በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

▪ ካረን፣ ሁለት ወጣቶች ትላልቅ ካርቶኖችን ይዘው ሲገቡ ስታይ ግብዣ ወደሚደረግበት ቤት ከደረሰች አሥር ደቂቃ እንኳ አልሆናትም ነበር። ካርቶኖቹ ውስጥ ያለው ምን እንደሆነ ለማወቅ ያን ያህል አልተቸገረችም። ቀደም ሲል እነዚሁ ልጆች በግብዣው ላይ “ብዙ የአልኮል መጠጥ” እንደሚኖር ሲናገሩ በጨረፍታ ሰምታለች። እርግጥ ነው፣ ካረን ይህን ለወላጆቿ አልነገረቻቸውም። ካረን ‘ልጆቹ እንዲህ ያሉት ለቀልድ ነው’ የሚል ሰበብ በማቅረብ ራሷን ለማሳመንም ሞክራለች። ደግሞም ቤት ውስጥ አዋቂዎች እንደሚኖሩ ጠብቃ ነበር።

በድንገት ካረን “ምን ሆነሽ ነው እዚህ የተገተርሽው? መቼም የሰው ግብዣ ማበላሸት ልማድሽ ነው!” የሚል ድምፅ ከኋላዋ ሰማች። ካረን ጓደኛዋን ጄሲካን ለማየት ዞር አለች። ጄሲካ ሁለት የተከፈቱ ቢራዎችን ይዛለች። ከዚያም አንዱን ቢራ ለካረን እየሰጠቻት “ደግሞ ለመጠጣት አልደረስኩም እንዳትይኝ!” አለቻት።

ካረን ግብዣውን ለመቀበል አልፈለገችም። ያም ሆኖ መጠጡን እንድትቀበል የሚገፋፋት ውስጣዊ ስሜት ከገመተችው በላይ ከፍተኛ ነበር። ካረንን ያሳሰባት አልኮል የመጠጣቱ ጉዳይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የጋበዘቻት ጓደኛዋ መሆኗ ነው። ከዚህም ሌላ ጄሲካ እንዳለችው የሰው ግብዣ የምታበላሽ ሆና መታየት አልፈለገችም። በተጨማሪም ጄሲካ አሉኝ ከምትላቸው ጓደኞቿ መካከል አንዷ ናት። ደግሞስ ብትጠጣ ምን አለበት? ካረን፣ ‘ዕፅ ውሰጂ ወይም የጾታ ብልግና ፈጽሚ አልተባልኩ፤ ቢራ እኮ ነው!’ እያለች ከራሷ ጋር ትሟገታለች።

በወጣትነትህ የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙሃል። እነዚህ ፈተናዎች አብዛኛውን ጊዜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የተያያዙ ናቸው። ራሞን * የተባለ የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ ብሏል:- “በትምህርት ቤታችን ያሉት ሴቶች በጣም ፈጣጦች ናቸው። ሊያሻሹህና ዝም የምትላቸው እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ለማየት ይፈልጋሉ። ‘ተዉ!’ ብትላቸው እንኳ አይሰሙህም።” የ17 ዓመቷ ዲያናም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሟታል። እንዲህ ብላለች:- “በአንድ ወቅት፣ አንድ ልጅ አቀፈኝ። እኔም እጁን መታሁትና ‘ምን ማድረግህ ነው? የት ታውቀኛለህ?’ ብዬ ጮኽኩበት።”

አንተም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። ምናልባትም እነዚህ ሁኔታዎች ማቆሚያ ያላቸው ላይመስሉ ይችላሉ። አንድ ክርስቲያን እንደተናገረው “ተፈታታኝ ሁኔታ፣ አለማቋረጥ በራችሁን እንደሚያንኳኳ ሰው ነው፤ በሩን መክፈት ባትፈልጉም እንኳ ማንኳኳቱን አያቋርጥም።” አንተስ ሳትፈልገው ብዙ ጊዜ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥምሃል? ለምሳሌ ያህል፣ ከሚከተሉት መካከል የሚፈትንህ የትኛው ነው?

□ ሲጋራ ማጨስ

□ አልኮል መጠጣት

□ ዕፅ መውሰድ

□ የብልግና ፊልሞችንና ሥዕሎችን መመልከት

□ የጾታ ብልግና መፈጸም

□ ሌላ ․․․․․

ከእነዚህ ውስጥ ምልክት ያደረግህበት ካለ ‘ፈጽሞ ክርስቲያን መሆን አልችልም’ ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። መጥፎ ምኞቶችን መቆጣጠርና ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ትማራለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? እንድትፈተን የሚያደርግህ ነገር ምን መሆኑን ማወቅህ ጠቃሚ ነው። ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ሦስት ምክንያቶች ተመልከት።

1. አለፍጽምና። የሰው ልጆች ፍጽምና ስለሚጎድላቸው መጥፎ ነገር የማድረግ ዝንባሌ አላቸው። ጎልማሳ ክርስቲያን የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ “በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። (ሮሜ 7:21) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጻድቅ የሆነ ሰውም ቢሆን አንዳንዴ ‘የሥጋ ምኞትና የዐይን አምሮት’ ያስቸግረው ይሆናል። (1 ዮሐንስ 2:16) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች” ስለሚል መጥፎ ነገሮችን ማውጠንጠን ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።—ያዕቆብ 1:15

2. ውጭያዊ ተጽዕኖዎች። በየትኛውም ቦታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ትሩዲ እንዲህ ብላለች:- “በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ ሰዎች ሁልጊዜ ስለ ጾታ ግንኙነት ያወራሉ። በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችም ሆነ በፊልሞች ላይ የጾታ ግንኙነት የሚያጓጓና አስደሳች እንደሆነ ተደርጎ ይቀርባል። እንዲህ ያለ ድርጊት መፈጸም የሚያስከትለው መዘዝ አብዛኛውን ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርብ አይታይም።” ትሩዲ እንዲህ ያሉት ነገሮች ምን ያህል ከባድ ተጽዕኖዎች እንደሚያሳድሩ ከተሞክሮዋ ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች:- “የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ የወረት ፍቅር ያዘኝ። እናቴ በዚህ ሁኔታ የምቀጥል ከሆነ ማርገዜ እንደማይቀር ቁጭ አድርጋ ነገረችኝ። እናቴ እንደዚያ ማሰቧ በጣም አስደነገጠኝ! ይሁንና ከሁለት ወር በኋላ አረገዝኩ።”

3. ‘የወጣትነት ምኞት።’ (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ይህ ሐረግ፣ ተቀባይነት ማግኘትንና በሌሎች ዘንድ እንደ ትልቅ ሰው የመታየት ፍላጎትን ጨምሮ ወጣቶች ያላቸውን ማንኛውንም ዓይነት ምኞት ያመለክታል። እነዚህ ምኞቶች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም ቁጥጥር ካልተደረገባቸው ግን መጥፎ ፍላጎቶችን ለመቋቋም የምናደርገውን ትግል ይበልጥ ያከብዱብናል። ለአብነት ያህል፣ እንደ ትልቅ ሰው ለመታየት ያለህ ፍላጎት ወላጆችህ ያስተማሩህን ጥሩ የሥነ ምግባር ደንቦች ቀስ በቀስ ችላ እንድትል ሊያደርግህ ይችላል። ስቲቭ በ17 ዓመቱ ያጋጠመው ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ ይላል:- “ከተጠመቅሁ ብዙም ሳይቆይ በወላጆቼ ላይ ያመጽኩ ሲሆን አታድርግ ያሉኝን ሁሉ ማድረግ ጀመርኩ።”

ቀደም ሲል የተጠቀሱት ተጽዕኖዎች ከባድ እንደሆኑ አይካድም። ያም ሆኖ መጥፎ ምኞቶችን ማሸነፍ ትችላለህ። ሆኖም ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

▪ በመጀመሪያ በጣም ፈታኝ የሆነብህን ነገር ማወቅ ይኖርብሃል። (ምናልባትም ቀደም ሲል ባለው መጠይቅ አማካኝነት አውቀኸው ይሆናል።)

▪ ቀጥሎም ‘ፈተናው ይበልጥ የሚከሰተው መቼ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከሚከተሉት ውስጥ በአንዱ ላይ ምልክት አድርግ:-

□ በትምህርት ቤት

□ በሥራ ቦታ

□ ብቻዬን ስሆን

□ ሌላ

ተፈታታኝ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥምህ መቼ እንደሆነ ማወቅህ ፈተናዎቹን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ አስብ። ካረን በግብዣው ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥማት የሚችል መሆኑን የሚጠቁም ምን ነገር ነበር? እንዲህ ዓይነቱን ተፈታታኝ ሁኔታ ለማስወገድስ ቀድሞውኑ ምን ልታደርግ ትችል ነበር?

▪ አሁን (1) ተፈታታኝ የሚሆንብህን ነገር እና (2) ብዙውን ጊዜ ሁኔታው የሚያጋጥምህ መቼ እንደሆነ ለይተህ አውቀሃል። በመሆኑም እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተሃል ማለት ነው። ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባው፣ መጥፎ ምኞት ከሚያሳድሩብህ ነገሮች ጋር ያለህን ግንኙነት መቀነስ ወይም ከእነዚህ ነገሮች ጭራሹኑ መራቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ነው። ምን ማድረግ እንደምትችል ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

․․․․․

(ምሳሌዎች:- ሲጋራ እንድታጨስ የሚገፋፉህ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት በኋላ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙህ ከሆነ ከእነሱ ጋር ላለመገናኘት ስትል መንገድህን መለወጥ ትችል ይሆናል። ኢንተርኔት ስትጠቀም በኮምፒውተርህ ላይ ሳትፈልግ የብልግና ሥዕሎች የሚመጡ ከሆነ እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ መልእክቶችን የሚያግድ ፕሮግራም መጫን ትችል ይሆናል። በተጨማሪም ከኢንተርኔት ላይ መረጃ ስትፈልግ የምታስገባቸውን ቃላት በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብህ ይሆናል።)

እርግጥ ነው፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አትችልም። ውሎ አድሮ አንድ ያልተጠበቀ ነገር እጅግ ተፈታታኝ ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ ሊያደርግህ ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ዝግጁ ሁን። ኢየሱስ ‘ሰይጣን በፈተነው’ ጊዜ ወዲያውኑ ተቃውሞታል። (ማርቆስ 1:13) ይህን ለማድረግ ያስቻለው ምንድን ነው? ከተጠየቀው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከማን ጎን መሰለፍ እንዳለበት ያውቅ ስለነበር ነው። እስቲ አስበው፣ ኢየሱስ ሮቦት አልነበረም። በፈተናው ሊሸነፍ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ምንጊዜም አባቱን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። (ዮሐንስ 8:28, 29) ኢየሱስ “ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነው” በማለት መናገሩ ይህን ያረጋግጣል።—ዮሐንስ 6:38

ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም ያለብህ ለምን እንደሆነ የሚገልጹ ሁለት ምክንያቶችን እንዲሁም ፈተናውን ለመቋቋም ማድረግ የምትችላቸውን ሁለት ነገሮች ከዚህ በታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

1. ․․․․․

2. ․․․․․

በሚያጋጥሙህ ፈተናዎች ስትሸነፍ ለምኞቶችህ ባሪያ እንደምትሆን አስታውስ። (ቲቶ 3:3) ታዲያ ምኞትህ እንዲቆጣጠርህ ለምን ትፈቅድለታለህ? ምኞትህ እንዲቆጣጠርህ ከመፍቀድ ይልቅ አንተ ራስህ እሱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጉልምስና ይኑርህ።—ቈላስይስ 3:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ፍጹም የሆኑ ፍጥረታት ሊፈተኑ ይችላሉ?—ዘፍጥረት 6:1-3፤ ዮሐንስ 8:44

▪ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በታማኝነት መቋቋም በሌሎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?—ምሳሌ 27:11፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:12

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እንዲህ ለማድረግ ሞክር

አንድ ኮምፓስ ውሰድና የኮምፓሱን አቅጣጫ አመልካች ቀስት ወደ ሰሜን አድርገው። ከዚያም ከኮምፓሱ ጎን ማግኔት አስቀምጥ። የኮምፓሱ አቅጣጫ አመልካች ቀስት ምን ሆነ? ቀስቱ ትክክለኛውን አቅጣጫ ማመልከቱን ትቶ ወደ ማግኔቱ ዞሯል።

ሕሊናህም ልክ እንደ ኮምፓሱ ነው። በሚገባ ከሠለጠነ ወደ “ሰሜን” ማለትም ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚያመለክት ሲሆን ጥበብ የተሞላባቸውን ውሳኔዎች እንድታደርግም ይረዳሃል። ይሁን እንጂ እንደ ማግኔቱ ካሉ መጥፎ ጓደኞች ጋር የምትገጥም ከሆነ የሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ የሥነ ምግባር አቋምህን ሊያዛባብህ ይችላል። ታዲያ ከዚህ ምን ትማራለህ? የሥነ ምግባር አቋምህን ሊያበላሹብህ ከሚችሉ ሰዎችም ሆኑ ሁኔታዎች ለመራቅ ጥረት አድርግ!—ምሳሌ 13:20

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እንዲህ አድርግ

አንድ ሰው መጥፎ ነገር እንድትፈጽም ሊገፋፋህ ሲሞክር ምን መልስ ልትሰጠው እንደምትችል አስብ። በዚህ ጊዜ ራስህን እያመጻደቅክ እንዳለ የሚያሳይ መልስ መስጠት አይኖርብህም። ከዚህ ይልቅ ሳትጨነቅ የመተማመን ስሜት እንዳለህ የሚያሳዩ ቀጥተኛ የተቃውሞ ሐሳቦችን መሰንዘርህ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አብሮህ የሚማር አንድ ልጅ ሲጋራ እንድታጨስ ቢጋብዝህ “ሲጋራህን አታባክን፤ አላጨስም!” ልትለው ትችላለህ።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚያጋጥሙህ ፈተናዎች ስትሸነፍ ለምኞቶችህ ባሪያ ትሆናለህ