ሁለተኛ ዜና መዋዕል 18:1-34

  • ኢዮሳፍጥ ከአክዓብ ጋር ግንባር ፈጠረ (1-11)

  • ሚካያህ ትንቢት ተናገረ (12-27)

  • አክዓብ ራሞትጊልያድ ላይ ተገደለ (28-34)

18  ኢዮሳፍጥ ብዙ ሀብትና ታላቅ ክብር አገኘ፤+ ይሁንና ከአክዓብ+ ጋር በጋብቻ ተዛመደ።  ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም በሰማርያ ወደሚገኘው ወደ አክዓብ ወረደ፤+ አክዓብም ለኢዮሳፍጥና አብረውት ለነበሩት ሰዎች እጅግ ብዙ በግና ከብት መሥዋዕት አደረገ። ደግሞም በራሞትጊልያድ+ ላይ እንዲዘምት ገፋፋው።*  ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “ወደ ራሞትጊልያድ ከእኔ ጋር አብረህ ትሄዳለህ?” አለው። እሱም “እኔ ማለት እኮ አንተ ማለት ነህ፤ ሕዝቤም ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱም አብረንህ እንሰለፋለን” አለው።  ሆኖም ኢዮሳፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ “እባክህ፣ በመጀመሪያ ይሖዋ ምን እንደሚል ጠይቅ” አለው።+  በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ 400 የሚሆኑ ነቢያትን አንድ ላይ ሰብስቦ “ራሞትጊልያድን ለመውጋት ልዝመት ወይስ ይቅርብኝ?” አላቸው። እነሱም “ዝመት፤ እውነተኛው አምላክ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” አሉት።  ከዚያም ኢዮሳፍጥ “በዚህ ቦታ የይሖዋ ነቢይ የለም?+ ካለ በእሱም አማካኝነት እንጠይቅ” አለ።+  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “በእሱ አማካኝነት ይሖዋን ልንጠይቅ የምንችልበት አንድ ሰው ይቀራል፤+ ሆኖም ሁልጊዜ ስለ እኔ መጥፎ ነገር እንጂ መልካም ነገር ፈጽሞ ስለማይተነብይ በጣም እጠላዋለሁ።+ እሱም የይምላ ልጅ ሚካያህ ነው” አለው። ኢዮሳፍጥ ግን “ንጉሡ እንዲህ ሊል አይገባም” አለ።  ስለሆነም የእስራኤል ንጉሥ አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚካያህን በአስቸኳይ ይዘኸው ና” አለው።+  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ የንግሥና ልብሳቸውን ለብሰው በየዙፋናቸው ተቀምጠው ነበር፤ የተቀመጡትም በሰማርያ መግቢያ በር በሚገኘው አውድማ ላይ ሲሆን ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 10  ከዚያም የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’”* አለ። 11  ሌሎቹ ነቢያትም ሁሉ “ወደ ራሞትጊልያድ ውጣ፤ ይሳካልሃል፤+ ይሖዋም እሷን በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር። 12  ሚካያህን ለመጥራት የሄደው መልእክተኛም “እነሆ፣ ነቢያቱ ሁሉ በአንድ ድምፅ ለንጉሡ የተናገሩት ነገር ጥሩ ነው። እባክህ፣ የአንተም ቃል እንደ እነሱ ይሁን፤+ አንተም ጥሩ ነገር ተናገር” አለው።+ 13  ሚካያህ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፤ የምናገረው አምላኬ የሚለውን ብቻ ነው” አለ።+ 14  ከዚያም ወደ ንጉሡ ገባ፤ ንጉሡም “ሚካያህ፣ ራሞትጊልያድን ለመውጋት እንዝመት ወይስ ይቅርብኝ?” ሲል ጠየቀው። እሱም ወዲያውኑ “ውጡ፤ ይቀናችኋል፤ በእጃችሁም አልፈው ይሰጣሉ” በማለት መለሰለት። 15  በዚህ ጊዜ ንጉሡ “በይሖዋ ስም ከእውነት በስተቀር ሌላ አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማስምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። 16  በመሆኑም ሚካያህ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እስራኤላውያን ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አያለሁ።+ ይሖዋም ‘እነዚህ ጌታ የላቸውም። እያንዳንዳቸው በሰላም ወደየቤታቸው ይመለሱ’ ብሏል።” 17  ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “‘ስለ እኔ መጥፎ ነገር ብቻ እንጂ ጥሩ ነገር አይተነብይም’ ብዬህ አልነበረም?” አለው።+ 18  በዚህ ጊዜ ሚካያህ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የይሖዋን ቃል ስሙ፦ ይሖዋ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣+ የሰማያት ሠራዊትም+ ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።+ 19  ከዚያም ይሖዋ ‘በራሞትጊልያድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ማን ያሞኘዋል?’ አለ። በዚህ ጊዜ አንዱ አንድ ነገር፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር ተናገረ። 20  ከዚያም አንድ መንፈስ*+ ወደ ፊት ወጥቶ ይሖዋ ፊት በመቆም ‘እኔ አሞኘዋለሁ’ አለ። ይሖዋም ‘እንዴት አድርገህ?’ አለው። 21  ‘እኔ እወጣና በነቢያቱ ሁሉ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እሱም ‘እንግዲያው ታሞኘዋለህ፤ ደግሞም ይሳካልሃል። ውጣና እንዳልከው አድርግ’ አለው። 22  ይሖዋም በእነዚህ ነቢያትህ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ አኑሯል፤+ ሆኖም ይሖዋ ጥፋት እንደሚመጣብህ ተናግሯል።” 23  የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስም+ ወደ ሚካያህ+ ቀርቦ በጥፊ መታውና+ “ለመሆኑ የይሖዋ መንፈስ እኔን በየት በኩል አልፎ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው።+ 24  ሚካያህም “በየት በኩል እንዳለፈማ፣ ለመደበቅ ወደ ውስጠኛው ክፍል በምትገባበት ቀን ታውቀዋለህ” አለው። 25  ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚካያህን ወስዳችሁ ለከተማው አለቃ ለአምዖን እና የንጉሡ ልጅ ለሆነው ለዮአስ አስረክቡት። 26  እንዲህም በሏቸው፦ ‘ንጉሡ “በሰላም ተመልሼ እስክመጣ ድረስ ይህን ሰው እስር ቤት አቆዩት፤+ ጥቂት ምግብና ውኃ ብቻ ስጡት” ብሏል።’” 27  ሚካያህ ግን “እውነት አንተ በሰላም ከተመለስክ ይሖዋ በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ።+ ከዚያም “እናንተ ሰዎች፣ ሁላችሁም ልብ በሉ” አለ። 28  በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ወደ ራሞትጊልያድ+ ወጡ። 29  የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “እኔ ማንነቴ እንዳይታወቅ ራሴን ለውጬ ወደ ውጊያው እገባለሁ፤ አንተ ግን ንጉሣዊ ልብስህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ማንነቱ እንዳይታወቅ ራሱን ለወጠ፤ ከዚያም ወደ ውጊያው ገቡ። 30  በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገሎቹን አዛዦች “ከእስራኤል ንጉሥ በስተቀር ከትንሹም ሆነ ከትልቁ፣ ከማንም ጋር እንዳትዋጉ” በማለት አዟቸው ነበር። 31  የሠረገሎቹ አዛዦችም ኢዮሳፍጥን ባዩት ጊዜ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” ብለው አሰቡ። በመሆኑም ሊወጉት ወደ እሱ ዞሩ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ እርዳታ ለማግኘት ጮኸ፤+ ይሖዋም ረዳው፤ አምላክም ወዲያውኑ ከእሱ እንዲርቁ አደረገ። 32  የሠረገሎቹ አዛዦችም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ሲያዩ ወዲያውኑ እሱን ማሳደዳቸውን ትተው ተመለሱ። 33  ይሁንና አንድ ሰው በነሲብ* ቀስቱን ሲያስወነጭፍ የእስራኤልን ንጉሥ የጥሩሩ መጋጠሚያ ላይ ወጋው። ስለሆነም ንጉሡ ሠረገላ ነጂውን “ክፉኛ ስለቆሰልኩ ሠረገላውን አዙረህ ከጦርነቱ* ይዘኸኝ ውጣ” አለው።+ 34  ያን ቀን ሙሉ የተፋፋመ ውጊያ ተካሄደ፤ የእስራኤልንም ንጉሥ ሠረገላው ውስጥ እንዳለ ፊቱን ወደ ሶርያውያን አዙረው እስከ ምሽት ድረስ ደግፈው አቆሙት፤ ፀሐይ ስትጠልቅም ሞተ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አግባባው።”
ወይም “ትገፋቸዋለህ።”
ወይም “አንድ መልአክ።”
ወይም “ሳያስብ።”
ቃል በቃል “ከሰፈሩ።”