በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አደጋ ለመጋረጡ ምልክት ናቸው?

አደጋ ለመጋረጡ ምልክት ናቸው?

አደጋ ለመጋረጡ ምልክት ናቸው?

ዘ ኒው ዚላንድ ሄራልድ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “በቱቫሉ ደሴት ላይ የሚኖሩ ቫል ሌሳ የተባሉ የ73 ዓመት አረጋዊ የባሕር መጠን እየጨመረ ለመሆኑ ሳይንሳዊ መረጃ አያስፈልጋቸውም። እሳቸው ልጅ ሳሉ የነበሩ የባሕር ዳርቻዎች እየጠፉ ነው። ቤተሰባቸው ለምግብነት የሚጠቀምባቸው ሰብሎች ጨዋማ በሆነው ውኃ ተበላሽተዋል። በሚያዝያ [2007] ቤታቸው በጎርፍ በመጥለቅለቁ እንዲሁም ማዕበሉ ባመጣው ድንጋይና ፍርስራሽ በመሞላቱ መኖሪያቸውን ለቀው መሄድ ግድ ሆኖባቸዋል።”

ከባሕር ወለል በላይ ከ4 ሜትር የማይበልጥ ከፍታ ባላቸው በቱቫሉ ደሴቶች ላይ ለሚኖሩ ሰዎች የምድር ሙቀት መጨመር ሳይንስ የፈጠረው ወሬ ሳይሆን “በዕለታዊ ሕይወታቸው የሚመለከቱት ሐቅ” መሆኑን ሄራልድ ተናግሯል። * በሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ደሴቶቹን ለቀው የሄዱ ሲሆን ሌሎች በርካታ ሰዎችም ለመልቀቅ እየተዘጋጁ ነው።

በሌላ በኩል ግን በብሪዝበን፣ አውስትራሊያ የሚኖረው ሮበርት አትክልቱን ውኃ የሚያጠጣው በጎማ ሳይሆን በባልዲ እየቀዳ ነው። መኪናውን የቆሸሸ ውኃ ተጣርቶ እንደገና ጥቅም ላይ ወደሚውልበት የመኪና ማጠቢያ ቤት ካልወሰደ በቀር ቤቱ ማጠብ የሚችለው መስታወቱን፣ መስኮቶቹንና ታርጋውን ብቻ ነው። ለምን? ምክንያቱም ሮበርት የሚኖረው በምዕተ ዓመቱ ውስጥ ከደረሱት ሁሉ የከፋ ነው የተባለለት ድርቅ ባጠቃው የአገሪቱ ክፍል ስለሆነ ነው። ከዚህ የከፋ ችግር የሚታይባቸው ሌሎች አካባቢዎችም አሉ። በአውስትራሊያና በቱቫሉ ያሉት ችግሮች የምድር ሙቀት እንደጨመረ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው?

የአንዳንዶች ትንበያ

ብዙዎች ለምድር ሙቀት መጨመር ዋነኛው መንስኤ የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የምድር ሙቀት መጨመር በአየር ንብረትም ሆነ በአካባቢ ላይ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዋልታዎች አካባቢ ያለው ግግር በረዶ መቅለጡ እንዲሁም ውኃው በመሞቁ ምክንያት የውቅያኖሱ መጠን መጨመሩ የባሕር ወለል ከፍታ በፍጥነት እንዲጨምር ሊያደርገው ይችላል። በዚህም ምክንያት በዝቅተኛ ቦታ ላይ የሚገኙት እንደ ቱቫሉ ያሉ ደሴቶች በውኃ ሊዋጡ ይችላሉ። ተመሳሳይ ዕጣ ከሚጠብቃቸው ሥፍራዎች ሁለቱን ብቻ ለመጥቀስ ያክል የኔዘርላንድስና የፍሎሪዳ አብዛኞቹ አካባቢዎች ይገኙበታል። በሻንጋይ፣ በካልካታ፣ በከፊል ባንግላዴሽና በመሳሰሉት ቦታዎች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ከቀዬአቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ።

ከዚህም በላይ የምድር ሙቀት መጨመር በየጊዜው የሚከሰተውን ማዕበል፣ ጎርፍና ድርቅ ሊያባብስ ይችላል። ለሰባት ወንዞች መነሻ በሆነው በሂማልያ ሰንሰለታማ ተራራ ላይ ያለው ግግር በረዶ መቅለጡ፣ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ለንጹሕ ውኃ እጥረት እንዲጋለጥ ሊያደርገው ይችላል። ሕልውናው በበረዶ ላይ የተመካውን የዋልታ ድብን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ የእንስሳት ዝርያዎችም አደጋ ተደቅኖባቸዋል። እንዲያውም ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ብዙ ድቦች እየከሱ አልፎ ተርፎም በረሃብ እየተጠቁ ነው።

የምድር ሙቀት መጨመር ፈንገሶችን ጨምሮ ትንኞች፣ መዥገሮችና ሌሎች በሽታ አማጭ ተሕዋስያን በሰፊው እንዲሠራጩ ስለሚያደርግ በሽታ እንዲዛመት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። “በአየር ንብረት መለወጥ ሳቢያ የተደቀነው አደጋ የኑክሌር መሣሪያዎች ሊያስከትሉ ከሚችሉት አደጋ የማይተናነስ ነው” ሲል ቡሌቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “የሚያስከትለው ውጤት ቶሎ አይታይ ይሆናል። . . . ይሁን እንጂ የአየር ንብረት ለውጥ በቀጣዮቹ ሦስት ወይም አራት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ለሰብዓዊው ኅብረተሰብ ሕልውና መሠረት በሆነው ሥነ ምሕዳር ላይ ሊጠገን የማይችል ጉዳት ያስከትላል።” አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚያምኑት ለምድር ሙቀት መጨመር መንስኤ የሆኑት ነገሮች ከተጠበቀው በላይ እየተባባሱ መጥተዋል፤ ይህ ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

እነዚህ ትንበያዎች እምነት የሚጣልባቸው ናቸው? በምድር ላይ ያሉ ሕያዋን ፍጥረታት በእርግጥ አደጋ ተደቅኖባቸዋል? የምድር ሙቀት መጨመሩን የሚጠራጠሩ ሰዎች እንዲህ ያሉት ትንበያዎች መሠረተ ቢስ እንደሆኑ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ የትኛውን ወገን ማመን እንዳለባቸው እርግጠኞች አይደሉም። ታዲያ ሐቁ ምንድን ነው? የምድርም ሆነ የእኛ ሕልውና አደጋ ተጋርጦበታል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 “የምድር ሙቀት መጨመር” የሚለው አገላለጽ የምድር ከባቢ አየርና የውቅያኖስ አማካይ ሙቀት መጨመሩን ያመለክታል።