በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 3

“አምላክ የገለጠልኝን ራእዮች ማየት ጀመርኩ”

“አምላክ የገለጠልኝን ራእዮች ማየት ጀመርኩ”

ሕዝቅኤል 1:1

ፍሬ ሐሳብ፦ ሕዝቅኤል ስለ ሰማያዊው ሠረገላ ያየው ራእይ

1-3. (ሀ) ሕዝቅኤል ያየውንና የሰማውን ግለጽ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ሕዝቅኤል ራእዩን እንዲያይ ያደረገው ኃይል ምንድን ነው? ራእዩን ሲያይስ ምን ተሰማው?

ሕዝቅኤል ከፊት ለፊቱ ካለው ሰፊ አሸዋማ ሜዳ ባሻገር ያለውን አድማስ ትኩር ብሎ እየተመለከተ ነው። የሚያየውን ነገር ማመን አቅቶት ዓይኑን አንዴ እያጠበበ አንዴ እያፈጠጠ ለማየት ይሞክራል። ከአድማስ ባሻገር ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ሊነሳ ይመስላል። ግን የተለመደው ዓይነት አውሎ ነፋስ አልነበረም። ሕዝቅኤል ከሰሜን አቅጣጫ የሚነፍስ ኃይለኛ ነፋስ ልብሱንና ፀጉሩን እያውለበለበው ሳለ እጅግ ግዙፍ የሆነ ደመና ሲወጣ ተመለከተ። በደመናው ውስጥ የእሳት ብልጭታ ይታያል፤ የእሳቱ ድምቀት የሚያብረቀርቅ ብረት ይመስላል። * ደመናው ወደ ሕዝቅኤል እየተጠጋ ሲመጣ እንደ ታላቅ ሠራዊት ያለ የሚያስገመግም ድምፅ ይሰማው ጀመር።—ሕዝ. 1:4, 24

2 ዕድሜው 30 ዓመት ገደማ የሚሆነው ይህ ወጣት በሕይወቱ ውስጥ ካጋጠሙት የማይረሱ ክንውኖች መካከል ይህ የመጀመሪያው ነው። “የይሖዋ እጅ” ማለትም ማንም ሊቋቋመው የማይችለው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ሲያርፍበት ተሰማው። ሕዝቅኤል በዚህ መንፈስ አማካኝነት ያየውና የሰማው ነገር የዛሬዎቹ ፊልም ሠሪዎች ከሚያዘጋጇቸው ልዩ የፊልም ቅንብሮች ሁሉ ይበልጥ በጣም የሚያስደንቅና የሚያስደምም ነው። ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ በጣም ከመደነቁ የተነሳ በግንባሩ ተደፋ።—ሕዝ. 1:3 ግርጌ, 28

3 ይሁን እንጂ ይሖዋ ለዚህ ሰው ራእይ ያሳየው በአድናቆት እንዲዋጥ ለማድረግ ብቻ አልነበረም። ሕዝቅኤል ያየው የመጀመሪያ ራእይ በትንቢት መጽሐፉ ውስጥ እንዳሰፈራቸው ሌሎች አስደናቂ ራእዮች ሁሉ ለራሱም ሆነ ዛሬ ላሉት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጥልቅ ትርጉም አለው። እስቲ ሕዝቅኤል ያየውንና የሰማውን ነገር በጥልቀት እንመርምር።

መቼቱ

4, 5. የሕዝቅኤል ራእይ መቼት ምን ነበር?

4 ሕዝቅኤል 1:1-3ን አንብብ። እስቲ በመጀመሪያ መቼቱን እንመልከት። ጊዜው 613 ዓ.ዓ. ነበር። ከዚህ በፊት በነበረው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ሕዝቅኤል በባቢሎን በኬባር ወንዝ አቅራቢያ ግዞተኛ ከሆኑ ወገኖቹ ጋር ይኖር ነበር፤ ይህ ወንዝ ከኤፍራጥስ ወንዝ ከተገነጠለ በኋላ ተመልሶ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ የሚገባ ጀልባዎች ሊንቀሳቀሱበት የሚችል ሰፊ ሰው ሠራሽ ቦይ ነው።

ሕዝቅኤል ከሌሎች ግዞተኞች ጋር በኬባር ወንዝ አጠገብ ይኖር ነበር (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

5 የግዞተኞቹ የትውልድ ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም 800 ኪሎ ሜትር ርቃ ትገኛለች። * የሕዝቅኤል አባት በክህነት ያገለግልበት የነበረው ቤተ መቅደስ ብልሹ በሆነ ሥነ ምግባርና በጣዖት አምልኮ ረክሷል። በአንድ ወቅት ዳዊትና ሰለሞን በታላቅ ክብር ይገዙበት የነበረው በኢየሩሳሌም ያለው ዙፋን አሁን ተዋርዷል። እምነት የለሹ ንጉሥ ዮአኪን ከግዞተኞቹ ጋር በባቢሎን ይገኛል። እሱን ተክቶ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ክፉው ንጉሥ ሴዴቅያስም ቢሆን ከአሻንጉሊትነት ያለፈ ሥልጣን አልነበረውም።—2 ነገ. 24:8-12, 17, 19

6, 7. ሕዝቅኤል ጨለማ በነገሠበት ዘመን ውስጥ እንደሚኖር ተሰምቶት ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

6 እንደ ሕዝቅኤል ላለ የእምነት ሰው ይህ ወቅት ጨለማ የነገሠበት ዘመን ነው ማለት ይቻላል። ከግዞተኛ ወገኖቹ መካከል አንዳንዶቹ እንደሚከተለው ያለ ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል፦ ‘ይሖዋ ለዘላለም ትቶናል ማለት ነው? በክፋትና በሐሰት አምልኮ የተሞላችው ባቢሎን የይሖዋን ንጹሕ አምልኮና አገዛዙን ከምድር ገጽ ጠራርጋ ታጠፋው ይሆን?’

7 ሕዝቅኤል ያየውን የመጀመሪያ ራእይ መመርመር ከመጀመርህ በፊት አሁን የተመለከትነውን አጠቃላይ መረጃ በአእምሮህ በመያዝ ሕዝቅኤል ስለ ራእዩ የሰጠውን መግለጫ ለምን አታነብም? (ሕዝ. 1:4-28) እንዲህ በምታደርግበት ጊዜ ራስህን በሕዝቅኤል ቦታ በማስቀመጥ እሱ ያየውን ለማየትና እሱ የሰማውን ለመስማት ሞክር።

ኤፍራጥስ ወንዝ በካርከሚሽ አቅራቢያ (ከአንቀጽ 5-7⁠ን ተመልከት)

በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሠረገላ

8. ሕዝቅኤል በራእይ ምን ተመለከተ? የተመለከተው ነገርስ ምን ያመለክታል?

8 ሕዝቅኤል የተመለከተው ነገር ምንድን ነው? በጣም ግዙፍና አስደናቂ የሆነ ሠረገላ ተመልክቶ ነበር። ሠረገላው አራት ትላልቅ መንኮራኩሮች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ መንኮራኩር አጠገብ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር አለ፤ እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ኪሩቦች እንደሆኑ ቆየት ብሎ ተገልጿል። (ሕዝ. 10:1) ከሕያዋን ፍጥረታቱ በላይ እንደ በረዶ ያለ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር፤ ከጠፈሩ በላይ ግርማ የተላበሰ ዙፋን ይገኛል፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ይሖዋ ራሱ ነው! ለመሆኑ ይህ ሠረገላ ምን ያመለክታል? ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ሠረገላ ከታላቁ የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ውጭ ምንም ነገር ሊያመለክት አይችልም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርጉንን ሦስት ምክንያቶች እንመልከት።

9. ስለ ሠረገላው የተሰጠው መግለጫ ይሖዋ ከሰማያዊ ፍጥረታቱ ጋር ያለውን ዝምድና ጥሩ አድርጎ ይገልጻል የምንለው ለምንድን ነው?

9 ይሖዋ በሰማያዊ ፍጥረታቱ ላይ ያለው ሥልጣን። በዚህ ራእይ ላይ የይሖዋ ዙፋን ከኪሩቦቹ በላይ እንደሚገኝ መገለጹን ልብ በል። ይሖዋ ከኪሩቤል በላይ ወይም በኪሩቦች መካከል እንደተቀመጠ የተገለጸባቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም አሉ። (2 ነገሥት 19:15ን አንብብ፤ ዘፀ. 25:22፤ መዝ. 80:1) እርግጥ ይህ ሲባል ቃል በቃል በኪሩቤል ላይ ተቀምጧል ማለት አይደለም፤ ይሖዋ ቃል በቃል ሠረገላ ላይ መቀመጥ እንደማያስፈልገው ሁሉ በኪሩቤል ላይ መቀመጥም አያስፈልገውም። ነገር ግን ኪሩቦቹ ሉዓላዊነቱን ይደግፋሉ፤ እንዲሁም ፈቃዱን እንዲፈጽሙ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ወደሚገኝ ወደ የትኛውም ቦታ ሊልካቸው ይችላል። እንደ ሌሎቹ የአምላክ ቅዱሳን መላእክት ሁሉ ኪሩቦችም የይሖዋ አገልጋዮች ወይም ወኪሎች በመሆን የእሱን ውሳኔ ያስፈጽማሉ። (መዝ. 104:4) ሉዓላዊ ገዢ የሆነው ይሖዋ መላእክቱን ሁሉ በዚህ መንገድ ስለሚመራ ሁሉንም መላእክት ባቀፈ ትልቅ ሠረገላ ላይ “እንደተቀመጠ” ሊቆጠር ይችላል።

10. ሰማያዊው ሠረገላ አራት ኪሩቦችን ብቻ ያቀፈ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

10 ሠረገላው ያቀፈው አራቱን ኪሩቦች ብቻ አይደለም። ሕዝቅኤል የተመለከታቸው ኪሩቦች አራት ነበሩ። ይህ ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙላትን ወይም ሁሉን አቀፍ መሆንን ለማመልከት ብዙ ጊዜ ተሠርቶበታል። ስለሆነም ኪሩቦቹ አራት መሆናቸው የይሖዋ ታማኝ መንፈሳዊ ልጆች በሙሉ መወከላቸውን ያመለክታል። በተጨማሪም መንኮራኩሮቹና ኪሩቦቹ በዓይኖች የተሞሉ መሆናቸውን ልብ በል፤ ይህም ንቁና ዝግጁ እንደሆኑ ያመለክታል፤ እንዲህ ያለ ንቃት ያላቸው ደግሞ አራቱ መንፈሳዊ ፍጡራን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው። በተጨማሪም ሕዝቅኤል እንደገለጸው ሠረገላው እጅግ በጣም ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ አስደናቂ የሆኑት ኪሩቦች ራሱ ከሠረገላው ጋር ሲነጻጸሩ ትንሽ መስለው ይታያሉ። (ሕዝ. 1:18, 22፤ 10:12) በተመሳሳይም የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በጣም ሰፊ በመሆኑ አራት ኪሩቦችን ብቻ ያቀፈ ሊሆን አይችልም።

ሕዝቅኤል የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ በራእይ ማየቱ በታላቅ አድናቆት እንዲዋጥ አድርጎታል (ከአንቀጽ 8-10⁠ን ተመልከት)

11. ዳንኤል ምን ተመሳሳይ ራእይ ተመልክቷል? ይህስ ምን ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል?

11 ዳንኤል ያየው ተመሳሳይ ራእይ። ነቢዩ ዳንኤል አብዛኛውን የሕይወቱን ክፍል በባቢሎን ከተማ በግዞት ያሳለፈ ሲሆን እሱም ሰማይን የሚያሳይ ራእይ ተመልክቶ ነበር። የሚያስገርመው በዚህ ራእይ ላይም የይሖዋ ዙፋን መንኮራኩሮች እንዳሉት ሆኖ ተገልጿል። ዳንኤል ያየው ራእይ በሰማይ የሚገኘው የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተሰብ ምን ያህል ስፋት እንዳለው የሚያጎላ ነው። ዳንኤል “ሺህ ጊዜ ሺዎች . . . እልፍ ጊዜ እልፍ” የሚሆኑ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በይሖዋ ፊት ቆመው ተመልክቷል። በሰማይ በተሰየመ ችሎት ላይ ሁሉም በቦታቸው ተገኝተው ነበር። (ዳን. 7:9, 10, 13-18) ታዲያ ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ሠረገላ በዳንኤል ራእይ ላይ የተጠቀሱትን መንፈሳዊ ፍጥረታት ሁሉ ያመለክታል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይሆንም?

12. በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ራእይ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን ማጥናታችን ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

12 ይሖዋ፣ እኛ የሰው ልጆች አእምሯችን “በማይታዩት ነገሮች ላይ” እንዲያተኩር ማድረጋችን ጥበቃ እንደሚሆንልን ያውቃል። ሰብዓዊ ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን “በሚታዩት ነገሮች” ማለትም ጊዜያዊ በሆኑት ጭንቀቶቻችን ላይ ከልክ በላይ ማተኮር ይቀናናል። (2 ቆሮንቶስ 4:18ን አንብብ።) ሰይጣን ብዙ ጊዜ ይህን ዝንባሌያችንን በመጠቀም ሥጋዊ አስተሳሰብ እንድናዳብር ለማድረግ ይሞክራል። ይሖዋ ይህን የሰይጣን ተጽዕኖ እንድንቋቋም ለመርዳት ሲል በሰማይ ያለው ቤተሰቡ ምን ያህል ክብር የተላበሰ እንደሆነ እንድናስታውስ የሚያደርጉ በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኘው እንደዚህ ራእይ ያሉ ሐሳቦችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል።

“ተሽከርካሪ መንኮራኩሮች!”

13, 14. (ሀ) ሕዝቅኤል ያያቸውን መንኮራኩሮች የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ሠረገላ መንኮራኩሮች ያሉት መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ሕዝቅኤል በመጀመሪያ ያተኮረው በአራቱ ኪሩቦች ላይ ነው። እነዚህ ሕያዋን ፍጥረታትና አስደናቂ ቁመናቸው ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምረን በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ እንመለከታለን። ይሁን እንጂ ሕዝቅኤል ከእነዚህ ኪሩቦች ጎን አራት መንኮራኩሮችንም ተመልክቷል፤ መንኮራኩሮቹ ሰፊ አራት ማዕዘን ቅርጽ ሠርተው የቆሙ ሳይሆኑ አይቀሩም። (ሕዝቅኤል 1:16-18ን አንብብ።) እነዚህ መንኮራኩሮች ክርስቲሎቤ ከሚባል የከበረ ድንጋይ የተሠሩ ይመስላሉ፤ ይህ የከበረ ድንጋይ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ብርሃን የሚያስተላልፍ ሲሆን ቢጫ ወይም ቢጫማ አረንጓዴ ቀለም ሊኖረው ይችላል። ይህ ውብ ድንጋይ በጣም ያብረቀርቃል።

14 የሠረገላው መንኮራኩሮች በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። መንኮራኩሮች ያሉት ዙፋን የተለመደ ነገር አይደለም። ስለ ዙፋን ስናስብ ወደ አእምሯችን የሚመጣው አንድ ቦታ ላይ ያለ የነገሥታት መቀመጫ ሊሆን ይችላል፤ ምድራዊ ነገሥታት መግዛት የሚችሉት በተወሰነ አካባቢ ላይ ብቻ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ብለን ማሰባችን አያስገርምም። የይሖዋ ሉዓላዊነት ግን ከየትኛውም ሰብዓዊ አገዛዝ የተለየ ነው። ሕዝቅኤል ከራእዩ እንደተገነዘበው የይሖዋ ሉዓላዊ ሥልጣን ዳርቻ የለውም። (ነህ. 9:6) በሉዓላዊው ገዢ በይሖዋ ሥልጣን ሥር ያልሆነ አንድም ቦታ የለም!

15. ሕዝቅኤል ስለ መንኮራኩሮቹ መጠንና አሠራር ምን ገልጿል?

15 የመንኮራኩሮቹ ግዝፈት ሕዝቅኤልን በጣም አስደምሞታል። “የመንኮራኩሮቹም ጠርዝ እጅግ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ የሚያስፈራ ነበር” በማለት ጽፏል። ሕዝቅኤል ቁመታቸው እስከ ሰማይ የሚደርሰውን የሚያብረቀርቁ ግዙፍ መንኮራኩሮች ለማየት ወደ ላይ ሲያንጋጥጥ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ሕዝቅኤል “የአራቱም መንኮራኩሮች ጠርዝ ዙሪያውን በዓይኖች የተሞላ ነበር” የሚል የሚያስገርም ተጨማሪ መግለጫ ሰጥቷል። ከሁሉ በላይ የሚያስደንቀው ግን የመንኮራኩሮቹ እንግዳ አሠራር ሳይሆን አይቀርም። ሕዝቅኤል “መልካቸውና አሠራራቸው ሲታይ በአንድ መንኮራኩር ውስጥ በጎን በኩል ሌላ መንኮራኩር የተሰካ ይመስላል” የሚል ማብራሪያ ይሰጠናል። ይህ ምን ማለት ነው?

16, 17. (ሀ) የሠረገላው መንኮራኩሮች አሠራር ምን ዓይነት ነው? (ለ) መንኮራኩሮቹ የይሖዋ ሠረገላ ስላለው ቅልጥፍና ምን ይጠቁማሉ?

16 ሕዝቅኤል የተመለከተው እያንዳንዱ መንኮራኩር ሁለት መንኮራኩሮችን በቁመታቸው በማሰካካት የተሠራ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ሕዝቅኤል እንደገለጸው መንኮራኩሮቹ “በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መዞር ሳያስፈልጋቸው በአራቱም ጎን በፈለጉበት አቅጣጫ መሄድ” የቻሉት በዚህ መንገድ ስለተሠሩ ነው። እነዚህ መንኮራኩሮች ሕዝቅኤል ስለተመለከተው ሰማያዊ ሠረገላ ምን ይጠቁማሉ?

17 ይህን የሚያክል ረጅም ቁመት ያላቸው መንኮራኩሮች አንዴ እንኳ ሲሽከረከሩ ሰፊ ርቀት ሊሸፍኑ ይችላሉ። በዚህ ላይ ራእዩ ሠረገላው እንደ መብረቅ ባለ ፍጥነት እንደሚጓዝ ይገልጻል! (ሕዝ. 1:14) ከዚህም በላይ ይህ ሠረገላ በአራት አቅጣጫ መጓዝ የሚችሉ መንኮራኩሮች ያሉት መሆኑ ሰብዓዊ መሐንዲሶች ሊያልሙት እንኳ የማይችሉት ቅልጥፍና እንዳለው ያመለክታል። ሠረገላው ፍጥነቱን መቀነስ ወይም መዞር ሳያስፈልገው በቅጽበት አቅጣጫውን መቀየር ይችላል! እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ግን እንዲሁ በጭፍን አይደለም። የመንኮራኩሮቹ ጠርዝ በዓይኖች የተሞላ መሆኑ ይህ ሠረገላ በሁሉም አቅጣጫ በዙሪያው ያለውን እያንዳንዱን ነገር እንደሚያይ ይጠቁማል።

መንኮራኩሮቹ እጅግ ግዙፍ ከመሆናቸውም ሌላ በአስገራሚ ፍጥነት ይንቀሳቀሱ ነበር (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

18. መንኮራኩሮቹ በጣም ግዙፍና በዓይኖች የተሞሉ መሆናቸው ምን ያስገነዝበናል?

18 ታዲያ ይሖዋ ሕዝቅኤልንም ሆነ ታማኝ ሕዝቦቹን በሙሉ ስለ ድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ምን እያስተማራቸው ነው? እስካሁን ምን ነገሮችን እንደተመለከትን ለማሰብ ሞክር። መንኮራኩሮቹ የሚያብረቀርቁና ግዙፍ መሆናቸው የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ታላቅ ግርማ የተላበሰና የሚያስደምም እንደሆነ ያመለክታል። መንኮራኩሮቹ በዓይኖች የተሞሉ መሆናቸው ደግሞ የድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ሁሉንም ነገር እንደሚያይ ይጠቁማል። የይሖዋ ዓይኖች ሁሉንም ነገሮች ይመለከታሉ። (ምሳሌ 15:3፤ ኤር. 23:24) ከዚህም በላይ ይሖዋ ወደ የትኛውም የአጽናፈ ዓለም ክፍል ሊልካቸው የሚችል በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት አሉት፤ እነዚህ መላእክት ነገሮችን አጣርተው ከተመለከቱ በኋላ ያዩትን ነገር ለሉዓላዊ ገዢያቸው ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ።ዕብራውያን 1:13, 14ን አንብብ።

የመንኮራኩሮቹ አሠራር ሠረገላው ቀልጣፋ እንዲሆን አድርጎታል (አንቀጽ 17, 19⁠ን ተመልከት)

19. የይሖዋ ሠረገላ ያለው ፍጥነትና ቅልጥፍና ስለ ይሖዋና ስለ ድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ምን ያስተምረናል?

19 በተጨማሪም ሠረገላው እጅግ በጣም ፈጣንና ቀልጣፋ እንደሆነ አስታውስ። በይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል እና በሰብዓዊ መንግሥታት፣ ተቋማትና ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት እስቲ ለማሰብ እንሞክር። ሰብዓዊ መንግሥታት፣ ተቋማትና ድርጅቶች በጭፍን ስለሚጓዙ የሚያጋጥሟቸውን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እንደ አመጣጣቸው ማስተናገድ አይችሉም፤ በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ውድቀት ይዳረጋሉ። ይሖዋ ምክንያታዊና ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው ማስተናገድ የሚችል አምላክ እንደሆነ ሁሉ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ሠረገላም እንደዚሁ ነው። ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን እንደሚችል ከስሙ ትርጉም ራሱ መረዳት ይቻላል። (ዘፀ. 3:13, 14) ለምሳሌ በቅጽበት ለሕዝቦቹ የሚዋጋ ኃያል ተዋጊ መሆን ይችላል፤ ወዲያውኑ ደግሞ ከልብ ተጸጽተው ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር የሚልና የሚንከባከብ መሐሪ አባት ይሆናል።—መዝ. 30:5፤ ኢሳ. 66:13

20. ለይሖዋ ሠረገላ አድናቆት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

20 የሕዝቅኤል ራእይ ‘ለይሖዋ ሠረገላ አድናቆት አለኝ?’ ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ሊያነሳሳን ይገባል። ሠረገላው አሁን በእውን ያለ ነገርን እንደሚያመለክት ማስታወስ ያስፈልገናል። ይሖዋ፣ ልጁና መላእክቱ የሚደርሱብንን ችግሮች እንደማያዩ አድርገን ፈጽሞ ልናስብ አይገባም። አሊያም ደግሞ አምላካችን ችግሮች ሲያጋጥሙን ቶሎ ላይደርስልን ይችላል ወይም ድርጅቱ በዙሪያችን ባለው ተነዋዋጭ ዓለም ውስጥ የሚነሱትን አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም ያቅተዋል ብለን መጨነቅ አይኖርብንም። የይሖዋ ድርጅት ምንጊዜም በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልገናል። ሕዝቅኤል አንድ ድምፅ ከሰማይ “ተሽከርካሪ መንኮራኩሮች!” ብሎ ሲጣራ ሰምቷል፤ ይህም መንኮራኩሮቹ በሆነ አቅጣጫ እንዲሄዱ የተላለፈ ትእዛዝ ሊሆን ይችላል። (ሕዝ. 10:13) በእርግጥም ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራበት መንገድ እጅግ አስደናቂ አይደለም? ከሁሉ ይበልጥ እንድንደመም የሚያደርገን ግን ስለ ይሖዋ የተሰጠው መግለጫ ነው።

የሠረገላው ተቆጣጣሪ

21, 22. ሠረገላውን በተቀናጀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው ምንድን ነው?

21 አሁን ደግሞ የሕዝቅኤል ትኩረት ከመንኮራኩሮቹ በላይ በተዘረጋው “እጅግ አስደናቂ እንደሆነ በረዶ የሚያብረቀርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር” ላይ አረፈ። (ሕዝ. 1:22) ከኪሩቦቹ ከፍ ብሎ የሚገኘው በከፊል ብርሃን አስተላላፊ የሆነው ጠፈር መሰል ነገር እጅግ ደምቆ ያበራል። የቴክኒክ እውቀት ያላቸው ሰዎች ስለዚህ ራእይ ሲያነቡ ስለ ሠረገላው አሠራር የተለያዩ ጥያቄዎች ሊፈጠሩባቸው ይችላሉ። ለምሳሌ ‘ጠፈር የሚመስለው ነገር ምንም ሳይዘው ከመንኮራኩሮቹ በላይ ሊቆም የቻለው እንዴት ነው? መንኮራኩሮቹስ እርስ በርስ የሚያያይዛቸው ነገር ሳይኖር እንዴት ተቀናጅተው ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ይሁንና ሠረገላው መንፈሳዊውን ዓለም የሚያሳይ ምሳሌያዊ ሠረገላ እንጂ በተፈጥሮ ሕጎች የሚገዛ ቃል በቃል ያለ ሠረገላ እንዳልሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። በተጨማሪም “በሕያዋን ፍጥረታቱ ላይ የሚሠራው መንፈስ በመንኮራኩሮቹም ውስጥ ነበር” የሚለውን አገላለጽ ልብ በል። (ሕዝ. 1:20, 21) ታዲያ በኪሩቦቹና በመንኮራኩሮቹ ላይ የሚሠራው መንፈስ ምንድን ነው?

22 ይህ መንፈስ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል ማለትም የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ሠረገላውን ፍጹም በተቀናጀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው ይህ የአምላክ ኃይል ነው። እስቲ አሁን እኛም እንደ ሕዝቅኤል ትኩረታችንን በሠረገላው ተቆጣጣሪ ላይ እናድርግ።

ሕዝቅኤል ያየው ነገር በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ነበር

23. ሕዝቅኤል ይሖዋን ለመግለጽ ሲሞክር እንዴት ባሉ አገላለጾች ተጠቅሟል? ለምንስ?

23 ሕዝቅኤል 1:26-28ን አንብብ። ሕዝቅኤል ስለ ራእዩ በሰጠው መግለጫ ላይ “ያለ ነገር” እና “የሚመስል ነገር” እንደሚሉት ያሉ አገላለጾችን በተደጋጋሚ ይጠቀማል። በእነዚህ ቁጥሮች ላይ ደግሞ እንዲህ ያሉትን አገላለጾች ከሌላ ጊዜ ይበልጥ ተጠቅሟል። ያየውን በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ነገር የሚገልጽበት መንገድ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ያለ ይመስላል። ሕዝቅኤል “የሰንፔር ድንጋይ የመሰለ እንደ ዙፋን ያለ ነገር” ተመለከተ። ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ካለው ግዙፍ የሰንፔር ድንጋይ ወጥ ሆኖ የተቀረጸ ዙፋን ምን እንደሚመስል መገመት ትችላለህ? በዙፋኑ ላይ ደግሞ “መልኩ የሰው መልክ የሚመስል” ተቀምጧል።

24, 25. (ሀ) በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ ያለው ቀስተ ደመና ምን ያስታውሰናል? (ለ) አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሕዝቅኤል እንዳየው ዓይነት ራእይ ማየታቸው ምን ስሜት አሳድሮባቸዋል?

24 ታላቅ ግርማ የተላበሰውን የይሖዋን መልክ በግልጽ ማየት አይቻልም፤ ምክንያቱም ከወገቡ በላይም ሆነ ከወገቡ በታች የግርማው ነበልባል በኃይል ያንጸባርቃል። ነቢዩ ይህን ታላቅ ግርማ ሲያይ ዓይኑን ከነጸብራቁ ለመከለል መሞከሩ እንደማይቀር መገመት እንችላለን። በመጨረሻም ሕዝቅኤል የራእዩ ማሳረጊያ የሆነውን የሚከተለውን ትዕይንት ተመለከተ፦ “በዙሪያውም ደማቅ ብርሃን ነበር፤ ይህም ዝናባማ በሆነ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታይ ቀስተ ደመና ነበር።” ቀስተ ደመና አይተህ መንፈስህ ታድሶ ያውቃል? የፈጣሪያችንን ግርማና ክብር እንድናስብ የሚያደርግ እንዴት ያለ አስደናቂ ትዕይንት ነው! ይህ በቀለማት ያሸበረቀ ቀስተ ደመና ይሖዋ ከጥፋት ውኃ በኋላ የገባውን የሰላም ቃል ኪዳንም ሊያስታውሰን ይችላል። (ዘፍ. 9:11-16) ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ እጅግ ኃያል ቢሆንም የሰላም አምላክ ነው። (ዕብ. 13:20) በልቡ ውስጥ ሰላም የነገሠ ሲሆን ይህ ሰላም በታማኝነት በሚያመልኩት አገልጋዮቹ ላይም ይሰፍናል።

የይሖዋን ዙፋን የከበበው ባለታላቅ ግርማ ቀስተ ደመና የምናመልከው አምላክ የሰላም አምላክ መሆኑን ያስታውሰናል (አንቀጽ 24⁠ን ተመልከት)

25 ሕዝቅኤል የይሖዋን ክብርና ግርማ በራእይ መመልከቱ ምን ስሜት አሳድሮበታል? “እኔም ባየሁት ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ” በማለት ዘግቧል። ሕዝቅኤል በአድናቆትና በአክብሮታዊ ፍርሃት ስለተዋጠ መሬት ላይ ተደፋ። ሌሎች ነቢያትም እንዲህ ያሉ ራእዮችን ባዩበት ወቅት ተመሳሳይ ስሜት አድሮባቸዋል፤ ራእይ መመልከታቸው ራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉና በፍርሃት እንዲርዱ እንዳደረጋቸው ጥርጥር የለውም። (ኢሳ. 6:1-5፤ ዳን. 10:8, 9፤ ራእይ 1:12-17) ይሁን እንጂ ሁኔታው ካለፈ በኋላ፣ ይሖዋ በገለጠላቸው ነገር በእጅጉ ተበረታተዋል። ሕዝቅኤልም እንደተበረታታ የታወቀ ነው። እኛስ እንዲህ ያሉትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩ ዘገባዎች ስናነብ ምን ሊሰማን ይገባል?

26. ሕዝቅኤል የተመለከተው ራእይ አበረታቶት መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?

26 ሕዝቅኤል የአምላክ ሕዝቦች በባቢሎን የሚገኙበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ተሰምቶት ከነበረ ይህ ራእይ እንዳበረታታው ጥያቄ የለውም። አስደናቂ የሆነው የይሖዋ ሠረገላ ሊደርስበት የማይችል ቦታ ስለሌለ የአምላክ ታማኝ ሕዝቦች የሚገኙት በኢየሩሳሌምም ይሁን በባቢሎን አሊያም በሌላ በየትኛውም ቦታ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ሰይጣን የሚጠቀምበት የትኛውም ኃያል መንግሥት እንዲህ ያለውን ባለግርማ ሰማያዊ ሠረገላ የሚቆጣጠረውን አምላክ ሊቋቋም አይችልም! (መዝሙር 118:6ን አንብብ።) በተጨማሪም ሕዝቅኤል ሰማያዊው ሠረገላ የሚገኘው ከሰው ልጆች ርቆ እንዳልሆነ ተመልክቷል። እንዲያውም የሠረገላው መንኮራኩሮች ምድርን እንደነኩ ገልጿል። (ሕዝ. 1:19) ስለዚህ ይሖዋ በግዞት ላይ የሚገኙ ሕዝቦቹን ሁኔታ በቅርበት ይከታተል እንደነበር መረዳት ይቻላል። ሕዝቦቹ መቼም ቢሆን የአባታቸው ፍቅራዊ እንክብካቤ አይለያቸውም!

ሠረገላውና አንተ

27. የሕዝቅኤል ራእይ በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ምን መልእክት ይዞልናል?

27 የሕዝቅኤል ራእይ በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛም የያዘው መልእክት ይኖራል? እንዴታ! ሰይጣን በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እያፋፋመ ነው። ብቻችንን እንደሆንን እንዲሁም የሰማዩ አባታችንና ድርጅቱ ሊደርሱልን እንደማይችሉ አድርገን እንድናስብ ይፈልጋል። እንዲህ ያለውን ውሸት በአእምሯችንም ሆነ በልባችን ውስጥ ፈጽሞ ቦታ ልንሰጠው አይገባም! (መዝ. 139:7-12) እኛም እንደ ሕዝቅኤል በአድናቆት እንድንዋጥ የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉ። እርግጥ እኛ እንደ እሱ በግንባራችን አንደፋ ይሆናል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ያለው ኃይል፣ ፍጥነት፣ ቅልጥፍና፣ ታላቅ ግርማና ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታ በታላቅ አድናቆት እንድንዋጥ ሊያደርገን አይገባም?

28, 29. የይሖዋ ሠረገላ ባለፈው መቶ ዘመን ሲገሰግስ እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?

28 በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት፣ ሰማያዊ ክፍል ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ክፍልም እንዳለው አስታውስ። እርግጥ ነው፣ ምድራዊው ክፍል ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች የተዋቀረ መሆኑ አይካድም። ያም ቢሆን ይሖዋ በዚህች ምድር ላይ ምን እንዳከናወነ እስቲ ለማሰብ ሞክር! ይሖዋ በመላው ምድር ላይ የሚገኙ ተራ ሰዎችን በራሳቸው አቅም ፈጽሞ ሊያከናውኑ የማይችሉትን ነገር ማከናወን እንዲችሉ ረድቷቸዋል። (ዮሐ. 14:12) ባለፈው መቶ ዓመት የስብከቱ ሥራ ምን ያህል በአስደናቂ ሁኔታ እንደተስፋፋ ለማየት የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! የተባለውን መጽሐፍ ገለጥ ገለጥ አድርጎ ማየት ብቻ ይበቃል። በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት እውነተኛ ክርስቲያኖችን በማስተማር፣ ሕግ ነክ ጉዳዮችን በመርታት እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ ያገኘውን ስኬት ማስታወስ እንችላለን!

29 በዚህ ብልሹ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ንጹሕ አምልኮን መልሶ በማቋቋም ረገድ የተከናወኑትን ነገሮች ስናስብ የይሖዋ ሠረገላ ወደፊት በመገስገስ ላይ መሆኑ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል። በዚህ ድርጅት ውስጥ መታቀፍና እንዲህ ያለውን ሉዓላዊ ገዢ ማገልገል መቻል እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው!—መዝ. 84:10

የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ምንጊዜም በመገስገስ ላይ ነው (አንቀጽ 28, 29⁠ን ተመልከት)

30. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመረምራለን?

30 ይሁን እንጂ ከሕዝቅኤል ራእይ የምናገኘው ሌላም ትምህርት አለ። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ አራቱ አስደናቂ “ሕያዋን ፍጥረታት” ወይም ኪሩቦች በጥልቀት እንመረምራለን። ታላቅ ግርማ የተላበሰውን ሉዓላዊ ገዢያችንን ይሖዋ አምላክን በተመለከተ ከእነዚህ ሕያዋን ፍጥረታት ምን እንማራለን?

^ አን.1 ሕዝቅኤል የጠቀሰው የሚያብረቀርቅ ብረት የወርቅንና የብርን ቅይጥ የሚያመለክት ነው።

^ አን.5 ይህ አሃዝ በኢየሩሳሌምና በባቢሎን መካከል ያለውን ቀጥተኛ ርቀት የሚያመለክት ሲሆን ግዞተኞቹ የተጓዙበት መንገድ ርቀት ግን የዚህ እጥፍ ሳይሆን አይቀርም።