በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአውሎ ነፋስ ይበልጥ ኃይል ያለው ፍቅር!

ከአውሎ ነፋስ ይበልጥ ኃይል ያለው ፍቅር!

ከአውሎ ነፋስ ይበልጥ ኃይል ያለው ፍቅር!

በ2005 በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ጠረፍ አካባቢ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች፣ ካትሪና እና ሪታ የሚል ስያሜ በተሰጣቸው ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች በተመቱበት ወቅት ከፍተኛ ውድመት ከመድረሱም በላይ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በዚህ አደጋ ከተጎዱት መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ይገኙበታል።

በዚህ ጊዜ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር የተቋቋሙ የእርዳታ ኮሚቴዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት መንቀሳቀስ ጀመሩ። እነዚህ ኮሚቴዎች በሉዊዚያና 13 የእርዳታ ማዕከሎችን፣ 9 መጋዘኖችንና 4 የነዳጅ ማጠራቀሚያዎችን አዘጋጁ። ኮሚቴዎቹ 80,000 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ ለሚገኙ ሰዎች እርዳታ አበርክተዋል። ከመላው ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም ከ13 ሌሎች አገሮች የተውጣጡ ወደ 17,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለመስጠት እንዲሁም በመልሶ ግንባታው ሥራ ለመካፈል በቦታው ተገኝተው ነበር። እነዚህ ወንድሞች ያከናወኑት ሥራ ክርስቲያናዊ ፍቅር ከተፈጥሮ ኃይሎች ይበልጥ ኃይል እንዳለው አሳይቷል።—1 ቆሮንቶስ 13:1-8

ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ከ5,600 የሚበልጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን መኖሪያ ቤቶችና 90 የመንግሥት አዳራሾችን (የይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ ቦታዎች) ጠግነዋል። ከእነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች እንደምንመለከተው በአደጋው የተጎዱ ቤቶችና ሕንፃዎች በሙሉ ተጠግነዋል ማለት ይቻላል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ‘ለሰው ሁሉ፣ መልካም እንዲያደርጉ’ ከሚያሳስበው ከገላትያ 6:10 ጋር በሚስማማ መልኩ እምነታቸውን ለማይጋሩ በርካታ ሰዎችም እርዳታ አድርገዋል።

እርዳታ በመስጠቱ ሥራ የተካፈሉት ሰዎች የከፈሉት መሥዋዕትነት ቢኖርም የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል። በእርዳታ ኮሚቴ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሥራውን በበላይነት ሲከታተሉ የነበሩ ሰባት የይሖዋ ምሥክሮች የሰጡትን አስተያየት እንመልከት።

“በሕይወቴ ውስጥ ልዩ ቦታ የምሰጠው አጋጣሚ”

ሮበርት:- በእርዳታው ኮሚቴ ውስጥ ገብቼ መሥራቴ በሕይወቴ ውስጥ ልዩ ቦታ የምሰጠው አጋጣሚ ሆኖልኛል። ስልሳ ሰባት ዓመቴ ሲሆን ከኮሚቴው አባላት መካከል በዕድሜ አንጋፋው እኔ ነኝ። ጥሩ ባሕርይና መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወጣቶችን ጨምሮ ከበርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጋር ሠርቻለሁ። ወጣቶች፣ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለይሖዋም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ፍቅር ሲያሳዩ መመልከት በጣም ያበረታታል!

ባለቤቴ ቬሮኒካ ጥሩ ረዳት ሆናልኛለች። በእርዳታው ሥራ መካፈል እንድንችል ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት የቆየሁበትን ሥራዬን ለመልቀቅ ስወስን ደግፋኛለች። በአሁኑ ወቅት በሳምንት አንድ ቀን ምሽት ላይ ቢሮዎችን በማጽዳት ኑሯችንን እንመራለን። ቀድሞ እናገኘው ከነበረው ባነሰ ገቢ ቀላል ሕይወት መምራት እንደሚቻል ተምረናል። ይሖዋን ለማስደሰት ከሚጥሩ ወንድሞች ጋር መሥራታችን፣ በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት ማስቀደም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንድንገነዘብ አስችሎናል። (ማቴዎስ 6:33) ይሖዋ ሕዝቡን በሚገባ እንደሚንከባከብ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተመልክተናል።

ፍራንክ:- በባተን ሩዥ ከተማ በሚገኘው የእርዳታ ማዕከል ውስጥ ለፈቃደኛ ሠራተኞች ምግብ የማቅረቡን ሥራ በበላይነት እከታተላለሁ። የእርዳታውን ሥራ በጀመርንበት ወቅት ፈቃደኛ ሠራተኞቹን ለመመገብ ሳምንቱን ሙሉ በየቀኑ ከ10 እስከ 12 ለሚደርሱ ሰዓታት መሥራት ነበረብን። ያም ሆኖ ክርስቲያናዊ ፍቅር ያለውን ኃይል በገዛ ዓይናችን የማየት አጋጣሚን ጨምሮ የተትረፈረፈ በረከት አግኝተናል።

በምግብ አቅርቦት ክፍሉ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ የሠሩ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በድጋሚ መጥተው ለመርዳት የጠየቁ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ እርዳታ በመስጠቱ ሥራ የመካፈል መብት በማግኘታቸው አመስጋኞች መሆናቸውን ፖስት ካርድ በመላክና ስልክ በመደወል ገልጸዋል። እኔና ባለቤቴ ቬሮኒካ፣ እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ባሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ልባችን ተነክቷል።

በስሜት ተውጠው ነበር

ግሪጎሪ:- እኔና ባለቤቴ ካቲ በላስ ቬጋስ፣ ኔቫዳ የሚገኘውን ቤታችንን ሸጠን አነስተኛ የጭነት መኪና እንዲሁም ተጎታች ቤት ገዛን። አኗኗራችንን ቀላል ማድረጋችን በሉዊዚያና በሚካሄደው የእርዳታ ሥራ ከሁለት ዓመት በላይ ለመካፈል አስችሎናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚልክያስ 3:10 ላይ የሚገኘውን “የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት በሕይወታችን ውስጥ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተመለከትን ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች “ብዙ መሥዋዕትነት ከፍላችኋል” ይሉናል፤ እኛ ግን ያገኘነው በረከት እንደሚበልጥ ይሰማናል። ከ30 ዓመት በፊት እኔና ካቲ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ማገልገል እንፈልግ የነበረ ቢሆንም ልጆቻችንን ማሳደግ ነበረብን። በአደጋው የተጎዱትን የመርዳቱ ሥራ በአምላክ አገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል የነበረን ምኞት እንዲሳካ አድርጓል። በዚህ ሥራ በመካፈላችን ያገኘነው ሌላው በረከት ደግሞ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ተቀራርበን መሥራታችን ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የተዋጣላቸው ባለሞያዎች ነበሩ። ለአብነት ያህል፣ ምግብ ከሚሠሩት ወንድሞች መካከል አንደኛው ታዋቂ በሆነ ምግብ ቤት ውስጥ የወጥ ቤት ዋና ኃላፊ ሆኖ ይሠራ የነበረ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለሁለት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ምግብ ያበስል ነበር።

የእርዳታው ሥራ የበርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞችን አመለካከት ለውጦታል። አምሳ ሰባት ዓመት የሆናቸው አንድ ወንድም ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በመርዳት ረገድ ያከናወኑትን ሥራ የገለጹት በስሜት ተውጠው ነበር። በሥራው ላይ መገኘት ያልቻሉ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮችም እንኳ ሌሎችን ያበረታቱ ነበር። ለምሳሌ፣ ሻጋታ በማስወገዱ ሥራ የሚካፈሉ ሁለት ፈቃደኛ ሠራተኞች እነሱ በሚኖሩበት በነብራስካ ግዛት ውስጥ የሚገኙ የሦስት ጉባኤዎች አባላት ያዘጋጁትንና ልጆችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ፊርማውን ያሰፈረበትን በጨርቅ ላይ የተጻፈ መልእክት በስጦታ መልክ አበርክተውልናል።

‘አምላክ ጉዳት የደረሰባቸውን ሲንከባከብ ተመልክተናል’

ዌንድል:- ካትሪና ተብላ የተሰየመችው አውሎ ነፋስ አደጋ ባደረሰች ማግስት፣ በሉዊዚያና እንዲሁም በሚሲሲፒ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶችና የመንግሥት አዳራሾች ላይ የደረሰውን ጉዳት እንዳጣራ የሚጠይቅ ደብዳቤ ከዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ደረሰኝ። በዚህ መንገድ በአንድ በኩል የሥራ ምድብ የተሰጠኝ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ልምድ ለማግኘት የሚያስችል አጋጣሚ ተከፈተልኝ። እኔና ባለቤቴ ጃኒን የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ለ32 ዓመታት በመኖራችን ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚንከባከብ በግልጽ የተመለከትን ቢሆንም አሁን ግን የአምላክን እንክብካቤ ከዚያ ይበልጥ ሰፊ በሆነ መንገድ ማስተዋል ችለናል።

በባተን ሩዥ በሚገኘው የእርዳታ ኮሚቴ ውስጥ በሊቀ መንበርነት የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ይህን ኃላፊነት መወጣት ተፈታታኝ ቢሆንም ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶልኛል። በእርግጥም በዚህ የእርዳታ ሥራ ላይ አምላክ ችግሮቻችንን ሲፈታ፣ መውጫ መንገዱን ሲያዘጋጅልን እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን ሲንከባከብ ብዙ ጊዜ ተመልክተናል፤ ሁሉን ቻይ ከሆነው አፍቃሪ አባት በቀር ማንም ይህንን ሊያደርግ አይችልም።

በርካታ ሰዎች፣ “አንተም ሆንክ ባለቤትህ እርዳታ በመስጠቱ ሥራ መካፈል ከጀመራችሁ ሁለት ዓመት ቢያልፋችሁም አሁንም በዚህ ሥራ መቀጠል የቻላችሁት እንዴት ነው?” ብለው ይጠይቁኛል። በእነዚህ ጊዜያት ምንም ችግር አልገጠመንም ማለት አይደለም። በሕይወታችን ውስጥ በርካታ ማስተካከያዎችን ማድረግ ጠይቆብናል። ይሁንና በመልካም ጎኑ ካየነው ‘ዓይናችን ጤናማ’ በመሆኑ ብዙ ጥቅሞች አግኝተናል።—ማቴዎስ 6:22

መጀመሪያ አካባቢ በኒው ኦርሊየነስ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን የመፈለጉ ሥራ ፋታ የሚሰጥ አልነበረም። በከተማዋ ውስጥ ሁከት ከመንገሡም በላይ የጭካኔ ድርጊቶች በየቦታው ይፈጸሙ ስለነበር ወታደሮች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን ይህ ደግሞ ሥራችንን ይበልጥ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር። የሥራው ብዛት ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ እንዲሰማን የሚያደርግ ነበር።

በአደጋው ቤት ንብረታቸውን ያጡ የይሖዋ ምሥክሮችን አግኝተን ነበር። አብረናቸው የጸለይን ከመሆኑም በላይ ልናጽናናቸው ሞከርን። ከዚያም በይሖዋ እርዳታ ሥራውን ማከናወን ጀመርን። በዚህ ሥራ ላይ የቆየሁት ለሁለት ዓመት ብቻ ቢሆንም ካየኋቸውና ካጋጠሙኝ ነገሮች አንጻር አንዳንድ ጊዜ የሁለት ሰው ዕድሜ የኖርኩ ያህል ሆኖ ይሰማኛል።

በተደጋጋሚ ጊዜያት ሁኔታው ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ሲሰማኝ አዳዲስ ፈቃደኛ ሠራተኞች ይጎርፉ የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹ ለወራት ሌሎቹ ደግሞ ላልተወሰነ ጊዜ ይቆዩ ነበር። በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ሰዎች በደስታ እንዲሁም በፈቃደኝነት መንፈስ ሲረዱን መመልከታችን በሥራው እንድንቀጥል ብርታት ሰጥቶናል።

አብዛኛውን ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ ረድቶናል። ለምሳሌ ያህል፣ መጀመሪያ ላይ ወደ አካባቢው ስንሄድ ከ1,000 በሚበልጡ የወንድሞች ቤቶች ላይ ዛፎች እንደወደቁባቸው ተገነዘብን። ዛፎቹን ከቤቶቹ ላይ የማንሳቱን አደገኛ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል መሣሪያም ሆነ የሰው ኃይል ስላልነበረን ወደ ይሖዋ ጸለይን። በነጋታው አንድ ወንድም የጭነት መኪና እና የሚያስፈልገንን መሣሪያ በመያዝ ሊረዳን መጣ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ጸሎታችን በ15 ደቂቃ ውስጥ ምላሽ ያገኘ ሲሆን እንዲያውም በአንድ ወቅት ገና ጸልየን ሳንጨርስ የምንፈልገው መሣሪያ በጉዞ ላይ ነበር! በእርግጥም ይሖዋ ‘ጸሎትን የሚሰማ’ አምላክ መሆኑን አሳይቷል።—መዝሙር 65:2

“የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ኩራት ተሰምቶኛል”

ማቲው:- ካትሪና የተባለችው አውሎ ነፋስ አደጋ ባደረሰች ማግስት 150 ኩንታል የሚመዝን በእርዳታ የተገኘ ምግብ፣ የታሸገ ውኃ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በአደጋ ወደተጠቃው አካባቢ የመላኩን ሥራ በማደራጀት አገልግያለሁ። የይሖዋ ሕዝቦች በእርግጥም ለጋሶች መሆናቸውን አስመሥክረዋል!

እኔና ባለቤቴ ዳርሊን፣ በእርዳታው ሥራ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመካፈል ስንል አደጋው ከደረሰበት አካባቢ በመኪና የሁለት ሰዓት መንገድ በሚሆን ርቀት ላይ ወደሚገኝ አካባቢ ተዛወርን። በአካባቢው የሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክር፣ አብዛኛውን ጊዜያችንን እርዳታ በመስጠቱ ተግባር ላይ ማዋል እንድንችል በሳምንቱ ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓቶች የምንሠራው ሰብዓዊ ሥራ ሰጠን። ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ መኖሪያ ሰጠን። እንደዚህ ባለው አፍቃሪ የወንድማማች ኅብረት ውስጥ በመሆኔ ልቤ በአድናቆት ከመሞላቱም በላይ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ኩራት ተሰምቶኛል።

ቴድ:- ካትሪና፣ አደጋ ካደረሰች ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔና ባለቤቴ ዴቢ በእርዳታው ሥራ ለመካፈል ራሳችንን በፈቃደኝነት አቀረብን። በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ የጭነት መኪናችን በቀላሉ ሊጎትተው የሚችልና ርዝመቱ 9 ሜትር የሚሆን ያገለገለ ተጎታች ቤት አገኘን። የዚህ ተጎታች ቤት ዋጋ፣ ገበያ ላይ ከሚገኝበት ዋጋ በግማሽ ያነሰ በመሆኑ ቤቱን ለመግዛት አቅማችን ይፈቅድ ነበር፤ ይህም የጸሎታችን መልስ ነበር። በዚህ ተጎታች ቤት ውስጥ ከሁለት ዓመት በላይ ኖረናል።

ሥራው ጋብ ሲል የቀድሞ ቤታችንንና አብዛኛውን ንብረታችንን ሸጥን፤ ይህም በኒው ኦርሊየንስ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት ነፃ እንድንሆን የረዳን ሲሆን በዚያም በመልሶ ግንባታው ሥራ አስተባባሪ ሆኜ እያገለገልኩ ነው። በዚህ ቦታ ስንሠራ ካሳለፍናቸው ነገሮች ሁሉ ትልቁን ቦታ የምንሰጠው ይሖዋ ለሕዝቡ ‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ የሆነላቸው እንዴት እንደሆነ መመልከት መቻላችን ነው። ብዙዎች በአደጋው ወቅት ቤቶቻቸውንና የመንግሥት አዳራሾቻቸውን ከማጣታቸውም በተጨማሪ አካባቢያቸውን ለቅቀው በመሄዳቸው ከጉባኤያቸው አባላት ጋር ተለያይተዋል፤ ሌላው ቀርቶ የአገልግሎት ክልላቸውን በሙሉ ትተው ለመሄድ ተገድደዋል።—2 ቆሮንቶስ 1:3

‘እምነታቸው ልባችንን ነክቶታል’

ጀስቲን:- በጥቅምት 2005 የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ጠረፍ አካባቢ በደረሰው አደጋ የተጎዱትን ለመርዳት ፈቃደኛ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ገለጸ። እኔና ባለቤቴ ቲፋኒ፣ ወዲያውኑ ያመለከትን ሲሆን በየካቲት ወር 2006 ጣሪያ የሚያለብሰውን ቡድን እንድንረዳ ተመደብን፤ ይህ ቡድን የሚሠራው ኒው ኦርሊየንስ አቅራቢያ በምትገኘው ኬነር በተባለች ከተማ ውስጥ በተቋቋመው የእርዳታ ማዕከል ሥር ሆኖ ነው።

በየዕለቱ የአንድ ቤት ጣሪያ ስንሠራ በአካባቢው ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ የነበረን ሲሆን እምነታቸውና በአምላክ የሚታመኑ መሆናቸው ልባችንን ነክቶታል። በቁሳዊ ነገሮች መታመን ሞኝነት መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ በየቀኑ እንመለከት ነበር። የይሖዋ ሕዝቦች በእሱ እርዳታ ማከናወን የቻሉትን ነገር መመልከት እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻችንን መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በእርዳታ ማዕከሉ በየዕለቱ የሚከናወነው ሥራ

በእርዳታ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙት የወጥ ቤት ሠራተኞች ሥራቸውን የሚጀምሩት ከሌሊቱ 10:30 ገደማ ነው። ከጠዋቱ 1:00 ላይ ሠራተኞቹ በሙሉ ከቁርስ በፊት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ለአሥር ደቂቃ ውይይት ለማድረግ በሚመገቡበት ቦታ ላይ ይሰበሰባሉ። ሊቀ መንበሩ፣ አዳዲስ ፈቃደኛ ሠራተኞች መምጣታቸውን ለማስታወቅና በቅርቡ የተገኙ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥም ይህን አጋጣሚ ይጠቀምበታል።

ከዚያም የምስጋና ጸሎት ከቀረበ በኋላ ሁሉም ቁርሳቸውን ተመግበው ወደ ሥራቸው ይሰማራሉ። በቢሮዎች፣ በልብስ እጥበት ክፍል ወይም በወጥ ቤት ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ፈቃደኛ ሠራተኞች እዚያው ማዕከሉ ውስጥ ይቆያሉ። ወጥ ቤት ውስጥ የሚሠሩት ወንድሞች ምሳ የሚያዘጋጁ ሲሆን ሰዓቱ ሲደርስ የተወሰኑ ወንድሞች መጥተው በመስክ ላይ የሚገኘውን ቡድናቸውን በመወከል ምሳ ይወስዳሉ።

በየሳምንቱ ሰኞ ማታ “ቤተሰቡ” የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጁት መጠበቂያ ግንብ በተባለው መጽሔት ላይ የተመሠረተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ይሰበሰባል። እንደዚህ ያለው የቤተሰብ ጥናት ሁሉም በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነው እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል፤ ይህ ደግሞ ደስተኞች እንዲሆኑና ለሥራቸው ተገቢ አመለካከት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።—ማቴዎስ 4:4፤ 5:3

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ስለ እናንተ የነበረኝ አመለካከት የተሳሳተ ነው”

በኒው ኦርሊየንስ የምትኖር አንዲት ሴት በሯ ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች፣ ቤቴን እንዳታንኳኩ” የሚል ምልክት ለጥፋ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን ፈቃደኛ ሠራተኞች ከቤቷ ፊት ለፊት ከመንገዱ ባሻገር የሚገኘውን በአውሎ ነፋስ ጉዳት የደረሰበት ቤት ሲጠግኑ ተመለከተች። በሠራተኞቹ መካከል ፍቅር የሚንጸባረቅበት ወዳጃዊ መንፈስ እንዳለ በየዕለቱ ታስተውል ነበር። ብዙም ሳይቆይ ስለ እነዚህ ሰዎች የማወቅ ጉጉት ስላደረባት ምን እንደሚሠሩ ለማየት ወደ ቦታው ሄደች። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ስትገነዘብ፣ አውሎ ነፋሱ ከተከሰተ ጀምሮ ከእሷ ቤተ ክርስቲያን ስልክ እንኳ የደወለላት ሰው እንደሌለ ገለጸች። “አሁን እንዳስተዋልኩት ስለ እናንተ የነበረኝ አመለካከት የተሳሳተ ነው” በማለት ተናገረች። ይህቺ ሴት ምን አድርጋ ይሆን? በሯ ላይ የለጠፈችውን ምልክት ያነሳች ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷ ቢመጡ እንደምትቀበላቸው ገልጻለች።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮበርት እና ቬሮኒካ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍራንክ እና ቬሮኒካ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግሪጎሪ እና ካቲ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዌንድል እና ጃኒን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማቲው እና ዳርሊን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴድ እና ዴቢ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀስቲን እና ቲፋኒ