፀአት 32:7-14፤ ዘዳግም 9:14, 19

ይሁንና ወላጆችህ የአምላክን ያህል ምክንያታዊ እንዳልሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ደግሞም ሙሴ ለይሖዋ ባቀረበው ጉዳይና አንተ ከወላጆችህ ጋር በምትነጋገርበት ነገር መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ ሙሴ ያቀረበው ጥያቄ የአንድን ብሔር ዕጣ የሚመለከት ሲሆን አንተ ከወላጆችህ ጋር የምትነጋገረው ግን ትንሽ አምሽተህ መግባት ስለፈለግህ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ በሁለቱም ሁኔታዎች የሚሠራው ደንብ ተመሳሳይ ነው፦

የምትናገረው ነገር ምክንያታዊ ከሆነ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች፣ ይኸውም ወላጆችህ ጆሯቸውን ሊሰጡህ ይችላሉ።

ተሰሚነት እንድታገኝ የሚያደርገው ቁልፍ ጉዳይህን የምታቀርብበት መንገድ ነው! ቀጥሎ ያሉት ነጥቦች ጉዳይህን ስታቀርብ ይበልጥ ተሰሚነት እንድታገኝ ይረዱሃል፦

  1. ጉዳዩ ምንድን ነው? አንተና ወላጆችህ ልትስማሙበት ያልቻላችሁትን ጉዳይ ከዚህ በታች ጻፍ።

  2. ምን ይሰማሃል? ወላጆችህ በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮብሃል? የሰጡህ ምላሽ ስሜትህን ጎድቶታል? አሳዝኖሃል? አሳፍሮሃል? በእነሱ ላይ እምነት እንድታጣ አድርጎሃል? ወይስ ሌላ ስሜት ፈጥሮብሃል? ስሜትህን ከታች ባለው ቦታ ላይ ጻፍ። (ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ዳንኤል ቤት የሚገባበትን ሰዓት በተመለከተ ወላጆቹ ያወጡት ጥብቅ መመሪያ በጓደኞቹ ፊት እንደሚያሳፍረው ገልጿል።)

  3. እንደ ወላጅ ሆነህ ለማሰብ ሞክር። በመጀመሪያው ነጥብ ላይ የገለጽከው ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ልጅ እንዳለህ አድርገህ አስብ። አንተ ወላጅ ብትሆን ኖሮ በጣም የሚያሳስብህ ነገር ምን ይሆን ነበር? ለምን? (ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተገለጹት የዳንኤል ወላጆች ልጃቸው ቢያመሽ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ፈርተው ሊሆን ይችላል።)

  4. ጉዳዩን እንደገና ገምግም። ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስጥ፦

    የወላጆችህ አመለካከት ምን ጥቅም ያስገኛል?

    ስጋታቸውን ለመቀነስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

  5. ጉዳዩን ከወላጆችህ ጋር ተወያይበት፤ እንዲሁም አብራችሁ መፍትሔ ፈልጉ። ከላይ የተገለጹትን ነጥቦች በተግባር በማዋል እንዲሁም “ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ . . . ” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች ከግምት በማስገባት ከወላጆችህ ጋር ብስለት በሚንጸባረቅበት መንገድ መነጋገር ትችላለህ። ኬሊ ከአባቷና ከእናቷ ጋር በዚህ መንገድ መነጋገር ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “መከራከር የትም አያደርሳችሁም፤ ደግሞም ተከራክራችሁ አታሸንፉም። እኔ የምጠቀምበት ዘዴ በጉዳዩ ላይ ከወላጆቼ ጋር ተነጋግሬ መፍትሔ መፈለግ ነው። እኔም ሆንኩ ወላጆቼ በአቋማችን ድርቅ ከማለት ይልቅ ሁላችንንም የሚያስማሙ ነጥቦች ስለምናነሳ በአብዛኛው መግባባታችን አይቀርም።”

 

^ አን.12  በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።