በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መስቀል

መስቀል

ብዙ ሰዎች መስቀል የክርስትና ምልክት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ መስቀል በአንገት ወይም በእጅ ላይ መታሰር እንዳለበት እንዲሁም በመኖሪያ ቤትም ሆነ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መቀመጥ ወይም መሰቀል እንዳለበት አያምኑም።

ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ ነው?

አንዳንድ ሰዎች ምን ይላሉ?

 

ሮማውያን ኢየሱስን የሰቀሉት ከሁለት እንጨቶች በተሠራ መስቀል ላይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

ኢየሱስ የተገደለው ‘በእንጨት ላይ ተሰቅሎ’ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 5:30) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ኢየሱስ በምን ላይ እንደተገደለ ለመግለጽ የተጠቀሙባቸው ሁለቱም ቃላት የሚያመለክቱት ሁለት እንጨቶችን ሳይሆን አንድን እንጨት ነው። ክሩስፊክሽን ኢን አንቲክዊቲ የተባለው ጽሑፍ እንደገለጸው ስታውሮስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ማንኛውንም ምሰሶ ያመለክታል። ‘መስቀል’ ለሚለው ቃል አቻ ትርጉም አይደለም።” በሐዋርያት ሥራ 5:30 ላይ የተሠራበት ዛይሎን የሚለው ቃል ደግሞ የሚያመለክተው “ሮማውያን ስቅላት የተፈረደባቸውን ሰዎች በሚስማር የሚቸነክሩበትን ቀጥ ያለ ግንድ ወይም እንጨት ነው።” *

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተገደለበትን መንገድ ከአንድ የጥንት እስራኤላውያን ሕግ ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። ሕጉ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት ሠርቶ ቢገደልና በእንጨት ላይ ብትሰቅለው . . . እንጨት ላይ የሚሰቀለው፣ አምላክ የረገመው ነው።” (ዘዳግም 21:22, 23) ክርስቲያን የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሕግ ጠቅሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ክርስቶስ በእኛ ፋንታ የተረገመ ሆኖ እኛን ከሕጉ እርግማን ነፃ በማውጣት ዋጅቶናል፤ ምክንያቱም ‘በእንጨት [ዛይሎን] ላይ የተሰቀለ ሰው ሁሉ የተረገመ ነው’ ተብሎ ተጽፏል።” (ገላትያ 3:13) ጳውሎስ የተናገረው ይህ ሐሳብ ኢየሱስ የተሰቀለው በአንድ ቀጥ ያለ እንጨት ላይ እንደሆነ ይጠቁማል።

“በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።” የሐዋርያት ሥራ 10:39

 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መስቀልን ለአምልኮ አሊያም ለክርስትና ምልክት አድርገው ተጠቅመውበታል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች መስቀልን ሃይማኖታዊ ምልክት አድርገው እንደተጠቀሙበት የሚጠቁም ሐሳብ አይገኝም። እንዲያውም አማልክታቸውን ለመወከል መስቀልን እንደ ምልክት አድርገው የሚጠቀሙት በዘመኑ የነበሩት ሮማውያን ነበሩ። ከዚያም ኢየሱስ ከሞተ ከ300 ዓመታት ገደማ በኋላ የሮሙ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ መስቀልን የጦር ሠራዊቱ ዓርማ አድርጎ ይጠቀምበት ጀመር፤ መስቀል ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር ተያይዞ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ከዚያ ጊዜ በኋላ ነው።

በመስቀል ተጠቅመው አማልክታቸውን ያመልኩ የነበሩት አረማውያን ሆነው ሳለ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ መስቀልን ተጠቅመዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አምላክ ከጥንት ጀምሮ አገልጋዮቹ “የትኛውንም ዓይነት ምስል” ለአምልኮ እንዲጠቀሙ እንደማይፈልግ እንዲሁም ክርስቲያኖች ‘ከጣዖት አምልኮ መሸሽ’ እንደሚገባቸው ያውቁ ነበር። (ዘዳግም 4:15-19፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) ‘አምላክ መንፈስ ስለሆነ’ በዓይን ሊታይ አይችልም። በመሆኑም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አምላክ ይበልጥ እውን እንዲሆንላቸው ለማድረግ ሲሉ የሚታዩ ነገሮችንና ምልክቶችን አልተጠቀሙም። ከዚህ ይልቅ አምላክን “በመንፈስ” ማለትም በዓይን በማይታየው ቅዱስ መንፈሱ በመመራት እንዲሁም “በእውነት” ማለትም አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሰፈረው ፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ ያመልኩት ነበር።—ዮሐንስ 4:24

“እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት [ያመልኩታል]።”ዮሐንስ 4:23

ክርስቲያኖች ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

 

“መዳን ላስገኘው መሣሪያ ለየት ያለ አክብሮትና ከፍ ያለ ቦታ መሰጠቱ ምክንያታዊና ተገቢ የሆነ ድርጊት ነው። . . . ምስሉን የሚያከብር ሰው፣ ምስሉ የሚወክለውንም አካል ያከብራል።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

ክርስቲያኖች የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት፣ ወደ አምላክ መቅረብና የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ የተከፈተላቸው በኢየሱስ ሞት አማካኝነት እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስ ትልቅ ውለታ ውሎላቸዋል። (ዮሐንስ 3:16፤ ዕብራውያን 10:19-22) እሱ ለዋለላቸው ውለታ ያላቸውን አድናቆት ማሳየት የሚችሉት በእሱ እንደሚያምኑ በቃል በመናገር ብቻ አሊያም እሱን የሚወክል ምስል በመያዝ እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ደግሞም ‘በሥራ ያልተደገፈ እምነት የሞተ ነው።’ (ያዕቆብ 2:17) ክርስቲያኖች በኢየሱስ እንደሚያምኑ በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። እንዴት?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ለሁሉም መሞቱን ስለተረዳን ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናልና፤ . . . በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ክርስቶስ ያሳየው ታላቅ ፍቅር ክርስቲያኖች የእሱን ምሳሌ ለመከተል ሲሉ በሕይወታቸው ላይ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ግድ ይላቸዋል። ክርስቲያኖች ለኢየሱስ ያላቸውን አክብሮት ማሳየት የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ሃይማኖታዊ ምስሎችን መጠቀም ሳይሆን እሱ የተወውን ምሳሌ መከተል ነው።

“የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያውቅና በእሱ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።”ዮሐንስ 6:40 ግርጌ

^ አን.8 ኤ ክሪቲካል ሌክሲከን ኤንድ ኮንኮርዳንስ ቱ ዚ ኢንግሊሽ ኤንድ ግሪክ ኒው ቴስታመንት፣ 11ኛ እትም፣ በኢተልበርት ቡሊንገር፣ ገጽ 818-819