ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ
“በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ በረከት፣ ክብር፣ ግርማና ኃይል ለዘላለም ይሁን።”—ራእይ 5:13
1. አንዳንድ ሰዎች አክብሮት ሊሰጣቸው የሚገባው ለምን ሊሆን ይችላል? ከዚህ ቀጥሎ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?
አንድን ሰው ማክበር ሲባል ለዚያ ሰው የተለየ ትኩረትና ከፍ ያለ ግምት መስጠት ማለት ነው። ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሥራ ያከናወኑ ወይም ለየት ያለ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ሰዎች እንዲህ ያለ ክብር እንደሚሰጣቸው የታወቀ ነው። በመሆኑም በዚህ ርዕስ ውስጥ አክብሮት ማሳየት ያለብን ለማን እንደሆነና እንዲህ ዓይነቱን ክብር መስጠታችን ተገቢ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመረምራለን።
2, 3. (ሀ) ይሖዋ የተለየ ክብር ይገባዋል የምንለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ራእይ 5:13 ላይ የተጠቀሰው በግ ማን ነው? ክብር የሚገባውስ ለምንድን ነው?
2 ራእይ 5:13 ‘በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውና በጉ’ ክብር እንደሚገባቸው ይናገራል። በዚሁ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ ደግሞ ይሖዋ ክብር ይገባዋል እንድንል ከሚያደርጉን ምክንያቶች አንዱ ተገልጿል። በሰማይ ያሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ “ለዘላለም የሚኖረውን” ይሖዋን እንዲህ እያሉ ያወድሱታል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:9-11
3 በጉ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ” ተብሎ ተገልጿል። (ዮሐ. 1:29) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ እስካሁን በምድር ላይ ከገዙትም ሆነ እየገዙ ካሉት ነገሥታት ሁሉ የላቀ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እሱ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ነው፤ ያለመሞትን ባሕርይ የተላበሰው እሱ ብቻ ነው፤ ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤ እሱን ያየ ወይም ሊያየው የሚችል አንድም ሰው የለም።” (1 ጢሞ. 6:14-16) በእርግጥም ከነገሥታት መካከል ለኃጢአታችን ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት ቤዛ አድርጎ የሰጠ ማን አለ? አንተስ በሰማይ ከሚገኙት እልፍ አእላፍ ፍጥረታት ጋር በመሆን በጉን ለማወደስ አትገፋፋም? እነሱ እንዲህ ብለዋል፦ “ታርዶ የነበረው በግ ኃይል፣ ብልጽግና፣ ጥበብ፣ ብርታት፣ ክብር፣ ግርማና በረከት ሊቀበል ይገባዋል።”—ራእይ 5:12
4. ይሖዋንና ክርስቶስን ማክበር ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋንና ክርስቶስን ማክበር ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም። የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ይህን በማድረጋችን ላይ ነው። በዮሐንስ 5:22, 23 ላይ ኢየሱስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ይህን ሐሳብ በግልጽ እንድንረዳ ያስችሉናል፦ “አብ በማንም ላይ አይፈርድምና፤ ከዚህ ይልቅ የመፍረዱን ሥልጣን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶታል፤ ይህን ያደረገውም ሁሉም አብን እንደሚያከብሩ ሁሉ ወልድንም እንዲያከብሩ ነው። ወልድን የማያከብር ሁሉ እሱን የላከውን አብንም አያከብርም።”—መዝሙር 2:11, 12ን አንብብ።
5. ሁሉም ሰው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አክብሮት ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?
5 ሰዎች የተፈጠሩት “በአምላክ መልክ” ነው። (ዘፍ. 1:27) በመሆኑም አብዛኞቹ ሰዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአምላክን አንዳንድ ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። የሰው ልጆች አንዳቸው ለሌላው እንደ ፍቅር፣ ደግነትና ርኅራኄ ያሉትን ባሕርያት ማሳየት ይችላሉ። አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥራቸው ሕሊና ይኸውም ክፉና ደጉን ለመለየት የሚረዳ ተፈጥሯዊ ችሎታ ሰጥቷቸዋል፤ ሕሊና አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ወይም የተዛባ ምልክት ሊሰጥ ቢችልም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ትክክልና ስህተት፣ እውነትና ውሸት እንዲሁም ተገቢ የሆነና ያልሆነን ነገር ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። (ሮም 2:14, 15) ንጹሕና ውብ የሆነ ነገር ብዙዎችን ይማርካል። በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የይሖዋን ክብር በተወሰነ ደረጃ እንደሚያንጸባርቁ የሚያሳይ ነው፤ በዚህም ምክንያት አክብሮት ይገባቸዋል።—መዝ. 8:5
ለሌሎች አክብሮት በማሳየት ረገድ ሚዛናዊ መሆን
6, 7. ለሌሎች አክብሮት በማሳየት ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ከአብዛኞቹ ሰዎች የሚለዩት በምን መንገድ ነው?
6 ለሰዎች ምን ዓይነት አክብሮት ማሳየት እንደሚገባንና ምን ያህል ልናከብራቸው እንደሚገባ ግራ ሊገባን ይችላል፤ በመሆኑም በዚህ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበራችን አስፈላጊ ነው። በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያለው መንፈስ በብዙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በዚህም ምክንያት ብዙዎች፣ ለሌሎች ሰዎች ተገቢውን አክብሮት ከማሳየት ይልቅ አምልኮ አከል ክብር ይሰጧቸዋል። ለሃይማኖትና ለፖለቲካ መሪዎች፣ ለታዋቂ ስፖርተኞችና በመዝናኛው ዓለም ላሉ ስመ ጥር ሰዎች እንዲሁም ለሌሎች ዝነኛ ግለሰቦች በጣም የተጋነነ አመለካከት ስላላቸው ለሰው ከሚገባው ያለፈ አክብሮት ያሳዩዋቸዋል። ወጣት አዋቂ ሳይል አብዛኛው ሰው እነዚህን ግለሰቦች እንደ አርዓያ በመውሰድ የእነሱን አኳኋን፣ አለባበስ ወይም ምግባር ይከተላል።
7 እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሰዎች አክብሮት በማሳየት ረገድ እንዲህ ያለ የተዛባ አመለካከት ላለማዳበር ይጠነቀቃሉ። ፍጹም አርዓያ የተወልን፣ ልንመስለው የሚገባ ሰው ክርስቶስ ብቻ ነው። (1 ጴጥ. 2:21) ሰዎችን ከሚገባቸው በላይ ክብር የምንሰጣቸው ከሆነ አምላክን እናሳዝናለን። “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” የሚለውን እውነታ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ሮም 3:23) በእርግጥም አምልኮ አከል ክብር የሚገባው አንድም ሰው የለም።
8, 9. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ለመንግሥት ባለሥልጣናት ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) ባለሥልጣናትን መታዘዝ የሚገባን እስከ ምን ድረስ ነው?
8 በዓለም ላይ ባለሥልጣናት ሆነው ወይም የኃላፊነት ቦታ ተረክበው የሚሠሩ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ሕግና ሥርዓት የሚያስከብሩ ከመሆኑም ሌላ ዜጎቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ሮም 13:1, 7
ነገሮች ያሟላሉ። እነዚህ ባለሥልጣናት የሚሰጡት አገልግሎት ለሁላችንም ጥቅም ያስገኛል። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንደ “በላይ ባለሥልጣናት” ሊመለከቷቸውና ሊገዙላቸው እንደሚገባ ተናግሯል። በተጨማሪም ‘ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ ስጡ፤ መከበር የሚፈልገውን አክብሩ’ የሚል መመሪያ ሰጥቷል።—9 የይሖዋ ምሥክሮች ለመንግሥት ባለሥልጣናት አክብሮት ለማሳየት የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ አገር የየራሱ ባሕል ስላለው አክብሮት በማሳየት ረገድ የሚጠበቅብን ነገር እንደየአገሩ ሊለያይ ይችላል። ያም ቢሆን ባለሥልጣናቱ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ከእነሱ ጋር ለመተባበር እንጥራለን። በእርግጥ የምናሳየው አክብሮትና ታዛዥነት ገደብ እንዳለው ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቁማሉ። የአምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ ወይም ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን እንድናላላ የሚያደርግ ነገር አናደርግም።—1 ጴጥሮስ 2:13-17ን አንብብ።
10. በጥንት ጊዜ የኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት አክብሮት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትተውልናል?
10 በጥንት ጊዜ የኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት አክብሮት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። የሮም መንግሥት፣ በግዛቱ ውስጥ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዋጅ ባወጣ ጊዜ ዮሴፍና ማርያም ታዘዋል። በወቅቱ ማርያም የበኩር ልጇን የምትወልድበት ጊዜ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ለመመዝገብ ወደ ቤተልሔም ተጉዘዋል። (ሉቃስ 2:1-5) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጳውሎስ፣ ጥፋት ሠርተሃል ተብሎ በተከሰሰበት ወቅት ትሕትና በተሞላበት መንገድ የመከላከያ ሐሳቡን ያቀረበ ሲሆን ለንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳና በሮም ግዛት ሥር የነበረችው የይሁዳ አገረ ገዢ ለሆነው ለፊስጦስ ተገቢውን አክብሮት አሳይቷል።—ሥራ 25:1-12፤ 26:1-3
11, 12. (ሀ) ለመንግሥት ባለሥልጣናትና ለሃይማኖት መሪዎች እኩል ክብር የማንሰጠው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ኦስትሪያዊ የይሖዋ ምሥክር ለአንድ ፖለቲከኛ አክብሮት ማሳየቱ ምን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል?
11 በሌላ በኩል ግን የይሖዋ ምሥክሮች ለሃይማኖት መሪዎች የተለየ አክብሮት አይሰጡም፤ እርግጥ እነዚህ መሪዎች ልዩ አክብሮት እንዲሰጣቸው ይጠብቁ ይሆናል። የሐሰት ሃይማኖት፣ ሰዎች ስለ አምላክ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በተዛባ መንገድ ያቀርባል። በመሆኑም የሃይማኖት መሪዎችን እንደ ማንኛውም ሰው የምናከብራቸው ቢሆንም ልዩ ክብር አንሰጣቸውም። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን እንዲህ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች፣ ግብዞች እንዲሁም ዕውር መሪዎች በማለት እንዳወገዛቸው እናውቃለን። (ማቴ. 23:23, 24) ከዚህ በተቃራኒ ግን ለመንግሥት ባለሥልጣናት ተገቢውን አክብሮት ማሳየታችን አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ አልፎ ተርፎም ያልተጠበቀ ነገር እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
12 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች፣ ሌኦፖልት ኤንግላይትነር የተባለውን የኦስትሪያ ተወላጅ የሆነ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር በቡከንዋልድ ወደሚገኝ ማጎሪያ ካምፕ ልከውት ነበር። ወንድም ኤንግላይትነር በተጓዘበት ባቡር ላይ ዶክተር ሃይንሪች ግላይስነር የተባሉ ሰው ነበሩ። ኦስትሪያ ውስጥ ፖለቲከኛ የነበሩትን እኚህን ሰው ናዚዎች አስረዋቸው ነበር። ወደ ማጎሪያ ካምፑ እየተጓዙ እያለ ወንድም ኤንግላይትነር፣ ለዶክተር ግላይስነር አክብሮት በተሞላበት መንገድ ስለ እምነቱ የነገራቸው ሲሆን እሳቸውም በጥሞና አዳመጡት። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ ዶክተር ግላይስነር ያላቸውን ሥልጣን በመጠቀም በኦስትሪያ ያሉ ወንድሞችን በተደጋጋሚ ጊዜ ረድተዋል። አንተም ክርስቲያኖች ለመንግሥት ባለሥልጣናት ተገቢውን አክብሮት ማሳየት እንዳለባቸው የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መከተላቸው ጥሩ ውጤት እንዳስገኘ የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን ታስታውስ ይሆናል።
ክብር ልንሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ሰዎች
13. አክብሮት ልናሳያቸው ከሚገቡ ሰዎች መካከል እነማን ይገኙበታል? ለምንስ?
13 በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች አክብሮት ማሳየት እንዳለብን ግልጽ ነው። በተለይ ደግሞ በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡን ሽማግሌዎች ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:17ን አንብብ።) እነዚህ ወንድሞች ብሔራቸው፣ የትምህርት ደረጃቸው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ወይም የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን አክብሮት እናሳያቸዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎች “ስጦታ” እንደሆኑ የሚናገር ሲሆን እነዚህ ወንድሞች፣ አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ባደረገው ዝግጅት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። (ኤፌ. 4:8) የጉባኤ ሽማግሌዎችን፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የበላይ አካል አባላትን እስቲ እናስብ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም አመራር የሚሰጡንን የተሾሙ ወንድሞች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። እርግጥ ነው፣ የክርስቲያን ጉባኤን ወክለው ለሚያገለግሉ የታወቁ ወንድሞች አምልኮ አከል ክብር አንሰጣቸውም፤ ወይም ደግሞ መልአክ ያየን ይመስል ለእነሱ የተለየ ቦታ ለመስጠት አንሞክርም። ይሁንና እነዚህ ወንድሞች ሥራቸውን በትጋት ስለሚያከናውኑና ትሑት ስለሆኑ አክብሮት እናሳያቸዋለን።—2 ቆሮንቶስ 1:24ን እና ራእይ 19:10ን አንብብ።
14, 15. በእውነተኛ ክርስቲያን እረኞችና በብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
14 እነዚህ ሽማግሌዎች፣ ትሑት የሆኑ መንፈሳዊ እረኞች ናቸው። እንደ ዝነኛ ሰዎች እንድንመለከታቸው አይፈልጉም፤ ይህ ደግሞ ትሑት እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። በዚህ መንገድ በአሁኑ ጊዜ ካሉትም ሆነ በኢየሱስ ዘመን ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ይለያሉ፤ ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “በራት ግብዣ ላይ የክብር ቦታ ማግኘት፣ በምኩራብ ደግሞ ከፊት መቀመጥ ይወዳሉ፤ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ።”—ማቴ. 23:6, 7
15 እውነተኛ ክርስቲያን እረኞች፣ ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ ትሑት እንደሆኑ ያሳያሉ፤ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “መምህራችሁ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። በተጨማሪም አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ። ይልቁንም ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል። ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።” (ማቴ. 23:8-12) በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች የወንድሞቻቸውን ፍቅርና አክብሮት ያተረፉት ለምን እንደሆነ መገመት አያዳግትም።
16. መጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ማሳየትን በተመለከተ የሚሰጠውን መመሪያ ለመረዳትና በተግባር ለማዋል ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
16 ለእነማን አክብሮት ማሳየት እንደሚገባንና በምን መንገድ አክብሮት ማሳየት እንዳለብን ማወቃችን አስፈላጊ ነው፤ በእርግጥ በዚህ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ጊዜ ይጠይቃል። በጥንት ጊዜ የነበሩት እውነተኛ ክርስቲያኖችም እንዲህ ያለ ሥራ 10:22-26፤ 3 ዮሐ. 9, 10) ያም ቢሆን አክብሮት ማሳየትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ በተግባር ለማዋል ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆናችን ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል።
አመለካከት ለማዳበር ጊዜ ወስዶባቸዋል። (ተገቢውን ክብር ማሳየት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
17. በሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች አክብሮት ማሳየት የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
17 የመንግሥት ባለሥልጣናትንና በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን ማክበራችን፣ የስብከቱ ሥራችንን ያለምንም ችግር የማከናወን መብታችንን እንዲያስከብሩልን ሊያነሳሳቸው ይችላል። በተጨማሪም ለስብከቱ ሥራችን ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። ቢርጊት የምትባል በጀርመን የምትኖር አንዲት አቅኚ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ልጇ ከትምህርት ቤት ስትመረቅ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝታ ነበር። አስተማሪዎቹ ባለፉት ዓመታት ውስጥ የይሖዋ ምሥክር ልጆችን የማስተማር አጋጣሚ በማግኘታቸው እንደተደሰቱ ለቢርጊት ነገሯት። አክለውም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የይሖዋ ምሥክር ልጆች ባይኖሩ በጣም ያዝኑ እንደነበር ገልጸውላታል። ቢርጊትም “ልጆቻችን የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንዲከተሉ ይማራሉ፤ ይህ ደግሞ አስተማሪዎችን ማክበርን ይጨምራል” በማለት ለአስተማሪዎቹ ነገረቻቸው። አንዲት መምህርት “ሁሉም ተማሪዎች እንደ እናንተ ልጆች ቢሆኑ ኖሮ ማስተማር በጣም አስደሳች ይሆን ነበር” ብላለች። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ከአስተማሪዎቹ አንዷ በላይፕሲግ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝታለች።
18, 19. ለሽማግሌዎች አክብሮት ከመስጠት ጋር በተያያዘ ልንጠነቀቅበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው?
18 ለጉባኤ ሽማግሌዎች ተገቢውን አክብሮት ከማሳየት ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ጥበብ የተንጸባረቀበትና ፍጹም የሆነ መመሪያ መከተል ይኖርብናል። (ዕብራውያን 13:7, 17ን አንብብ።) ለሚያከናውኑት ትጋት የተሞላበት ሥራ ማመስገንና የሚሰጡንን መመሪያ በመታዘዝ ከእነሱ ጋር መተባበር ይገባናል። ይህን ማድረጋችን ሥራቸውን በደስታ እንዲሠሩ ይረዳቸዋል። እንዲህ ሲባል ግን “ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን” አንድ ሽማግሌ አለባበስና አጋጌጥ፣ ንግግር የሚያቀርብበትን መንገድ አልፎ ተርፎም የአነጋገር ዘይቤውን ለመኮረጅ እንጥራለን ማለት አይደለም። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የተሳሳተ መልእክት ልናስተላልፍ እንችላለን። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ይህ ሽማግሌም ቢሆን ፍጹም አለመሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። አርዓያ አድርገን ልንከተለውና ልንመስለው የሚገባን ክርስቶስን ነው።
19 ሽማግሌዎችን እንደ ዝነኛ ሰዎች አድርገን ከማየት በመቆጠብ ተገቢውን አክብሮት የምናሳያቸው ከሆነ እነሱም ይጠቀማሉ። እንዲህ ማድረጋችን ከኩራት፣ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ከመመልከትና ከመመጻደቅ እንዲርቁ ይረዳቸዋል።
20. ለሌሎች አክብሮት ማሳየታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
20 ክብር ለሚገባቸው ክብር መስጠታችን በራሳችን ላይ ብቻ እንዳናተኩር ያደርገናል። ሰዎች አክብሮት ሲያሳዩን ለራሳችን የተጋነነ አመለካከት እንዳናዳብር ይረዳናል። በተጨማሪም ለእምነት አጋሮቻችንም ሆነ ለማያምኑ ሰዎች ከልክ ያለፈና ተገቢ ያልሆነ አክብሮት ባለመስጠት የይሖዋ ድርጅት ያለው ዓይነት አቋም እንዲኖረን ያስችለናል። ከዚህም ሌላ ለሌሎች ተገቢውን አክብሮት መስጠታችን፣ እናከብረው የነበረ አንድ ሰው ያልጠበቅነው ነገር ቢያደርግ እንዳንደናቀፍ ስለሚረዳን ጥበቃ ይሆንልናል።
21. ክብር ለሚገባው ክብር መስጠታችን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ሁሉ የላቀው የትኛው ነው?
21 ክብር ለሚገባው ክብር መስጠታችን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ሁሉ የላቀው፣ ይህን ማድረጋችን አምላክን የሚያስደስት መሆኑ ነው። በዚህ መንገድ አምላክ የሚጠብቅብንን የምናደርግ ከመሆኑም ሌላ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንሆናለን። ይህም ይሖዋን ለሚነቅፍ ሁሉ መልስ ለመስጠት ያስችለናል። (ምሳሌ 27:11) በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ለሌሎች ክብር በማሳየት ረገድ ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። እኛ ግን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ለሌሎች እንዴት ክብር ማሳየት እንደምንችል ማወቃችን አመስጋኝ እንድንሆን ያነሳሳናል።