በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍትሕ ማጣት ያንገበግባል!

ፍትሕ ማጣት ያንገበግባል!

ፍትሕ ማጣት ያንገበግባል!

ማይክል አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተከስሶ በቴክሳስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለ27 ዓመታት ያለጥፋቱ ከታሰረ በኋላ በ2010 ተለቀቀ። ከእስር ነፃ የሆነው የዲ ኤን ኤ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ነው፤ በእሱ ላይ ፍርድ በተሰጠበት ወቅት በዚህ የማጣራት ዘዴ መጠቀም አልተጀመረም ነበር። ባለሥልጣናቱ ድርጊቱን የፈጸሙትን ሰዎች ማንነት ከጊዜ በኋላ ቢያውቁም በይርጋ ሕግ መሠረት ክስ መመሥረት የሚቻልበት ጊዜ በማለፉ ወንጀለኞቹን ለፍርድ ማቅረብ አልተቻለም።

ብዙ ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት ሳያገኙ ያመልጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በብሪታንያ “ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ መፍትሔ ያላገኙ የግድያ ወንጀሎች በእጥፍ የጨመሩ ሲሆን ፖሊስና ፍርድ ቤቶች ለወንጀል ድርጊቶች በተሳካ ሁኔታ እልባት መስጠት አለመቻላቸው ፍርሃት እንዲነግስ [ማድረጉን]” ዘ ቴሌግራፍ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ይናገራል።

የብሪታንያ ፖሊስ በነሐሴ 2011 ተከስቶ የነበረን ሌላ ዓይነት ወንጀል ለመቆጣጠር አበሳውን አይቶ ነበር፤ በዚህ ወቅት በለንደን፣ በሊቨርፑል፣ በበርሚንግሃምና በሌሎች ከተሞች ሕዝባዊ ዓመፅ ተነስቶ ነበር። ረብሸኞቹ የተለያዩ ነገሮችን በእሳት አያይዘዋል፣ የመደብሮችን መስኮት ሰብረዋል እንዲሁም ዝርፊያ አካሂደዋል። በመሆኑም በንግድ ቦታዎች፣ በመኖሪያ ቤቶችና በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ብቻ ሳይሆን ሰዎች መተዳደሪያቸውን ጭምር እንዲያጡ አድርገዋል። ለመሆኑ ይህን ዓመፅ ለማካሄድ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? አብዛኞቹን ሰዎች ለረብሻ እንዲወጡ ያነሳሳቸው ስግብግብነት እንጂ ሌላ ምክንያት አልነበረም። አንዳንዶች ግን በዚህ ድርጊት የተካፈሉት ተፈጽሞብናል ብለው ለሚያስቡት የፍትሕ መጓደል አጸፋውን ለመመለስ ይመስላል። አንዳንድ ተንታኞች እንደተናገሩት እነዚህ ነውጠኞች፣ በተጎሳቆሉ ሰፈሮች ያደጉና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ተስፋ የሌላቸው፣ ብስጩ ብሎም መንግሥት እንደረሳቸው የሚሰማቸው ወጣቶች ሳይሆኑ አይቀሩም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ኢዮብ “‘ተበደልሁ!’ ብዬ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ ባሰማም፣ ፍትሕ አላገኝም” ብሎ ነበር። (ኢዮብ 19:7) በዛሬው ጊዜም ቢሆን ‘የፍትሕ ያለህ’ ብለው የሚጮኹ ብዙ ሰዎች በአብዛኛው ሰሚ አያገኙም። በእርግጥ የፍትሕ መዛባትን ማስወገድ የሚችል አካል ይኖራል? ወይስ ወደፊት ፍትሕ የሚሰፍንበት ሥርዓት እንደሚመጣ ተስፋ ማድረግ ሞኝነት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ለፍትሕ መዛባት መንስኤ የሆኑትን አንዳንድ ነገሮች መመርመር አለብን።