በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ ስለሚያሳስቡን ነገሮች በነፃነት ሁልጊዜ እንድንነግረው ይፈልጋል። (ሉቃስ 18:1-7) ስለሚያስብልን ስንጸልይ ይሰማናል። ታዲያ የሰማዩ አባታችን እንድንጸልይ በደግነት እስከጋበዘን ድረስ ግብዣውን የማንቀበልበት ምን ምክንያት ይኖራል?—ፊልጵስዩስ 4:6ን አንብብ።

የምንጸልየው ከአምላክ እርዳታ ለመጠየቅ ብቻ አይደለም። ጸሎት ወደ አምላክ እንድንቀርብም ይረዳናል። (መዝሙር 8:3, 4) የሚሰማንን ነገር ሁሉ አዘውትረን ለአምላክ የምንገልጽለት ከሆነ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን።—ያዕቆብ 4:8ን አንብብ።

መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?

አምላክ በምንጸልይበት ጊዜ የተራቀቁ ቃላትን እንድንጠቀም ወይም የተሸመደዱ ጸሎቶችን እንድንደግም አይፈልግም። አሊያም ደግሞ ስንጸልይ የተለየ ዓይነት አኳኋን ወይም አቋቋም እንዲኖረን አይጠብቅብንም። ይሖዋ የሚፈልገው ከልብ የመነጨ ጸሎት እንድናቀርብ ነው። (ማቴዎስ 6:7) ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቷ እስራኤል የነበረችው ሐና በቤተሰቧ ውስጥ ስላጋጠማት ከባድ ችግር ጸልያ ነበር። በኋላም የሚያስጨንቃት ነገር ተወግዶ ምኞቷ ሲሳካ ከልብ በመነጨ ጸሎት አምላክን አመስግናለች።—1 ሳሙኤል 1:10, 12, 13, 26, 27ን እና 1 ሳሙ 2:1ን አንብብ።

ጸሎት እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! ስለሚያሳስቡን ነገሮች ወደ ፈጣሪ መጸለይ እንችላለን። በተጨማሪም ልናወድሰውና ለሚያደርግልን ነገር ሁሉ ልናመሰግነው እንችላለን። በእርግጥም እንዲህ ዓይነቱን ውድ መብት ፈጽሞ ችላ ልንለው አይገባም።መዝሙር 145:14-16ን አንብብ።