በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ከጥበበኞች ጋር በመሄዴ ተጠቅሜያለሁ

ከጥበበኞች ጋር በመሄዴ ተጠቅሜያለሁ

ቦታው ብሩኪንግዝ፣ ሳውዝ ዳኮታ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን የዚያን ቀን ጠዋት አየሩ ይቀዘቅዝ ነበር። ይህም የቅዝቃዜው ወቅት እየተቃረበ እንደሆነ የሚጠቁም ነበር። የሚገርመው ነገር በዚያ ዕለት እኔና አብረውኝ የነበሩት ጥቂት ሰዎች፣ ከብቶች በሚቀለቡበት ቤት ውስጥ በብርድ እየተንቀጠቀጥን ቆመን ነበር። ፊት ለፊታችን በቀዝቃዛ ውኃ የተሞላ የከብቶች ውኃ መጠጫ ገንዳ ነበር። ይህ የሆነው ለምን እንደሆነ መረዳት እንድትችሉ እስቲ ታሪኬን ላጫውታችሁ።

የልጅነት ሕይወቴ

አጎቴ አልፍሬድ እና አባቴ

የተወለድኩት መጋቢት 7, 1936 ሲሆን ከአራት ልጆች መካከል የመጨረሻው ነኝ። የምንኖረው በምሥራቃዊ ሳውዝ ዳኮታ በሚገኝ አነስተኛ የእርሻ ቦታ ነበር። ቤተሰባችን የሚተዳደረው በግብርና ሥራ ነበር፤ ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ይህ ሥራ አልነበረም። በ1934 ወላጆቼ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ለሰማዩ አባታችን ለይሖዋ ራሳቸውን ወስነው ስለነበር የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። በመጀመሪያ አባቴ ክላረንስ፣ በኋላ ደግሞ አጎቴ አልፍሬድ በካንዲ፣ ሳውዝ ዳኮታ በሚገኘው አነስተኛ ጉባኤያችን ውስጥ የቡድን አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) ሆነው አገልግለዋል።

ቤተሰባችን አዘውትሮ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠውን አስደሳች ተስፋ ለሰዎች ይናገር ነበር። ወላጆቻችን የተዉልን ምሳሌና የሰጡን ሥልጠና በእኛ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። እኔም ሆንኩ እህቴ ዶረቲ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የሆንነው ስድስት ዓመት ሲሞላን ነው። በ1943 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መካሄድ የጀመረ ሲሆን እኔም በዚያው ዓመት በትምህርት ቤቱ መካፈል ጀመርኩ።

በ1952 በአቅኚነት ሳገለግል

ትላልቅ ስብሰባዎች በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ነበራቸው። በ1949 በሱ ፎልስ፣ ሳውዝ ዳኮታ የተደረገውን ትልቅ ስብሰባ አስታውሳለሁ። በስብሰባው ላይ ጎብኚ ተናጋሪ የነበረው ወንድም ግራንት ሱተር “መጨረሻው ከምታስቡት በላይ ቀርቧል!” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር አቅርቦ ነበር። ወንድም ሱተር ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ ሕይወታቸውን ስለ አምላክ መንግሥት ለማወጅ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ገለጸ። ይህ ንግግር ራሴን ለይሖዋ እንድወስን አነሳሳኝ። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት፣ በቀዝቃዛ ውኃ በተሞላ የከብቶች ውኃ መጠጫ ፊት ለፊት ቆሜ ስጠባበቅ የነበረው ለዚህ ነው። ይህ ትልቅ ስብሰባ ከተካሄደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በብሩኪንግዝ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠመቅኩ። ኅዳር 12, 1949 እኔና አብረውኝ የነበሩት ሦስት ሰዎች የተጠመቅነው ከብቶች ውኃ በሚጠጡበት በዚህ የብረት ገንዳ ውስጥ ነው።

ከዚያ በኋላ አቅኚ ለመሆን ግብ አወጣሁ። ጥር 1, 1952 በ15 ዓመቴ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል፤ በርካታ የቤተሰቤ አባላት አቅኚ ለመሆን ያደረግኩትን ውሳኔ የደገፉ ሲሆን ይህም ጥበበኛ እንደሆኑ ያሳያል። (ምሳሌ 13:20) አጎቴ ጁልየስ የአገልግሎት ጓደኛዬ ሆነ፤ በወቅቱ 60 ዓመቱ ነበር። በመካከላችን የዕድሜ ልዩነት ቢኖርም በአገልግሎት አስደሳች ጊዜያት አሳልፈናል። ካካበተው ተሞክሮ ጥበብ ያዘሉ በርካታ ትምህርቶች አግኝቻለሁ። ብዙም ሳይቆይ እህቴ ዶረቲም አቅኚ ሆነች።

የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ያደረጉልኝ እርዳታ

ልጅ እያለሁ ወላጆቼ የተለያዩ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን እኛ ጋር እንዲያርፉ ይጋብዙ ነበር። ጄሲ እና ሊን ካንትዌል የተባሉ ባልና ሚስት በጣም ረድተውኛል። እነሱ የሰጡኝ ማበረታቻ አቅኚ ለመሆን ያደረግኩትን ውሳኔ አጠናክሮልኛል። በግለሰብ ደረጃ ያደረጉልኝ እርዳታ ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ግቦችንም እንዳወጣ አነሳስቶኛል። በአቅራቢያችን ያሉ ጉባኤዎችን ሲጎበኙ አብሬያቸው አገልግሎት እንድወጣ ይጋብዙኝ ነበር። ይህም በጣም ያስደስተኝና ያበረታታኝ ነበር!

ቀጥሎ ጉባኤያችንን የጎበኘው በድ ሚለር የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች ነበር። እሱና ባለቤቱ ጆአን ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ 18 ዓመት ሞልቶኝ የነበረ ሲሆን ወታደራዊ አገልግሎት እንድሰጥ ጥያቄ ቀረበልኝ። የምልመላ ቦርዱ ሊሰጠኝ ያሰበው ሥራ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ እንዲሆኑ የሰጠውን መመሪያ እንደሚያስጥሰኝ ተሰማኝ። እኔ የምፈልገው የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነው። (ዮሐ. 15:19) ስለዚህ የምልመላ ቦርዱ ሃይማኖታዊ አገልጋይ አድርጎ እንዲመለከተኝ ጥያቄ አቀረብኩ።

ወንድም ሚለር የምልመላ ቦርዱ ጉዳዩን ወደሚመለከትበት ቦታ አብሮኝ ለመሄድ እንዳሰበ ሲነግረኝ በጣም ተደሰትኩ። ወንድም ሚለር በተፈጥሮው ተግባቢና ደፋር ሰው ነበር። እንዲህ ያለ ባሕርይ ያለው መንፈሳዊ ወንድም ከጎኔ መኖሩ በራስ የመተማመን ስሜቴ እንዲጨምር አድርጓል! የምልመላ ቦርዱ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በ1954 የበጋ ወቅት መገባደጃ ላይ፣ ሃይማኖታዊ አገልጋይ እንደሆንኩ አድርጎ እንዲመለከተኝ ያቀረብኩትን ጥያቄ ተቀበለው። ይህ ደግሞ ሌላ ቲኦክራሲያዊ ግብ ላይ እንድደርስ መንገድ ከፍቷል።

ቤቴል ውስጥ፣ የእርሻ መኪና አጠገብ ቆሜ

ብዙም ሳይቆይ በቤቴል እንዳገለግል ተጠራሁ፤ የተመደብኩት በስታትን ደሴት፣ ኒው ዮርክ ይገኝ በነበረው ዎችታወር ፋርም ነበር። በዚያም ለሦስት ዓመታት የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ቤቴል ውስጥ አስተዋይና ጥበበኛ ከሆኑ የተለያዩ ሰዎች ጋር መኖሬና አብሬ መሥራቴ አስደሳች ተሞክሮዎችን እንዳገኝ አስችሎኛል።

የቤቴል አገልግሎት

በደብልዩ ቢ ቢ አር የሬዲዮ ጣቢያ ከወንድም ፍራንዝ ጋር

ደብልዩ ቢ ቢ አር የተባለው የሬዲዮ ጣቢያ የሚገኘው በስታትን ደሴት ባለው የእርሻ ቦታ ነበር። የሬዲዮ ጣቢያውን የይሖዋ ምሥክሮች ከ1924 እስከ 1957 ተጠቅመውበታል። በእርሻ ቦታው እንዲያገለግሉ የተመደቡት ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ብቻ ነበሩ። በዚህ ቦታ ከተመደብነው ቤቴላውያን መካከል አብዛኞቻችን ወጣቶችና ተሞክሮ የሌለን ነበርን። ሆኖም ኤልደን ዉድዎርዝ የተባለ በዕድሜ የገፋ ቅቡዕ ወንድም አብሮን ነበር። ወንድም ዉድዎርዝ በእርግጥም ጥበበኛ ሰው ነበር። እንደ አባት ያስብልን የነበረ ሲሆን መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ረድቶናል። በአለፍጽምና ምክንያት ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መሥራት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ወንድም ዉድዎርዝ “ጌታ፣ ፍጽምና በሌላቸው ሰዎች ተጠቅሞ የሚያከናውነው ሥራ በጣም ያስደንቃል” ይል ነበር።

ሃሪ ፒተርሰን ለአገልግሎት ከፍተኛ ቅንዓት ነበረው

ከዚህም ሌላ ከወንድም ፍሬድሪክ ዊልያም ፍራንዝ ጋር የመሥራት ልዩ መብት አግኝተናል። የነበረው ጥበብና እጅግ ጥልቅ የሆነ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት በሁላችንም ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ደግሞም ለእያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጠን ነበር። ምግብ ይሠራልን የነበረው ወንድም ሃሪ ፒተርሰን ነው፤ ይህ ወንድም ትክክለኛ መጠሪያ ስሙ ሃሪ ፓፓሪሮፑሎስ ቢሆንም እኛ ግን ሃሪ ፒተርሰን ብለን መጥራት ይቀለን ነበር። ወንድም ፒተርሰን ቅቡዕ የነበረ ሲሆን ለአገልግሎት ከፍተኛ ቅንዓት ነበረው። የቤቴል ሥራውን በሚገባ ያከናውን የነበረ ቢሆንም በመስክ አገልግሎትም ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። በየወሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጽሔቶችን ያበረክት ነበር። በተጨማሪም ጥልቅ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ስለነበረው ለምናነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠን ነበር።

ጥበበኛ ከሆኑ እህቶች መማር

ከእርሻ ቦታው የሚገኙት ምርቶች እዚያው በሚገኝ ፋብሪካ እየታሸጉ ይላኩ ነበር። በየዓመቱ የፍራፍሬና የአትክልት ውጤቶችን የያዙ 45,000 ገደማ የሚሆኑ የታሸጉ ቆርቆሮዎች ለመላው የቤቴል ቤተሰብ ይላኩ ነበር። እዚያ በነበርኩበት ወቅት ኤታ ሁዝ ከተባለች ጥበበኛ እህት ጋር የመሥራት መብት አግኝቻለሁ። በፋብሪካው ውስጥ የሚታሸጉትን ምግቦች የአዘገጃጀት መመሪያ የምታወጣው እሷ ነበረች። ምግቦቹ በሚታሸጉበት ወቅት በአካባቢው ያሉ እህቶች መጥተው ያግዙ የነበረ ሲሆን ሥራውን የምታደራጀው ኤታ ነች። ኤታ በዚህ ሥራ ትልቅ ሚና ትጫወት የነበረ ቢሆንም የእርሻ ቦታውን በበላይነት ይከታተሉ የነበሩ ወንድሞችን በማክበር ረገድ ግሩም ምሳሌ ናት። ለቲኦክራሲያዊ አመራር በመገዛት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆናልኛለች።

እኔና አንጀላ ከኤታ ሁዝ ጋር

በዚህ ሥራ ለማገዝ ይመጡ ከነበሩ ወጣት እህቶች መካከል አንጀላ ሮማኖ ትገኝበታለች። አንጀላን ወደ እውነት እንድትመጣ የረዳቻት ኤታ ናት። በቤቴል ሳገለግል ከተዋወቅኳቸው ጥበበኛ ሰዎች አንዷ አንጀላ ናት። ሚያዝያ 1958 ከአንጂ ጋር የተጋባን ሲሆን ይሖዋን ባገለገልንባቸው 58 ዓመታት በርካታ የአገልግሎት መብቶችን አግኝተናል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንጂ በታማኝነት ከይሖዋ ጎን መቆሟ ትዳራችን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል። ምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን በጽናት እንደምትወጣው እተማመናለሁ።

በሚስዮናዊነትና በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል

በ1957 በስታትን ደሴት የነበረው ደብልዩ ቢ ቢ አር የሬዲዮ ጣቢያ ሲሸጥ፣ በብሩክሊን ቤቴል ለአጭር ጊዜ አገልግያለሁ። ከአንጂ ጋር ስንጋባ ግን ከቤቴል ወጣሁ፤ ከዚያም በስታትን ደሴት ለሦስት ዓመታት አቅኚ ሆነን አገለገልን። የሬዲዮ ጣቢያውን የገዙት ሰዎች ጣቢያውን ደብልዩ ፒ ኦ ደብልዩ ብለው የሰየሙት ሲሆን ከእነሱ ጋርም ለተወሰነ ጊዜ ሠርቻለሁ።

እኔና አንጂ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ሁሉ ማገልገል እንድንችል ሕይወታችንን ቀላል ለማድረግ ቆርጠን ነበር። በመሆኑም በ1961 መጀመሪያ ላይ በፎልስ ሲቲ፣ ነብራስካ ልዩ አቅኚ ሆነን እንድናገለግል ስንመደብ ግብዣውን ለመቀበል አልተቸገርንም። እዚያ ሄደን ብዙም ሳንቆይ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት እንድንካፈል ተጠራን፤ በዚያ ወቅት ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ ሲሆን አንድ ወር ያህል ይፈጅ ነበር። በትምህርቱ የተደሰትን ከመሆኑም ሌላ ወደ ነብራስካ ተመልሰን ያገኘነውን ሥልጠና ተግባራዊ ለማድረግ ጓጉተን ነበር። ይሁን እንጂ በካምቦዲያ ሚስዮናዊ ሆነን እንድናገለግል እንደተመደብን ስናውቅ በጣም ተገረምን። በደቡብ ምሥራቅ እስያ ወደምትገኘው ወደዚች ውብ አገር ስንሄድ ከዚያ በፊት አይተንም ሆነ ሰምተን የማናውቃቸው አስደናቂ ነገሮች አጋጥመውናል፤ በተጨማሪም ካምቦዲያ ግሩም መዓዛ ባላቸው ነገሮች የተሞላች ናት። በዚህች አገር ምሥራቹን ለማዳረስ ጓጉተን ነበር።

ይሁንና በዚያ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በመለወጡ ወደ ደቡብ ቬትናም ተዛወርን። የሚያሳዝነው ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ከባድ የጤና ችግር አጋጠመኝ፤ በመሆኑም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመመለስ ተገደድን። ከበሽታዬ ለማገገም የተወሰነ ጊዜ ወስዶብኛል፤ ጤናዬ ከተስተካከለ በኋላ ግን በድጋሚ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን።

በ1975 እኔና አንጀላ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ ቃለ ምልልስ ከማድረጋችን በፊት

ከመጋቢት 1965 ጀምሮ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ጉባኤዎችን የማገልገል መብት አገኘን። እኔ እና አንጂ በወረዳ እና በአውራጃ ሥራ ለ33 ዓመታት አገልግለናል፤ ይህ ሥራ ትላልቅ ስብሰባዎችን ማደራጀትን ይጨምራል። ለትላልቅ ስብሰባዎች ከፍ ያለ አድናቆት ስላለኝ እነዚህን ስብሰባዎች ማደራጀት ያስደስተኝ ነበር። ለተወሰኑ ዓመታት ያገለገልነው በኒው ዮርክ ሲቲ አካባቢ ሲሆን በወቅቱ በያንኪ ስታዲየም በርካታ ስብሰባዎች ይደረጉ ነበር።

በቤቴልና በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ማገልገል

በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንደተሰማሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ እኔና አንጂም አስደሳች ሆኖም ተፈታታኝ የሆኑ የአገልግሎት ምድቦች ተሰጥተውን ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በ1995 በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት እንዳስተምር ተመደብኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ ቤቴል እንድንገባ ተጋበዝን። ከ40 ዓመታት በፊት ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ወደጀመርኩበት ቦታ መመለሴ በጣም አስደስቶኝ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ በአገልግሎት ዘርፍ ሠርቻለሁ፤ እንዲሁም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ አስተማሪ ሆኜ አገልግያለሁ። በ2007 የበላይ አካሉ የቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ክፍል በማቋቋም በቤቴል ያሉ ትምህርት ቤቶች በዚህ ክፍል ሥር እንዲሆኑ አደረገ፤ ለጥቂት ዓመታት የዚህ ክፍል የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቲኦክራሲያዊ ትምህርት ጋር በተያያዘ ትላልቅ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ተመልክተናል። በ2008 የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤት ተቋቋመ። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ፣ ከ12,000 የሚበልጡ ሽማግሌዎች በፓተርሰን እንዲሁም በብሩክሊን ቤቴል ተምረዋል። ይህ ትምህርት ቤት በሠለጠኑ የመስክ አስተማሪዎች አማካኝነት በተለያዩ ቦታዎች እየተካሄደ ነው። በ2010፣ የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ስሙ ተቀይሮ ለነጠላ ወንድሞች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተባለ፤ ከዚህም ሌላ ለባለትዳሮች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተባለ አዲስ ትምህርት ቤት ተቋቋመ።

በ2015 የአገልግሎት ዓመት ሁለቱ ትምህርት ቤቶች አንድ ላይ የተጣመሩ ሲሆን ትምህርት ቤቱ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተብሎ መጠራት ጀመረ። ተማሪዎቹ ባለትዳሮች፣ ነጠላ ወንድሞች ወይም እህቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞች፣ ይህ ትምህርት ቤት በተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንደሚካሄድ ሲሰሙ በጣም ተደስተዋል። ብዙዎች በእነዚህ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የመማር አጋጣሚ የተከፈተላቸው መሆኑ በጣም ያስደስታል፤ እኔም ይህን ሥልጠና ለማግኘት የመጡ በርካታ ወንድሞችንና እህቶችን ማግኘት በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ።

በቀዝቃዛ ውኃ በተሞላው ገንዳ ውስጥ ከመጠመቄ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ያለውን ሕይወቴን መለስ ብዬ ስመለከተው፣ በእውነት ጎዳና እንድጓዝ የረዱኝ በርካታ ጥበበኛ ሰዎች እንዳሉ ይሰማኛል፤ ለዚህም ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በዕድሜ ይበልጡኛል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከእኔ ያነሱ ናቸው። አስተዳደጋችንም ቢሆን የተለያየ ነው። ሆኖም መንፈሳዊ ሰዎች ነበሩ። አመለካከታቸውም ሆነ ተግባራቸው ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ አብረናቸው ልንሄድ የምንችል በርካታ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች አሉ። እኔም ከእነሱ ጋር በመሄዴ በእጅጉ ተጠቅሜያለሁ።

ከተለያየ የዓለም ክፍል ከሚመጡ ተማሪዎች ጋር መገናኘት ያስደስተኛል