በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

 ከዓለም አካባቢ

በ2007 ቻይና ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ ተከስቶ የማያውቅ ከባድ ድርቅ ስላጋጠማት 47 ሚሊዮን የሚያክሉ ቻይናውያን ለመጠጥ ውኃ እጥረት ተጋልጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ 42 ሚሊዮን ሰዎች አውሎ ነፋስ በቀላቀለ ከባድ ዝናብ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 180 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ በጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ ለችግር ተዳርጓል።—ዢንሁዋ የዜና አገልግሎት፣ ቻይና

“በ2003 በመላው ዓለም ከነበሩት ነፍሰ ጡሮች መካከል አንድ አምስተኛ የሚያህሉት ውርጃ ፈጽመዋል። በአውሮፓ ይህ አኃዝ ወደ አንድ ሦስተኛ ይጠጋል። . . . በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አገሮች . . . በ2003 ወደ 45 በመቶ የሚጠጉ ነፍሰ ጡሮች ውርጃ ፈጽመዋል።”—ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል፣ ብሪታንያ

አሰቃቂ ድርጊቶች የሚታዩባቸው የቪድዮ ጨዋታዎች በቤተ ክርስቲያን

‘በመቶ የሚቆጠሩ ቀሳውስትና ፓስተሮች ወጣት ምዕመናንን ወደ አብያተ ክርስቲያናት ለመሳብ ሲሉ እንግዳ የሆነ ዘዴ ማለትም እጅግ ተወዳጅ ሆኖም አሰቃቂ ድርጊቶች የሚታዩባቸው የቪድዮ ጨዋታዎችን መጠቀማቸው ከፍተኛ ጭንቀትና ትችት አስከትሏል’ ሲል ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ተናግሯል። ይህ ጨዋታ ለትላልቅ ሰዎች ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በዚህ ጨዋታ ወታደር ሆኖ የሚጫወተው ገጸ ባሕርይ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ ሌሎችን መግደል ይኖርበታል። ጋዜጣው እንደዘገበው የፕሮቴስታንትና የወንጌላውያን ወጣት ቡድኖችን ያደራጁት ሰዎች እንዲህ ያለው ትችት ቢሰነዘርባቸውም “ብዙ ወጣቶች የተኩስ ጨዋታ ለመጫወት ትልልቅ ስክሪን ወዳላቸው ቴሌቪዥኖች እንዲጎርፉ ለማድረግ ሲሉ ማዕከላቸውን በረቀቁ የቪድዮ ማጫወቻዎች ከመሙላት ወደኋላ አላሉም።”

የልጆች ማንነት ተሰረቀ

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ልጆች ማንነታቸው በመሰረቁ ምክንያት ወደፊት ብድር የማግኘት አጋጣሚያቸውና ከሌሎች ጋር የሚኖራቸው ዝምድና አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ወንጀል የሚፈጸመው በቤተሰባቸው አባል ስለሆነ ለበርካታ ዓመታት ሳይታወቅ ሊቆይ ይችላል። ጋዜጣው እንደዘገበው “አብዛኞቹ ሰዎች ሥራ ለመቀጠር፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት፣ የተማሪ ብድር ለማግኘት ወይም ቤት መግዣ ገንዘብ ለመበደር እስከሚያመለክቱበት ጊዜ ድረስ አንድ ሰው በሕገ ወጥ መንገድ ማንነታቸውን ሲጠቅም እንደነበር አይገነዘቡም።” አንዳንዶች ከዚያ ቀደም ብለው ሊያውቁ የሚችሉት አንድ አበዳሪ ድርጅት በስማቸው ሲጠራቀም የቆየውን ዕዳ ለማስከፈል በሚጠይቃቸው ጊዜ ብቻ ነው።

“ጠፍተው የቆዩት” የኑክሌር አረሮች

ነሐሴ 30, 2007 አንድ የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ቢ-52 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን “በክንፉ ላይ በስህተት የተጠመዱ” ስድስት ኑክሌር ክሩዝ ሚሳይሎችን ተሸክሞ በዩናይትድ ስቴትስ አየር ላይ ለሦስት ሰዓት ተኩል በረራ እንዳደረገ ዘ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። ጋዜጣው፣ የአውሮፕላኑ አብራሪዎቹም ሆኑ ሚሳይሎቹን የጫኑት ሠራተኞች “የተፈጠረውን ስህተት ለ36 ሰዓታት አላወቁም ነበር” ሲል ተናግሯል። ዘገባዎች እንዳመለከቱት “አረሮቹ የተቀባበሉ ባለመሆናቸው በሕዝብ ላይ ጥፋት የማድረስ አጋጣሚ እንዳልነበራቸው የአየር ኃይል ባለሥልጣናት ተናግረዋል።” ሆኖም አንድ አስተያየት ሰጪ “ይህ ጉዳይ በጣም ሊያሳስበን አይገባም?” ብለዋል።

እርግቦች የአየር ብክለትን መጠን ይለካሉ

በሰሜን ሕንድ የሚገኘው የራጃሽታን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ በጃይፑር ከተማ በሚኖሩ እርግቦች ላይ ባደረጉት ጥናት እነዚህ አእዋፍ የከተማ አየር ብክለት ምን ያህል እንደሆነ ለመለካት ሊያገለግሉ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። ዳውን ቱ ኧርዝ የተባለው መጽሔት ተጨማሪ ክፍል የሆነው የኒው ዴልሂው ግሎባል ታይምስ “በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙት የብረት አተሞች (Heavy metals) ወደ ላባዎቹ የሚገቡ ሲሆን [ላባዎቹ] ከረገፉ በኋላም እዚያው ይኖራሉ” ብሏል። እርግቦች አብዛኛውን ጊዜ የሚኖሩት በአንድ የተወሰነ አካባቢ በመሆኑ በላባቸው ላይ የሚገኘው የካድምየም፣ የክሮምየም፣ የመዳብና የሊድ መጠን አካባቢው ምን ያህል እንደተበከለ በትክክል ሊጠቁም ይችላል።