በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የጥንት መርከብ ሠሪዎች፣ መርከቦች ውኃ እንዳይገባባቸው የሚያደርጉት እንዴት ነበር?

የጥንታዊ መርከቦች ጠበብት የሆኑት ላየነል ካሰን በሮማውያን ዘመን መርከብ ሠሪዎች መርከቡ ላይ ባሉት ጣውላዎች መካከል ያለውን ስንጥቅ ለመድፈን ምን ያደርጉ እንደነበረ ገልጸዋል። መርከብ ሠሪዎቹ “የጣውላዎቹን መገጣጠሚያ ወይም የመርከቡን ውጨኛ ክፍል ቅጥራን [ሬንጅ] ወይም ቅጥራንና ሰም ይቀቡ ነበር፤ የመርከቡን ውስጠኛ ክፍልም ቅጥራን ይለቀልቁት” ነበር። ከሮማውያን በፊትም የጥንቶቹ አካዳውያንና ባቢሎናውያን መርከቦቻቸው ውኃ እንዳይገባባቸው ለማድረግ ሬንጅ ይጠቀሙ ነበር።

እንደዚህ ያለ ፈሳሽ ሬንጅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሱ ቦታዎች በብዛት ይገኝ ነበር

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትም፣ ተመሳሳይ ዘዴ ጥቅም ላይ መዋሉን በዘፍጥረት 6:14 ላይ ይጠቅሳሉ። እዚህ ጥቅስ ላይ “ቅጥራን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በተፈጥሮ የሚገኘውን ሬንጅ ያመለክታል።

ተፈጥሯዊው ሬንጅ በፈሳሽ ወይም በጠጣር መልክ ይገኛል። የጥንት መርከብ ሠሪዎች የሚጠቀሙት በፈሳሽ መልክ የሚገኘውን ሬንጅ ነው፤ መርከቦቹን ይህን ሬንጅ ይቀቧቸዋል። ፈሳሽ የሆነው ሬንጅ ሲደርቅ ውኃ የማያስገባ ጠንካራ መከላከያ ይፈጥራል።

ሬንጅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሱ ቦታዎች በብዛት ይገኝ ነበር። በሙት ባሕር አቅራቢያ በሚገኘው በሲዲም ሸለቆ “ብዙ የቅጥራን ጕድጓዶች” ነበሩ።—ዘፍጥረት 14:10

በጥንት ዘመን ዓሣ እንዳይበላሽ ለመከላከል የሚሠራበት ዘዴ ምን ነበር?

ሰዎች ከጥንት ጊዜ አንስቶ ዓሣ ይመገቡ ነበር። አንዳንዶቹ የኢየሱስ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር መጓዝ ከመጀመራቸው በፊት በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። (ማቴዎስ 4:18-22) በዚህ ባሕር ላይ ከሚጠመዱት ዓሣዎች ቢያንስ የተወሰነው በአቅራቢያው በነበሩ “ፋብሪካዎች” እንዲዘጋጅ ይላክ ነበር።

የጥንት ግብፃውያን ዓሣ አጥማጆችን የሚያሳይ በእንጨት ላይ የተሠራ ምስል

ዓሣ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ በጥንቷ ገሊላ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበረ የሚታመነው ዘዴ አሁንም ድረስ በአንዳንድ ቦታዎች ይሠራበታል። በመጀመሪያ የዓሣዎቹ የሆድ ዕቃ ከወጣ በኋላ በውኃ ይታጠባሉ። ስተዲስ ኢን ኤንሸንት ቴክኖሎጂ የተባለው መጽሐፍ ቀጥሎ የሚከናወኑትን ነገሮች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የዓሣው መተንፈሻ አካል፣ አፉና ቆዳው ባልተፈጨ ጨው ይታሻል። በዚህ መንገድ የታሸው ዓሣ ጨው እየተነሰነሰበት ይነባበርና ተሸፍኖ ይቀመጣል። በዚህ ሁኔታ ከ3 እስከ 5 ቀናት ከቆየ በኋላ ተገልብጦ ለተመሳሳይ ጊዜ እንዲቆይ ይደረጋል። በዚህ የማድረቅ ሂደት ዓሣው ውስጥ ያለው ፈሳሽ ወጥቶ የሚያልቅ ሲሆን የጨዉ ውህድ ደግሞ ወደ ዓሣው ውስጥ ዘልቆ ይገባል። ይህም ዓሣዎቹ ደረቅና ጠንካራ እንዲሆኑ ያደርጋል።”

እንዲህ ባለ ዘዴ የተዘጋጀው ዓሣ ምን ያህል ጊዜ መቆየት ይችል እንደነበረ አይታወቅም። ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ግብፃውያን እንዳይበላሽ ተደርጎ የተቀመመውን ዓሣ ወደ ሶሪያ ይልኩ የነበረ መሆኑ የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች ከሞላ ጎደል ውጤታማ እንደነበሩ ይጠቁማል።