በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

 ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሕፃኑን ኢየሱስን ሊጠይቁት የመጡት ሰብአ ሰገል እነማን ነበሩ?

ማቴዎስ ስለ ኢየሱስ መወለድ በወንጌሉ ላይ ባሰፈረው ዘገባ መሠረት አዲስ ንጉሥ መወለዱን የሚያመለክት ኮከብ አይተው “ከምሥራቅ” የመጡ ሰዎች ለሕፃኑ ኢየሱስ ስጦታ አበርክተውለታል። የማቴዎስ ወንጌል በግሪክኛው ጽሑፍ ላይ እነዚህን ሰዎች ሜጆይ (በእንግሊዝኛ ሜጃይ) ብሎ የሚጠራቸው ሲሆን በአማርኛ እነዚህ ሰዎች “ሰብአ ሰገል” ተብለዋል። (ማቴዎስ 2:1 የ1954 ትርጉም) ስለ እነዚህ ሰዎች ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

ስለ ሜጆይ ወይም ሰብአ ሰገል የሚገልጽ ቀደምትነት ያለው በቂ መረጃ የምናገኘው ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ ካሰፈረው ዘገባ ነው። በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ሄሮዶተስ፣ ሰብአ ሰገል በኮከብ ቆጠራ፣ ሕልም በመፍታትና በድግምት የተካኑ ፋርሳውያን ካህናት እንደነበሩ ጽፏል። በሄሮዶተስ ዘመን የፋርሳውያን ሃይማኖት ዞሮአስትሪያኒዝም ነበር። በመሆኑም ሄሮዶተስ የጠቀሳቸው ሰብአ ሰገል የዞሮአስተር እምነት ካህናት ሳይሆኑ አይቀሩም። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “በጥቅሉ ሲታይ፣ የግሪክ ባሕል ተስፋፍቶ በነበረበት ዘመን ሜጎስ [ሜጆይ] የሚባለው ከሰው በላይ የሆነ እውቀትና ችሎታ የነበረውና አንዳንድ ጊዜም አስማት የሚያደርግ ሰው ነበር።”

እንደ ጀስቲን ማርተር፣ ኦሪጀንና ተርቱሊያን ያሉ “ክርስቲያን” የሚባሉ በርካታ የጥንት ተንታኞች፣ ኢየሱስን ሊጠይቁ የመጡትን ሰብአ ሰገል ኮከብ ቆጣሪዎች እንደሆኑ አድርገው ገልጸዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ተርቱሊያን ኦን አይዶላትሪ በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “አስማትና ኮከብ ቆጠራ ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች መሆናቸውን እናውቃለን። በመሆኑም . . . [ለኢየሱስ] መጀመሪያ ‘ስጦታ’ ያመጡለት ሰዎች ኮከቦችን በማየት ፍቺ የሚሰጡ ግለሰቦች ነበሩ።” ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ሜጆይ የሚለውን ቃል “ኮከብ ቆጣሪዎች” በማለት ተርጉመውታል፤ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ በ1954 ትርጉም ላይ እነዚህን ሰዎች ሰብአ ሰገል የሚላቸው ሲሆን ፍቺውም “ኮከብ ቆጣሪዎች፣” “የጥንቆላ ሰዎች” ማለት ነው።

ማቴዎስ፣ ከዘካርያስ መጽሐፍ የወሰደውን ሐሳብ ከኤርምያስ መጽሐፍ ላይ እንደወሰደው አድርጎ የተናገረው ለምንድን ነው?

ይህ ጥያቄ የተነሳው በ⁠ማቴዎስ 27:9, 10 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በተመለከተ ሲሆን ማቴዎስ በዚህ ጥቅስ ላይ አስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ በመስጠቱ ስለተቀበለው ገንዘብ ተናግሯል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በዚህ ጊዜ በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፦ ‘. . . ለሰውየው የወጣውን የዋጋ ተመን ሠላሳ የብር ሳንቲሞች ወሰዱ፤ . . . ሳንቲሞቹን ለሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉ’።” ስለ 30 የብር ሳንቲሞች የሚናገረው ትንቢት የሚገኘው በኤርምያስ መጽሐፍ ሳይሆን በዘካርያስ መጽሐፍ ላይ ነው።—ዘካርያስ 11:12, 13

አንዳንድ ጊዜ፣ “ነቢያት” ተብለው በሚጠሩት መጻሕፍት ስብስብ መጀመሪያ ላይ የሚደረገው ትንቢተ ኢሳይያስ ሳይሆን ትንቢተ ኤርምያስ የነበረ ይመስላል። (ማቴዎስ 22:40) በመሆኑም ማቴዎስ ከላይ ባለው ጥቅስ ላይ “ኤርምያስ” ሲል ነቢያት ተብለው የሚጠሩትን መጻሕፍት በአጠቃላይ ለማመልከት በዚህ ስብስብ መጀመሪያ ላይ በሚገኘው መጽሐፍ ስም መጠቀሙ ነበር። በዚህ ስብስብ ውስጥ የዘካርያስ መጽሐፍም ይገኝበታል።

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ኢየሱስ፣ መጻሕፍት በመባልም ይታወቁ የነበሩትን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች “መዝሙራት” በማለት ጠርቷቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ “በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት” ስለ እሱ የተጻፉት ትንቢቶች በሙሉ መፈጸም እንዳለባቸው ሲናገር በመላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች ማመልከቱ ነበር።—ሉቃስ 24:44