ሁለተኛ ዜና መዋዕል 22:1-12

  • አካዝያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-9)

  • ጎቶልያ በጉልበት ዙፋን ላይ ወጣች (10-12)

22  ከዚያም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የመጨረሻ ልጁን አካዝያስን* በእሱ ምትክ አነገሡት፤ ከዓረቦቹ ጋር ወደ ሰፈሩ የመጡት ወራሪዎች ታላላቆቹን በሙሉ ገድለዋቸው ነበር።+ በመሆኑም የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ።+  አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ+ የተባለች የኦምሪ+ የልጅ ልጅ* ነበረች።  እናቱ ክፉ ነገር እንዲያደርግ ትመክረው ስለነበር እሱም የአክዓብን+ ቤት መንገድ ተከተለ።  ከአባቱ ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት ሰዎች አማካሪዎቹ በመሆን ወደ ጥፋት ስለመሩት ልክ እንደ አክዓብ ቤት እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጠለ።  እሱም የእነሱን ምክር ተከትሎ ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል+ ጋር በራሞትጊልያድ+ ለመዋጋት ከእስራኤል ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሄደ፤ በዚያም ቀስተኞች ኢዮራምን አቆሰሉት።  እሱም ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር በተዋጋበት ጊዜ+ በራማ ካቆሰሉት ቁስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል+ ተመለሰ። የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም+ ልጅ አካዝያስ* የአክዓብ ልጅ ኢዮራም+ ቆስሎ*+ ስለነበር እሱን ለማየት ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።  ይሁንና አካዝያስ ወደ ኢዮራም በመምጣቱ አምላክ ለውድቀት ዳረገው፤ እዚያ ከደረሰ በኋላም ከኢዮራም ጋር የኒምሺን የልጅ ልጅ* ኢዩን+ ለማግኘት ሄዱ፤ ኢዩ የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ ይሖዋ የቀባው ሰው ነበር።+  ኢዩም በአክዓብ ቤት ላይ የተላለፈውን ፍርድ ማስፈጸም ሲጀምር የአካዝያስ አገልጋዮች የነበሩትን የይሁዳን መኳንንትና የአካዝያስን ወንድሞች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው።+  ከዚያም አካዝያስን ለመፈለግ ሄደ፤ እነሱም በሰማርያ ተደብቆ ሳለ ያዙት፤ ወደ ኢዩም አመጡት። ከዚያም ገደሉት፤ ይሁንና “ይሖዋን በሙሉ ልቡ የፈለገው የኢዮሳፍጥ የልጅ ልጅ ነው” በማለት ቀበሩት።+ ከአካዝያስ ቤት የመንግሥቱን ሥልጣን የመያዝ ብቃት ያለው ሰው አልነበረም። 10  የአካዝያስ እናት ጎቶልያ+ ልጇ መሞቱን ባየች ጊዜ ተነስታ የይሁዳን ንጉሣውያን ቤተሰብ* በሙሉ አጠፋች።+ 11  ይሁንና የንጉሡ ልጅ የሆነችው ዮሳቤት ሊገደሉ ከነበሩት የንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮዓስን+ ሰርቃ በመውሰድ እሱንና ሞግዚቱን በውስጠኛው መኝታ ክፍል አስቀመጠቻቸው። የንጉሥ ኢዮራም+ ልጅ የሆነችው ዮሳቤት (የካህኑ ዮዳሄ+ ሚስትና የአካዝያስ እህት ነበረች) ከጎቶልያ ደብቃ አቆየችው፤ በመሆኑም ጎቶልያ ሳትገድለው ቀረች።+ 12  እሱም ከእነሱ ጋር ለስድስት ዓመት በእውነተኛው አምላክ ቤት ተደብቆ ቆየ፤ በዚህ ጊዜ ጎቶልያ በምድሪቱ ላይ ትገዛ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

በ2ዜና 21:17 ላይ ኢዮዓካዝ ተብሎም ተጠርቷል።
ቃል በቃል “ሴት ልጅ።”
ወይም “ታሞ።”
በአንዳንድ የዕብራይስጥ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ አዛርያስ ተብሎም ተጠርቷል።
ቃል በቃል “ወንድ ልጅ።”
ቃል በቃል “የመንግሥት ዘር።”