በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 32

በፈጣሪ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ

በፈጣሪ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ

“እምነት . . . የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።”—ዕብ. 11:1

መዝሙር 11 ፍጥረት ይሖዋን ያወድሳል

ማስተዋወቂያ *

1. ስለ ፈጣሪያችን ምን ተምረሃል?

ያደግከው እውነት ውስጥ ከሆነ ስለ ይሖዋ ከልጅነትህ ጀምሮ ተምረህ መሆን አለበት። ይሖዋ ፈጣሪ እንደሆነ፣ ግሩም ባሕርያት እንዳሉት እንዲሁም ምድርን ገነት የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተምረሃል።—ዘፍ. 1:1፤ ሥራ 17:24-27

2. አንዳንዶች በፈጣሪ ለሚያምኑ ሰዎች ምን አመለካከት አላቸው?

2 ይሁንና ብዙ ሰዎች አምላክ ፈጣሪ መሆኑን ይቅርና መኖሩን እንኳ አያምኑም። ከዚህ ይልቅ ሕይወት በአጋጣሚ እንደጀመረ ይናገራሉ፤ ከዚያም ውስብስብ ያልሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት ይበልጥ ውስብስብ ወደሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት ቀስ በቀስ እየተለወጡ እንደሄዱ ያምናሉ። እንዲህ ብለው ከሚያምኑት ሰዎች አንዳንዶቹ ምሁራን ናቸው። እነዚህ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑን ሳይንስ እንዳረጋገጠ እንዲሁም በፈጣሪ የሚያምኑት ሞኞችና ያልተማሩ ሰዎች እንደሆኑ ይናገሩ ይሆናል።

3. እያንዳንዳችን እምነታችንን ማጠናከራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ተሰሚነት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች የሚናገሩት ነገር ይሖዋ የሚወደን ፈጣሪያችን ስለመሆኑ ያለንን እምነት ያናጋብን ይሆን? ይህ በዋነኝነት የተመካው ‘ይሖዋ ፈጣሪ እንደሆነ የምናምነው ለምንድን ነው?’ በሚለው ላይ ነው። ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑን የምናምነው ሌሎች ስለነገሩን ነው? ወይስ እኛ ራሳችን ጊዜ ወስደን ማስረጃዎቹን መርምረናል? (1 ቆሮ. 3:12-15) በይሖዋ ቤት ምንም ያህል ረጅም ጊዜ ብንቆይ ሁላችንም እምነታችንን ለማጠናከር ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን የአምላክን ቃል የሚቃወሙ ሰዎች በሚያስተምሩት “ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ” አንወሰድም። (ቆላ. 2:8፤ ዕብ. 11:6) ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚህ ርዕስ ውስጥ ሦስት ነገሮችን እንመረምራለን፦ (1) ብዙዎች በፈጣሪ የማያምኑት ለምንድን ነው? (2) ይሖዋ ፈጣሪ እንደሆነ ያለህን እምነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? (3) እምነትህ ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

ብዙዎች በፈጣሪ የማያምኑት ለምንድን ነው?

4. በዕብራውያን 11:1 መሠረት እምነት በምን ላይ የተመሠረተ ነው?

4 አንዳንዶች፣ እምነት ሲባል አንድን ነገር ያለምንም ማስረጃ መቀበል ማለት እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሚሰጠው ፍቺ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። (ዕብራውያን 11:1ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነት በማስረጃ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይናገራል፤ ስለዚህ ይሖዋን፣ ኢየሱስን ወይም የአምላክን መንግሥት ማየት ባንችልም እንኳ እውን መሆናቸውን የምናምነው ተጨባጭ ማስረጃ ስላለን ነው። (ዕብ. 11:3) የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር “እምነታችን በጭፍን አመለካከት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ በሳይንስ የተረጋገጡ እውነታዎችን አምነን እንቀበላለን” ብሏል።

5. ብዙዎች ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ የማያምኑት ለምንድን ነው?

5 ‘ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ካለ ብዙዎች ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረው አምላክ እንደሆነ የማያምኑት ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። አንዳንዶች ይህን የማያምኑት ራሳቸው ማስረጃውን ስላልመረመሩ ነው። አሁን የይሖዋ ምሥክር የሆነው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ፍጥረት በትምህርት ቤት ምንም ነገር ስላልተማርን ‘ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው’ የሚለው ትምህርት እውነት እንዳልሆነ አሰብኩ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተነጋገርኩትና ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ የሚያሳየውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ምክንያታዊና አሳማኝ ማስረጃ የተመለከትኩት ወደ 20ዎቹ ዕድሜ ከገባሁ በኋላ ነው።” *—“ ወላጆች፣ አደራ እንላችኋለን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

 

6. አንዳንዶች በፈጣሪ የማያምኑት ለምንድን ነው?

6 አንዳንዶች በፈጣሪ የማያምኑት ለምን እንደሆነ ሲገልጹ ‘የማላየውን ነገር ማመን አልችልም’ ይላሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ባያዩአቸውም የሚያምኗቸው ነገሮች አሉ። የስበት ኃይልን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ የስበት ኃይል ባይታይም መኖሩን የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ አለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው እምነትም በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው፤ የምናምንበት ነገር “በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ” ማስረጃ አለው። (ዕብ. 11:1) ማስረጃውን ራሳችን ለመመርመር ጊዜና ጥረት ይጠይቃል፤ ብዙ ሰዎች ደግሞ ይህን ለማድረግ ተነሳሽነቱ የላቸውም። በመሆኑም አንድ ሰው ማስረጃውን ራሱ ካልመረመረ ‘አምላክ የለም’ የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ይችላል።

7. ጽንፈ ዓለምን የፈጠረው አምላክ መሆኑን የማይቀበሉት ሁሉም የተማሩ ሰዎች ናቸው? አብራራ።

7 አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ማስረጃውን ከመረመሩ በኋላ ጽንፈ ዓለምን የፈጠረው አምላክ እንደሆነ አምነዋል። * ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እንደ ሮበርት ሁሉ አንዳንዶች ፈጣሪ የለም ብለው ያመኑት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለ ፍጥረት ስላልተማሩ ይሆናል። ይሁንና በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት ይሖዋን ማወቅ ችለዋል፤ በዚህም ምክንያት እሱን ወደውታል። የትምህርት ደረጃችን ምንም ይሁን ምን፣ ሁላችንም እንደ እነዚህ የሳይንስ ሊቃውንት በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር አለብን። እምነታችንን ማጠናከር ያለብን እኛው ራሳችን ነን፤ ማንም ሰው ይህን ሊያደርግልን አይችልም።

በፈጣሪ ላይ ያለህን እምነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?

8-9. (ሀ) የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን? (ለ) ስለ ፍጥረት ሥራዎች ማጥናትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

8 በፈጣሪ ላይ ያለህን እምነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችልባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት።

9 ስለ ፍጥረት ሥራዎች ለማጥናት ጥረት አድርግ። ስለ እንስሳት፣ ስለ ዕፀዋትና ስለ ከዋክብት ምርምር በማድረግ በፈጣሪ ላይ ያለህን እምነት ማጠናከር ትችላለህ። (መዝ. 19:1፤ ኢሳ. 40:26) ስለ እነዚህ ነገሮች ባጠናህ መጠን፣ ይሖዋ ፈጣሪ ስለመሆኑ ያለህ እምነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። ስለተለያዩ ፍጥረታት በዝርዝር የሚያወሱ ርዕሶች በጽሑፎቻችን ላይ ብዙ ጊዜ ይወጣሉ። እነዚህን ርዕሶች ሙሉ በሙሉ መረዳት ቢከብድህም እንኳ ከማንበብ ወደኋላ አትበል። የቻልከውን ያህል ትምህርት ለመቅሰም ጥረት አድርግ። ባለፉት ዓመታት በክልል ስብሰባዎች ላይ የወጡትን ስለ ፍጥረት የሚናገሩ ግሩም ቪዲዮዎችም ደግመህ መመልከት ትችላለህ፤ እነዚህን ቪዲዮዎች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ ታገኛቸዋለህ።

10. የፍጥረት ሥራዎች ፈጣሪ መኖሩን የሚያረጋግጡት እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ። (ሮም 1:20)

10 ስለ ፍጥረት ሥራዎች ስታጠና፣ እነዚህ ነገሮች ስለ ፈጣሪያችን ምን እንደሚያስተምሩህ ለማስተዋል ሞክር። (ሮም 1:20ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ ፀሐይ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነውን ሙቀት ብቻ ሳይሆን ጎጂ የሆኑ አልትራቫዮሌት ጨረሮችም እንደምታመነጭ ታውቅ ይሆናል። እኛ የሰው ልጆች ከእነዚህ ጨረሮች ከለላ ያስፈልገናል። ደግሞም እንዲህ ያለ ከለላ ተዘጋጅቶልናል! እንዴት? ምድራችን የራሷ የሆነ መከለያ አላት፤ ይህም ጎጂ የሆኑ ጨረሮችን ውጦ የሚያስቀር የኦዞን ንጣፍ ነው። ከፀሐይ የሚመጡት አልትራቫዮሌት ጨረሮች በጨመሩ መጠን በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የኦዞን መጠንም እየጨመረ ይሄዳል። እነዚህ ነገሮች በዚህ መልኩ እንዲሠሩ ያደረገ አፍቃሪና ጥበበኛ የሆነ ፈጣሪ መኖር አለበት ቢባል አትስማማም?

11. ስለ ፍጥረት የሚገልጹ እምነት የሚያጠናክሩ መረጃዎችን የት ማግኘት ትችላለህ? (“ እምነት ለመገንባት የሚረዱ መረጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

11 ስለ ፍጥረት የሚገልጹ እምነት የሚያጠናክሩ በርካታ መረጃዎችን የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ እና jw.org ላይ ምርምር በማድረግ ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ “ንድፍ አውጪ አለው?” በሚለው ዓምድ ሥር የሚገኙትን ርዕሶች በማንበብና ቪዲዮዎቹን በመመልከት መጀመር ትችላለህ። እነዚህ አጫጭር ርዕሶችና ቪዲዮዎች ስለ እንስሳት እና ስለ ሌሎች ፍጥረታት አስደናቂ የሆኑ መረጃዎችን ያቀርባሉ። በተጨማሪም የሳይንስ ሊቃውንት በተፈጥሮ ላይ የሚታየውን ጥበብ ለመኮረጅ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ማግኘት ይቻላል።

 

12. መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

12 መጽሐፍ ቅዱስን አጥና። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ መጀመሪያ ላይ በፈጣሪ ለማመን ፈቃደኛ አልነበረም። ውሎ አድሮ ግን ፈጣሪ መኖሩን አመነ። እንዲህ ብሏል፦ “እምነት እንዳዳብር ያደረገኝ በሳይንሱ መስክ ያደረግሁት ጥናት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናቴም ጠቅሞኛል።” አንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ እውቀት እስካሁን ቀስመህ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን በፈጣሪህ ላይ እምነት ለማዳበር የአምላክን ቃል ማጥናትህን መቀጠል ይኖርብሃል። (ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 119:97) መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ ክንውኖችን በተመለከተ የሚሰጠውን ዝርዝር ማብራሪያ ለማስተዋል ጥረት አድርግ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች በትኩረት አጥና፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑን ልብ በል። እንዲህ ማድረግህ አፍቃሪና ጥበበኛ የሆነ አምላክ እንደፈጠረንና መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ እንዳስጻፈው ያለህን እምነት ያጠናክረዋል። *2 ጢሞ. 3:14፤ 2 ጴጥ. 1:21

13. በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ምክር ጥበብ ያዘለ መሆኑን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

13 የአምላክን ቃል ስታጠና፣ የሚሰጣቸው ምክሮች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን መውደድ ጎጂ እንደሆነና “ብዙ ሥቃይ” እንደሚያስከትል ከረጅም ጊዜ በፊት አስጠንቅቋል። (1 ጢሞ. 6:9, 10፤ ምሳሌ 28:20፤ ማቴ. 6:24) ይህ ማስጠንቀቂያ ዛሬም ይሠራል? አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ቁሳዊ ነገር የሚያሳድዱ ሰዎች በአብዛኛው ሲታይ ደስታ የሚርቃቸው ከመሆኑም ሌላ ይበልጥ በጭንቀት ይዋጣሉ። ተጨማሪ ገንዘብ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም የአእምሯቸው ጤንነት ሊታወክ ይችላል፤ እንዲሁም [ሌሎች] የጤና እክሎች ያጋጥሟቸዋል።” * በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ፍቅር እንዳያድርብን የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንኛ ጠቃሚ ነው! በሕይወትህ ውስጥ የጠቀሙህ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መጥቀስ ትችላለህ? የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ባስተዋልን መጠን አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን በሰጠን ጊዜ የማይሽረው ጥበብ ያዘለ ምክር ላይ ይበልጥ እንተማመናለን። (ያዕ. 1:5) ይህም ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ያደርግልናል።—ኢሳ. 48:17, 18

14. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ስለ ይሖዋ ምን ለማወቅ ያስችልሃል?

14 መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ዓላማህ ይሖዋን ይበልጥ ማወቅ ይሁን። (ዮሐ. 17:3) ቅዱሳን መጻሕፍትን ስታጠና ስለ ይሖዋ ማንነት እና ስለ ባሕርያቱ ትማራለህ፤ እነዚህ ባሕርያቱ በፍጥረት ሥራዎቹም ላይ እንደተንጸባረቁ ማስተዋልህ አይቀርም። ስለ እነዚህ ባሕርያት መማርህ ይሖዋ ምናብ የፈጠረው ሳይሆን እውን አካል መሆኑን እንድታምን ያደርግሃል። (ዘፀ. 34:6, 7፤ መዝ. 145:8, 9) ይሖዋን ይበልጥ እያወቅኸው ስትሄድ በእሱ ላይ ያለህ እምነት ይጎለብታል፤ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይጨምራል፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት ይጠናከራል።

15. ስለ እምነትህ ለሌሎች መናገርህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

15 በአምላክ ላይ ያለህን እምነት በተመለከተ ለሌሎች ተናገር። ይህን ማድረግህ እምነትህ እንዲጠናከር ይረዳሃል። ሆኖም የመሠከርክለት ሰው ስለ አምላክ መኖር ጥያቄ ቢያነሳና ምን ብለህ መመለስ እንዳለብህ ግራ ቢገባህስ? በጽሑፎቻችን ላይ የወጣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያ ለማግኘት ጥረት አድርግ፤ ከዚያም ያገኘኸውን ሐሳብ ለግለሰቡ አካፍለው። (1 ጴጥ. 3:15) ከዚህም ሌላ ተሞክሮ ያለው አንድ የእምነት ባልንጀራህን እንዲረዳህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ግለሰቡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰጠኸውን ማብራሪያ ተቀበለም አልተቀበለ ምርምር ማድረግህ አንተን ይጠቅምሃል። እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል። ይህም ጥበበኛና የተማሩ የሚባሉ ሰዎች ‘ፈጣሪ የለም’ በማለት በሚያስተምሩት የሐሰት ትምህርት እንዳትታለል ይረዳሃል።

እምነትህ ምንጊዜም ጠንካራ ይሁን!

16. ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይዘን ለመቀጠል ጥረት ካላደረግን ምን ሊያጋጥመን ይችላል?

16 በይሖዋ አገልግሎት የቱንም ያህል ረጅም ጊዜ ብንቆይ ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይዘን ለመቀጠል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም ካልተጠነቀቅን እምነታችን ሊዳከም ይችላል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የምናምንባቸው ነገሮች በማስረጃ የተደገፉ ቢሆኑም በዓይን አይታዩም። የማናየውን ነገር ደግሞ በቀላሉ ልንረሳው እንችላለን። ጳውሎስ እምነት ማጣትን “በቀላሉ ተብትቦ [የሚይዘን] ኃጢአት” ብሎ የጠራው ለዚህ ነው። (ዕብ. 12:1) ታዲያ በዚህ ወጥመድ ላለመያዝ ምን ማድረግ እንችላለን?—2 ተሰ. 1:3

17. ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይዘን ለመቀጠል ምን ያስፈልገናል?

17 በመጀመሪያ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው፤ እንዲህ ያለውን ልመናም አዘውትረህ አቅርብ። ለምን? ምክንያቱም እምነት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። (ገላ. 5:22, 23) የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ካላገኘን በፈጣሪያችን ላይ እምነት መገንባትና ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይዘን መቀጠል አንችልም። ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን አዘውትረን ከለመንነው ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:13) እንዲያውም “እምነት ጨምርልን” ብለን በቀጥታ መጸለይ እንችላለን።—ሉቃስ 17:5

18. በአሁኑ ወቅት ምን መብት አግኝተናል? (መዝሙር 1:2, 3)

18 በተጨማሪም የአምላክን ቃል የምታጠናበት ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ። (መዝሙር 1:2, 3ን አንብብ።) መዝሙር 1 በተቀናበረበት ወቅት አብዛኞቹ እስራኤላውያን በጽሑፍ የሰፈረ ሙሉው የአምላክ ሕግ ቅጂ አልነበራቸውም። ሆኖም ንጉሡና ካህናቱ የአምላክን ሕግ ቅጂዎች ማግኘት ይችሉ ነበር፤ እንዲሁም በየሰባት ዓመቱ ‘ወንዶች፣ ሴቶች፣ ልጆች’ እና በእስራኤል የሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎች የአምላክ ሕግ ሲነበብ የሚያዳምጡበት ዝግጅት ነበር። (ዘዳ. 31:10-12) በኢየሱስ ዘመን ደግሞ የቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅልሎች የሚገኙት በጥቂት ሰዎች እጅ እና በምኩራቦች ውስጥ ብቻ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን አብዛኞቹ ሰዎች የአምላክን ቃል በሙሉ ወይም በከፊል ማግኘት ይችላሉ። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ታዲያ ይህን መብት እንደምናደንቀው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

19. እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

19 የአምላክን ቃል በእጃችን ማግኘት መቻላችን ትልቅ መብት ነው። ቃሉን አዘውትረን በማንበብ ለዚህ መብት አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። የግል ጥናት ሲመቸን ብቻ የምናደርገው ነገር መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ጊዜ ልንመድብለት ይገባል። ቋሚ የጥናት ፕሮግራም በመከተል እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን።

20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

20 ከዚህ ዓለም ‘ጥበበኞችና አዋቂዎች’ በተለየ መልኩ እኛ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ጠንካራ እምነት አለን። (ማቴ. 11:25, 26) ይህን ቅዱስ መጽሐፍ ማጥናታችን፣ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ የሄደው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ ይህን ለማስተካከል ምን እንደሚያደርግ ለማወቅ አስችሎናል። እንግዲያው የራሳችንን እምነት ለማጠናከር ብሎም በተቻለ መጠን ብዙዎች በፈጣሪያችን ላይ እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (1 ጢሞ. 2:3, 4) እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖር ሁሉ በራእይ 4:11 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ የሚያስተጋባበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቅ፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ . . . ልትቀበል ይገባሃል።”

መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው

^ አን.5 ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ መሆኑን በግልጽ ያስተምራሉ። ብዙ ሰዎች ግን ይህን አያምኑም። ሕይወት የተገኘው ያለፈጣሪ እንደሆነ ይናገራሉ። በአምላክ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር ጥረት ካደረግን በፈጣሪ የማያምኑ ሰዎች የሚናገሩት ነገር እምነታችንን አያናጋውም። እምነታችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

^ አን.5 በብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አስተማሪዎች ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ ሲያስተምሩ ‘ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ሊሆን ይችላል’ የሚለውን ሐሳብ ጨርሶ አያነሱትም። አንዳንድ መምህራን ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ፍጥረት ማስተማር፣ ተማሪዎቹ የፈለጉትን የማመን ነፃነታቸውን እንደሚገድብባቸው ይናገራሉ።

^ አን.7 የሳይንስ ሊቃውንትን ጨምሮ ከ60 የሚበልጡ በፍጥረት የሚያምኑ ምሁራን የሰጧቸው ሐሳቦች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) ላይ ይገኛሉ። “Science” በሚለው ርዕስ ሥር “scientists expressing belief in creation” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት። ከእነዚህ ሐሳቦች መካከል አንዳንዶቹ የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍም ላይ ይገኛሉ። “ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ” በሚለው ርዕስ ሥር “‘ቃለ ምልልስ’ (የንቁ! ዓምድ)” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት።

^ አን.12 ለምሳሌ በየካቲት 2011 ንቁ! ላይ የወጣውን “ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ይስማማሉ?” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በጥር 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ይሖዋ የሚናገረው ትንቢት ይፈጸማል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.13 ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ።