በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የመጣው ከየት ነው?

ኢየሱስ የመጣው ከየት ነው?

“[ጲላጦስ] ዳግመኛም ወደ ገዥው ቤተ መንግሥት ገብቶ ኢየሱስን ‘ለመሆኑ ከየት ነው የመጣኸው?’ አለው። ኢየሱስ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም።”—ዮሐንስ 19:9

ሮማዊው ገዥ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ኢየሱስ ለፍርድ እሱ ፊት በቀረበበት ጊዜ ነበር። * ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ከየትኛው የእስራኤል አውራጃ እንደመጣ ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 23:6, 7) በተጨማሪም ኢየሱስ ተራ ሰው እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። ጲላጦስ ይህን ጥያቄ ያነሳው ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት በሕይወት ይኖር እንደነበረ ለማወቅ ፈልጎ ይሆን? ይህ አረማዊ አገረ ገዥ እውነትን ለመቀበልና ከእውነት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ፈልጎ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ የጲላጦስን ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበረም፤ ይሁንና ጲላጦስ ይበልጥ አሳስቦት የነበረው የእውነት ወይም የፍትሕ ጉዳይ ሳይሆን የሥልጣን ጉዳይ እንደነበረ ብዙም ሳይቆይ ግልጽ ሆነ።​—ማቴዎስ 27:11-26

ደስ የሚለው ነገር፣ በቅን ልቦና ተነሳስተው ኢየሱስ ከየት እንደመጣ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች መልሱን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከየት እንደመጣ በግልጽ ይናገራል። እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት፦

የተወለደበት ቦታ፦

በዘመናችን ያለው የቀን አቆጣጠር እንደሚያሳየው በአሁኑ ጊዜ 2 ዓ.ዓ. ተብሎ በሚጠራው ዓመት በመጸው ወራት መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ ይሁዳ ውስጥ በምትገኝ ቤተልሔም በተባለች መንደር ባልተጠበቀ ቦታ ተወለደ። ማርያምና ባልዋ ዮሴፍ የእሱ የትውልድ ቦታ ወደሆነችው ወደ ቤተልሔም የተጓዙት አውግስጦስ ቄሳር ሕዝቡ እንዲመዘገብ አዋጅ አውጥቶ ስለነበር ሲሆን በወቅቱ ማርያም “የመውለጃዋ ጊዜ ተቃርቦ” ነበር። ባልና ሚስቱ በሰው በተጨናነቀችው መንደር ውስጥ ማረፊያ ቦታ ማግኘት ስላልቻሉ ጋጣ ውስጥ ማረፍ ግድ ሆነባቸው፤ በዚህም ምክንያት ማርያም ኢየሱስን እዚያ ወልዳ በግርግም ውስጥ አስተኛችው።​—ሉቃስ 2:1-7

ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኢየሱስ ስለሚወለድበት ቦታ እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር፦ “አንቺ ግን፣ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፤ ከይሁዳ ነገዶች መካከል ትንሿ ብትሆኚም፣ . . . የእስራኤል ገዥ፣ ከአንቺ ይወጣልኛል።” * (ሚክያስ 5:2) ቤተልሔም በጣም ትንሽ መንደር ስለነበረች በይሁዳ ክልል ውስጥ ካሉት ከተሞች ዝርዝር ውስጥ የምትካተት አልነበረችም። ሆኖም ይህች ትንሽ መንደር ልዩ ክብር አገኘች። ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ ከቤተልሔም ሊወጣ ነው።​—ማቴዎስ 2:3-6፤ ዮሐንስ 7:40-42

ያደገበት ቦታ፦

የኢየሱስ ቤተሰብ ለአጭር ጊዜ በግብፅ ከቆየ በኋላ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን 96 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወዳለችውና በገሊላ አውራጃ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ሄዶ በዚያ መኖር ጀመረ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ሦስት ዓመት እንኳ አልሞላውም ነበር። ኢየሱስ ገበሬዎች፣ እረኞችና ዓሣ አጥማጆች በሚኖሩባት በዚህች ውብ ከተማ በሚኖር ደሃ በሆነ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ አደገ።​—ማቴዎስ 13:55, 56

ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ መሲሑ “የናዝሬት ሰው” እንደሚባል ትንቢት ተናግሮ ነበር። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ “‘የናዝሬት ሰው ይባላል’ ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ” የኢየሱስ ቤተሰብ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ መኖር እንደጀመረ ጽፏል። (ማቴዎስ 2:19-23) ናዝሬት የሚለው ቃል “ቁጥቋጥ” ተብሎ ከተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው ይመስላል። በመሆኑም ማቴዎስ ከላይ ያለውን ሐሳብ ሲጽፍ ኢሳይያስ ከእሴይ ግንድ የሚወጣ “ቍጥቋጥ” በማለት ስለ መሲሑ የተናገረውን ትንቢት መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም፤ በሌላ አባባል ኢሳይያስ መሲሑ የንጉሥ ዳዊት አባት የሆነው የእሴይ ዘር መሆኑን እየተናገረ ነበር። (ኢሳይያስ 11:1) በእርግጥም ኢየሱስ በዳዊት በኩል የእሴይ ዘር ነበር።​—ማቴዎስ 1:6, 16፤ ሉቃስ 3:23, 31, 32

የመጣበት ቦታ፦

ኢየሱስ ቤተልሔም በሚገኝ ጋጣ ውስጥ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ በሕይወት ይኖር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የሚክያስ ትንቢት “አመጣጡ ከጥንት፣ ከቀድሞ ዘመን [ነው]” እንደሚልም ልብ በል። (ሚክያስ 5:2) ኢየሱስ የአምላክ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን ሰው ሆኖ ምድር ላይ ከመወለዱ በፊት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር ነበር። ኢየሱስ ራሱ ‘የመጣሁት ከሰማይ ነው’ ብሏል። (ዮሐንስ 6:38፤ 8:23) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

ይሖዋ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተአምር በመፈጸም በሰማይ ይኖር የነበረውን የልጁን ሕይወት አይሁዳዊት ወደሆነችው ድንግል ማርያም ማህፀን አዘዋወረው፤ በዚህም ምክያት ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ሊወለድ ችሏል። * ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ ይህን ተአምር መፈጸም ቀላል ነው። መሲሑን እንደምትወልድ ለማርያም ያበሰራት መልአክ እንደገለጸው ለአምላክ “የሚሳነው ነገር የለም።”​—ሉቃስ 1:30-35, 37 አ.መ.ት.

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከየት እንደመጣ በመናገር ብቻ አይወሰንም። አራቱ ወንጌሎች ማለትም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ሕይወቱ ምን ይመስል እንደነበር ይበልጥ በዝርዝር ይነግሩናል።

^ አን.3 ስለ ኢየሱስ መያዝና ፍርድ ፊት መቅረብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “በኢፍትሐዊነቱ አቻ የማይገኝለት የፍርድ ሂደት” የሚለውን ከገጽ 18-22 የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.6 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኤፍራታ የቤተልሔም የቀድሞ ስሟ ነው።​—ዘፍጥረት 35:19

^ አን.10 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ይሖዋ የአምላክ ስም ነው።