በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ‘ታላላቅ ነገሮችን ያደርጋል’ ይህን ማወቅ የቻልኩበት መንገድ

አምላክ ‘ታላላቅ ነገሮችን ያደርጋል’ ይህን ማወቅ የቻልኩበት መንገድ

አምላክ ‘ታላላቅ ነገሮችን ያደርጋል’ ይህን ማወቅ የቻልኩበት መንገድ

ሞሪስ ራጅ እንደተናገረው

ቤተሰባችን በሺዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞች ጋር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከነበረው አስፈሪ ወረራ ለማምለጥ በሽሽት ላይ ነበር። ቀን ቀን ጥቅጥቅ ባለው የበርማ ጫካ ውስጥ ስንጓዝ ከዋልን በኋላ ሌሊቱን ዛፍ ሥር ተኝተን እናድራለን፤ በዚህ ሁኔታ ለበርካታ ቀናት ስንጓዝ ቆየን። በወቅቱ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበርኩ። አሉኝ የምላቸውን ነገሮች በሙሉ በትንሽ ከረጢት አድርጌ አዝያለሁ። ይሁንና ያሳለፍኩት ችግር ገና መጀመሩ ነበር።

ጊዜው 1942 ሲሆን መላው ዓለም በጦርነት እየታመሰ ነበር። እኛም እየገሰገሰ ከሚመጣው የጃፓን ሠራዊት ለማምለጥ ሽሽት ጀምረናል። የጃፓን ሠራዊት በአሁኑ ጊዜ ምያንማር ተብላ ወደምትጠራው ወደ በርማ ዘልቆ በመግባት በየናንጃውንግ የሚገኘውን የነዳጅ ማውጫ በቁጥጥሩ ሥር አድርጓል። ወደ ሕንድ ድንበር ከመድረሳችን በፊት የጃፓን ወታደሮች ደርሰው ወደ ቤታችን እንድንመለስ አስገደዱን።

ልጅ እያለሁ የምንኖረው አባቴ የሚሠራበት የበርማ ነዳጅ ማውጫ ኩባንያ በሚገኝበት በየናንጃውንግ ነበር። በርካታ የነዳጅ ማውጫዎች ያሏት የየናንጃውንግ ከተማ ከጃፓን ወረራ በኋላ የእንግሊዝ ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች የጥቃት ዒላማ ሆነች። በአንድ ወቅት በዙሪያችን ቦንብ ይዘንብ ስለነበር ቤተሰባችን ለሦስት ቀናት በአንድ ምሽግ ውስጥ ለመደበቅ ተገዶ ነበር። በመጨረሻም በአንዲት ትንሽ ጀልባ ተሳፍረን በኤያርዋዲ ወይም በኢረዋዲ ወንዝ ዳርቻ ወደምትገኝ ሰሌ የተባለች ትንሽ ከተማ ሸሽተን ሄድን። ሕይወታችን በመትረፉ በጣም የተደሰትን ሲሆን የጦርነቱ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ እዚያው ቆየን።

የደረሰብኝ አሳዛኝ ሁኔታ እውነትን እንዳውቅ ረዳኝ

በ1945 ማለትም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ባበቃበት ዓመት ታናሽ ወንድሜ ተወለደ። አባቴ ዕድሜው ከገፋ በኋላ ልጅ በመውለዱ በጣም ተደስቶ ነበር። ይሁንና ደስታው ብዙም አልዘለቀም። ከሦስት ወራት በኋላ ወንድሜ ሞተ። አባቴም የልጁ ሞት ያስከተለበት ሐዘን በጣም ስለጎዳው ብዙም ሳይቆይ አረፈ።

ጓደኞቼ አምላክ ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ሲል አባቴንና ወንድሜን ወደ ሰማይ እንደወሰዳቸው በመናገር ሊያጽናኑኝ ሞከሩ። እኔም ከአባቴና ከወንድሜ ጋር የመሆን ፍላጎት አድሮብኝ ነበር። ቤተሰባችን፣ በልጅነቴ ሃይማኖታዊ ትምህርት ወደተከታተልኩበት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ ነበር። ቀሳውስትና መነኮሳት በሚሞቱበት ጊዜ ቀጥታ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ሌሎች ግን ከኃጢአታቸው ለመንጻት ጊዜያዊ የመሠቃያ ቦታ በሆነው በመንጽሔ ለተወሰነ ጊዜ እንደሚቆዩ በዚያ ተምሬ ነበር። ከአባቴና ከወንድሜ ጋር ለመገናኘት ቆርጬ ስለነበር 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና በአሁኑ ጊዜ ፒን ዩ ልዊን ተብላ በምትጠራው በማምዮ ከተማ በሚገኝ አንድ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ለመማር ግብ አወጣሁ።

ወደ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቱ ለመግባት መደበኛ ትምህርት መከታተል ያስፈልግ ነበር። እኔ ግን ስደተኛ እንደመሆኔ መጠን ትምህርት ቤት ገብቼ የተማርኩት ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ ጦርነቱ ስለጀመረ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተዘጉ። ውሎ አድሮ ትምህርት ቤቶች የተከፈቱ ቢሆንም ቤተሰባችን ከባድ የገንዘብ ችግር ስለነበረበት ትምህርቴን መቀጠል አልቻልኩም። እናቴ እኔንና ሁለት ወንድሞቼን ብቻ ሳይሆን በቅርብ የሞተችውን የእህቷን ሦስት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት ነበረባት። ስለሆነም እኛን ትምህርት ቤት አስገብታ ለማስተማር የሚያስችል አቅም አልነበራትም።

ታላቅ ወንድሜ ሥራ አግኝቶ መሥራት ጀመረ፤ እኔ ግን ገና የ13 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ልሠራው የምችለው ነገር አልነበረም። ማኑዌል ኔተን የሚባል የአባቴ ወንድም ሰሌ አቅራቢያ በምትገኝ ቻውክ በምትባል ከተማ ይኖር ነበር። ‘እኔ ከቤት ብወጣ እናቴ የምትቀልበው አንድ ሰው ይቀንስላታል’ ብዬ ስላሰብኩ ከአጎቴ ጋር ለመኖር ወደ ቻውክ ሄድኩ።

አጎቴ በቅርቡ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቶ ስለነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያገኘውን አዲስ እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፤ እርግጥ እኔ ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር አልነበረም። አባታችን ሆይ የተባለውን ጸሎት ትርጉም ከማብራራት አንስቶ፣ የተማረውን ነገር ቀስ በቀስ ያካፍለኝ ነበር። ጸሎቱ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት ይጀምራል።—ማቴዎስ 6:9, 10

አጎቴ “ስለዚህ አምላክ ስም አለው ማለት ነው፤ ስሙ ደግሞ ይሖዋ ነው” በማለት አስረዳኝ። ከዚያም የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየኝ። እኔም ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት አደረብኝ። ይሁንና አፍ መፍቻዬ በሆነው በታሚል ቋንቋም እንኳ ጥሩ የማንበብ ችሎታ አልነበረኝም፤ በዚህ ላይ አጎቴ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የሚያነባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እኔ እምብዛም በማልረዳው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ነበሩ። የትምህርት ደረጃዬ ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ቀስ በቀስ መረዳት ቻልኩ። (ማቴዎስ 11:25, 26) ከዚህ ቀደም የተማርኳቸው መሠረተ ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዳልነበራቸው ማስተዋል ጀመርኩ። በመጨረሻም፣ “ይህ ነገር እውነት ነው!” በማለት ለአጎቴ ነገርኩት።

የ16 ዓመት ወጣት እያለሁ የተማርኩትን ለሌሎች ማካፈል ጀመርኩ። በወቅቱ በምያንማር 77 የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ሮበርት ኪርክ የተባለ ሚስዮናዊ አጎቴን ለመጠየቅ ከዋና ከተማዋ ከራንጉን (አሁን ያንጎን ትባላለች) ወደ ቻውክ መጣ። በዚህ ጊዜ ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን ለሮበርት ነገርኩት። በመሆኑም ታኅሣሥ 24, 1949 ራሴን ለአምላክ መወሰኔን ለማሳየት በኤያርዋዲ ወንዝ ውስጥ ተጠመቅሁ።

መሰናክሎችን መወጣት

ከተጠመቅሁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተስማሚ የሆነ ሥራ ለመፈለግ ወደ መንደሌይ ሄድኩ። ግቤ አቅኚ (የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚጠሩበት ስም ነው) መሆን ነበር። አንድ ቀን የእግር ኳስ ጨዋታ እየተመለከትኩ እያለ ድንገት አንቀጠቀጠኝና ተዝለፍልፌ ወደቅሁ። የሚጥል በሽታ እንደያዘኝ ስለታወቀ ቤተሰብ እንዲንከባከበኝ ተመልሼ ወደ ቤት መሄድ ግድ ሆነብኝ።

በሽታው ለስምንት ዓመት ያህል አልፎ አልፎ ይነሳብኝ ነበር። የጤንነቴ ሁኔታ በሚሻሻልበት ጊዜ ተቀጥሬ መሥራት እጀምራለሁ። እናቴ የጤንነቴ ሁኔታ ስለሚያሳስባት የሙሉ ጊዜ አገልገሎት እንዳልጀምር ግፊት ታደርግብኝ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን “ከዚህ በላይ መቆየት አልችልም፤ አቅኚ መሆን እፈልጋለሁ። ይሖዋም ቢሆን አይጥለኝም!” በማለት ነገርኳት።

በ1957 ወደ ያንጎን በመሄድ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። የሚያስገርመው የነበረብኝ የሚጥል በሽታ ለ50 ዓመታት ያህል ማለትም እስከ 2007 ድረስ ተነስቶብኝ አያውቅም ነበር። በአሁኑ ጊዜ በሽታው እንዳይነሳብኝ መድኃኒት እወስዳለሁ። በ1958 ልዩ አቅኚ ሆኜ የተሾምኩ ሲሆን በስብከቱ ሥራ ላይ በየወሩ 150 ሰዓት አሳልፍ ነበር።

መጀመሪያ የተመደብኩት ከያንጎን ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጆንሻ በምትባል መንደር ነበር። በዚህች መንደር የነበሩ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን አንብበው ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት አድሮባቸው ነበር። እኔና ሮበርት እዚያ ስንደርስ በጣም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ለነበሯቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ከሰጠናቸው በኋላ ስብሰባዎችን እንዴት ማካሄድ እንደሚችሉ አሳየናቸው። ብዙም ሳይቆይ አንዳንዶቹ በስብከቱ ሥራ አብረውን መሳተፍ ጀመሩ። እኔም በቋሚነት እንዳገለግል እዚያው ተመደብኩ። እዚያ የነበረው አነስተኛ ቡድን በጥቂት ወራት ውስጥ ጥሩ እድገት አድርጎ ጉባኤ ሆነ። በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ ከ150 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።

ከጊዜ በኋላ ተጓዥ አገልጋይ ሆኜ ስለተሾምኩ በመላው ምያንማር የሚገኙ ጉባኤዎችንና በገለልተኛ አካባቢ ያሉ ቡድኖችን መጎብኘት ጀመርኩ። ይህ ሥራ ዕቃ ጭነው በአቧራማ መንገዶች ላይ በሚጓዙ መኪኖች አናት ላይ ተሳፍሮ መጓዝን፣ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ ረጅም የእግር ጉዞ ማድረግን፣ በወንዞች ላይ በጀልባ መጓዝንና በተራራማ አካባቢ አድካሚ የሆነ የእግር ጉዞ ማድረግን የሚጠይቅ ነበር። ያን ያህል ጠንካራ የምባል ሰው ባልሆንም ይሖዋ በዚህ ሥራ ለመቀጠል የሚያስችል ኃይል እንደሰጠኝ ይሰማኛል።—ፊልጵስዩስ 4:13

“ይሖዋ ይረዳሃል”

በ1962 ያንጎን ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛወርኩ፤ በዚያም ሮበርት አንዳንድ ሥልጠናዎችን ሰጠኝ። ብዙም ሳይቆይ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ከውጪ የመጡ ሚስዮናውያን በሙሉ ምያንማርን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ አስተላለፉ፤ በዚህ ምክንያት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሁሉም የውጪ አገር ዜጎች አገሪቱን ለቀው ወጡ። በጣም የሚያስገርመው የቅርንጫፍ ቢሮውን በበላይነት የመከታተል ኃላፊነት ለእኔ ተሰጠኝ።

‘ትምህርትም ሆነ ተሞክሮ የለኝም፤ ታዲያ ይህን ሥራ የማከናውነው እንዴት ነው?’ ብዬ አሰብኩ። በዕድሜ የገፉ በርካታ ወንድሞች ጭንቀቴን አስተውለው “ሞሪስ አትጨነቅ፤ ይሖዋ ይረዳሃል። እኛም ብንሆን ከጎንህ ነን” በማለት አበረታቱኝ። እነዚህ ወንድሞች የተናገሩት ሐሳብ በጣም አረጋግቶኛል። ከጥቂት ወራት በኋላ በ1967 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ የሚወጣውን በምያንማር የተደረገውን የስብከት እንቅስቃሴ ዓመታዊ ሪፖርት አጠናቀርኩ። ከዚያ በኋላ በነበሩት 38 ዓመታትም የአገሪቱን ዓመታዊ ሪፖርት ያጠናቀርኩት እኔ ነበርኩ። በጊዜ ሂደት የተከሰቱት ሁኔታዎች በእርግጥም ሥራችንን እየመራ ያለው ይሖዋ እንደሆነ ይበልጥ እንድገነዘብ አስችለውኛል።

ለምሳሌ ያህል፣ የምያንማር ዜግነት ለማግኘት ማመልከቻ አስገብቼ በነበረበት ወቅት ለክፍያ የሚሆን 450 ቻት * ስለጎደለኝ ጉዳዩን ለጊዜው ተውኩት። አንድ ቀን ከዓመታት በፊት እሠራበት በነበረው ድርጅት አጠገብ ሳልፍ የቀድሞ አለቃዬ አየኝ። ሰውየው ድምፁን ከፍ አድርጎ “ራጅ፣ ና ገንዘብህን ውሰድ። ሥራህን በለቀቅክበት ጊዜ ለጡረታ ስትከፍል የነበረውን ገንዘብ አልወሰድክም” አለኝ። የገንዘቡ መጠን 450 ቻት ነበር።

ገንዘቡን ወስጄ ስወጣ ባገኘሁት 450 ቻት ላደርግ ስለምችላቸው ነገሮች በሙሉ ማሰብ ጀመርኩ። ይሁንና ገንዘቡ ዜግነት ለማግኘት ከጎደለኝ ጋር እኩል ስለነበር ይሖዋ ገንዘቡን ለዚህ ዓላማ እንድጠቀምበት እንደሚፈልግ ተሰማኝ። እንዲህ ማድረጌ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነበር። ዜግነት ማግኘቴ በአገሪቱ ውስጥ ለመኖር፣ በነፃነት ለመንቀሳቀስ፣ ጽሑፎችን ከውጪ ለማስገባትና በምያንማር ለሚካሄደው የስብከት ሥራ የሚያስፈልጉ ሌሎች ጠቃሚ ተግባሮችን ለማከናወን ያስችለኛል።

በሰሜን ምያንማር የተደረገ የአውራጃ ስብሰባ

በሰሜን ምያንማር በምትገኘው በማይትክላይና ከተማ የስብከቱ ሥራ ፈጣን እድገት ስላደረገ በ1969 በዚህች ከተማ የአውራጃ ስብሰባ ለማድረግ ወሰንን። ይሁንና በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የሚያስችል የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆኖብን ነበር። በጉዳዩ ላይ ከጸለይን በኋላ የምያንማር የባቡር ትራንስፖርት ድርጅት 6 ፉርጎዎችን እንዲይዝልን ጠየቅን። ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ስንሰማ ሁላችንም በጣም ተገረምን።

በዚህ መሃል ለአውራጃ ስብሰባው የሚያስፈልገውን ዝግጅት አጠናቀቅን። የስብሰባው ልዑካን በሚመጡበት ዕለት ባቡሩ ከሰዓት በኋላ 8:30 ላይ እንደሚደርስ አስበን ስለነበር እኩለ ቀን አካባቢ ወደ ባቡር ጣቢያው ሄድን። የባቡሩን መምጣት እየጠበቅን ሳለ የጣቢያው ኃላፊ አንድ የቴሌግራም መልእክት ይዞልን መጣ፤ መልእክቱ “የዎች ታወር ማኅበር ስድስት ፉርጎዎችን መላክ አልቻልንም” የሚል ነበር። ኃላፊው ባቡሩ ተጨማሪ ስድስት ፉርጎዎችን እየጎተተ ዳገት መውጣት እንደማይችል ነገረን።

ታዲያ ምን ማድረግ ይሻለናል? መጀመሪያ የመጣልን ሐሳብ የአውራጃ ስብሰባውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ነበር። እንዲህ ካደረግን ደግሞ ከስብሰባው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገሮችን ለማስፈቀድ ሳምንታት ይወስድብናል። ወደ ይሖዋ አጥብቀን እየጸለይን ሳለ ባቡሩ ወደ ጣቢያው ገባ። የይሖዋ ምሥክሮች የተሳፈሩባቸውን ስድስት ፉርጎዎች ስናይ ዓይናችንን ማመን አቃተን! ወንድሞች በፈገግታ ተሞልተው እጃቸውን እያውለበለቡ ነበር። ምን እንደተከሰተ ስንጠይቅ አንድ ወንድም “እርግጥ ስድስት ፉርጎዎችን ቀንሰዋል፤ የእኛን ፉርጎዎች ግን አልነኳቸውም!” በማለት ነገረን።

ከ1967 እስከ 1971 ባሉት ዓመታት በምያንማር የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በእጥፍ አድጎ 600 አካባቢ ደረሰ። በ1978 ቅርንጫፍ ቢሮው ወደ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ተዛወረ። ከ20 ዓመት በኋላ የወንድሞች ቁጥር ከ2,500 በላይ ሆኗል። የቅርንጫፍ ቢሮው የማስፋፊያ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ጆን ባር ከዩናይትድ ስቴትስ በመምጣት ጥር 22, 2000 በዛሬው ጊዜ ለቢሮ ሥራና ለመኖሪያነት ለምንጠቀምበት ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ የውሰና ንግግር አቀረበ።

ያገኘሁትን በረከት መለስ ብዬ ስቃኝ

በአሁኑ ወቅት ያንጎን በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ 52 ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚያገለግሉ ሲሆን በመላው አገሪቱ ውስጥ በ74 ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ የታቀፉ 3,500 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። በጣም የምወዳት እናቴ ከመሞቷ ትንሽ ቀደም ብሎ ማለትም በ1969 የይሖዋ ምሥክር መሆኗን መመልከቴ በጣም አስደስቶኛል።

በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ዶረስ በ ኤ የምትባል የአገሬው ተወላጅ የሆነች አንዲት አቅኚ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የትርጉም ሥራ መሥራት ጀመረች። በ1959 ዶረስ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሚስዮናውያንን በሚያሠለጥነው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 33ኛ ክፍል በመግባት ሥልጠና ወስዳ ነበር። ተፈጥሮ ያደላት ውበቷ፣ ተግባቢና ተጫዋች መሆኗ እንዲሁም መንፈሳዊነቷ ልቤን ማረከው። በ1970 ከዶረስ ጋር ተጋባን። ለይሖዋም ሆነ እርስ በርስ ያለን ፍቅር አሁን ድረስ አልቀዘቀዘም።

በምያንማር የተካሄደው የስብከት ሥራ የይሖዋ እጅ እንደነበረበት ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት መመልከት ችያለሁ። በእርግጥም አምላክ ታላቅ ስለሆነ ከፍተኛ ውዳሴ ይገባዋል። ካሳለፍኩት ሕይወት መመልከት እንደቻልኩት ይሖዋ ‘ታላላቅ ነገሮችን የሚያደርግ’ አምላክ ነው።—መዝሙር 106:21

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.23 ይህ ገንዘብ በወቅቱ ወደ 95 የአሜሪካ ዶላር ይጠጋ ነበር።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1957 አካባቢ ራንጉን፣ በርማ ውስጥ አገልግሎት ላይ ሳለሁ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1970ዎቹ መገባደጃ ላይ በካሌምዮ፣ በርማ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ስጓዝ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2000 ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነው በጣም የሚያምረው አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከዶረስ ጋር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከዶረስ ጋር ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል