በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ሕይወቱ ምን ይመስል ነበር?

ኢየሱስ ሕይወቱ ምን ይመስል ነበር?

“የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው።”​—ዮሐንስ 4:34

ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሐሳብ እንዲናገር ያደረገውን ሁኔታ መመልከታችን ሕይወቱ በዋነኝነት በምን ላይ ያተኮረ እንደነበረ ፍንጭ ይሰጠናል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ በሙሉ ኮረብታማ በሆነችው በሰማርያ ከተማ ሲጓዙ ነበር። (ዮሐንስ 4:6) ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ርቦታል ብለው ስላሰቡ ምግብ እንዲበላ ይጉተጉቱት ጀመር። (ዮሐንስ 4:31-33) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው መልስ ላይ የሕይወቱ ዓላማ ምን እንደሆነ ጠቅለል አድርጎ ገልጾላቸዋል። ለእሱ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ከምግብ የበለጠ አስፈላጊ ነገር ነበር። ኢየሱስ በቃልም ሆነ በተግባር ሕይወቱ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ አሳይቷል። ይህ ምንን ይጨምራል?

ስለ አምላክ መንግሥት ሰብኳል እንዲሁም አስተምሯል፦

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ስላከናወነው ሥራ ሲናገር “እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ . . . በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ” ይላል። (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት በመስበክ ወይም በማወጅ ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ሰዎችን አስተምሯል ማለትም ስለነገራቸው ነገር አብራርቶላቸዋል እንዲሁም አሳማኝ ምክያት በማቅረብ አስረድቷቸዋል። የአምላክ መንግሥት የኢየሱስ መልእክት ዋና ጭብጥ ነበር።

ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ዓመታት ሁሉ አድማጮቹን የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ ብሎም መንግሥቱ ወደፊት ምን እንደሚያከናውን አስተምሯቸዋል። የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ከዚህ ቀጥሎ የሰፈሩትን እውነታዎችና ኢየሱስ እነዚህን ሐቆች አስመልክቶ የተናገረውን ሐሳብ የያዙ ጥቅሶችን ተመልከት።

  • የአምላክ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር ሲሆን ይሖዋ በዚህ መንግሥት ላይ ንጉሥ እንዲሆን ኢየሱስን ሾሞታል።​—ማቴዎስ 4:17፤ ዮሐንስ 18:36

  • መንግሥቱ የአምላክን ስም የሚያስቀድስ ሲሆን ፈቃዱ በሰማይ ላይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲሆን ያደርጋል።​—ማቴዎስ 6:9, 10

  • በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር መላዋ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች።​—ሉቃስ 23:42, 43

  • የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በመምጣት አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደርጋል። *​—ማቴዎስ 24:3, 7-12

▪ ተአምራትን ፈጽሟል፦

ኢየሱስ በዋነኝነት የሚታወቀው ‘በመምህርነቱ’ ነበር። (ዮሐንስ 13:13) ሆኖም ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ተአምራትን ፈጽሟል። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ቢያንስ ሁለት ዓላማዎችን አከናውነዋል። በመጀመሪያ ኢየሱስ በእርግጥ በአምላክ የተላከ መሆኑን አረጋግጠዋል። (ማቴዎስ 11:2-6) ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሲሆን ምን እንደሚያከናውን የሚያሳዩ ናሙናዎች ሆነው አገልግለዋል። እስቲ ያከናወናቸውን አንዳንድ ተአምራት እንመልከት።

እንዲህ ዓይነቱ ኃያል ንጉሥ ወደፊት ምድርን ሲያስተዳድር ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት!

ሌሎች ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እንዲያውቁ አድርጓል፦

ስለ ይሖዋ ለሌሎች በማስተማር ረገድ  ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ ከሚጠራው ከአምላክ ልጅ የበለጠ ብቁ ሊሆን የሚችል የለም። ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” እንደመሆኑ መጠን ከማንኛውም መንፈሳዊ ፍጡር በላይ ከይሖዋ ጋር በሰማይ ኖሯል። (ቆላስይስ 1:15) የአባቱን አስተሳሰብ፣ ፈቃድ፣ መመሪያ እንዲሁም መንገድ ለመማር ምን ያህል ሰፊ አጋጣሚ እንደነበረው አስብ።

በመሆኑም ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት መናገሩ ተገቢ ነው፦ “ከአብ በስተቀር ወልድ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም፤ እንዲሁም ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድለት በስተቀር አብ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም።” (ሉቃስ 10:22) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በኖረባቸው ዓመታት በፈቃደኝነትና በደስታ አባቱ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እንዲታወቅ አድርጓል። ኢየሱስ በመንፈሳዊው ዓለም እጅግ ከፍ ባለ ሥፍራ ከሚኖረው ከሉዓላዊው አምላክ ጋር በኖረባቸው ዓመታት በቀጥታ የተመለከታቸውን ነገሮች አስታውሶ ስለተናገረ አባቱን በሚመለከት ያስተማራቸው ነገሮች ፈጽሞ የተለዩ ነበሩ።​—ዮሐንስ 8:28

ኢየሱስ አባቱ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው እንዲታወቅ ያደረገበት መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠንን ከሚቀይር ትራንስፎርመር ከሚባል መሣሪያ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እንዲህ ያለው መሣሪያ ወደ ውስጡ የገባውን ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌትሪክ ኃይል ቀይሮ ተጠቃሚው ሰው የሚፈልገውን ያህል አነስተኛ የኤሌትሪክ ኃይል እንዲወጣ ያደርጋል። ኢየሱስ በሰማይ ሳለ ስለ አባቱ የተማረውን ነገር ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ዝቅተኛ የሆኑ ሰብዓዊ ፍጡራን በቀላሉ ሊረዱትና ተግባራዊ ሊያደርጉት በሚችሉት መንገድ አስተምሯል።

ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት የገለጠባቸውን ሁለት መንገዶች እንመልከት፦

  • ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርት አማካኝነት ስለ ይሖዋ እውነቱ ማለትም ስሙ፣ ዓላማውና መንገዶቹ እንዲታወቁ አድርጓል።​—ዮሐንስ 3:16፤ 17:6, 26

  • ኢየሱስ ባከናወናቸው ነገሮች አማካኝነት ግሩም የሆኑት የይሖዋ የተለያዩ ባሕርያት በግልጽ እንዲታወቁ አድርጓል። ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ በዚህም ምክንያት ‘አባቴ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ እኔን ተመልከቱ’ የሚል አንድምታ ያላቸውን አገላለጾች ተጠቅሟል።​—ዮሐንስ 5:19፤ 14:9

በእርግጥም ኢየሱስ ሕይወቱን የተጠቀመበት መንገድ በጣም የሚያስደንቅ ነው። ኢየሱስ የሞተበትን ምክንያት መርምረን ከተማርነው ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ ከፍተኛ ጥቅም ልናገኝ እንችላለን።

^ አን.9 ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት በቅርቡ እንደሚመጣ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንደምንችል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 8⁠ን እና “የምንኖረው ‘በመጨረሻው ዘመን’ ውስጥ ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 9⁠ን ተመልከት።