የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ምትሃታዊ ድርጊቶች ምን ጉዳት አላቸው?
የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ነው!
“ቫምፓየሮች፣ ጭራቆችና ዞምቢዎች ጊዜ አልፎባቸዋል፤ አጋንንት ስላደሩባቸው ሰዎች የሚያሳዩና አጋንንትን ስለማስወጣት የሚናገሩ መዝናኛዎች ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል።” —ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል
አስማተኞች፣ ጠንቋዮችና ቫምፓየሮች የመጻሕፍት፣ የፊልምና የቪዲዮ ጨዋታ ኢንዱስትሪዎችን ካጥለቀለቁ ምትሃታዊ ኃይል ያላቸው ገጸ ባሕርያት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ለመሆኑ እነዚህ መዝናኛዎች ይህን ያህል ተወዳጅ የሆኑት ለምንድን ነው? *
የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ክሎድ ፊሸር እንዲህ ብለዋል፦ “ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በሙታን መናፍስት የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት፣ በሙታን መናፍስት የሚያምነው ከአሥር አሜሪካውያን አንዱ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን ከሦስት አሜሪካውያን አንዱ በሙታን መናፍስት ያምናል። ከሰው በላይ የሆነ የማወቅ ችሎታ አላቸው የሚባሉ ሰዎችን እንዳማከሩ የሚናገሩ እንዲሁም የሙታን መናፍስት እንዳሉና እነዚህ መናፍስት በአንዳንድ ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ የሚያምኑ ወጣት አሜሪካውያን ቁጥር እንዲህ ያለ አመለካከት ካላቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ይበልጣል።”
አጋንንት ስላደሩባቸው ሰዎች የሚናገሩ ታሪኮች በአስደንጋጭ ሁኔታ ዳግም ተወዳጅነት እያገኙ መጥተዋል፤ ይህም የሚያስገርም አይደለም። ማይክል ካሊያ የተባለው ጸሐፊ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል በተባለው መጽሔት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ባለፉት አሥር ዓመታት ዞምቢዎች፣ ጭራቆችና ቫምፓየሮች ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው መሆኑ በአሁኑ ጊዜ በአጋንንት በተያዙ ሰዎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ታሪኮች ተወዳጅነት እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።”
አንድ ሪፖርት እንደዘገበው “በዓለም ዙሪያ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል ከ25 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት በሙታን መናፍስት ያምናሉ፤ እንዲሁም በብዙ ባሕሎች ውስጥ ስለ ሙታን መናፍስት የሚናገሩ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች አሉ።” በተጨማሪም የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስቶፈር ቤደር እና ካርሰን ሜንከን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያካሄዱት ጥናት እንደሚያሳየው “ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን በምትሃታዊ ኃይል ከሚፈጸሙ ድርጊቶች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ጠንካራ እምነት አላቸው።”
በእርግጥ ከምትሃታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች መካፈል ምንም ጉዳት የለውም?
^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ “ምትሃታዊ ድርጊቶች” የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው በሳይንስ ወይም በተፈጥሮ ሕጎች ሊብራሩ የማይችሉ ክንውኖችን ነው።