አስቀድሞ ለተጻፉት ነገሮች ትኩረት ትሰጣላችሁ?
‘እነዚህ ነገሮች የተጻፉት የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።’ —1 ቆሮ. 10:11
1, 2. የአራቱን የይሁዳ ነገሥታት ምሳሌ መመርመራችን ምን ጥቅም አለው?
ከፊት ለፊትህ የሚሄድ ሰው ተንሸራትቶ ሲወድቅ ብታይ አንተም በዚያ መንገድ ስታልፍ ላለመውደቅ እንደምትጠነቀቅ የታወቀ ነው። ሌሎች ሰዎች የሠሩትን ስህተት መመልከታችን እኛም ተመሳሳይ ስህተት ላለመሥራት እንድንጠነቀቅ ሊረዳን ይችላል። ከመንፈሳዊ ሕይወታችን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች ከሠሩት ስህተት ጠቃሚ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።
2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት አራቱ የይሁዳ ነገሥታት ይሖዋን በሙሉ ልባቸው አገልግለዋል። ያም ሆኖ ከባድ ስህተት የሠሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። እነሱ ከገጠማቸው ሁኔታ ምን ትምህርት እናገኛለን? እኛም ተመሳሳይ ስህተት እንዳንሠራ መጠንቀቅ የምንችለውስ እንዴት ነው? በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችን፣ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ሲባል ቀደም ብሎ ከተጻፈው ነገር ጥቅም እንድናገኝ ያስችለናል።—ሮም 15:4ን አንብብ።
በሰብዓዊ ጥበብ መታመን ለችግር ይዳርጋል
3-5. (ሀ) የአሳ ልብ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ የነበረ ቢሆንም ምን ስህተት ሠርቷል? (ለ) ባኦስ በይሁዳ ላይ በተነሳበት ወቅት አሳ በሰዎች የታመነው ለምን ሊሆን ይችላል?
3 በመጀመሪያ እስቲ የአሳን ታሪክ እንመርምር፤ ይህን ማድረጋችን የአምላክ ቃል በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ያቀፈው ሠራዊት በይሁዳ ላይ በዘመተበት ወቅት አሳ በይሖዋ ታምኖ ነበር፤ ይሁንና የእስራኤል ንጉሥ 2 ዜና 16:1-3) በዚህ ጊዜ አሳ በራሱ ጥበብ በመታመን ወደ ሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ስጦታ ላከ፤ ይህን ያደረገው የሶርያ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ ላይ ጦርነት እንዲከፍት ለማነሳሳት ሲል ነው። ታዲያ አሳ የተጠቀመበት ስልት ያሰበውን ውጤት አስገኝቶለት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ሶርያውያን በእስራኤል ከተሞች ላይ ዘመቱ፤ “ባኦስም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ።” (2 ዜና 16:5) በዚህ ጊዜ አሳ፣ የተጠቀመበት ስልት እንደሠራ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል።
የሆነው ባኦስ በአሳ ግዛት ድንበር ላይ የምትገኘውን ራማን ማጠናከር ሲጀምር አሳ የወሰደው እርምጃ በይሖዋ እንዳልታመነ ያሳያል። (4 ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ አሳ የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ምን ተሰማው? ይሖዋ፣ አሳ በእሱ ባለመታመኑ አልተደሰተም፤ በመሆኑም ቃል አቀባዩ የሆነውን ሃናኒን በመላክ ወቅሶታል። (2 ዜና መዋዕል 16:7-9ን አንብብ።) ሃናኒ አሳን “ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም” ብሎታል። አሳ የባኦስን ዕቅድ ማጨናገፍ የቻለ ቢሆንም በቀሪው የግዛት ዘመኑ እሱም ሆነ ሕዝቡ ጦርነት አልተለያቸውም።
5 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አምላክ የአሳን ልብ ከመረመረ በኋላ ልቡ በእሱ ዘንድ ሙሉ እንደሆነ ገልጿል። (1 ነገ. 15:14) አምላክ፣ በጥቅሉ ሲታይ አሳ መለኮታዊ ብቃቶችን እንዳሟላና ሙሉ በሙሉ ለእሱ ያደረ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። ያም ቢሆን አሳ፣ ጥበብ የጎደለው አካሄድ መከተሉ ካስከተለው መዘዝ አላመለጠም። የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በእሱ ላይ በተነሳበት ወቅት በይሖዋ ከመታመን ይልቅ በሰብዓዊ አስተሳሰብ በመመራት በራሱና በቤንሃዳድ እንዲታመን ያደረገው ምንድን ነው? የአምላክን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ወይም በወታደራዊ ስልት ለመፍታት መሞከር የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ተሰምቶት ይሆን? እንዲህ ዓይነት አካሄድ የተከተለው የሌሎችን መጥፎ ምክር በመስማቱ ይሆን?
6. አሳ ከሠራው ስህተት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ምሳሌ ስጥ።
6 ስለ አሳ የሚገልጸው ዘገባ የራሳችንን አካሄድ እንድንመረምር አያነሳሳንም? አንድ ችግር ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ሲሰማን በይሖዋ መታመን እንደሚያስፈልገን ስለምናውቅ የእሱን እርዳታ መጠየቃችን አይቀርም። ይሁንና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከሚያጋጥሙን ትናንሽ የሚመስሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘስ ምን እናደርጋለን? ጉዳዩን በራሳችን ለመፍታት በመሞከር በሰብዓዊ አስተሳሰብ እንደምንመራ እናሳያለን? ወይስ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመርመርና ተግባራዊ በማድረግ በይሖዋ እንደምንታመን እናሳያለን? ለምሳሌ ያህል፣ በጉባኤ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ከቤተሰብህ ተቃውሞ ያስነሳብህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ትክክለኛውን እርምጃ መውሰድ እንድትችል ይሖዋ እንዲረዳህ ትጠይቀዋለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ከሥራህ ብትፈናቀልና ሌላ ሥራ ለማግኘት ብትቸገርስ? ሥራ በምታገኝበት ጊዜ ለአዲሱ ቀጣሪህ በየሳምንቱ የምትገኝበት የጉባኤ ስብሰባ እንዳለህ አስቀድመህ ታሳውቀዋለህ? የገጠመን ችግር ምንም ይሁን ምን እንደሚከተለው በማለት የዘመረውን መዝሙራዊ ምክር መከተላችን ጠቃሚ ነው፦ “መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል።”—መዝ. 37:5
መጥፎ ጓደኝነት ምን ያስከትላል?
7, 8. ኢዮሳፍጥ ምን ስህተት ሠርቷል? ይህስ ምን ውጤት አስከትሎበታል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
7 የአሳ ልጅ ስለሆነው ስለ ኢዮሳፍጥስ ምን ማለት ይቻላል? ኢዮሳፍጥ በርካታ ግሩም ባሕርያት ነበሩት። በአምላክ በመታመን ብዙ መልካም ነገሮች አከናውኗል። ይሁን እንጂ ኢዮሳፍጥ ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎችም አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰሜናዊውን መንግሥት ያስተዳድር ከነበረው ከክፉው ንጉሥ ከአክዓብ ጋር በጋብቻ ተዛምዷል። ከዚህም ሌላ ነቢዩ ሚካያህ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት ከአክዓብ ጎን ተሰልፎ በሶርያውያን ላይ ዘምቷል። በውጊያው ላይ ኢዮሳፍጥ ከሞት የተረፈው ለጥቂት ነው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። (2 ዜና 18:1-32) በዚያ ወቅት ነቢዩ ኢዩ “ለክፉ ሰው እርዳታ መስጠት ይገባሃል? ይሖዋን የሚጠሉትንስ መውደድ ይገባሃል?” ሲል ጠይቆታል።—2 ዜና መዋዕል 19:1-3ን አንብብ።
8 ታዲያ ኢዮሳፍጥ ካጋጠመው ነገር ትምህርት ወስዶ ይሆን? ኢዮሳፍጥ ለአምላክ ያለው ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ያለው ፍላጎት ባይቀንስም ከአክዓብ ጋር በተያያዘ ካጋጠመው ሁኔታም ሆነ ኢዩ ከሰጠው ማስጠንቀቂያ ትምህርት የወሰደ አይመስልም። ከጓደኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ እንደገና የተሳሳተ አካሄድ ተከትሏል። ኢዮሳፍጥ የአክዓብ ልጅ ከሆነው ከክፉው ንጉሥ አካዝያስ ጋር ወዳጅነት መሥርቶ ነበር፤ አካዝያስ ደግሞ የአምላክ ጠላት ነበር። ኢዮሳፍጥና አካዝያስ መርከቦችን ለመሥራት ተሻረኩ፤ ሆኖም መርከቦቹ ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት ተሰባበሩ።—9. መጥፎ ጓደኝነት በመላ ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
9 የኢዮሳፍጥን ታሪክ ማንበባችን የራሳችንን ሕይወት እንድንመረምር ሊያነሳሳን ይገባል። በጥቅሉ ሲታይ ኢዮሳፍጥ ጥሩ ንጉሥ ነበር። ትክክል የሆነውን ነገር ያደረገ ከመሆኑም ሌላ “ይሖዋን በሙሉ ልቡ [ፈልጓል]።” (2 ዜና 22:9) ይሁን እንጂ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር መግጠሙ መዘዝ አስከትሎበታል። “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ምሳሌ እናስታውስ። (ምሳሌ 13:20) እርግጥ ነው፣ ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ወደ እውነት እንዲመጡ ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። ይሁን እንጂ ኢዮሳፍጥ ከአክዓብ ጋር የማያስፈልግ ቅርርብ መፍጠሩ ሕይወቱን ሊያሳጣው እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። እኛም ይሖዋን ከማያገለግሉ ሰዎች ጋር ሳያስፈልግ መቀራረባችን ችግሮች ማስከተሉ አይቀርም።
10. (ሀ) ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘ ከኢዮሳፍጥ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ከመጥፎ ጓደኞች ጋር መግጠምን በተመለከተ ማስታወስ የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
10 ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘስ ከኢዮሳፍጥ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድ ክርስቲያን፣ ከእምነት ባልንጀሮቹ መካከል ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት እንደማይችል በማሰብ፣ ይሖዋን ከማትወድ ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት ይጀምር ይሆናል። አሊያም አንዲት እህት፣ የማያምኑ ዘመዶቿ ‘ዕድሜዋ ሳያልፍ’ እንድታገባ ጫና ያሳድሩባት ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ “የሚወደንና አጋር የሚሆነን ሰው የማግኘት ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን” ብላ እንደተናገረችው እህት ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት ባይችል ምን ማድረግ ይኖርበታል? ኢዮሳፍጥ ባጋጠመው ነገር ላይ ማሰላሰሉ ሊረዳው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ኢዮሳፍጥ የአምላክን መመሪያ ይጠይቅ ነበር። (2 ዜና 18:4-6) ይሁንና ኢዮሳፍጥ፣ ይሖዋን ከማይወደው ከአክዓብ ጋር ወዳጅነት ሲመሠርት ምን አደረገ? የይሖዋን መመሪያ ችላ አለ። ኢዮሳፍጥ፣ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ [እንደሚመላለሱ]” ማስታወስ ነበረበት። በዘመናችንም የአምላክ ዓይኖች “በምድር ሁሉ ላይ [የሚመላለሱ]” ሲሆን ይሖዋ ለእኛ ሲል ‘ብርታቱን ለማሳየት’ ዝግጁ ነው። (2 ዜና 16:9) ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ የሚረዳልን ከመሆኑም ሌላ ይወደናል። ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ አምላክ ይህን ፍላጎትህን እንደሚረዳልህና ሊረዳህ እንደሚፈልግ እምነት አለህ? ይዋል ይደር እንጂ ይህን ማድረጉ እንደማይቀር እርግጠኛ ሁን!
ልባችን እንዳይታበይ እንጠንቀቅ
11, 12. (ሀ) በሕዝቅያስ ልብ ውስጥ ያለው ነገር የተገለጠው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ሕዝቅያስን ይቅር ያለው ለምንድን ነው?
11 ከሕዝቅያስ ታሪክስ ምን ትምህርት እናገኛለን? በአንድ ወቅት፣ ልብን የሚመረምረው አምላክ በሕዝቅያስ ልብ ውስጥ ያለው ነገር እንዲገለጥ አድርጎ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 32:31ን አንብብ።) አምላክ፣ ሕዝቅያስ በጠና በታመመበት ወቅት ከሕመሙ እንደሚያገግም የሚያሳይ ምልክት ሰጠው፤ ማለትም ጥላው ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ። የባቢሎን መኳንንት ስለዚህ ምልክት ለማወቅ የፈለጉ ይመስላል፤ በመሆኑም ስለ ምልክቱ እንዲጠይቁ መልእክተኞችን ላኩ። (2 ነገ. 20:8-13፤ 2 ዜና 32:24) በዚህ ወቅት ይሖዋ፣ ሕዝቅያስ ምን እንደሚያደርግ “ለማወቅ ሲል ተወው።” ሕዝቅያስ ለባቢሎናውያኑ “ግምጃ ቤቱን ሁሉ” አሳያቸው፤ እንዲህ ያለ ማስተዋል የጎደለው ድርጊት መፈጸሙ “በልቡ ያለውን ሁሉ” የሚያሳይ ነበር።
12 የሕዝቅያስ ልብ እንዲታበይ ያደረገው ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። ይህ የሆነው በአሦራውያን ላይ ድል ስለተጎናጸፈ አሊያም አምላክ በተአምራዊ መንገድ ስለፈወሰው ይሆን? ወይስ “እጅግ ብዙ ሀብት” እና “ታላቅ ክብር” ስላገኘ ነው? ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ሕዝቅያስ ስለታበየ “ለተደረገለት መልካም ነገር አድናቆት ሳያሳይ [ቀርቷል]።” ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ሕዝቅያስ አምላክን በሙሉ ልቡ ያገለገለ ቢሆንም ይሖዋን ያሳዘነበት ጊዜ ነበር። በኋላ ላይ ግን ሕዝቅያስ “ራሱን ዝቅ አደረገ።” በመሆኑም እሱም ሆነ ሕዝቡ የይሖዋ ቁጣ አልመጣባቸውም።—2 ዜና 32:25-27፤ መዝ. 138:6
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ‘እኛን ለመፈተንና በልባችን ያለው እንዲታወቅ ለማድረግ ሲል የሚተወን’ መቼ ሊሆን ይችላል? (ለ) ላከናወንነው ነገር ሌሎች ሲያመሰግኑን ምን ልናደርግ ይገባል?
13 የሕዝቅያስን ታሪክ ማንበባችንና ባነበብነው ላይ ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ሕዝቅያስ ልቡ እንደታበየ ግልጽ የሆነው፣ ይሖዋ ሰናክሬምን ድል ካደረገውና ሕዝቅያስን ሞት አፋፍ ላይ ካደረሰው በሽታ ከፈወሰው በኋላ እንደነበር እናስታውስ። እኛስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ስናከናውን ወይም ሌሎች ሲያመሰግኑን ምን እናደርጋለን? በዚህ ጊዜ ይሖዋ ‘እኛን ለመፈተንና በልባችን ያለው እንዲታወቅ ለማድረግ ሲል ይተወን’ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የሚያቀርበውን ንግግር ለመዘጋጀት ብዙ ለፍቷል እንበል። ታዲያ ላቀረበው ንግግር ብዙዎች ሲያመሰግኑት ምን ይሰማዋል?
14 ሌሎች ሲያመሰግኑን ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው፦ “እናንተም የተሰጣችሁን ሥራ ሁሉ ባከናወናችሁ ጊዜ ‘ምንም የማንጠቅም ባሪያዎች ነን። ያደረግነው ልናደርገው የሚገባንን ነገር ነው’ በሉ።” (ሉቃስ 17:10) በዚህ ረገድም ሕዝቅያስ ከሠራው ስህተት ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሕዝቅያስ ልቡ ስለታበየ “ለተደረገለት መልካም ነገር አድናቆት ሳያሳይ [ቀርቷል]።” ይሖዋ ባደረገልን በርካታ መልካም ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን እሱ የሚጠላውን ዝንባሌ እንድናስወግድ ይረዳናል። ስለ ይሖዋና ስላደረገልን ነገሮች መናገራችንም ጠቃሚ ነው። ደግሞም ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲሁም ለሕዝቡ ድጋፍ የሚያደርገውን ቅዱስ መንፈሱን የሰጠን እሱ ነው።
ውሳኔ ስታደርጉ ጠንቃቃ ሁኑ
15, 16. ኢዮስያስ የአምላክን ጥበቃም ሆነ ሕይወቱን ያጣው ለምንድን ነው?
15 ጥሩ ንጉሥ የነበረው ኢዮስያስ ካጋጠመው ሁኔታስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ኢዮስያስ በጦርነት ተሸንፎ ሕይወቱን እንዲያጣ ምክንያት 2 ዜና መዋዕል 35:20-22ን አንብብ።) በአንድ ወቅት ኢዮስያስ፣ የግብፁን ንጉሥ ኒካዑን ‘ሊገጥም ወጥቶ ነበር።’ እርግጥ ይህን ለማድረግ የሚያነሳሳ ምንም ምክንያት አልነበረውም፤ ንጉሥ ኒካዑ ራሱ ከእሱ ጋር መዋጋት እንደማይፈልግ ለኢዮስያስ ነግሮት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “በኒካዑ በኩል የተነገረውን የአምላክ ቃል አልሰማም” ይላል። ታዲያ ኢዮስያስ ሊዋጋ የወጣው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም።
የሆነው ነገር ምን እንደሆነ እንመልከት። (16 ኢዮስያስ፣ ኒካዑ የተናገረው ነገር ከአምላክ የመጣ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይችል ነበር? ታማኝ ከሆኑት ነቢያት አንዱ የሆነውን ኤርምያስን መጠየቅ ይችል ነበር። (2 ዜና 35:23, 25) ይሁንና እንዲህ እንዳደረገ የሚገልጽ ዘገባ የለም። ከዚህም ሌላ ኒካዑ የሚሄደው ወደ ካርከሚሽ ነበር። ኒካዑ እየተጓዘ የነበረው ኢየሩሳሌምን ለመውጋት ሳይሆን “ከሌላ ብሔር ጋር” ለመዋጋት ነበር። በተጨማሪም ኒካዑ፣ ይሖዋንም ሆነ ሕዝቡን ስላልሰደበ ጉዳዩ ከአምላክ ስም ጋር የተያያዘ አልነበረም። ኢዮስያስ ከኒካዑ ጋር ለመዋጋት ያደረገው ውሳኔ ማስተዋል የጎደለው ነበር። እኛስ ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ትምህርት አለ? አንድ ችግር ሲያጋጥመን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን ጠቃሚ ነው።
17. ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ኢዮስያስ የፈጸመው ዓይነት ስህተት ከመሥራት እንድንርቅ ምን ሊረዳን ይችላል?
17 ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመርመርና በተግባር ማዋል ይኖርብናል፤ በእርግጥ ይህን ስናደርግ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገናል። አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎችን ማማከር እንፈልግ ይሆናል። ስለ ጉዳዩ ባለን እውቀት ላይ ተመሥርተን በጥሞና አስበንበት ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ጽሑፎቻችንን ተጠቅመን ምርምር እናደርጋለን። ሽማግሌዎችን ስናማክር ደግሞ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይጠቁሙን ይሆናል። የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላትን አንዲት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህች እህት ምሥራቹን የመስበክ ኃላፊነት እንዳለባት ታውቃለች። (ሥራ 4:20) ይሁን እንጂ በመስክ አገልግሎት ልትካፈል ባሰበችበት ቀን፣ ባለቤቷ አብረው ጊዜ ካሳለፉ እንደቆዩ በመግለጽ ከእሱ ጋር እንድትውል ጠየቃት እንበል። እህታችን ጥበብ ያዘለ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዷትን ጥቅሶች ትመረምር ይሆናል። አምላክን መታዘዝ እንዳለባት እንዲሁም ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ እንዳዘዘን ታውቃለች። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 5:29) በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት እንዳለባትና የአምላክ አገልጋዮች ምክንያታዊ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ማስታወስ ይኖርባታል። (ኤፌ. 5:22-24፤ ፊልጵ. 4:5) ባለቤቷ ጨርሶ አገልግሎት እንዳትወጣ ሊከለክላት እየሞከረ ነው? ወይስ በዚያ ዕለት ብቻ አብረው አንድ ነገር እንዲያከናውኑ መጠየቁ ነው? በእርግጥም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና ጥሩ ሕሊና ይዘን ለመኖር ስንጥር ሚዛናዊ መሆናችን አስፈላጊ ነው።
በሙሉ ልብ ይሖዋን ማገልገል ደስታ ያስገኛል
18. በዚህ ርዕስ ውስጥ የተመለከትናቸውን አራት ነገሥታት ታሪክ መመርመርህ ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል?
18 እኛም ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን እስካሁን የተመለከትናቸው አራት ነገሥታት የሠሯቸውን አንዳንድ ስህተቶች ለመሥራት እንፈተን ይሆናል። ምናልባትም (1) ሳናውቀው በሰብዓዊ ጥበብ ልንታመን፣ (2) ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ልንገጥም (3) ልባችን ሊታበይ ወይም (4) የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ሳንመረምር ውሳኔ ልናደርግ እንችላለን። ያም ቢሆን ይሖዋን ፈጽሞ ልናስደስተው እንደማንችል ማሰብ አይኖርብንም። ይሖዋ የእነዚያን ነገሥታት መልካም ጎን እንደተመለከተ ሁሉ የእኛንም መልካም ጎን ይመለከታል። በተጨማሪም ይሖዋ ምን ያህል እንደምንወደው እንዲሁም በሙሉ ልባችን ልናገለግለው እንደምንፈልግ ያውቃል። በመሆኑም ከባድ ስህተት ከመሥራት እንድንርቅ ሲል የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ እናሰላስል፤ እንዲሁም ይሖዋ እነዚህን ምሳሌዎች በቃሉ ውስጥ ስላሰፈረልን አመስጋኞች እንሁን!