በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የጥንት ሰዎች በእርግጥ ረጅም ዕድሜ ኖረዋል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የጥንት ሰዎች በእርግጥ ረጅም ዕድሜ ኖረዋል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የጥንት ሰዎች በእርግጥ ረጅም ዕድሜ ኖረዋል?

በደቡባዊ ምሥራቅ ፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩት ዣን ልዊዝ ካልሞ የተባሉ ሴት ነሐሴ 4, 1997 በትውልድ ከተማቸው አረፉ። እኚህ ሴት የሞቱት በ122 ዓመታቸው ነበር!

በዛሬው ጊዜ በሳይንስ፣ በጤና አጠባበቅና በሌሎች መስኮች የተገኘው እመርታ ሰዎች ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ እያስቻላቸው ነው። ያም ሆኖ መቶ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ መኖር የቻሉት በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው። ከማዳም ካልሞ ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ሰዎች ከመቶ ዓመት በላይ ሲኖሩ የዜና ሽፋን የሚሰጣቸው ለዚህ ሊሆን ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ጊዜ ሰዎች በጣም ረጅም ዕድሜ እንደኖሩ ይናገራል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ወደ አንድ ሺህ ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ ኖረዋል። ይህ በእርግጥ ሊታመን የሚችል ነገር ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የጥንት ሰዎች በእርግጥ ያን ያህል ረጅም ዕድሜ ኖረዋል? ስለዚህ ጉዳይ ማወቃችንስ ለእኛ የሚጠቅመን ነገር አለ?

ረጅም ዕድሜ የኖሩ ሰዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ከ900 ዓመታት በላይ ስለኖሩ ሰባት ሰዎች የሚናገር ሲሆን ሁሉም የተወለዱት በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በፊት ነው። እነሱም አዳም፣ ሴት፣ ሄኖስ፣ ቃይናን፣ ያሬድ፣ ማቱሳላና ኖኅ ናቸው። (ዘፍጥረት 5:5-27፤ 9:29) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በብዙ ሰዎች ዘንድ አይታወቁ ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያዎቹ አሥር ትውልዶች ውስጥ የኖሩ ናቸው። ለ969 ዓመታት የኖረው ማቱሳላ ከማንም በላይ ረጅም ዕድሜ በመኖሩ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል!

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቢያንስ 25 የሚያህሉ ሌሎች ሰዎች ዛሬ ከተለመደው ዕድሜ በላይ እንደኖሩ ይናገራል። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ 300፣ 400 አልፎ ተርፎም 700 ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት ኖረዋል። (ዘፍጥረት 5:28-31፤ 11:10-25) ይሁንና ብዙ ሰዎች ይህን ያህል ረጅም ዕድሜ የኖሩ ግለሰቦች እንደነበሩ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አፈ ታሪክ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በእርግጥ አፈ ታሪክ ነው?

 አፈ ታሪክ ወይስ እውነተኛ ታሪክ?

ጀርመን ውስጥ የማክስ ፕላንክ የሕዝብ አሰፋፈር ምርምር ተቋም ለኅትመት ያበቃው መረጃ እንደሚጠቁመው ተመራማሪዎች ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የማዳም ካልሞን ዕድሜ ትክክለኝነት ማረጋገጥ የቻሉት እሳቸው “እንደ ዋዛ የተናገሯቸውን ሊረጋገጡ የሚችሉ ሐሳቦች” በማሰባሰብ ነው። እነዚህ ሐሳቦች በእሳቸው ወይም በዘመዶቻቸው ዕድሜ ከተፈጸሙ አንዳንድ ክንውኖች ጋር የተያያዙ ናቸው። ከዚያም እሳቸው የተናገሯቸው ሐሳቦች ከታሪክ፣ ከውልና ከቤተ ክርስቲያን መዛግብት አልፎ ተርፎም በጋዜጣ ላይ ከወጡ ጽሑፎችና ከሕዝብ ቆጠራ መረጃዎች ጋር እንዲነጻጸሩ ተደረገ። የእያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ትክክለኝነት ማረጋገጥ ባይቻልም እንኳ ቀጥተኛም ሆኑ ቀጥተኛ ያልሆኑት ማስረጃዎች ሴትየዋ በእርግጥ ያን ያህል ረጅም ዕድሜ መኖራቸውን ለማረጋገጥ አስችለዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ዘገባዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ዘገባዎች ትክክለኛ መሆናቸው ተረጋግጧል? አዎን ተረጋግጧል! ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ባሉት ማስረጃዎች እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ማረጋገጥ ባይቻልም ማስረጃዎቹ በተደጋጋሚ እንደሚያሳዩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ዘገባ ከታሪክ፣ ከሳይንስና ታሪኮቹ ከተፈጸሙበት የጊዜ ቅደም ተከተል አንጻር ሲታይ ተአማኒነት ያለው ነው። * ይህ ደግሞ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ቢሆን እንኳ አምላክ እውነት ይናገራል” በማለት ይገልጻል። (ሮም 3:4 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ” መጽሐፍ በመሆኑ ለአፈ ታሪክ ቦታ የለውም።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

በይሖዋ አምላክ ተመርቶ የኦሪት መጻሕፍትን ወይም የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጻፈው ሙሴ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩ የተከበሩ ሰዎች መካከል መፈረጅ ይኖርበታል። አይሁዶች ከአስተማሪዎቻቸው ሁሉ የላቀ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ሙስሊሞችም ከታላላቅ ነቢያቶቻቸው አንዱ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ክርስቲያኖች ደግሞ ሙሴን የሚመለከቱት የኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ አድርገው ነው። ታዲያ በታሪክ ውስጥ ታላቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ ሰው ያዘጋጀው ጽሑፍ ተአማኒነት የለውም ቢባል ምክንያታዊ ይሆናል?

የጊዜ አቆጣጠሩ የተለየ ነበር?

አንዳንዶች በዚያን ዘመን የነበረው የጊዜ አቆጣጠር ከአሁኑ የተለየ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል፤ እንዲያውም በዚያ ዘመን አንድ ወር እንደ አንድ ዓመት ይቆጠር እንደነበር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የዘፍጥረትን ዘገባ ጠለቅ ብለን ስንመረምር በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ጊዜን የሚቆጥሩበት መንገድ ከአሁኑ ዘመን ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት። ስለ ጥፋት ውኃ በሚገልጸው ዘገባ ላይ የጥፋት ውኃው የጀመረው በኖኅ “600ኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን” እንደነበረ እናነባለን። ከዚያም ዘገባው በመቀጠል ውኃው ለ150 ቀን በምድር ላይ እንዳየለና “በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ” እንዳረፈች ይናገራል። (ዘፍጥረት 7:11, 24፤ 8:4) በመሆኑም ከሁለተኛው ወር 17ኛ ቀን አንስቶ እስከ ሰባተኛው ወር 17ኛ ቀን ድረስ ያሉት አምስት ወራት 150 ቀናት እንደሆኑ ተገልጿል። ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አንድ ወር እንደ አንድ ዓመት ይቆጠር ነበር የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ መሠረት የሌለው ነው።

አሁን ደግሞ ሁለተኛውን ምሳሌ እንመልከት። ዘፍጥረት 5:15-18 መላልኤል 65 ዓመት ሲሆነው ወንድ ልጅ እንደወለደና ከዚያ በኋላ 830 ዓመት ኖሮ በ895 ዓመቱ እንደሞተ ይናገራል። የእሱ የልጅ ልጅ የነበረው ሄኖክም ወንድ ልጅ የወለደው በ65 ዓመቱ ነበር። (ዘፍጥረት 5:21) በወቅቱ አንድ ወር እንደ አንድ ዓመት ይቆጠር የነበረ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሁለት ሰዎች ልጅ የወለዱት ገና በአምስት ዓመታቸው ነበር ማለት ነው! ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው!

የአርኪኦሎጂ ግኝቶችም መጽሐፍ ቅዱስ ረጅም ዕድሜ ስለኖሩ ሰዎች ከሚናገረው ዘገባ ጋር የሚስማማ ማስረጃ ያቀርባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በጥንት ዘመን የነበረው አብርሃም በዑር ከተማ ይኖር እንደነበረ በኋላም ከዚያ ወጥቶ በመጀመሪያ በካራን በኋላም በከነዓን ምድር እንደኖረ እንዲሁም ከኤላም ንጉሥ ከኮሎዶጎምር ጋር ተዋግቶ ድል እንዳደረገ ይናገራል። (ዘፍጥረት 11:31፤ 12:5፤ 14:13-17) የአርኪኦሎጂ ግኝቶች እነዚህ ቦታዎችና ሰዎች በእርግጥ እንደነበሩ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም እነዚህ ግኝቶች ከአብርሃም ጋር ተያይዘው የተጠቀሱ አገሮችን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የሕዝቦቹን ባሕል በተመለከተ ብርሃን ፈንጥቀዋል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብርሃም የሚናገራቸው ነገሮች ትክክል መሆናቸው ከተረጋገጠ አብርሃም 175 ዓመት ኖሯል መባሉን የምንጠራጠርበት ምን ምክንያት ይኖራል?—ዘፍጥረት 25:7

በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን ከተለመደው  በላይ ረጅም ዕድሜ ስለኖሩ ሰዎች የሚናገረውን ሐሳብ ለመጠራጠር የሚያበቃን ምንም ምክንያት የለም። ይሁን እንጂ “እነዚህ ሰዎች ይህን ያህል ረጅም ዕድሜ ኖሩ አልኖሩ ለእኔ ምን ጥቅም አለው?’ ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል።

ከምታስበው በላይ ረጅም ዕድሜ መኖር ትችላለህ!

ከኖኅ የጥፋት ውኃ በፊት የኖሩት ሰዎች ያስመዘገቡት ተወዳዳሪ የሌለው ረጅም ዕድሜ፣ የሰው አካል ረጅም ዘመናት የመኖር ችሎታ እንዳለው ያረጋግጣል። ዘመናዊው ቴክኖሎጂ፣ ሳይንቲስቶች የሰው አካል ያለውን አስገራሚ የሆነ ራሱን በራሱ የማደስና የመፈወስ ችሎታውን ጨምሮ ስላለው አስደናቂ ንድፍ በጥልቀት እንዲመረምሩ አስችሏቸዋል። ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? የሰው አካል ለዘላለም የመኖር ችሎታ አለው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። የሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ቶም ኪርክዉድ እርጅና “የሕክምናው ሳይንስ ሊፈታቸው ካልቻሉት ታላላቅ ሚስጥሮች አንዱ ነው” ብለዋል።

ለይሖዋ አምላክ ግን እርጅና ሚስጥርም ሆነ መፍትሔ የሌለው ችግር አይደለም። የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ፍጹም አድርጎ የፈጠረው ከመሆኑም በላይ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ ዓላማው ነበር። የሚያሳዝነው ግን፣ አዳም ለአምላክ ጀርባውን ሰጠ። አዳም በዚህ ምክንያት ኃጢአት ውስጥ በመውደቁ ፍጽምናውን አጣ። ሳይንቲስቶችን ግራ ያጋባቸው ጥያቄ መልስ በሚከተለው ጥቅስ ላይ ይገኛል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) የምንታመመው፣ የምናረጀውና የምንሞተው በኃጢአትና ባለፍጽምና ምክንያት ነው።

ይሁን እንጂ የአፍቃሪው ፈጣሪያችን ዓላማ ፈጽሞ አልተለወጠም። ይሖዋ ለዚህ ግሩም ማስረጃ እንዲሆነን የፍጽምናን እንዲሁም የዘላለም ሕይወትን በር የከፈተውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ አዘጋጅቶልናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:22) ከጥፋት ውኃው በፊት የነበሩ ሰዎች ከእኛ የበለጠ እጅግ ረጅም ዕድሜ የኖሩት ለፍጽምና ቅርብ ስለነበሩ ነው። እኛ የምንኖረው ግን የአምላክ ዓላማ ሊፈጸም በተቃረበበት ጊዜ ነው። በቅርቡ የኃጢአትና የአለፍጽምና ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ስለሚወገዱ ሰዎች ማርጀታቸውም ሆነ መሞታቸው ይቀራል።—ኢሳይያስ 33:24፤ ቲቶ 1:2

እንዲህ ዓይነቱን በረከት ልታገኝ የምትችለው እንዴት ነው? አምላክ ቃል የገባው ነገር እንዲያው ሕልም ሆኖ ይቀራል ብለህ አታስብ። ኢየሱስ “ቃሌን የሚሰማና የላከኝን የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ብሏል። (ዮሐንስ 5:24) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት በመቅሰም ተግባራዊ ለማድረግ ጣር። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ ይችሉ ዘንድ በዚህ መንገድ ለራሳቸው ውድ ሀብት ማከማቸታቸውን ይኸውም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት መጣላቸውን ይቀጥሉ” በማለት የተናገረላቸውን ሰዎች ምሳሌ ትከተላለህ። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ ያስቻላቸው አምላክ፣ አንተንም ለዘላለም እንድትኖር እንደሚያስችልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ዝርዝር ጉዳዮችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ግራፍ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

1000*

969* ማቱሳላ

950* ኖኅ

930* አዳም

900*

800*

700*

600*

500*

400*

300*

200*

100* ዘመናዊው ሰው

*ዕድሜ