በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

 ከአምላክ ቃል ተማር

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

ይህ ርዕሰ ትምህርት በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን የሚያነሳ ሲሆን መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችልም ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ቢወያዩ ደስ ይላቸዋል።

1. አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

ምድር የሰው ልጆች መኖሪያ ናት። አምላክ መላእክትን በሰማይ እንዲኖሩ ከፈጠረ በኋላ ሰውን ደግሞ በምድር ላይ እንዲኖር ፈጠረው። (ኢዮብ 38:4, 7) በመሆኑም የመጀመሪያውን ሰው ውብ በሆነችው ኤደን ገነት ውስጥ አስቀመጠው፤ ከዚያም ለአዳምና ወደፊት ለሚወልዳቸው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጣቸው።​—ዘፍጥረት 2:15-17፤ መዝሙር 115:16ን አንብብ።

ኤደን ገነት የሚሸፍነው ከምድር ክፍል ውስጥ በጣም ጥቂቱን ብቻ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የሆኑት አዳምና ሔዋን ልጆች መውለድ ይጠበቅባቸው ነበር። የሰው ልጆች ቁጥር በምድር ላይ እየተበራከተ ሲመጣ መላዋን ምድር ማልማትና ገነት ማድረግ ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 1:28) ምድርም ፈጽሞ አትጠፋም።​—መዝሙር 104:5ን አንብብ።

2. በአሁኑ ጊዜ ምድር ገነት ያልሆነችው ለምንድን ነው?

አዳምና ሔዋን አምላክን ለመታዘዝ አሻፈረኝ በማለታቸው ከኤደን ገነት ተባረሩ። ገነት የጠፋች ሲሆን ማንም ሰው መልሶ ሊያቋቁማት አልቻለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር በክፉዎች እጅ [ወድቃለች]” ይላል።​—ኢዮብ 9:24፤ ዘፍጥረት 3:23, 24ን አንብብ።

ይሁንና ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ አልረሳውም፤ ደግሞም አምላክ ምንጊዜም ዓላማውን ማሳካት ይችላል። (ኢሳይያስ 45:18) አምላክ፣ የሰው ልጆች መጀመሪያ ላይ ያሰበላቸውን ሕይወት እንዲያገኙ ያደርጋል።​—መዝሙር 37:11ን አንብብ።

3. አምላክ በምድር ላይ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገው እንዴት ነው?

የሰው ልጆች ሰላም እንዲያገኙ ከተፈለገ አምላክ አስቀድሞ ክፉ ሰዎችን ማጥፋት ይኖርበታል። በአርማጌዶን ጦርነት ጊዜ መላእክት የአምላክን ተቃዋሚዎች በሙሉ ጠራርገው ያጠፋሉ። ሰይጣን ለ1,000 ዓመት ይታሰራል፤ አምላክን የሚወዱ ሰዎች ግን ከዚህ ጥፋት ተርፈው ወደፊት በሚመጣው አዲስ ሥርዓት ውስጥ ይኖራሉ።​—ራእይ 16:14, 16⁠ን፤ 20:1-3⁠ን እና 21:3, 4ን አንብብ።

  4. መከራና ሥቃይ የሚወገደው መቼ ነው?

ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ ለ1,000 ዓመት ምድርን የሚያስተዳድር ሲሆን በዚህ ወቅት ወደ ገነትነት እንድትለወጥ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ አምላክን የሚወዱ ሰዎችን ኃጢአት ያስተሰርያል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ በሽታን፣ እርጅናንና ሞትን ያስቀራል።​—ኢሳይያስ 11:9⁠ን፤ 25:8⁠ን፤ 33:24⁠ን እና 35:1ን አንብብ።

ታዲያ አምላክ ክፋትን ከምድር ላይ የሚያስወግደው መቼ ነው? ኢየሱስ ክፋት መቼ እንደሚወገድ የሚጠቁም “ምልክት” ሰጥቷል። አሁን ያለንበት ጊዜ የሰዎችን ሕልውና የሚፈታተን መሆኑ የምንኖረው ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ውስጥ መሆኑን ይጠቁማል።​—ማቴዎስ 24:3, 7-14, 21, 22ን እና 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብብ።

5. ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖሩት እነማን ናቸው?

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩና የአምላክን ፍቅራዊ መንገዶች እንዲያስተምሯቸው ተከታዮቹን አዟል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይሖዋ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ምድር ላይ ለሚያቋቁመው አዲስ ሥርዓት እያዘጋጃቸው ነው። (ሶፎንያስ 2:3) በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ሰዎች ጥሩ ባልና አባት እንዲሁም ጥሩ ሚስትና እናት መሆን የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እየተማሩ ነው። ልጆችና ወላጆች ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ለማመን ምክንያት ስለሆኑት ነገሮች አንድ ላይ ሆነው ይማራሉ።​—ሚክያስ 4:1-4ን አንብብ።

ወደ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ብትሄድ አምላክን የሚወዱና እሱን ማስደሰት ስለሚቻልበት መንገድ መማር የሚፈልጉ ሰዎችን ታገኛለህ።​—ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።