በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መሣሪያዬ ምንጊዜም ከእኔ አይለይም ነበር

መሣሪያዬ ምንጊዜም ከእኔ አይለይም ነበር
  • የትውልድ ዘመን፦ 1958

  • የትውልድ አገር፦ ጣሊያን

  • የኋላ ታሪክ፦ ዓመፀኛና የወሮበሎች ቡድን አባል

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ተወልጄ ያደግሁት ከሮም ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ነው። ኑሮ ከባድ ነበር። ወላጅ እናቴን ጭራሽ አላውቃትም፤ ከአባቴም ጋር ቢሆን ጥሩ ግንኙነት አልነበረኝም። አስቸጋሪ በሆነ ሰፈር ውስጥ ስላደግሁ ከልጅነቴ ጀምሮ ዱርዬ ነበርኩ።

አሥር ዓመት ሳይሞላኝ መስረቅ ጀምሬ ነበር። በ12 ዓመቴ ከቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ወጣሁ። በተደጋጋሚ ጊዜያት አባቴ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየመጣ አስፈትቶ ወደ ቤት ይወስደኝ ነበር። ሁልጊዜ ከሰዎች ጋር እጋጭ ነበር፤ ዓመፀኛና ቁጡ በመሆኔ ከማንም ጋር አልስማማም ነበር። አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ ዳግም ላልመለስ ከቤት ወጣሁ። ከዚያም ዕፆችን መውሰድና በጎዳና ላይ መኖር ጀመርኩ። የማድርበት ቦታ ስላልነበረኝ የሰዎችን መኪና ከፍቼ በመግባት እስኪነጋጋ ድረስ እዚያ እተኛ ነበር። ከዚያም ጎዳና ላይ በሚገኝ የፏፏቴ ውኃ እተጣጠባለሁ።

በሌብነት ተክኜ ነበር፤ ቦርሳ ከመንጠቅ አንስቶ ሌሊት ላይ አፓርታማዎችንና ቪላዎችን እስከ መዝረፍ ድረስ በማንኛውም ዓይነት ስርቆት እካፈል ነበር። በምፈጽማቸው መጥፎ ድርጊቶች እየታወቅሁ ስለመጣሁ ብዙም ሳይቆይ፣ አገር ያሰለቹ ወሮበሎች ከቡድናቸው ጋር እንድቀላቀል ጋበዙኝ፤ ይህ ደግሞ ባንኮችን ወደ መዝረፍ እንድሸጋገር “ዕድል” ሰጠኝ። ጠብ አጫሪ በመሆኔ ብዙም ሳይቆይ የቡድኑ አባላት ያከብሩኝ ጀመር። መሣሪያዬ ምንጊዜም ከእኔ አይለይም ነበር፤ ስተኛ እንኳ ትራሴ ሥር አስቀምጠው ነበር። ዓመፅ፣ ዕፅ መውሰድ፣ ስርቆት፣ ጸያፍ ንግግርና የፆታ ብልግና በሕይወቴ ውስጥ የተለመዱ ነገሮች ሆኑ። ፖሊሶች ዘወትር ይከታተሉኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ተይዤ እታሰር ስለነበር ወህኒ ቤት፣ ቤቴ ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በአንድ ወቅት ከእስር ቤት ስለቀቅ አንድ አክስቴን ሄጄ ለመጠየቅ ወሰንኩ። አክስቴና ሁለቱ ልጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ አላወቅሁም። እነሱም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። ስብሰባው ምን እንደሚመስል ማየት ስለፈለግሁ ከእነሱ ጋር ለመሄድ ተስማማሁ። ወደ መንግሥት አዳራሹ ስንደርስ ወደ አዳራሹ የሚገቡትንና የሚወጡትን ለማየት እንዲያመቸኝ ስል በሩ አቅራቢያ መቀመጥ እንደምፈልግ ነገርኳቸው።  እንደተለመደው በዚህ ጊዜም ቢሆን ሽጉጤን ታጥቄ ነበር።

ይህ ስብሰባ ሕይወቴን ለወጠው። ያለሁት ሌላ ፕላኔት ላይ መሆን አለበት ብዬ እንዳሰብኩ ትዝ ይለኛል። በስብሰባው ላይ የነበሩት ሰዎች ሞቅ ያለ ሰላምታ የሰጡኝ ሲሆን ፊታቸው ላይ የወዳጅነት ስሜትና ፈገግታ ይነበብ ነበር። በእነዚያ የይሖዋ ምሥክሮች ፊት ላይ ይታይ የነበረው ደግነትና ቅንነት እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፋም። ይህ እኔ ከማውቀው ዓለም እጅግ የተለየ ነበር!

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ አኗኗሬን ሙሉ በሙሉ መለወጥ እንዳለብኝ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ። በምሳሌ 13:20 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ አደረግሁ። ከወሮበላ ቡድኑ መራቅ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም በይሖዋ እርዳታ ተሳክቶልኛል።

በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሴን መግዛትና ሕይወቴን ራሴ መምራት ቻልኩ

በተጨማሪም አካላዊ ንጽሕናዬን መጠበቅ ጀመርኩ። ሲጋራ ማጨስና ዕፅ መውሰድ ለማቆም ብዙ ቢያታግለኝም ይህንን አደረግሁ። ረጅሙን ፀጉሬን ተቆረጥኩ፣ የጆሮ ጉትቻዎቼን አስወገድኩ፤ እንዲሁም ጸያፍ ቃላት መጠቀም አቆምኩ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሴን መግዛትና ሕይወቴን ራሴ መምራት ቻልኩ።

ማንበብና ማጥናት የሚያስደስተኝ ሰው ስላልነበርኩ ሐሳቤን ሰብስቤ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ላይ ትኩረት ማድረግ ተፈታታኝ ሆኖብኝ ነበር። ይሁን እንጂ ጥረት ማድረጌን በመቀጠሌ እያደር ይሖዋን እየወደድኩት መጣሁ፤ እንዲሁም አመለካከቴ እየተለወጠ በመሄዱ ሕሊናዬ ይወቅሰኝ ጀመር። ብዙ መጥፎ ነገሮችን ስለሠራሁ ይሖዋ ይቅር ሊለኝ እንደማይችል ይሰማኝ ነበር፤ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ ስለ ራሴ መጥፎ አመለካከት ነበረኝ። እንዲህ በሚሰማኝ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአቶች ከፈጸመ በኋላ ይሖዋ ምሕረት እንዳደረገለት የሚገልጸውን ታሪክ ማንበብ በጣም ያጽናናኛል።—2 ሳሙኤል 11:1 እስከ 12:13

ፈታኝ የሆነብኝ ሌላው ነገር ደግሞ ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ እምነቴን ለሌሎች ማካፈል ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ቀደም ሲል በሆነ መንገድ የጎዳሁት ወይም የበደልኩት ሰው ቢያጋጥመኝስ ብዬ በጣም እፈራ ነበር። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ፍርሃቴን ማሸነፍ ቻልኩ። ምሕረቱ ብዙ ስለሆነው ድንቅ የሰማዩ አባታችን እንዲማሩ ሰዎችን በመርዳት እውነተኛ እርካታ ማግኘት ጀመርኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ስለ ይሖዋ መማሬ ሕይወቴን አትርፎልኛል! አብዛኞቹ የቀድሞ ጓደኞቼ ሞተዋል፤ አለዚያም ወህኒ ወርደዋል፤ እኔ ግን እውነተኛ እርካታ ያለው ሕይወት ብሎም በልበ ሙሉነት የምጠብቀው ተስፋ አለኝ። ትሑትና ታዛዥ መሆንን እንዲሁም የዓመፀኝነትና የግልፍተኝነት ባሕርዬን ማሸነፍን ተምሬያለሁ። በዚህም የተነሳ በዙሪያዬ ካሉት ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ውብ ከሆነች ካርሜን የተባለች እህት ጋር አስደሳች ትዳር መሥርቻለሁ። አብረን ሆነን ሌሎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር በጣም ያስደስተናል።

አሁን ሥራዬን የማከናውነው በሐቀኝነት ነው፤ አንዳንድ ጊዜ በሥራዬ ምክንያት ወደ ባንኮች እሄዳለሁ፤ የምሄደው ግን ባንኩን ልዘርፍ ሳይሆን ላጸዳ ነው!