በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ማነጋገር ያለብን ማንን ነው?

በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ማነጋገር ያለብን ማንን ነው?

 በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ማነጋገር ያለብን ማንን ነው?

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ፣ ሌሎቹ መንፈሳዊ ፍጥረታት እሱን ወክለው አንዳንድ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ምድርን የመግዛትን ኃላፊነት ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ሲሆን ታማኝ የሆኑ መላእክትን ደግሞ ምሥራቹን በማወጁ ሥራ እገዛ እንዲያደርጉ ሾሟቸዋል። (ራእይ 14:6) ከጸሎት ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። አምላክ ጸሎትን የመስማትን መብት ለማንም አልሰጠም። ጸሎት መቅረብ ያለበት ለአምላክ ብቻ ነው።

ይሖዋ ‘ጸሎትን የሚሰማ’ አምላክ መሆኑ ተገልጿል። (መዝሙር 65:2) አምላክ ጸሎቶቻችንን የሚሰማ ከመሆኑም ሌላ መልስ ይሰጠናል። ሐዋርያው ዮሐንስ ጸሎትን አስመልክቶ ለእምነት አጋሮቹ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ [አምላክ] ይሰማናል። በተጨማሪም የምንጠይቀውን ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን ከእሱ እንደጠየቅን ስለምናውቅ የጠየቅናቸውን ነገሮች እንደምናገኝ እናውቃለን።”—1 ዮሐንስ 5:14, 15

ታማኞቹ መላእክት እነሱን ለማነጋገር እንድንሞክር ወይም ወደ እነሱ እንድንጸልይ አይፈልጉም። አምላክ በጸሎት ረገድ ያደረገውን ዝግጅት የሚገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ ከዚህ ዝግጅት ጋር ተባብረው ይሠራሉ፤ አንዳንድ ጊዜ በዚህ ዝግጅት ውስጥ እነሱም የሚጫወቱት ሚና አለ። ምን ሚና ይጫወታሉ? ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ  ዳንኤል ስለ ኢየሩሳሌም ባድማ መሆን ወደ ይሖዋ በጸለየ ጊዜ አምላክ በመልአኩ ገብርኤል አማካኝነት የሚያጽናና መልእክት በመላክ ለጸሎቱ መልስ ሰጥቶታል።—ዳንኤል 9:3, 20-22

ከሙታን የሚመጣ መልእክት አለ?

ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመነጋገር መሞከር ይኖርብናል? ሰዎች ከሙታን መናፍስት ጋር እንደተነጋገሩ የሚገልጹ ብዙ ታሪኮችን መስማት የተለመደ ነው። ለምሳሌ አንዲት መናፍስት ጠሪ በአየርላንድ ከምትኖር አንዲት ሴት ባል ጋር እንደተነጋገረች ለሴትየዋ ገለጸችላት። ሆኖም ፍሬድ የተባለው የዚህች ሴት ባል ከሞተ ጥቂት ሳምንታት አልፈው ነበር። መናፍስት ጠሪዋ፣ “ፍሬድ” የነገራትን ነገሮች ለሚስቱ ገለጸችላት፤ የፍሬድ ሚስት እነዚህን ነገሮች እሷ ብቻ እንደምታውቃቸው ታስብ ነበር። በመሆኑም ባሏ የሞተባት ይህች ሴት መናፍስት ጠሪዋ የተናገረችውን ስትሰማ ፍሬድ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እንደሚኖርና በመናፍስት ጠሪዋ አማካኝነት እሷን ለማነጋገር እየሞከረ እንዳለ ብታምን ምክንያታዊ ይመስል ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያለው ድምዳሜ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ በግልጽ ከሚናገረው ሐሳብ ጋር ይጋጫል።—ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ታዲያ እንዲህ ያሉ ታሪኮችን የምንሰማው ለምንድን ነው? አጋንንት የሚጠቀሙበት አንዱ የማታለያ ዘዴ ሙታንን መስሎ መቅረብ ሲሆን ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ላይ ፍሬድን መስለው ቀርበዋል። እንዲህ የሚያደርጉበት ዓላማ ምንድን ነው? ሰዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማራቅና በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት ማዳከም ነው። ሰይጣንና አጋንንቱ “በተአምራት፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሁሉ እንዲሁም ለማታለል ማንኛውንም ዓይነት የክፋት ዘዴ በመጠቀም” ሰዎችን እያሳሳቷቸው እንዳሉ ግልጽ ነው።—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10

መናፍስት ጠሪዎች እንዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም፤  ወደ እነዚህ ሰዎች የሚሄዱ ግለሰቦችም ይህን የሚያደርጉት ከሙታን ጋር እንደሚነጋገሩ ስለሚያምኑ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ሰዎች የሚያነጋግሩት በይሖዋ ላይ ያመፁትን መናፍስት እንጂ ሙታንን አይደለም። በተመሳሳይም አምላክን የሚያመልኩ ቢመስላቸውም የተሳሳቱ ሰዎች አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ የሚል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “አሕዛብ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቧቸውን ነገሮች የሚሠዉት ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 10:20, 21

በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሁሉም የበላይ ወደሆነው እንዲሁም ወደሚወደንና ወደሚያስብልን ፈጣሪያችን መጸለይ እንደምንችል እያወቅን ወደ ሌላ አካል የምንጸልይበት ምን ምክንያት አለ? ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—2 ዜና መዋዕል 16:9

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሁሉም የበላይ ወደሆነው እንዲሁም ወደሚወደንና ወደሚያስብልን ፈጣሪያችን መጸለይ እንደምንችል እያወቅን ወደ ሌላ አካል የምንጸልይበት ምን ምክንያት አለ?

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እውነታውን ከውሸቱ መለየት

እውነታው፦ ሰይጣን የራሱ ስብዕና ያለው አካል ነው

“ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ዘወትር ራሱን ይለዋውጣል።”—2 ቆሮንቶስ 11:14

“የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፤ ንቁዎች ሆናችሁ ኑሩ። ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።”—1 ጴጥሮስ 5:8

“በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ የዲያብሎስ ወገን ነው፤ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያው አንስቶ ኃጢአት ሲሠራ ቆይቷል።”—1 ዮሐንስ 3:8

“ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።”—ያዕቆብ 4:7

“ዲያብሎስ . . . በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም። ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል።”—ዮሐንስ 8:44

ውሸቱ፦ ሁሉም ሰዎች ሲሞቱ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መኖር ይቀጥላሉ

“ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።”—ዘፍጥረት 3:19

“ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም።”—መክብብ 9:5

“እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።”—መክብብ 9:10

“መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።”—መዝሙር 146:4

እውነታው፦ ታማኞቹ መላእክት ያስቡልናል

“እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም።”—መዝሙር 34:7፤ 91:11

“ሁሉም [መላእክት] መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉም?”—ዕብራውያን 1:14

“ሌላም መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ እንዲሁም ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ ልክ እንደ አስደሳች ዜና የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች ይዞ ነበር፤ በታላቅ ድምፅም ‘አምላክን ፍሩ፣ ክብርም ስጡት’ . . . አለ።”—ራእይ 14:6, 7

ውሸቱ፦ ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነው

“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 11:3

“ሁሉም ነገር ከተገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር መሆን ይችል ዘንድ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:28

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ወልድ አብ ሲያደርግ ያየውን ብቻ እንጂ በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ አይችልም።”—ዮሐንስ 5:19