በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በባሕር ዳርቻዎች፣ በመናፈሻዎችና በአደባባዮች ላይ ማጨስን የሚከለክል ሕግ በኒው ዮርክ ሲቲ ወጣ። ሕጉን የተላለፉ ሁሉ 50 የአሜሪካ ዶላር መቀጫ ይከፍላሉ። ባለሥልጣናቱ፣ ሌላ ተቆጣጣሪ ሳያስፈልግ ሁሉም መብትና ግዴታውን አክብሮ እንደሚንቀሳቀስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።​—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ሴት [ሕፃናትን] እየመረጡ ማስወረድ (በተለይ ደግሞ ሴት የበኩር ልጅ ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ) በሕንድ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።” ሴት የበኩር ልጅ ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚወለዱት ሴት ሕፃናት ቁጥር ከወንዶቹ ጋር ሲነጻጸር በ1990 ለ1,000 ወንዶች 906 ሴቶች የነበረ ሲሆን በ2005 ግን ይህ ቁጥር አሽቆልቁሎ 836 ደርሷል።​—ዘ ላንሴት፣ ብሪታንያ

የዓለም የጤና ድርጅት፣ “ገመድ አልባ ከሆኑ የመገናኛ መሣሪያዎች እንደሚወጡ ያሉ” የሬዲዮ ሞገድ አስተላላፊ የሆኑ የኤሌክትሮማግኔቲክ ሞገዶችን “በሰው ልጆች ላይ ካንሰር ሊያመጡ ከሚችሉ ነገሮች” ተርታ ፈርጇቸዋል።​—ኢንተርናሽናል ኤጀንሲ ፎር ሪሰርች ኦን ካንሰር፣ ፈረንሳይ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪንደርፔስት ወይም ‘የከብቶች ቀሳፊ’ የተባለው በሽታ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አበሰረ። “ሰዎች ባደረጉት ርብርብ . . . ይህ ቫይረስ በመወገዱ . . . ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ የተደረገ የመጀመሪያው የእንስሳት በሽታ ሊሆን ችሏል፤ እንዲጠፉ ከተደረጉ የበሽታ ዓይነቶች ደግሞ ከፈንጣጣ ቀጥሎ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል።”​—የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ ጣሊያን

ለመዓት ቀን መዘጋጀት

ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት “የመዓት ቀን በኒው ዮርክ ቢመጣ ሊረዳ የሚችል የሕግ መመሪያ” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። መጽሔቱ፣ ወደፊት “ሌላ የሽብርተኞች ጥቃት ሲሰነዘር፣ ጎጂ የሆኑ ጨረሮች ወይም ኬሚካሎች ብክለት ሲፈጥሩ ወይም ስፋት ያለው ወረርሽኝ ሲከሰት” ሊነሱ ከሚችሉ ከባድ ሕግ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዳኞችንና ጠበቆችን ሊጠቅም የሚችል መመሪያ የያዘ ጽሑፍ እንደወጣ ዘግቧል። የኒው ዮርክ ግዛት ፍርድ ቤት እና በዚያ ግዛት የሚገኘው የጠበቆች ማኅበር ያዘጋጁት ይህ መመሪያ የታመሙ ሰዎችን አግልሎ ማቆየትን፣ ሕዝብ አካባቢን ለቆ እንዲወጣ ማድረግን፣ ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ፍተሻ ማካሄድን፣ የተበከሉ እንስሳትን መግደልን እና የማኅበረሰቡን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ሕጋዊ መብት መንጠቅን የመሳሰሉ ጉዳዮችን በተመለከተ በሥራ ላይ ያለው ሕግ ምን እንደሚል በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችሉ ማጣቀሻዎችን ይዟል።

አሮጌ ትራሶች

ንጹሕ ከሆኑ የትራስ ልብሶች ሥር “በጣም ቀፋፊ የሆኑ ነገሮች” እንደሚገኙ ለንደን ባለው ሴይንት ባርትስ ሆስፒታል ውስጥ ዋና የሳይንስ ሊቅ የሆኑት አርት ተከር ተናግረዋል። የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት የእኚህን ሰው የምርምር ውጤት አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ላይ ሁለት ዓመት ያገለገለ አንድ ትራስ ከጠቅላላ ክብደቱ አንድ ሦስተኛውን የሚይዘው “በሕይወት ያሉና የሞቱ ጥቃቅን ነፍሳት፣ ከነፍሳቱ የሚወጣ ቆሻሻ፣ ከሰውነታችን ላይ የሚረግፍ የደረቀ ቆዳና ባክቴሪያ” ጥርቅም እንደሆነ ገልጿል። ትራሶች አለርጂ ለሚያመጡ ነገሮች፣ ለጀርሞችና ለጥቃቅን ነፍሳት ምቹ የመራቢያ ስፍራ ናቸው። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? ዘ ታይምስ እንዲህ ብሏል፦ “ጥቃቅን ነፍሳት . . . ለፀሐይ ብርሃን ሲጋለጡ ደርቀው ይሞታሉ። በሌላ አባባል እንደ ድሮው አልጋን ማናፈስ ጥቃቅን ነፍሳትን ለማስወገድ ይጠቅማል ማለት ነው።” ትራሱን በሳሙና ማጠብ ብቻውን ነፍሳቱን ለመግደል አይረዳም፤ ይሁንና ከ60 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚበልጥ ሙቀት ባለው ውኃ ማጠብ ነፍሳቱን የሚገድል ከመሆኑም ባሻገር ውኃው አብዛኞቹን ነፍሳት አጥቦ ያወጣቸዋል።